በ ሰለሞን ተስፋዬ ገብሬ
መጋቢት 13 2014 ዓ. ም.
አሁን ባለንብት ዘመን የዓለም ኢኮኖሚ እጅጉን የተሳሰረ ነው፡፡ የትስስር ጥንካሬው የተለያየ ቢሆንም የአገሮች ኢኮኖሚያዊ ትስስር በደንብ የሚታይ ነው፡፡ በተለይ በሸቀጦች (የካፒታል እና ፍጆታ ዕቃዎች) እና የአገልግሎት ወጪና ገቢ ንግድ እንዲሁም የፋይናንስ ገበያ (ለምሳሌ stock market)፡፡
ስለዚህ በአንድ አገር የሚከሰት የኢኮኖሚ እና የፋይናንስ ቀውስ በሌላ አገር ኢኮኖሚ ላይ ቀውስ ይፈጥራል ወይም ተፅዕኖ አለው፡፡ ያደጉት አገራት የዓለም አቀፉን ኢኮኖሚ ሂደት አስቀድሞ የሚተነብዩ እና ሚተነትኑ፤ ወቅታዊ ምቹ ሁኔታዎችን ለመጠቀም ወይም ለራሳቸው በሚጠቅም ሁኔታ ለመዘወር እንዲሁም ቀውስን ለመቋቋም የሚሰሩ በሰው ሀይል እና ቴክኖሎጂ የጎለበቱ ተቋማት ወይም አደረጃጀቶች አሉአቸው፡፡
በእኛ ሀገር ግን አንድ ቁንፅል ነገር ሲከሰት ትርምስ፡፡ የሚገርመኝ በዚህ ሁኔታ እንዴት ነው የፋይናንስ ካፒታል ገበያ ሊመሰረት እየታሰበ ያለው፡፡ የዓለም አቀፍ ነዳጅ ዋጋ ጨመረ ትርምስ፣ የዓለም አቀፍ ምግብ ወይም ማዳበሪያ ዋጋ ጨመረ ትርምስ፡፡ ከተከሰተ በኋላ በየተቋማቱ እና የጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት ስር ድክሞ የጨረባ ኮሜቴ ለማቋቋም ትርምስ፣ ከዛም ከሳምንታት በኋት ዝም ጪጭ አለቀ፡፡
ለምን ከተባለ ጉዳዩ በሚመለከታቸው በሶስቱም ዋናዋና ተቋማት (የፕላንና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር፣ የገንዘብ ሚኒስቴር እና ብሄራዊ ባንክ) የዓለም አቀፉን ኢኮኖሚ ሂደት አስቀድሞ የሚተነብይ እና የሚተነትን እና ተፅዕኖውን የሚፈትሽ፤ ወቅታዊ ምቹ ሁኔታዎችን ለመጠቀም የሚከታተል እና የፖሊሲ ምክረ-ሀሳብ የሚያቀርብ አካል የለም፡፡ ምናልባት በብሄራዊ ባንክ ከዓለም የገንዘብ ድርጅት እና የዓለም ባንክ የሚወረወሩ ቁርጥራጭ ሀሳቦችን የሚቃርም ኮሚቴ ነገር ሊኖር ይችል ይሆናል፡፡ ነገርግን በአጠቃላይ ይህን ተግባር የሚከውን ወጥ የሆነ ተቋም ወይም አደረጃጀት የለም፡፡
ስለዚህ አገሪቱ ከዓለም አቀፉ ኢኮኖሚ ጋር ያላትን ትስስር እና ያለውን በጎም ሆነ አሉታዊ ክስተቶች የሚተነብይ እና የሚተነትን እና የፖሊሲ ምክረ-ሀሳብ የሚያቀርብ አደረጃጀት ከላይ በተጠቀሱት ተቋማት ውስጥ ሊፈጠር ይገባል ወይም ስራው ይሄ ብቻ የሆነ ተቋም የግድ ሊመሰረት ይገባል፡፡
ይህ ተግባር በጠቅላይ ሚኒስቴር ጽ/ቤት የማክሮ ኮሚቴ ወይም በየክስተቱ የሚቋቋሙ የጨረባ ኮሜቴዎች የቶሎ በሉ አይነት ስራ የሚከወን ተግባር አይደለም፡፡
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com