spot_img
Friday, June 14, 2024
Homeነፃ አስተያየትሁሉም ነገር ወደ አፋር ግንባር---ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ለመታደግ ህወሓትን መደምሰስ ያስፈልጋል (ክፍል ሁለት)

ሁሉም ነገር ወደ አፋር ግንባር—ኢትዮጵያን ከመፈራረስ ለመታደግ ህወሓትን መደምሰስ ያስፈልጋል (ክፍል ሁለት)

አክሎግ ቢራራ (ዶር)
ክፍል ሁለት
ጥር 24 2014 ዓ. ም.

የጦረንቱ ዋና መሰረት ስርዓቱ ነው። 

የዚህ ሰፊ ትንተና ዋና አላማ ያለውን ሰው ሰራሹን የዘውግ መከፋፈልና ጥላቻ (Ethnic division and polarization) ለማጠናከርና ለማባባስ  አይደለም። ኢትዮጵያዊያን የዘውግ ጎራ ለይተው እርስ በእርሳቸው እየተገዳደሉ፤ በቂም በቀል እየተጨፋጨፉ፤ የሰሩትን እያፈራረሱ፤ ወጣቱን ትውልድ ተስፋ እያስቆረጡ፤ የጥፋት ስራቸውን ከኢትዮጵያ የውጭ ጠላቶች ጋር አብረው እየዶለቱ ወዘተ ኢትዮጵያ ከኋላ-ቀርነትና ከድህነት አሮንቃ ራሷን ነጻ ለማውጣት የምትችልበት ሁኔታ አይታየኝም። 

እትዮጵያ ስንት እድሎች አጋጥመዋት ሳትጠቀምባቸው ቀርታለች? ስንት ብርቃማ ዜጎቿን መስዋእት አድርጋለች? 

በእኔ ጥናት፤ ምርምርና ግምገማ፤ የኢትዮጵያ ምሁራን፤ የፖለቲካ ልሂቃንና ሌሎች አካላት “እኛ ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች” የሚለውን ሕገ መንግሥት፤ የከፋፍለህ ግዛውና ብላውን የአስተዳድር መዋቅር በአስቸኳይ ለመቀየር ካልደፈሩ፤ ህወሓትም ቢወገድ እንኳን የተተትኪነት ባህሪው አይቀየረም። “እኛ ኢትዮጵያዊያን”  ብለን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ መብቱ/መብቷ የሚከበርባትን ኢትዮጵያን የመመስረት ግዴታ አለብን። 

እኔ ራሴን የምጠይቀው፤ የኢትዮጵያ ሕዝብ መቸ ይሆን፤ እፎይ ብሎ፤ አብሮነትን ሙሉ በሙሉ ተቀብሎ፤ በሰላም ወጥቶ፤ በሰላም ገብቶ፤ መብቱና ደህንነቱ ተከብሮ፤ በየትኛውም የኢትዮጵያ ክፍል በዜግነቱ መብት ተማምኖ፤ ሰርቶ ወዘተ ለመኖር የሚችለው? የሚለውን ጥያቄ ለመመለስ  እሞክራለህ። ይህንን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ካልቻልን ዲሞክራሳዊ ለውጥ ተካሂዷል ወይንም እየተካሄደ ነው ለማለት አልችልም። ይህ ሰው ሰራሽ ወይንም የዘውግ የፖለቲካ ልሂቃን የጫኑብንና እንደ ግብጽ ያሉ መንግሥታት መሳሪያ አድርገው የሚጠቀሙበት የከፋፍለህ ግዛውና አድክመው ስርዓት ለውጭ ኃይሎች ወንፊት ሆኖ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር፤ ኢትዮጵያዊነት እንደ ዜግነት መለያ ለመቀበል ስንቸገር አያለሁ፤ እታዘባለሁ። የውጭ ኃይሎችን ከመተቸት ባሻገር ግን፤ መጀመሪያ ራሳችንን እንተች። 

የታወቁት ሳይንቲስትና ፈላስፋ አልበርት አይንስታይን መሰረታዊ “ችግሮችን ለመፍታት መጀመሪያ ችግሩ ምን እንደ ሆነ ማወቅ፤ ችጉሩን የፈጠረውን መርህና ዘዴ ተቀብሎ ለመፍታት እንደ ማይቻል መቀበል ነው” ብለው መክረው ነበር። “We cannot solve our problems with the same thinking we used when we created them.” ቁም ነበሩ የአስተሳሰብ ለውጥ ከሌለ ችግሩን ለመፍታት አይቻልም የሚለው ነው። ለምሳሌ፤ የአማራው ህዝብ ለሌሎች ኢትዮጵያዊያን ጠላት ነው የሚለው የተሳሳተና አደገኛ ብሂል ስር መስደዱን ፉርሽ ነው ለማለት ለምን አይቻልም? ይንን ማለት ያለባቸው ተከሳሾች ሊሆኑ አይችሉም። 

ማንኛውም አገር በዘውግ ሆነ በኃይማኖት ጥላቻና የእርስ በእርስ ግጭት ከተበከለ የመልማት እድሉ ዝቅ ያለ መሆኑን ባለፉት አስርት ዓመታት ለመጠቆም ሞክሬ ነበር። ዛሬ ኢትዮጵያዊያን ሌላ ምሳሌ አያስፈልጋቸውም። ህወሓት/ትህነግና አጋሩ ኦነግ ሸኔ ያካሄዱትና አሁንም የሚያካሂዱት እልቂትና ውድመት ተመሳሳይ ቀውስ ከተደረገባቸው አገሮች ጋር እንኳን ሲነጻጸር—ቦዝንያ፤ ሊቢያ፤ ሶርያ፤ ኢራክ፤ የመን፤ አፍጋኒስታን፤ ላይቤርያ፤ ሴራሊኦን፤ ናይጀሪያ ወዘተ–የኢትዮጵያው እልቂትና ውድመት ተወዳዳሪ የለውም። ይህ እልቂትና ውድመት ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ዝቅ አድርጓቸዋል ለማለት እደፍራለሁ። ሰብእነታችን ወድቋል!!

ኢትዮጵያን ከሶስት ሽህ እስከ ስድስት ሽህ አመታት ታራክ ያላትና ሉዓላዊ አገር ናት ብለው ከሚከራከሩት መካከል አንዱ ለሆንኩት ግለሰብ ገና ያላለቀውን ጦርነት እስካሁን ማን አሸነፈ? ማን ተሸነፈ? ለሚለው ጥያቄ የምሰጠው መልስ ተሸናፊ እንጅ አሸናፊ የለም የሚል ነው። የዘውግ መለያችን ወደ ጎን ትተን ስንት የሴት ልጆቻችን፤ ስንት እህቶቻችን፤ ስንት እናቶቻችን ተደፍረዋል? ስንት ንጹህ ወገኖቻችን ተጨፍጭፈዋል? ስንት ኢንዱስትሪ፤ ስንት ዘመናዊ እርሻ፤ ስንት መሰረተ ልማት እንዲወድም ተደርጓል? ያለው ከወደመ እንዴት ዘላቂ ልማት ይቻላል?

የዘውግ ክፍፍል ለውክልና ጦርነት ወንፊት ነው። 

በኔ ግምገማ ያሸነፉት የውጭ ኃይሎች ናቸው፤ በተለይ ግብጽና ኢትዮጵያ ራሷን ችላ ለመላው ጥቁር አፍሪካና ጥቁር ህዝብ ተምሳሌት እንድትሆን የማይፈቅዱት መንግሥታት። ግብጽን በተደጋጋሚ የምጠቅስበት መሰረታው ምክንያት ኢትዮጵያ የዐባይን ወንዝ እንዳትጠቀምና ሶስት መሰረታዊ ፍላጎቶችን—ምግብ፤ ውሃና ኤሌክትሪም–ግድቦችን ሰርታ እንዳታሟላ ከፍተኛ ጫናዎችን በዓለም አቀፍ ደረጃ አካሂዳለች። ዓለም ባንክ ለኢትዮጵያ የግድብ ፕሮጀክቶች እንዳያበድር ጫና ያደረገችው ግብጽ ናት። በአሁኑ ጦርነት ህወሓትንና ኦነግ ሽኔ እየደገፈች ከአንድ ቢሊየን ዶላር በላይ ፈሰስ ያድረገችው ግብጽ ናት። የአሜሪካ የስለላ ድርጅት እንደሚለው ከሆነ በአኑ ወቅት የሕዳሴን ግድብ ስኬታማነት ለማኮላሸት ቀን ከሌት የምትሰራው ግብጽ ናት። በዚህ ዙሪያ ከፍተኛ ዝግጅት ያስፈልጋል። 

ኢትዮጵያን ወንፊት ያደረገውን ህወሃትንና እንደ ፈረስ የሚጋልበውን ኦነግ ሽኔን በሃላፊነት በሕግ መጠየቅ ካልተቻለ “የሕግ የበላይነትን እናክብርና እናስክብር” የሚለው እሴት ቀፎ ሆኖ አገኘዋለሁ። የመሳሪያ ኃይልና ኃብት ያለው ብቻ ነው ሊከበር የሚችለው። 

እስካሁን በህወሃት እብሪተኛነት የተካሄደውን እልቂትና ውድመት ስገመግም፤ ከእነዚህ የምእራብ መንግሥታት መካከል መሪው የአሜሪካ መንግሥት እንደሆነ በምንም አልጠራጠርም። የተባበሩት መንግሥታትን በበላይነት የሚያሽከረክረውም የአሜሬካ መንግሥት ነው። ቢሆን ነው፤ የተባበሩት መንግሥታት ልዩ ልዩ ተቋማት፤ አንድ ሽህ ሶስት መቶ ወይንም አንድ ሽህ አምስት መቶ (1300 -1,500 food and other essential supply trucks) የቁሳቁስ ተሽከርካሪዎችን አሸባሪው ህወሓት ሲነጥቃቸውና መልሶ ለጦርነት ማጓጓዢያ  ሲጠቀምባቸው አንዴም ቢሆን ድርጊቱን አውግዘው እንዲመለሱ ያላስገደዱትም። ህወሓት ጦርነቱን ወደ አፋርና አማራ ክልል አስፋፍቶ እጅግ የሚዘገንን እልቂትና ውድመት ሲያካሂድ “እልቂቱን አቁም፤ ካላቆምክ ግን እናወግዝሃለን፤ ከፍተኛ ጫና እናደርግብሃለን” አላሉትም። ወቀሳውን ያስተጋቡት በኢትዮጵያና በኤርትራ መከላከያ፤ በአማራውና በአፋሩ ልዩ ኃይሎች፤ በፋኖ ወዘተ ላይ ነው። 

የአሜሪካ መንግሥትና የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፍላጎት ጅዖፖለቲካዊ እንጅ ስብአዊና ፍትሃዊ አይደለም። የአሜሪካ መንግሥት ዋና ትኩረት ለአሜሪካ ብሄራዊ ጥቅም አገልጋይ የሆነ መንግሥት እንዲመሰረት ማድረግ ነው። “ያልጠረጠረ ተመነጠረ” እንዲሉ ይህንን የአሜርካን መንግሥት መርህ የማያሟላ ኃይል ሁሉ ዋጋ ቢከፍል ለእነሱ ፋይዳ የለውም። 

ይህ አጠቃላይ ዘገባየ ወደ ችግሩ መሰረት ወይንም እምብርት ያመራኛል። የጣልያን ፋሽስቶች ኢትዮጵያን ሙሉ በሙሉ ለመያዝና ለመግዛት ባላቸው ፍላጎትና እቅድ መሰረት የተጠቀሙበት ምሁራዊና ጥናታዊ ዘዴ የኢትዮጵያን ህዝብ እርስ በእርሱ እንዲናከስና እንዲጣላ ለማድረግ በዘውግ መከፋፈል” ነበር። ይህ ሁኔት እንዳይቀጥል እመክራለሁ። ሁኔታው ሲቀጥል፤ ቀስ በቀስ በህወሓት መንግሥት የተከሰተው እልቂት ሌላውንም ይጎዳዋል። “ነግ በኔ” ብሎ ማሰቡ የተሻለ አወንታዊ ውጤት ያስከትላል። 

ለዚህ የከፋፍለህ ግዛውና ብላው ምሁራዊ የመርህ ሰነድ ያቀረበው የባሮን ፕሮቻስካ ሰንድ ዛሬ ህወሓትና ኦነግ ሽኔ የሚጠቀሙበትን የአማራ የበላይነትና አምካኝነትን ትርክት ነው። ከማከብራቸው የኢትዮጵያ ምሁራን መካከል ከፍተኛ ቦታ የያዘው ፕሮፌሰር አለሜ እሸቴ “ Origin of Tribalization of Ethiopian Politics: From Fascism to Fascism (የዘውጋዊነት ፖለቲካ፦ ከፋዝም ወደ ፋሽዝም” ብሎ የሰየመውን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ ደጋግሞ ማንበብ ያለበትን መጽሃፉን እንዲጽፍ ያስገደደው የአውስትርያው የፋሺዝም ደጋፊ ባሮን ፕሮቻስካ ( Baron Prochaska) ነው። ኢትዮጵያ ባለፉት ሰላሳ ዓመታት የተመራችበት ሕገ መንግሥትና የአስተዳደር አወቃቀር ተመሳሳይነት እንዳለው ለመካድ አይቻልም። የዘውግ ልሂቃን የሚረባረቡት በመሬትና በሌላ የተፈጥሮ ይገባኛልነት ላይ ነው።

ሙሶሎኔ ኢትዮጵያን ለመግዛት የሚችለው ሃበሻው የፖለቲካ ሚና እንዳይኖረው በማድረግና የኢትዮጵያ ብሄር፤ ብሄረሰቦችና ሕዝቦች እርስ በእርሳቸው እንዲጣሉና እንዳይተማመኑ በማድረግ፤ ኢትዮጵያን ዘውግ ተኮር አወቃቀር ደንግጎ በመከፋፈል ብቻ ነው ከሚል ውሳኔ ላይ የደረሰው በተሰጠው ምክርና ስልት መሰረት ነው።  ይህንን ድንጋጌ “Legge Organica” በሚል ህጋዊ ስያሜ ኢትዮጵያን በሕግ ከፋፈላት። አሁን ያለው ሕገ መንግሥት በምን ይለያል? 

በመላው “ሃበሻ” ላይ በፈረንጅዎች በኩል ከፍተኛ ጥላቻንና ፍርሃትን የፈጠረው ጉዳይ ምንድን ነው?  ሮማን ፕሮቻዝካ Baron (Roman Prochaska “የሃበሻዋ የባሩድ በርሚል Abyssinia the Powder Barrel፣ Vienna 1935) የሚለው መጽሃፍ መጀመሪያ በጣልያንኛ የተጻፈው “ABYSSINIA PERI COLO NERO ጥቁሯ” ለዓለም (ለምእራባዊያን) ዋና ጠንቅ ወይንም አደጋ የሆነችው” አገር በሚል ነበር። ይህች አገር ማንንም አልወረረችም። ኢላማ የሆነችው ባላት አቀማመጥ፤ የተፈጥሮ ኃብት፤ በሕዝቧ አገር ወዳድነት፤ በነጻነት ናፋቂነት፤ በዜጎቿ አርበኛነት ነው። ይህንን ባህል ባለፉት አስራ አምስት የትግራይ ጦርነት አይተናል። በኢትዮጵያዊነት መተባበር ከፍተኛ አወንታዊ ውጤት ይገኛል። ለዘላቂ ልማትም መሰረቱ በኢትዮጵያዊነት አብሮ መስራት ነው። ተተኪነት ግን አፍራሽ ነው። ከህወሃት መርህ አይለይም። 

አጼ ኃይለ ሥላሴ የኢትዮጵያን አርበኞች እየመሩ ከጃፓን ጋር ግንኙነት ፈጥረዋል በሚል ህሳቤ እንዲህ ብሎ ነበር። “የሞትና የሽረት ጦርነት በሚመስል መልኩ ይህች የሃበሻ አገር ለመላው የነጭን ዘር ሁሉ” እየተዋጋችን ነው። “ይህች አገር አሸናፊ ከሆነች የሚያስከፍለው “ዋጋ ሊታሰብና ሊገመት አይችልም። ይህች አገር ኢላማ ያደረገችው የራሷን ነጻነት ብቻ ሳይሆን በተዛማጅ መላውን የጥቁር አፍሪካን አገራትና ህዝቦች ጭምር ነው” ብሎ አሳሳቢነቱን ፕሮቻስካ አስምሮበት ነበር። “It is hardly possible to imagine a more unhappy situation of a white man than to have to live under the oppression of an Abyssinian grandee. The prevalence of this contemptuous invective is characteristic of the mentality and attitude of the natives who imagine themselves to be infinitely superior to the white race. “ሃበሻው በነጭዎች ላይ ያለውን ንቀትና የበላይነት ስነ ልቦና” ለማሰብ መቻል አለብን ብሎ ጥቁር አፍሪካን በሙሉ የተቀራመቱትን የነጭ ገዢዎች አስጠንቅቆ ነበር።

ዛሬ፤ “በቃ (NO MORE” የሚለውን ዓለም አቀፍ እንቅስቃሴ ማየት ያለብን ከዚህ ካለፈው ታሪካችን ጋር አያይዘን ነው። ልክ ያኔ የጣሊያንን ፋሽስት ኢትዮጵያዊያን (ሃበሻዎች) እንደ ተዋጉት ሁሉ፤ በአሁኑ ወቅት የአዲሱ የቅኝ ገዢዎች አለቃ የሆነውን የአሜሪካን መንግሥት ያስፈራውን “በቃ” የሚለውን መፈክርና መርህም ሳናመናታ ማስተጋባት ያለብን ለዚህ ነው። ይህንን አፍሪካ አቀፍ፤ ጥቁር ሕዝቦች አቀፍ፤ ጭቁን ሕዝቦች አቀፍ የሆነን መርህ በአስርት ቢሊየን ዶላርም ቢሆን ልንተካው አንችልም። ነጻነት፤ ሉዐላዊነት፤ ክብርና ብሄራዊ ጥቅም በገንዘብ ሊገዛ አይችልም። የአሜሪካን መንግሥት ካሳሰቡት አስኳል ጉዳዮች መካከል “በቃ” የሚለው እንቅስቃሴ ከፍተኛ ቦታ ይዟል። 

ፕሮቻስካና የእሱን መርህ የተከተሉት የኢትዮጱያ ምሁራንና የፖለቲካ ልሂቃን፤ ከተማሪው እንቅስቅሴ ጀምሮ እስካሁን ድረስ የሚያስተጋቡት የብሄር፤ ብሄረሰብና ሕዝቦች የማይታረቀው ልዩነትና መስመር ተመሳሳይነት አለው። ህወሓትና ኦነግ ሽኔ “የራስን እድል በራስ መወሰን” መብት ነው የሚሉት ከየት መጣ? ብለን መጠየቅ አለብን። የፌደራል አስተዳደርን መፈለግና “የኔ መንግሥት ብቻ ለራሴ የዘውግ አባላት” የሚለው የተለያዩ ናችው። ዲሞክራሳዊ የፌደራል ስርዓት ለኢትዮጵያ እንደሚያስፈልጋት አምናለሁ። ኢትዮጵያን የሚከፋፍል መርህ በሕገ መንግሥት አስገብቶ ኢትዮጵያን ለመታደግ ይቻላል ወይ? የሚለውን ግን አቀርባለሁ። ፕሮቻስካ እንዲህ ብሎ ነበር፤ 

 “The numerous peoples and tribes who inhabit the territory of the Ethiopian state, and which differ in race, language, culture and religion from the ruling minority of the Abyssinians proper, would long ago have thrown off the Abyssinian yoke if they had been given the right of self-determination. Instead, they are being forcibly kept cut off from European influences and from the advantages that progressive colonization could confer upon the country. The final aim of (Abyssinian) policy of antagonism to the white race, in co-operation with Japan, is nothing less than to act as the champions of all the colored peoples of Africa… It is incumbent on the legations of the civilized nations in Abyssinia to warn their governments to take a definite stand before the Abyssinians attack and destroy western culture and civilization in its entirety. There is no such thing as a united Abyssinian people. The greater part of the non-Christian tribes in Abyssinia has no more burning desire than to be freed from the tyranny of the Amhara… If they would vote freely, they would certainly prefer a European protectorate to universally hated extortionists and slave drivers. This country is cracking at all its joints and has only been kept together up to the present by methods of ruthless coercion.”

አናስታውስ፤ የሃበሻ፤ በኋላ አማራ ብሎ ፕሮቻስካ የገለጸው የበላይነት አመራር ባለፉት አምሳ አመታት የት አለ? የፖለቲካ ሆነ የኢኮኖሚ የበላይነት ስለሌለው ጭምር ነው፤ የአማራው ሕዝብ በየቦታው የሚጨፈጨፈውና ለእልቂቱ እንኳን አንድ ጊዜም ቢሆን ጨፍጫፊዎቹ ለሕግ በተጠያቂነትና በሃላፊነት ያልቀረቡበት ዋና ምክንያት። ባለፈው “ኃጢያት” ከሆነ በአገር ውስጥም ሆነ በመላው ዓለም አገራት ሁሉ ቢፈተሽ በየቤቱ ብዙ ጉድ አለ። እርግጥ ነው፤ በኢትዮጵያ ረዢም ታሪክ ግፍና በደል አልተፈጸመም ለማለት አልችልም። የምንወያየው ባለፈ ቅሬታ ሳይሆን አሁን ባለውና ወደ ፌት ሊሰራ በሚገባው መርህ ላይ ነው። ዋናው ጥያቄ ኢትዮጵያዊያን እንዴት አብረው፤ “ተደምረውና” ተባብረው ለወጣቱ ትውልድ ሰፊ የስራ እድል ይፍጠሩ፤ እንዴት እርስ በእርስ ከመጨፋጨፍ አልፈው ድህነትን ይቅረፉ? ወዘተ የሚሉ መሰረታዊ ጥያቄዎች ናቸው።

ህወሃትን ልውሰድና ፕሮቻስካ እንደሚለው ህወሓት በበላይነት እንዲገዛው የሚፈልገው አሰልጣኙን የነጮችን፤ የአሜሪካን መንግሥት ሊሆን ይችላል? አይመስለኝም፤ ነጻነቱ ተከብሮ ሊናገር ቢችል፤ አብዛኛው የትግራይ ሕዝብ የነጮች አምልኮ አለው ለማለት አልችልም። ነጭ ገዢዎች አንድም የጥቁር አፍሪካ አገር ያሰለጠኑትና ያዘመኑት የለም። “የራስን መብት በራስ” የሚለው መርህ ለከፋፍለህ ግዛውና ብላው ዋና መሳሪያ ነው። ለዚህ ነው፤ ህወሃት የራሴን ምርጫ አካሂጃለሁ፤ የፌደራሉ መንግሥት አያዘኝም፤ የሌላውን መሬት የመንጠቅ መብት አለኝ፤ “ምእራብ ትግራይ” የታላቋ ትግራይ አካል ነው ወዘተ የሚለው።

ፕሮቻስካ ከጻፈው እስካሁን ድረስ ትክክል ነው የምለው “There is no such thing as a united Abyssinian people.” ይህ ትክክል ነው። ለምሳሌ፤ አቢሲኒያ የትግራይን ሕዝብ ይጨምራል። የአማራው ህዝብም ቢሆን “የጎንደር፤ የወሎ፤ የጎጃም፤ የሸዋ፤ ቅማንት፤ አገው” ወዘተ እያለ ስለሚኖር አንድ ወጥ የሆነ አመለካከት አለው ለማለት አልችልም። ውጭ ያለውን ግዙፍ አማራ ብንገመግመው ከአንድነቱ ይልቅ ልዩነቱ ይበልጣል። አርባ ወይንም ከዚያ በላይ በውጭ የሚኖሩ የአማራ ድርጅቶች ይዞ ጭና ለማድረግ አይቻልም። ጫና ለማድረግ የሚቻለው የአላማ አንድነትን መርህ አድርጎ እየተናበቡ መስራት ብቻ ነው። አለያ የፖለቲካ ንግድ ነው። 

አንድ ወጥ የሆነ የአማራ ህዝብ ገና በጅማሮ ጉዞ ላይ እንጅ የሰከነና እየተናበበ የሚሰራ አንድ ወጥ የአማራ ህዝብ የለም። ለዚህ ግብአት የሆነባቸው ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል፤

  • አንድ፤ የአማራው ሕዝብ በመላው ኢትዮጵያ የሚሰራና የሚኖር መሆኑ (ኢትዮጵያዊነቱ ኩራቱ ስለሆነ)፤ 
  • ሁለት፤ የአማራው ልሂቃንና ምሁራን ከአማራነታቸው በበለጠ በኢትዮጵያዊነታቸው ማመናቸው ዋናዎቹ ናቸው። ይህም ሆኖ ግን አንድ ሃቅ አለ። ይኼውም አማራው በያለበት ስለሚጨፈጨፍ የአማራው ጥያቄ የህልውና መሆኑን መርሳት የለብንም። 

አማራው ህልውናውን ካስከበረ የኢትዮጵያን ህልውናም ለመታደግ ይችላል። በሰሜን በህወሓት ይጨፈጨፋል፤ በቤኒ-ሻንጉሉ ጉሙዝ፤ በወለጋና በሌሎች አካባቢዎች በአማራነቱ ብቻ እየተለየ ግፍና በደል ይደርስበታል። ለዚህ መከታ የሚሆነው መደራጀትና አቅምን ማጠናከር፤ መደራጀትና እየተናበቡ መስራት፤ መደራጀትና ወዳጆችን ማፍራት ወዘተ ነው።

በዘላቂነት ግን፤ ሕገ መንግሥቱና የአስተዳደር መዋቅሩ ካልተቀየረ የአማራው ሕዝብ ለጭፍጨፋና ለድህነት የተጋለጠ ሆኖ ይቆያል። 

ከላይ እንዳሳየሁት፤ የምእራብ መንግሥታት፤ በተለይ የአሜሪካ መንግሥትና የተባበሩት መንግሥታት ተቋማት ይህ ሁሉ ግፍና በደል በአማራው ላይ፤ ጦረንቱ ከተጀመረ ወዲህ ደግሞ በአፋሩ ላይ ሲደርስበት ለምን ድምጽ አያሰሙም” ለሚለው ጥያቄ መልሱ ከላይ ያቀረብኩት ነው። በአማራው ላይ ያላቸውን ቂም አልረሱትም፤ አይረሱትም። ይህ ቂም በአገር ወዳድነቱ እንጅ በሰራው ወንጀል አይደለም። ግን፤ በአማራው ላይ በተከታታይ እልቂት የሚካሄደው በሰራው ኃጥያት ምክንያት ነው፤ ይበለው የሚሉ የአገር ውስጥና የውጭ ኃይሎች አሉ። አንዳንድ የአማራ ወይንም ሌላ መለያ የያዙ ምሁራን ሁኔታውን በማባባስ በአማራው ላይ “ጭፍጨፋ (Genocide) አልተካሄደም” ይላሉ። ይባስ ብሎ በአማራው ላይ የተካሄደው ዘውግ ተኮር እልቂት የተባበሩት መንግሥታት የተቀበለውን መስፈርት ያሟላል ብለን የምንተቸውን ግለሰቦች ሃቀኛነትወይንምሙሉነት የጎደለው ክስ ነው ይላሉ። ለመሆኑ ስንት አማራ ቢጨፈጨፍ ነው መስፈርቱ የሚሟላው? ተብለው ቢጠየቁ ይሸሸጋሉ እንጅ አጥጋቢ መልስ የላቸውም። 

ጭፍጨፋ የተለመደ በሆነባት ኢትዮጵያ የተጨፈጨፈውና አሁንም የሚጨፈጨፈው አማራው ብቻ አይደለም። ህወሓት በአኟክ፤ በሶማሌ፤ በኦሮሞ፤ በአፋር፤ በኦሞቲክ ወገኖቻችን ላይ ጭፍጨፋ አካሂዷል። መረጃዎች የሚያሳዩት ግን፤ ሆነ ተብሎ በተከታታይ ባለፉት አምሳ አመታት ዘውግ ተኮር እልቂት የተፈጸመበት አካል አማራው ነው። በጥቅሉ ሲገመገም፤ የአማራው እልቂት እንደ ተራ ነገር የሚታየው፤ ኢትዮጱያ በብሄራዊ አንደነቷ ኮርታ፤ በኢኮኖሚዋ ጠንካራ ከሆነች የእሷ ተምሳሌነት ለመላው ጥቁር አፍሪካ በር ከፋች ይሆናል የሚል ስጋት እንዳለ አሳስባለሁ። 

ህወሓትን ለስልጣን ያበቁት የውጭ ኃይሎች ናቸው። ኢትዮጵያ እውነተኛ ዲሞክራሳዊ ፌደራል መንግሥት እንዳይኖራት በዘውግና በቋንቋ እንድትከፋፈል የረዱት እነሱ ናቸው። አሁንም “ኮንፊደሬሽን” ብለው ከጀርባ የሚገፉት እነሱው ናቸው። ግን፤ የውስጥ አጃቢና አገልጋይ ከሌላቸው ስኬታማ ለማድረግ አይችሉም። ለህወሓት መረጃና ሌላ መሳሪያ የሚለግሰው ማነው? ብየ ራሴን እጠይቃለሁ፤ አንባቢውም ራሱን ይጠይቅ። የውጭ ድጋፍ ባይኖረው ኖሮ፤ እንዴትና በምን ተአምር ነው አዲስ በባን ሊቆጣጠር ሳምንታት፤ ቀናት ቀርተውታል ይሉ የነበረው? 

የአሜሪካና ሌሎች ምእራባዊያን ለምንድነው ተከላካዩንና በህወሓት እየሰለጠነና እንደ አሸን የሚላከውን ህዝባዊ የትግራይን የጦር ኃይል አሁንም ቢሆን ትችት የማያቀርቡበት? የሚያደርጉት ሁሉ ተጻራሪውን ነው። ለምሳሌ፤ ቀን ከሌት የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነትና የዜጎቿን ደህንነት ለመታደግ የሚሞክረውን የኢትዮጵያንና የኤርትራን መንግሥታት፤ የአማራውን ልዩ ኃይል፤ ፋኖን፤ የአፋሩን ልዩ ኃይል ተከሳሽ ያደረጉት ለምንድን ነው? ብለን መጠየቅ አለብን። 

የተባበሩት መንግሥታት ጤና ጥበቃ ድርጅት ቦርድ ተሰብስቦ የኢትዮጵያን ተወካይ አምባሳደር ቴዎድሮስ አድሃኖምን እንዲተች አለመፍቀዱ ሁኔታውን ዓለም አቀፍ ያደርገዋል። ይኼንን እንደ ሴራ ማየት ግድ ይላል። 

እኛ፤ በተለይ በውጭ የምንኖር ትውልደ ኢትዮጵያዊያን ለህወሃት ድፍረትና አቅም የሚሰጡትን ኃይሎች በቃ ለማለት ካልደፈርን እልቂቱና ውድመቱ አያቆምም። ከህወሓት ጋር እርቅ ያስፈልጋል ለሚሉት የምጥይቀው፤ ለመሆኑ የተደፈሩ ሴት ልጆች፤ እህቶች፤ አክስቶች፤ ሚስቶች፤ እናቶች አሏችሁ? በኔ ቢደርስስ ምን አደርግ ነበር? ለማለት ድፈሩና ፍረዱ እላለሁ። 

እኔ፤ ህወሓት መርሆውን ይቀይራል የሚል እምነት የለኝም። ይህ ከሃዲ፤ የጥፋትና የእልቂት ቡድን ከጅምሩ ከጥፋቱ ለመማርና ለሰላም ድርድር ፈቃደኛ ሆኖ መሳሪያውን ወደ ጎን ትቶ ለዘላቂ ሰላምና ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ደህንነት የሚቆም አካል ሆኖ አላገኘሁትም። ከሀሓት መሪዎች ጋር የሰላም ድርድር ለማድረግ ይቻላል የሚሉ ኃይሎች መብታቸው ነው። ግን እጅግ በጣም ተሳስተዋል። በተለይ፤ በአፋሩና በአማራው ሕዝቦች ላይ ሲካሄድ የቆየው የከፋ እልቂትና ውድመት እንዲቀጥል የሚፈልጉ አካላት ይኖሩ ይሆን? የሚል ጥያቄ በየቦታው እየተነሳ ነውና ጥያቄው አግባብ ስላለው እውቅና ቢሰጠው የሚሻል ይመስለኛል። 

መዘናጋት ለምን? መዘናጋት ለማን? 

የኢትዮጵያ መንግሥት ህወሃት ማድረግ የሚገባውን አሳሪ (binding) ሁኔታ ከላይ በመግቢያው ላይ አቅርቤዋለሁ። ህወሃት ብቻውን የሚሰራ ድርጅት አይደለም። ልክ በጣልያን ወረራ ጊዜ ለቅኝ ገዢዎች ታማኝና አገልጋይ የሆኑ አካባቢዎች እንደ ነበሩ ሁሉ፤ በአሁኑ ወቅት ደግሞ ለእነዚህ የውጭ ኃይሎች አገልጋይና ታማኝ ሆኖ የሚገኘው ህወሓትና አጋሩ ኦነግ ሽኔ ነው። ይህ መሆኑን ከተቀበልን፤ ጦርነቱ በአንድ በኩል በአፋርና በአማራ፤ በሌላ በኩል በህወሓት መካከል ነው ለሚሉ አካላት ከታሪክ አለመማራቸውን እገልጻለሁ። በዋናነት የጦሩነቱ ኢላማ የአማራው ሕዝብ መሆኑ አይካድም። ግን፤ አማራው የሚታገለውና ከፍተኛ ዋጋ የሚከፍለው ለራሱ ህልውና ብቻ አይደለም፤ ሆኖም አያውቅም። አፋሩም ተመሳሳይ ነው። 

የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጥናት በገና ቀን የህወሓት መስራች፤ የውጊያ መሪ፤ የለየለት ሙሰኛና ቂመኛ የሆነውን ስብሃት ነጋን ሲፈቱ “እግዚኦ፤ ይህ ከአንድ ክህደት ወደ ሌላ ክህደት የሚያመራ ውሳኔ ይሆን ወይ” የሚል ማስታወሻ ጻፍኩ። ስብሃት ነጋ ከተናገራቸው ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚተላለፉ ደዌዎች መካከል “የአማራ ጥሩ የለም። አማራን መግደል፤ መቀጥቀጥ (እንደ እባብ)፤ ሴቶቹን መድፈር (ህጻናትን፤ መናኩስትን ሳይቀር)፤ ኃብቱን መዝረፍና ማውደም፤ ስነ ልቦናውን ማዳከም” የሚሉትን የጥላቻ ትምህርትና ቅድመ ዝግጀት ካዛመቱትና ካጠናከሩት የህወሓት አመራሮች መካከል ዋናው ስብሃት ነጋ ነው። ኢትዮጵያን ለማዳከምና ለመበታተን ከግብጽና ከሱዳን ወታደራዊ ኃይል ጋር የዶለተው አንዱ ስብሃት ነጋ ነው። ህወሓት በስልጣን ላይ በነበረበት ወቅት ራሱን፤ ቤተሰቡንና ዘመድ አዝማዱን በጉቦና በሙስና ካከበሩት ቢሊየነሮች መካከል አንዱ ስብሃት ነጋ ነው። 

በደደቢት በረሃ በተደረገው ውይይትና እቅም መሰረት፤ ወልቃይት፤ ጠገዴ፤ ጠለምትና ራያን በመሳሪያ ኃይል ይዘው የነዋሪውን ሕዝብ የዘውግ ስርጭት ከለወጡት መካከል ቁንጮ ነው ተብሎ የሚወራለት ስብሃት ነጋ ነው። እነዚህ ምክንያቶች በድምራቸው ሲገመገሙ ይህ ግለሰብ ለፍርድ ለማቅረብ እንጅ ለመፍታት የሚያስችል ምክንያት ፈልጌ ለማግኘት አልቻልኩም። ይህ ሰው ጠንቅነቱ ለአማራው ሕዝብ ብቻ አይደለም። ለኢትዮጵያና ለሁሉም በኢትዮጵያዊነታቸው ለሚያምኑ ሁሉ ነው። 

ሽብርተኞችን ለመፍታት ምክንያት አለ የሚለውን አስተናግዳለሁ። የመንግሥት ምስጢሮች እንዳሉ ይገባኛል። በመንግሥት ላይ ከፍተኛ የውጭ መንግሥታት ጫና እንደሚያደርጉ አውቃለሁ። ግን የውሳኔው ጥቅምና ጉዳት ታስቦበት ለኢዮጵያ ሕዝብ ሃቀኛና ሙሉነት ያለው ገለጻ መደረግ ነበረበት፤ አልተደረገም። ለምን?  

በአማራው ላይ የተከሰተው ጥላቻ (Amhara Xenophobia) ለምን?

ዜኖፎቢያ “የውጭ ዜጎችን መጥላት” የሚል ትርጉም አለው። የአማርው ሕዝብ በመላው ኢትዮጵያ ተሰራጭቶ የሌላውን ወገኑን ወግና ባህል ተቀብሎ ድሮና ግሮ የሚኖር ሕዝብ ነው። ባለፈው ጽሁፌ እንዳሳየሁት እስካልነኩት ድረስ እንደዚህ ሕዝብ “ጨዋና ሌላውን አስተናጋጅ ሕዝብ የለም” ብለው የሚናገሩት ፈረንጆች ብዙ ናቸው። ባለፉት አምሳ ዓመታት ግን፤ እነ ዋለለኝ ከፕሮቻስካና ከሌሎች የውጭ የፖለቲካ ልሂቃን እየቀዱ በአማራው ላይ ያሰራጩት ትርክት አማራውን ልክ እንደ ውጭ አገር የቅኝ ገዢ ሰው እንዲጠላ፤ “ወራሪና ጨቋኝ ነህ” ተብሎ እንዲጋለጥና እንዲጨፈጨፍ አመቻችተዋል። አብዛኛው የአማራ ሕዝብ ድሃ መሆኑን የረሱት ይመስላል።

በአማራው ላይ በጂምላ የተከሰተው የጥላቻ ችግር ጥልቅት እንዲይዝ የሆነባቸው ብዙ ምክንያቶች አሉ። ከእነዚህ መካከል የአማራውን ክልል የሚመሩት ኃይሎችና ካድሬዎች የታነጹትና የሚመሩት በህወሓት ዘውጋዊ ፍልስፍና፤ አደረጃጀትና ሕገ መንግሥት መሆኑ ዋናው ነው። የማራው ሕዝብ የቁርጥ ቀን መሪዎች አሉት ወይንስ የሉትም? የሚለውን ጥያቄ እኔ ለመመለስ አልችልም። መመለስ ያለበት ተራው ሕዝብ ነው። በጦርነቱ ፊት ለፊት በጀግንነት እየተዋጉ ህወሓት የነጠቃቸውን፤ እልቂትና ውድመት ያካሄደባቸውን የአፋርንና የአማራን መሬቶች ነጻ ያወጡት ኃይሎች ክብርና ምስጋና ይገባቸዋል። የአፋር ልዩ ኃይል፤ የአማራ ሚሊሽያ፤ ልዩ ኃይልና ፋኖ፤ መከላከያ፤ ከእነሱ ጀርባ ሆነው ስንቅና ትጥቅ ያቀረቡት ኢትዮጵያዊያን አጅግ ብዙ ናቸው። የቁርጥ ቀን ልጆች ቢባሉና ኒሻን ቢሸለሙ ደስ ይለኛል። 

ካለፈው እልቂትና ውድመት መማር ወሳኝ ነው። የኢህአዴግን ሕገ መንግሥትና የክልሎችን አወቃቀር እንዳለ ተቀብሎ ኢትዮጵያን ወደፊት ከሚከሰቱ ስርዓት ወለድ ተግዳሮቶች መንጥቆ ማውጣት አስቸጋሪና የማይቻል ነው። ህወሓት ቢወገድም፤ ሌላ ህወሓት መሰል ኃይል መመስረቱ አይቀርም። በተጨማሪ፤ የሕግ የበላይነት አለ ለሚል የኢትዮጵያ መንግሥት በአፋርና በአማራ ላይ እልቂት መካሄዱ ሃቅ ሆኖ ሳለ፤ በአማራው ሕዝብ ላይ፤ በአማራነቱ ብቻ እስካሁን ድረስ ጭፍጨፋ ያካሄዱ ወንጀለኞች የፌደራልና የክልል ባለሥልጣናት በጋራ ሆነ በተናጠል አጥፊዎቹ ለሕግ ቀርበው የእድሜ ልክ እስራት አለመፈረዱ እልቂቱና ውድመቱ እንዲባባስ አድርጎታል። የአማራው ግድያ እንደ ተራ ነገር የተለመደ ሆኗል የምለው ለዚህ ነው። ይህ ጨዋ ሕዝብ ለማን አቤቱታ ያቅርብ? የሚለውን መልሱልኝ!!!

እኔ ችግሩን የማየው ከኢትዮጵያ አገራዊና ግዛታዊ አንድነት፤ ሁሉን አሳታፊ ከሆነ አገዛዝና ከፍትሃዊና ዘላቂ ልማት ጋር አቆራኝቸ ነው። የአፋሩ፤ የአማራው፤ የሶማሌው፤ የአኟኩ፤ የኦሮሞው ወዘተ መብት መከበር ስኬታማነት ሊከፋፈል አይችልም። የሕግ የበላይነት አስፈላጊ የሚሆነው ለዚህ ነው። በሕግ ፊት እያንዳንዱ ግለሰብ እኩል መሆን አለበት። 

የዚህ ተከታታይ መሰረታዊ ችግር ለኢትዮጵያ ምን ፋይዳ አለው

የአቢሲንያን (በአብዛኛው አማራውን) በሚመከለት የፋሽስቱ መንግሥት የመሰረተው የአስተዳደር ወዋቅር መለስ ዜናውዊ እየመራ ከመሰረተው ሕገ መንግሥትና የአስተዳደር ስሪት አይለይም። ፕሮፌሰር አለሜ እሸቴ እንደ ገለጸው “ Mussolini’s five tribal governments… compared —with CIA-Woyanne Fascistic apartheid and bantustanization” show several instances that the CIA-Woyanne carried the tribal dismemberment of Ethiopia and the crime of ethnic cleansing, massacres and mass deportation to a much higher stage than was even contemplated by Mussolini.” 

ሰብአዊ መብትን እንደ ዋዛ የሚናገረው የአሜሪካ መንግሥት

የአሜሪካ ባለሥልጣናት ለሰብአዊ መብት መከበር ደንታ የላቸውም። ምክንያት አድርገው ግን በሊቢያ፣ በኢራክ፤ በሶርያ፤ በአፍጋኒስታን፤ በችሌ፤ በሆንዱራስ፤ በኒካራጓ፤ በዪክሬን፤ በሩሲያ፤ በቻይና፤ በኢራን ወዘተ ተጠቅመውበታል፤ ወደፊትም አያርፉም። ለሰብአዊ መብት ከተቆረቆሩ፤ ለምን ህወሓት የትግራይን እናቶች ልጅ አልባ እንዳይሆኑ ድምጽ አያሰሙም? ለምን ሰብአዊ መብት አይከፋፈልም ብለው በአፋሩና በአማራው ላይ የተካሄደውንና አሁንም የሚካሄደውን እልቂት አያወግዙም? የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጥናትስ የአማራውን እልቂት ለምን በቸልተኛነት ያዩታል? 

የኢትዮያን ድሃ ሕዝብ ሰብአዊ መብት ለመታደግ የሚቻለው ኢትዮጵያን ከአጓ በማስወጣት አይደለም፤ ብድር እንዳታገኝ ጫና በማድረግ አይደለም። የአሜሪካን ዜጎች ከኢትዮጵያ ውጡ በማለት አይደለም። ቻይና ብታደርገውም ባታደርገውም፤ ለራሷ ጥቅም ቢሆንም ባይሆንም፤ በአፍሪካና በቻይና የትብብር መድረክ ላይ በሚቀጥሉት ሶስት አመታት $300 ቢሊየን የሚያወጣ ሸቀጣ ሸቀጥ ከአፍሪካ እገዛለሁ ብላ ቃል ገብታለች። የአሜሪካ መንግሥት ግን፤ “ወዳጅ” ሆና የቆየችውን ኢትዮጵያን ለመቅጣት ከአጓ አስወጣለሁ ብሎ አስፈራርቷል። የትኛው ነው ፍትሃዊ? ብለን መጠየቅ አለብን።  

የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያ ጋር ያለውን የቆየ ግንኙነት ሊያድሰው ይችላል። ለዚህ ዋናው ምልክት ኢትዮጵያን ወደ አጓ መመለስና በዝቅተኛ ወለድ ብዙ ቢሊየን ዶላር ከአበዳሪ ድርጅቶች እንድታገኝ ማመቻቸት ነው። 

የአሜሪካ መንግሥት ከኢትዮጵያና ከሌሎች የጥቁር አፍሪካ አገሮች ጋር ወዳጅነት ከፈለገ አሁን የሚከተለውን የቅኝ ገዢዎች መርህ መከተሉን ማቆም አለበት። ጥቁር አፍሪካም አህጉር አቀፍ ትብብርና የጋራ ገበያ ለመመስረት መወሰን አለባት። “ድር ቢያብር አንበሳ ያስር” እንዲሉ የጥቁር አፍሪካ ህብረት ወሳኝ ነው። በቃ (NO MORE) መቀጠል አለበት የምለውም ለዚህ ነው። 

ዋናው የኢትዮጵያ ተግዳሮትና ፈተና ስርዓቱና የዘረጋቸው መዋቅሮች ናቸው። የሰላም ውይይት ይደረግ የሚለው እንዳለ ሆኖ፤ ዋናው ትኩረት ሕገ መንግሥቱንና የዘረጋውን የአተዳደር መዋቅር ባስቸኳይ ለመቀየር መድፈር ነው። 

በመጨረሻ የአማራው ሕዝብ ራሱን ለማዳን ምን ቢሰራ ይሻላል ለሚለው ከላይ መደራጀትና አቅምን በሁሉም መንገድ ማጠናከር በሚለው ክፍል ጠቁሜያለሁ። 

References and citations 

ህወሓት በአማራው ላይ ያካሄደውን የቂም በቀል እልቂት ከዚህ በታች ባለው ቪዲዮ ይመልከቱ  
Ethiopia civil war: Stories of war crimes uncovered in Amhara
https://www.channel4.com/news/ethiopia-civil-war-stories-of-war-crimes-uncovered-in-amhara
Aleme Eshete, Origin of Tribalization of Ethiopian Politics: From Fascism to Fascism, Copyright © 2003 by Prof. Aleme Eshet

የኤዲተሩ ማስታወሻ ፡ በሽፋን ምስልነት የተያያዘው የኢትዮጵያ እና አካባቢው ካርታ በጎግል ድረ ገጽ የተወሰደ ነው

_
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here