spot_img
Monday, May 29, 2023
Homeነፃ አስተያየት የሕወሃት ትግል - ወደ ነጻነት ወይስ ከ-ነጻነት?   

 የሕወሃት ትግል – ወደ ነጻነት ወይስ ከ-ነጻነት?   

- Advertisement -

ብርሃኑ ከበደ 
ካልጋሪ ካናዳ 
የካቲት 4 2014 ዓ ም  

የተለያዩ የማህበራዊ-ስነልቦና ጥናቶች እንደሚያሳዩት ሁለት አይነት የነጻነት ክስተቶች አሉ። አንደኛው ለነጻነት ወይም ወደ  ነጻነት ሲሆን ሌላው ደግሞ ከነጻነት ጋር የሚደረጉ ትግሎች ናቸው። 

 በመጀመሪያ ሕወሃት ለ15 አመታት ለነጻነት ተዋጋ። ቀጥሎም ለ27 አመት “አንድነትን” መረጠ። አሁን ደግሞ “ለነጻነት”  እያለ ነው? ወይስ… 

ሁሉም በየጎራው የጦርነቱን ፍጻሜ እንደየ ምኞቱ አንዲጠናቀቅ እየተጠባበቀ ነው። አንዳንዶች ፍጻሜው በቅርቡ  አንዳለቀው የአፍጋኒስታን የርስ በርስ ጦርነት ሕወሃት እንደ ታሊባን አማጽያን (Taliban) “እምበር ተጋዳላይ” እየተዘፈነለት  በድል ወደ አዲስ አባበ ሲገባ ለማየት ተመኙ። ሌሎች ደግሞ ከጥቂት አመታት በፊት በስሪላንካ ከምደረ ገጽ እንደጠፉት  የታሚል ነብሮች (Tamil Tigers) ሕወሃትም እንደ ዱቄት ከኢትዮጵያ ብን ብሎ እንዲጠፋ እየተመኙ ነው። 

ይህ በመሆኑም በጥይትም ይሁን በቃላት በሚገበረው ጦርነት ጩኸት የታፈነውን ጥያቄ መልስ ለመስጠት  መሞከር ወቅታዊ ነው። የሕወሀት ትግል ወደ ለነጻነት ወይስ ከ-ነጻነት? 

የመመሪያ ጽንስ 

የሕወሀት መስራች ሃሳብ የቀድሞው የአዲስ አበባ ዮኒቨርስቲ የተማሪዎች ንቅናቄ መሪ የነበረው ዋለልኝ መኮንን  የጻፈው ባለ አምስት ገጽ “On the Question of Nationalities in Ethiopia,” ወይም “በኢትዮጵያ ብሔሮች ጥያቄ ላይ” በሚል  ርዕስ የተፃፈው ጠያቂና የመወያያ ጽሑፍ ነው። በ 1961 የተጻፈው ይህ ዝነኛ ጽሑፍ አዲስ አከራካሪ ሃሳብና ጥያቄ  ቢያመጣም ላነሳው ጥያቄ ግን ግልፅ ያለ መልስ አላከተትም ነበር። በጣት የሚቆጠሩ የህወሀት መስራች አባላት ይህን ፅሁፍ  የድርጀታቸው መስራች ፀንሰ ሃሳብ አድርገው ተቀበሉት። በተለይም በአማራው ላይ ያተኮረው የጽሁፉ ወቀሳና ድምዳሜ  ለሕወሀት የትግል መጀመሪያ ጽንስ ሃሳብ የሃገሪቷ ጨቋኝ እና የችግሮቿ ሁሉ መነሻ በተለይም ለትግራይ ህዝብ የዘመናት  በመከራ መሰቃየት ብችኛው ምክንያት አማራ ሆኖ ታወጀ። የ 1976ን የቲ ፒ ኤል ኤፍን ( የሕወሀት) ማኒፌስቶ  ይመልከቱ። 

1976 TPLF manifesto። (page 14) 

ለዚህ የሕወሃት የማያረጅ የማንነት መገለጫ ማስረጂያ ከጥቂት ሳምንታት በፊት የሕወሀት ዋና የጦር መሪ የሆኑት  ሌተናነት ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሣኤ የሚከተለውን በ (theelepahnt.info) ጽፈው ነበር።

“ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረስቦች ሃገር ነች። ወደፊት መቀጠል ከተፈለገ ይህን ሃቅ መቀበል የግድ ነው። በምንም ሁኔታ የግዛት  ክምችት ወይም የአንድ ብሄር በሌሎች ላይ የበላይነት ወደሚኖርበት ዘመን መመለስ አንችልም ” (ትርጉሙ የኔ ነው) 

“የበላይ” ተብሎ የተከሰሰውን ብሄር ማንነት መገመት ቀላል ይመስለኛል ። ነገር ግን ጄኔራሉ ብዙ ዘመናት ባስቆጠረው  ረጅሙ የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ያለምንም ክርክር በግልጽ የአንድ ብሔር የበላይነት የታየበትን የ27 አመታት “ዘመነ ሕወሀት” ማለታቸው እንዳልሆነ መገመትም አስቸጋሪ አይሆንም። 

በተጨማሪም ለተመሰረተበት ጽንሰ-መመሪያ በዘመኑ ተማሪ ለነበረው ወጣት ቀልብ ሳቢና ዝነኛ የነበረውን የማርክሲዝም  ሌኒንዝምን ርዕዮተ አለም ሕወሃት እነ አንድ ተጨማሪ የመርህ ግብዐት አደርጎ ተቀበለው ። ትግራይን ከመከራና ከድህነት  ነፃ ለማውጣት በአርአያነት የተመረጠችው ሀገር ደግሞ በድህነቷ በአውሮፓ የመጀመሪያዋ የሆነችው እጅግ ድሃና ‘ዓለም  በቃኝ’ ያለችው ኮሚኒስቷ አልባኒያ ነበረች ።የህወሐት በውዥንብር የተሞላው ረጅም እና ባለብዙ ዋጋ አስከፋይ ጉዞ  የተጀመረው እነዚህን ሁለት ተጻራሪ መርሆዎች ይዞ ነበር ። በአንድ ጎኑ አማራን “ጠላቴ” ብሎ ኦውጆ በሌላው በኩል ደግሞ  አህጉርንና ባህሮችን ተሻግሮ የሶቪየት ህብረትን፣ የአልባኒያን እና የቻይናን አርሶ አደሮችንና ላብአደሮችን በኮሚንዝም ስም  “እንዛመድ” ማለቱ ገና ከማለዳው የጉዞውን ወለፈንዲ አቅጣጫ ጉልህ ማሣያ ነበር። 

 ለነጻነት እና ከነጻነት 

 የ1970ዎቹ ዓመታት በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ በእጅግ አሳዛኝ እና አስከፊ ክስተቶች የተሞላ ዘመን ነበር ። ሃገሪቷና  ህዝቧ በድርቅና በረሃብ፣ በጦርነትና በሰደት እጅግ የተፈተኑበት ወቅት ነበር ። በተለይ በትግራይ በነበረው ድርቅ አስከፊነት  ያዘኑና የተማረሩ የትግራይ ተማሪ ወጣቶች በብዛት ሕወሃትን ተቀላቀሉ ። ድርቁና ረሃቡም ሕወሃትን ለዓለም ህዝብ  ለማስተዎወቅ ጥሩ ዕድል ፈጠረለት። ይህን እጅግ አሳዛኝ የሰው ልጅ ሰቆቃ በማየት እና በመስማት ያዘኑና ያፈሩ  ምዕራባዊያን ለሕወሃት በርካታ የቁስና የገንዘብ ብሎም የዕውቅና ድጋፍ ሰጡ። 

 ይህ ለሕወሃት እጅግ ትልቅ ጉልበት ሆኖታል ። ምናልባትም ሕወሃት ጦርነቱን ከሻዕቢያ ቀድሞ ለማሸነፍ  ያስቻለው አንዱ ምክንያት ይህ ሊሆን የሚችለው። በ 1981 የኢትዮጵያ ጦር ትግራይን ሙሉ ለሙሉ ለቅቆ ሲወጣ  ትግራይም ‘ከኢትዮጵያ ነጻ ወጣ”። ከዚያ ጊዜ ጀምሮ እስከአሁን ድረስ ትግራይ ሕወሃት ያለአንዳች ተቃውሞ ብቻውን  የሚያዝባት “ነጻ ሀገር” ሆነች ። 

ነጻ ‘ሀገር’ ትግራይ ከኢትዮጵያ ሰራዊት እንጂ ከረሃብ፣ ከድርቅና ስር ከሰደደ ድህነት ለመላቀቅ “ከነጻነትም” ነጻ  መሆኗ የግድ ነበር። የዚህም እሳቤ ሊሆን ይችላል ሕወሀት ከኢትዮጵያዊነቱ “የሚያስታርቀውን” ኢህአደግን ከዚህም ከዚያም  ሰብስቦ ያበጃጀው። በእጅጉ የተዳከመውና ተስፋ የቆረጠው የኢትዮጵያ ሰራዊትና አመራሩ ሲፈታ ሕወሀት በአጃቢዎቹ  ደጋፊነት የመንግስትን ስልጣን ተቆናጠጠ። የአንድን ብሄር የበላይነት ለማጥፋት የዘመተው “ነጻ አውጪ” እሱ ራሱ  በበላይነት ቀንበር ስር ወደቀ። የታሪክ ምጸት ማለት ይህ ነው! ያ ሁሉ ደም መፋሰስ፣ ያ ሁሉ የህይወትና የንብረት ውድመት  ነጻ ለመውጣት ከነበረ ለምን ወደ ኢትዮጵያዊነት መመለስ አስፈለገ ? 

በሚሊዮኖች የሚገመት ሕዝብ በረሃብ፣ በድርቅና በሞት እንደቅጠል ሲረግፍ በቴሌቪዥን ይመለከት የነበረውና  ህሊናው የተሸማቀቀው “የአለም አቀፉ ማህበረሰብ” የሕወሃት ፕሮፓጋንዳ ምርኮኛ ሆነ ። የዓለምም ትኩረት እየተደጋገመ  በኢትዮጵያ የሚከሰተውን ረሃብና ድርቅ ጨርሶ ድጋሚ ላለማየት የሚቻለውን ሁሉ ለማድረግ “አለሁ!” አለ ። እንደ አይ  ኤም ኤፍና የአለም ባንክ ያሉ ትላልቅ የገንዘብ ተቋማት ሀገሪቷን በስጦታም፣ በድጎማም ይሁን በብድር ለማገዝ በመቶ  

ቢሊዮኖች የሚቆጠር የገንዘብና የዕውቅና ድጋፍ ሰጡ ።ከመቼውም ጊዜ በላይ ተስፋ ሰጪ ኢኮኖሚያዊ እንቅሰቃሴ መታየት  ጀመረ። ኢትዮጵያም ከድህነት ለመላቀቅ ማዝገም ጀመረች ። በብዙ ሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎች ከጀርባ ሰባሪ ድህነት  በትንሹም ቢሆን ተላቀቁ። ስለዘላቂነቱ በእርግጠኝነት መናገር ባይቻልም ወደ ብልጽግና መንገድ የሚያመሩ ምልክቶች ግን  በየቦታው መታየት ጀመሩ። 

ሕወሃት ስልጣን ላይ ከወጣ ከስድስት ዓመት በኋላ በ1997ቱ ሀገራዊ ምርጫ ላይ “ማን ነጻ አውጪ፣ማንስ ነጻ  ወጪ” እንደሆነ ፍንትው ብሎ የታየበት ታሪካዊ ገጠመኝ ነበር ። የ79ኙን ብሄሮች (ትግራይን ጨምሮ ግን (አማራን  ሳይጨምር) የዲሞክራሲ መብት አስከብራለሁ ብሎ የማለና የቆረበ ነጻ አወጪ የዜጎችን ራስን በራስ የማስተድደር መብት  ጥያቄ “ምቾት የወለደው ዲሞክራሲያዊ ቅብጠት ነው” በማለት ከነጻ አውጪነት ወደ “አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ  ጉልበተኝነት” ተሸጋገረ። ሁለቱ ቀጣይ ምርጫወቸም ሕወሃት መጠነ ስፊ ንቀት ያሳየባቸው ዲሞክራሲያዊ ፌዝ ሆነው  አለፉ።

የ 2002ቱ የቄሮ፣ የፋኖ፣ የዘርማና የሶማሌ ወጣቶች እምቢ-ባይ ህዝባዊ አመፅ ሕወሃታዊያን እና በአምሳሉ ያበጃቸውን  ድርጅቶች ከታዛዢነት ከሕወሃት ነጻ አወጣ ። 

የእጣ-ፋንታ ነገር ሆኖ በኢትዮጵያ ላይ ፈላጭ ቆራጭ ይሁን ብሎ ሕወሃትን ተሸክሞ ስልጣን ላይ ያወጣው  ኢሕአዴግ ከ27 አመታት በኋላ ጎትቷ አወረደው። ረጅሙ የሕወሀት ወደ ነጻነት ጉዞ ከ27 አመታት የአዲስ አበባ ቆይታ  በኋላ ወደመቀሌ አቀና ። ሃርነት ለሕወሀት ረጅም፣ ጠመዝማዛ፣ አዙሪታም የቅዠት መንገድ እንጂ የሚደረስበት የዕውነት  መዳረሻ አልሆን አለ። 

 ጦርነት ለዳግማዊ ሃርነት 

ነጻይቱ ትግራይ አማራጭ የሌላት የሕወሃት ብቸኛ መነሻና መዳረሻ ጣቢያ ብቻ ሳትሆን መፎከሪያና ማስፈራሪያ  ምሽግም ሆነች ። “የምን ታደርጉኛላችሁ” ፉከራ የተጀመረው የተናጠል ምርጫ በማካሄድ ነበር። በመቀጠልም በኢትዮጵያ  “ህጋዊ መንግስት የለም” ወደሚለው ቁርጥ ያለ ውሳኔ በፍጥነት አደገ ። ለፉከራው ግለት የሚመጥን በአንድ በኩል ”  ኢትዮጵያና ኤርትራ የትግራይን ህዝብ ከምድረ ገጽ ሊያጠፉት ነው። ዓለም ድረስለን!” የሚለውን ጩኸት በአለም ላይ  በየቦታው የሚኖሩ ደጋፊዎቹ ቀንና ሌሊት እጅግ በተቀነባበረ ድራማ ሲከወኑት፣ በሌላ በኩል ደግሞ “ጦርነት ሁሌም  ባህላችን ነው” በሚሉ ሁለት ተጻራሪ ፉከራና ለቅሶ ታጅቦ አዲሱ የትግራይ “ወደ ነጻነት” ጉዞ ተጋጋለ ። ዓለም አቀፍ የዜና  አዎታሮችም አስተጋቢ አንዳንዴም አቀነባባሪ በመሆን ለትግሉ ያላቸውን አጋርነት በሚገባ አሳዩ። 

አንዳንዶች ጦርነቱን የጀመሩት ኢትዮጵያና ኤርትራ ናቸው ሲሉ ሌሎች ደግሞ ሕወሀት “ሳልቀደም ልቅደም”  በማለት የጀመረው “መብረቃዊ” ጦርነት ነው ብለው ይደመደማሉ። “ሳልቀደም ልቅደም” የሚለውን ምክንያት ለምን  ኢትዮጵያና ኤርትራ እንደሚነፈጉ ግን ምንም አሳማኝ ምክንያት እስካሁን ድረስ የለም። 

ሁኔታዎችን በደንብ ላጠኔው ግን የሕወሀት ፉከራ በቀላሉ የሚታይ ጉዳይ መሆን አልነበረበትም።   

• ሕወሀት 250ሺ የሰለጠነና የታጠቀ ኃይሉን በአደባባይ አሰልፎ ዝግጁ ነን እያለ፣ 

• 70% የኢትዮጵያ ተዋጊ ኃይል በትግራይ የሕወሀት የቁም እስረኛ በሆነበት ሁኔታ ውስጥ እያለ፣ • እጅግ ብዛት ያላቸው የጦሩ መሪዎች እና የብረት ለባሹ አባላት ወገንተኞች ሆነው በቀላሉ ወደሕወሀት  እንደሚከዱ እየታወቀ፣ 

• ከዚያም አልፎ ሕወሀት በግልጽና በስውር በሚቆሰቁሰውና በሚያቀጣጥለው የብሄር ግጭት እሳት አገሪቱ  በአራት ማዕዘን እየነደደች ባለችበት ወቅት፣ 

ኢትዮጵያ ለጦርነት ያደረገችው ዝግጅትና ፈጣን ግብረ መልስ ራሷን ለማዳን ያደረገችው ብልሃት፣ አስተዋይነትና ሀላፊነት  የተሞላበት የነፍስ ማዳን ምላሽ ነበር ብሎ በድፍረት መከራከር ይቻላል። 

እንደወትሮው የተኮረጀ ቢመስልም የሕወሃትን አዲስ ለነጻነት የሚደረግውን ጉዞ ከመቼውም በላይ የተለየ  የሚያደርገው ነገር የአለምን ቀለብ የሚስብ፣ በእርግጠኝነት ማንም ሰምቶት ዝም የማይልበት፣ በመፈክርና በፕሮፓጋንዳ  ቋንቋ የታጀበ፣ በግፍ ትርክት የተሞላውን የአንድን ባእድ ሃገር ታሪክ ቅቡልነት እንዲኖረው በተደጋጋሚ የሚያሰራጨው  የተለመደ ጥረት መሆኑ ነው። ፍርዱን ለአንባቢው ልተውና 

ለምሳሌ  

“ዘ ስቴት ኦፍ እስራኤል” “ዘ ስቴት ኦፍ ትግራይ”፣ 

“እስራኤል ዲፌንስ ፎርስስ (IDF)” “ትግራይ ድፌንስ ፎርስስ (TDF )” 

ከሁሉም በላይ ደግሞ የእስራኤል ልዩ መለያ እና ለሀገር መስራች ዋነኛ ምክንያትና መሪ ቃል “ዘር ማጥፋት”  ወይንም “ጀኖሳይድ” ለሕወሃት አዲስ የትረካው መሪ ሃሳብ መሆኑ ነው ። ወደ ዕውነተኛ ነጻነት የሚወስደው ረጅምና  አድካሚ ጉዞ አቋራጭ መንገድ ተፈልጎለት ጄኖሳይድን እየተመኙና ለጀኖሳይድ ሁኔታዎችን በማመቻቸት የሚደረግ ትግል  ከሆነ ነጻነትን ትርጉመ ቢስ ያደርገዋል። (ይህን ስል በግፍ ህይወታችውን ያጡ፣ በህገ ወጥ አረመኔዎች የተደፈሩና አካለ  ስንኩል የሆኑትን ሁሉ እጅግ ሃዘን በተሞላው መንፈስ እያሰብኩኝ ነው ።) 

 ከ ነጻነት – ወደ ነጻነት ጉዞ  

ከተመሰረተ የመጀመሪያዎቹን 15 አመታት ሕወሀት ትግራይን ከኢትዮጵያ ነጻ ያወጣበት የትግል ጊዜ ሊባል  ይቻላል። የቀጠሉት 27 አመታት ደግሞ ሕወሀት የታገለለትን አላማ ከድቶ በኢትዮጵያዊነት ቀንበር ስር ያሳለፈበት ዘመን  ነበር ሊባል ይቻላል።  

የሕወሃት ማለቂያው ሩቅ የቁማርተኝነት ጀብድ የ110 ሚሊዮን ህዝቦችን ሃገርና አህጉራዊ ቀጠናውን ይዞ የሲኦልን በር  አንኳኩቶ ከደብረሲና ተመልሷል – ለጊዜው ። ይህ እጅግ አደገኛ የማወናበድ ጉዞ ሕወሀት ከትግራይ ህዝብ ጋር  የሚጫወተው የፖለቲካ ቁማር ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያንና አካባቢውን ብዙ ዋጋ እያስከፈለ የሚገኝ ትውልድ ተሻጋሪ የሆነ  የህልውናም ስጋት ነው ። 

ኢትዮጵያን በመሰለ እጅግ የተወሳሰበ ስርአ ውስጥ፣ ሁሉም ከሁሉም የተሳሰረባትና ጨርሶ የማይለያይ ሀብረ-ማንነት ላይ  በተመሰረተች ሃገር ላይ እየኖሩ ከሌሎች ተነጥሎ ራስን በዘላቂነት ጨርሶ ለመለየት እጀግ አስቸጋሪ ነው ። ትግራይ “ነጻ አገር” ሆና  ራሷን ብትችል እንኳን ነጻነቷ የፖለቲካ ነጻነት ብቻ ነው የሚሆነው። ያለትግራይ ኢትዮጵያ በአዲስ መሰረቶች ላይ መመሰረት  ያለባት አዲስ ፈጠራ መሆን አለባት። 

አገር ማለት ከፖለቲካና ከድንበር ክልሎች በላይ የሆኑ በርካታ ስርአቶች ተሳሳሪነት ማለት ነው ። ሃገር ከፈጠሯት  ስብስቦች ስሌትና ድምር በላይ ነች ። በተጨማሪም ሃገሮች በየጊዜው የሚለዋወጡ፣ ራሳቸውን የሚፈጥሩ፣ ለዘላለም ቋሚነት  የሌላቸው፣ አንዳንዴ የሚሰፉ አንዳንዴም በራሳቸው ውስጣዊ ውስብስብ ፈተናዎች ተጠልፈው የሚጠቡ ኩነቶች ውጤት  ናት። በብዙዎቻችን እድሜ ዘመን እንኳን በኤርትራ መገንጠል የሃገርን ቋሚ አለመሆን አይተናል። 

ስለ ሰላም ተብሎ “ትግራይ ትገንጠል” ብንል እንኳን፣ የኤርትራን መገንጠል ተከትሎ ያሳለፍናቸውን ፈተናዎች  ሰናስብ ፍጹም ተስፋ አይሰጥም። ምክንያቱም ኤርትራና ኢትዮጵያ በተለያዩ ጊዜያት የአሁኑንም ጨምሮ በእርስ በርስ  ነውጥና ጦርነት ውስጥ አንደተዘፈቁ ነው ።የትግራይም ነጻ መውጣት የቀጠናውን ሰላም የባሰ ያናጋው ይሆናል እንጂ ፈጽሞ  አያረግበውም። 

በመጨረሻም በጣም ለሚመኙትና ለሚፈልጉት አላማ በተለይም ለነጻነት የሚደረግ ጉዞ ሂደት ውስጥ አንዳንዴ  ከመስመር መልቀቅን የግድ ይላል። ነገር ግን ለ 47 ዓመታት ሙሉ ለነጻነት እና ከነጻነት ጋር እየታገሉ መንከራተት የማንነቱ  ልዮ መለያ የሆነውን የሕወሀትን ጎዞ ስናስተውል መጭው ዘመን ከሕወሀት ጋርም ይሁን ያለሕወሃት ምን አንደሚመስል  ማሰባችንና መጨነቃችን የግድ ነው ። 

__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,866FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here