spot_img
Friday, June 14, 2024
Homeነፃ አስተያየትኢትዮጵያ- ብታደርግ የተወገዘች፣ ባታደርግም ውጉዝ ነችና ቀበቶዋን ታጥብቅ!

ኢትዮጵያ- ብታደርግ የተወገዘች፣ ባታደርግም ውጉዝ ነችና ቀበቶዋን ታጥብቅ!

ሰማነህ ታምራት ጀመረ
ኦታዋ፤ ካናዳ
መጋቢት 22 , 2014 ዓ ም

ኢትዮጵያ ከሶስት ሽህ ዓመት በላይ በዘለቀው ታሪኳ ዘርፈ ብዙ ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ፍዳ እና መከራ ተፈራርቀውባታል። ጠላቶቿ ተራራ ሳይገድባቸው፤ ውቃያኖስ ሳይገታቸው፤ ርቀት ሳያሰንፋቸው ከውጪም ከውስጥም በኢትዮጵያ ላይ ሲዘምቱባት ኖረዋል። ዛሬም ቅርጽና ይዘቱን ቀይሮ እንደሆን እንጂ የማባራት ምልክት አይታይበትም።

የጣሊያን ወረራ፤ የመሃዲስቶችና የቱርኮች ጥቃት ኢትዮጵያን ቢቻል ማጥፋት ባይቻል ደካማ ሃገር ሁና በንርሱ ቸርነትና ፈቃድ እንድትኖር ለማድረግ ብዙ ጥፋት፤ ግፍና ሰቆቃ አድርሰውባታል። በእርስበርስ ሽኩቻ በበቂ ተተራምሳለች። ከጥንትም ኢትዮጵያን በግልጽና በስውር የሚአተራምሷት ምዕራባዊያን እንደሆኑም እናውቃለን። 

ኢትዮጵያ ከውጪም ከውስጥም የተቃጡባትን ጥቃቶች ሁሉ እንዳመጣጣቸው ተቋቁማ 21ኛው ክፍለ ዘመን ላይ ደርሳለች። ፈታናዎችን ትቋቁማ እስካሁን የዘለቀችበት ምክንያቶች ብዙ ቢሆኑም ዋናዎቹ ግን የሕዝቧ ጨዋነት፤ በራስ መተማመን፤ ፈሪሃ እግዚአብሔር፤ አይበገሬነትና ለሃገር ቀናዒነት ፈተናዎቹንና ችግሮችን ስትሻገር ቆይታለች። ዛሬም የአሜሪካንና የምዕራቡ ዓለምን መዓቀብና ጫና መጋፈጥ የምትችለው ያለፉ እሴቶቿን በማጎልበት፤ ቀበቶዋን ጠበቅ አርጋ አንድነቷን አጠናክራ በሕብረ ብሄራዊነት መንፍስ ታጅባ በሕብረት ስትዘምት ብቻ ነው።  

በድህነት ዓለም እየኖረች በዘምናዊ መሳሪያ ታጅቦ የወረራትን የመዕራብ ኅይል አሸንፋ በመጡበት የመለሰችው፤ ነፃነቷን ሳታስደፍርና በቅኝ ግዛት እጅ ሳትወድቅ እንድትቆይ የቻለችውም በዚሁ ምክንያት ነው። በቅኝ አገዛዝ ሲማቅቁ ለነበሩ የሶስተኛው ዓለም ህዝቦች አፍሪካን ጨምሮ የነፃነትና የአይበገሬነት ተምሳሌት ሆና የኖረች ሃገር ለያንኪ ፖለቲካ የምትበገር ትሆናልች ተብሎ አይገመትም።

ከዚህ ባሻገር የራሷ ሐይማኖት፤ ታሪክ፤ ባሕልና ትውፊት የምትመራ ሃገር በመሆኗ በምዕራቡ ዓለም በተልይም በዩኤስ አሜሪካ  ተወዳጅነትና ክብርን አላፈራላትም። የጣሊያንን ወረራ በማሸነፍዋ ውርደት የተሰማቸው የምእራቡ ዓለምና አሜሪካ ቁጭታቸውንና ቂማቸውን እንደቋጠሩባት አሉ። አጋጣሚውን ተጠቅመው የበቀል በትራቸውን ለመምዘዝ ቋጥነዋል። ልብ ያለው ልብ ይበል-የአሜሪካ ቂም ከግመል የባሰ፤ ትዕቢቱ ከአንበሳ የተባ፤ ንዴቱ ከነብር የጋለ፤ ተንኮሉ ከድመት የረቀቀ እንደሆነ የ245 ዓመታት ድርሳኑና የ125 ዓመት የዲፕሎማሲ ተመክሯችን ሕያው ምስክሮች ናቸው። 

ሌላው አሜሪካ ኢትዮጵያን ያቄመችበት ምክንያትና ብዙ ሰው ደፍሮ የማይናገረው ጉድ አለ። ይሄውም ኢትዮጵያዊያን በፈሪሃ እግዚአብሔር የታነፀ ስነምግባር ያላቸው ሕዝቦች በመሆናቸው የአሜሪካንን ውዳቂ ባህል ተቃውመዋል፤ የሰዶሜ ስነምግባርን ስላወገዙ አንደሆነ ግልጽ ሊሆንልን ይገባል። ይህም ጥላችንና ውግዘትን አስከትሏል። ነገሩ ጠብያለሽ በዳቦ ስለሆነ በነዚህ ምክንያቶች ኢትዮጵያ በአሜሪካ እንድትጠላና ቂም እንዲያዝባት ሆናለች። ያልንሽን ካልተቀበልሽ በሚል የማን አለብኝና የንቀት እሳቤ ኢትዮጵያን በፖለቲካ፤ በኢኮኖሚና በመከላከያ መአቀብ በማብርከክ ተግዥ ለማድረግ ብዙ ሞክረዋል። 

ማክሰኞ March 29, 2022 የአሜሪካ ሴኔት HR6600- S-3199 የተባለውን በኢትዮጵያ ሰላም እና ዲሞክራሲ ማበረታታት የቀረበው ረቂቅ ሕግ በኢትዮጵያ፣ በኤርትራ እንዲሁም በጦርነት ተሳታፊ ናቸው በተባሉ ግለሰቦች (ሕወሃትን በስም ላለመጥቀስ ሲባል) ላይ ጠንከር ያለ ማዕቀብ አዘጋጅተው መክረዋል። የውጭ ጉዳይ ኮሚቴን የመጀመሪያ ችሎት ይሁንታ አግኝቷል። ሆኖም በሕግነት ፀድቆ በፕሬዚደንቱ እስኪፈረም ድረስ ብዙ ሂደት ይቀረዋል። የኢትዮጵያ ወገኖች የሆናችሁ ሁሉ እንዳትዘናጉ። ምክንያቱም ይህ ሕግ ከዚህ በፊት የተጣሉትን መአቀቦች በእጅጉ የሚአጎለብት በመሆኑ በቀላል ማየት አያስፈልግም። 

አሜሪካ በዓለም ሕዝቦችና በ45ሃገራት ላይ ብዙ መአቀቦች ጥላለች። መአቀብ ያስገኘው ውጤት ምን እንደሆነ እስካሁን በኩራት የምትናገረው ምሳሌ ግን የላትም። መአቅብ በእጅጉ የሚጎዳው ከድሃው ማህበረሰብ ሌላ ማንንም ሲጎዳ አልታየም። የመአቀብ ዋናው ዓላማ ድሃውን ሕዝብ የበለጠ ማደህዬት፤ ማስራብ፤ ማጎሳቆልና ማጥቃት ነው። ይህ ደግሞ ከጅምላ ፍጅት የማይተናነስ ወንጀል እንደሆነ አውቀን ለአሜሪካ፤ ለምዕራቡ ዓለምና ለአጋሮቻችን ማሳወቅ ይጠበቅብናል።  

እሁን እነርሱ ማድረግ የሚፈልጉትን እያደረጉ ናቸው። ስለሆነም ሃሳባቸውንና ውሳኔአቸውን ለማስቀየር ከምናጠፋው ጊዜ፤ ሃብት፤ ዕውቀትና፤ ኀይል ቀነስ አድርገን ራስችንን በማጠናከርና ከአጋሮቻችን ጋር ያለን ግንኙነት ይበልጥ ማጎልበቱ ላይ ትኩረት ሰጠን እንስራ። ኢትዮጵያ ብታደርግ የተወገዘች፣ ባታደርግም ውጉዝ ነችና ቀበቶን ጠበቅ ይሻላል። ስለሆነም እኛ ወደራሳችን ዘወር ብለን የቤት ስራችንን እንከውን። ከዚህ በኋላ አሜሪካንና ምዕራቡን ዓለም መለማመጥ የሚአዋጣ አይደለም። 

ለምን ቢባል አሜሪካ የውሻ በሐሪ ነው ያለው። ውሻ ከሮጡለት አሳዶ ሳይናከስና ሳይባላ አይተውም። ቁጭ ብሎ ፊት ለፊት ከተገዳደሩት ዓይናከስም። አሜሪካ ልምምጥንና ትህትናን እንደፍርሃት የሚቆጥር ሃገር ነው። አሁንም እንላለን ኢትዮጵያና ሕዝቧ ቀበቷቸውን ጠበቅ አርገው የውጭ ጫና የሚገዳደሩበት ስዓት ላይ ደርሰዋል። ስለሆነም የኢትዮጵያ መንግስትና ሕዝብ ሆይ ጠላትን ለይቶ ማወቅ የውጊያው ግማሹ መፍትሔ እንደሆነ አውቀህ በአንድነት ተነስ። ሌላው ሁሉ የውድቀትና የቁልቁልት ግዞን ያፍጥን እንደሆነ እንጂ መፍትሔ አያመጣም። 

ኢትዮጵያ በልጆቿ ታፍራና ተከብራ ለዘላልም ትኑር፤
ፈጣሪ ኢትዮጵያን ጥሎ አይጥላትም

__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here