በገልፈቶ ፡ ዳሞ
አዋሳ የተለየ የተፈጥሮ ውበት ያላት ፤ሁሉም ለከተማዋ በተለያየ መልኩ አስተዋጽዖ ባላቸው ጋራዎች የተከበበች፣ ውኃ ሕይወት ነው የሚለውን መፈክር በተግባር የምናይበት የአዋሳ ሐይቅ ከነዘርፈ ብዙ ጥቅሙ ከጎኗ የቆመላት ፣ ከየትኛውም የዓለም ክፍል ለሚመጣ አገር ጎብኚም ሆነ ፣ ኢንቬስተር የከተማዋ አየር ተስማሚ የሆነ፤ በተፈጥሮ ፀጋ የታደለች ከተማ ነች፡፡ ቀድሞ የተሠራላት የከተማዋ ፕላን ከኢትዮጵያ ከተሞች ቀደምትና በዘመናዊነቱ የተሻለ፣ ከተማዋ ወደፊት እንደትሆን ከተፈለገው ወይም ከታቀደው አንፃር የተቃኘ ነበር፡፡
ለዚህም ይመስለኛል ከዛሬ ሃምሣ ዓመት በፊት መልካሙ ተበጀ “ አዋሳ ላንጋኖ ለሽርሽር ሄጄ…” እያለ ሲዘፍን ቅርቦቹ እራሳችንን በማድነቅ የሩቆቹ ደግሞ በምናብ የሳልናትን አዋሳ በማሰብ በልጅነት አንደበታችን ስንዘፍን የነበረው፡፡
የአዋሳ ከተማን አመሠራረት በሚመለከት የሲዳማ ብሔር ታሪክና ባህል በሚል ርዕስ የሲዳማ ዞን ባህል፣ ቱሪዝምና የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ( ዛሬ ሲዳማ ክልል መሆኑን ልብ ይሏል) የካቲት 2003 ዓ.ም. ባሳተመው መጽሐፍ እንዲህ ይላል:-
የአዋሳ ከተማ ከመቆርቆሩ በፊት ሥፍራውን የሲዳማ ብሔረሰብ ለከብት ግጦሽ ና ቀስ በቀስም ለእርሻ የሚጠቀምበት ሲሆን ፣ አካባቢውም አዳሬ…. በሚል ስያሜ ይታወቅ እንደነበር ለረጅም ዓመታት በቋሚ ነዋሪነትና በተመላላሽነትየሚያውቋት የአገር ሽማግሌዎች ያስረዳሉ፡፡ (ገጽ 140)
በመቀጠልም ለከታማዋ ዕድገት በዋናነት ምክንያት የሆኑት
… በዋናነት ከሚጠቀሱት ምክንያቶች መካከል ንጉሡ ከተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ጡረታ የወጡ በቁጥር 404 ሚሆኑ ወታደሮችና ቤተሰቦቻቸውን አምጥተው በአዋሳ ከተማ ማስፈራቸው አንዱ ምክንያት እንደነበር መረጃዎች ይጦቁማሉ፡፡
እነዚህ ወታደሮች የመጡት ከቦረና፣ከአ/አበባ፣ ከሐረር፣ ከውቅሮ እና ከኮረም ሲሆኑ… (ዝኒከማሁ ገጽ 142)በማለት እነዚህ ለከተማዋ በፍጥነት ማደግ ምክንያት የሆኑ ሰዎች በወቅቱ ሰፍረውባቸው የነበሩ አካባቢዎች ዛሬ በየትኛዋ የከተማ ክፍል እነደሚገኙ የሰፈሮቹን የቀድሞ መጠሪያ በመጥቀስ ይቀጥላል፡፡ እዚህ ላይ ልብ እንዲባልልኝ የምፈልገው ምክንያቱ ምንም ይሁን ምን ለከብት መዋያ ለእበት መጣያ ብቻ ሲውል የነበረው መሬት በአሰደናቂ ፍጥነት ወደከተማነት መለወጡን ነው፡፡ ወደከተማነት መለወጥ ብቻ ሣይሆን በአስደናቂ ፍጥነት መሆኑም ሌላ ሊሰመርበት የሚገባ ጉዳይ ነው፡፡
የሚገርመው ጉዳይ የከተማዋ ዕድገት መጀመር ብቻ ሳይሆን በማን ተፋጠነ ሲባል የሚገኘው መልስ ነው፡፡ እንደ መጽሐፉ አገላለጽ ከሆነ ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመጡ ቁጥራቸው አራት መቶ በሆኑ ጡረተኞች መሆኑ ነው፡፡ ይህ የሚያሳየው ሐዋሣ የተመሰረተቸውም ሆነ ያደገችው ከተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በመጡ ሥራ ወዳዶችና በአካባቢው ነዋሪዎች መሆኑን ነው፡፡
በአንድ ወቅት የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ምክትል እንደራሴና በኋላም የበላይ ባለሥልጣን የነበሩት ደጃዝማች ወልደሰማዕት ገብረወልድ ሕይወቴ በሚል ርዕስ በ2012ዓ.ም ባሰተሙት ግለ ታሪክ መጽሐፋቸው ስለሐዋሣ ከተማ አመሠራረት የሚከተለውን አስፍረው እናገኛለን፤
የአዋሳ ከተማ ለልማት ተግባር ማዕከልነት ተመሠረተው በ1952 ዓ.ም ነው፡፡የተመሠረተው ለከተማ ሳይሆን …….በ1951 ዓ.ም. ከመስኮብ በተገኘው 400 ሚሊዮን ሩብልስ የረጅም ጊዜ ብድር የኢትዮጵያ ጪሰኞች በዘመናዊ እርሻ ዘዴ እያሰለጠኑ ርስት ( ልብ በሉ የሚመረጡት ሠልጣኞች ሐዋሣ ሠልጥነው ርስት የሚሠጣቸው ሌላ አካባቢ ነው፡፡ በመጣጥፉ አቅራቢ የተጨመረ) በመስጠት ለዘመናዊ ገበሬዎች ማሠልጠኛ ሠርቶ ማሳያ ማዕከልነት ነው፡፡ሁለተኛው የአዋሳ ከተማ አመሰራረት ዓላማ ሁሉም ኢትዮጵያዊያን ወደኋላ የቀሩትን ኢትዮጵያውያን የሚያሠለጥኑ አሠልጣኞች ማሠልጠኛ ኮሌጅ ማቋቋሚያ እንዲሆን ነው፡፡ አዋሳ የሐይቁ ሥም ነው፡፡ የቦታው ሥም ሃዳሬ ይባል ነበር፡፡ ( ገጽ 427)
ሌላው እዚህ ላይ ሳልጠቅስ ማላልፈውና መልሱን ለታሪክ ተመራማሪዎች የምተወው የከተማዋ ማስተር ፕላን በማን ተሠራ የሚለው ነው፡፡እንደ ሲዳማ ብሔር ታሪክና ባህል መጽሀፍ አዘጋጆች ከሆነ ንጉሡ ለከተማዋ ማስተር ፕላን እንዲያዘጋጁ በኢጣሊያን መሐንዲሶች የሚመራ ሰባት አባላት ያሉት ቡድን እንደላኩ ነው፡፡ ( ገጽ 141) እንደ ደጃዝማች ወልደሰማዕት ከሆነ ደግሞ ማስተር ፕላኑ የተሠራው በቡልጋሪያው ፕሮፌሰር ሂሪስቶ ሂሪስቲኮፕ ነው፡፡ (ገፅ 429)
የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ስለአዋሳ ከተማ አመሠራረት ታሪክ ማቅረብ ሳይሆን የአዋሳን አመሠራረት ብልጭታ ለማመሳከሪያነት ያህል ብቻ ጠቅሶ ዛሬ በከተማዋ የሚታዩ ዋና ዋና የሚባሉ ችግሮችን ማሳየትና በፀሐፊው ለችግሮቹ መፍትሔ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው የሚገመቱ ነጥቦችን ማቅረብነው፡፡
የብዙኃን መኖሪያና የኢትዮጵያውን የአብሮ መኖር ተምሣሌት የሆነችው የአዋሳ ከተማ በጎሣ ፖለቲካ እየተናጠች ፤ ቅጥ ባጣ ዘረኝነት ከመስመር ወጥታ ፣በአድሎኣዊነትና በብልሹ አስተዳደር መናጥ ከጀመረች ውሎ አድሯል፡፡
አዋሳን የሚያክል ትልቅ ከተማ ይቅርና ቤተሰባቸውን እንኳን በቅጡ ማስተዳደር የማይችሉ የዕውቀት ድሆች ና ዝግ አዕምሮ ባላቸው ግለሰቦች እንድትተዳደር መደረጉ፣ ለከተማዋ የቁልቁለት ጉዞና ውድቀት ምክንያት ሆነዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ምክንያቱ ዕውቀት ሳይሆን ዘር ላይ የተመሠረተ የሹመት መለኪያ መበጀቱ ነው፡፡
በመንግሥት መ/ቤቶች ፣በግል ድርጅቶችና ሆቴሎች ውስጥ ሳይቀር የአንድ ብሔረሰብ (ሲዳማ) ብቻ በሚያስብል ደረጃ ሠራተኞች እንዲቀጠሩ የማድረግ የተሳሳተ አካሄድ ውጤቱ ከተማዋን ለብልሹ አሠራር፣ለደካማ አመራር፣ የተሠራን ይዞ ቀጣይ ግንባታ ከማካሄድ ይልቅ የነበረውን በማፍረስ መጪውን ማጨለም ወይም በአጠቃላይ የተስፋ ሰጪ ሳይሆን ለከተማ ዕድገት የቁልቁለት ጉዞ ለነዋሪዎቿ መጪን በተስፋ ዓልሞ ዕድገትን ከማሰብ ይልቅ የዛሬ ላይ ብቻ ትኩረት እንዲያደርጉ ከተቻለም ያፈሩትን ሀብት ንብረት እንዴት ከከተማዋ በማሸሽ ወደሌላ አካባቢ መዘዋወር እንደሚችሉ ማሰላሰል ብቻ እንዲሆን አድርጓል፡፡ይህ በአንድ ጎሣ የተያዘ የከተማ አስተዳደር እንኳን አዳዲስ ባለሀብቶችን በመሳብ ለከተማዋ ዕድገት የሚበጁ ተግባራት ማከናወን ቀርቶ ያሉትን እንኳን ይዞ ማቆየት ያልቻለ በመሆኑ ሥራ አጥነት በዝቷል፤ በውጤቱም ማኅበራዊ መቅሰፍት ወይም የመጥፎ ድርጊቶች መፈልፈል ምክንያት ሆኗል፡፡ ይህም ማለት ሌብነት ከከፍተኛ ባለሥልጣን እስከ ተራው ሠራተኛ፤ ከሥራ አጥ እስከ ጎዳና ተዳዳሪነት፣ ከማጅራት መቺነት እስከ ኪስ አውላቂነት፤ ከነጣቂነት እስከ አስፈራርቶ መዝረፍ ፣ከቤት ሰብሮ ስርቆት እስከ ተሰጣ ልብስ ወ ይም የተቀመጠ ዕቃ ይዞመሄድ/ መሮጥ ወዘተ ከዚህ አሠራር ያተረፍነው /ያገኘነው ትሩፋት ነው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ፡-
≠ የቀበሌ ቤቶችን ለብዙ ዘመናት በከተማዋ ውስጥ የኖሩ ድሃ ሰዎችን በማስወጣት ለአንድ ጎሣ ብቻ እንዲሰጥ የማድረግ የተሳሳተ አካሄድ፣
≠ የቀበሌ ቤቶችና መሬትን ያለ በቂ ፉክክር (ጨረታ) የከተማዋን ነዋሪዎች ሳያሳትፉ ለአንድ ጎሣ ብቻ እንዲሰጥ የማድረግ የተሳሳተ አካሄድ ፤
≠ነጋዴው ነግዶ እንዳይበላ ከሚገባው በላይ ግብር በመጫንና ጉቦ እንዲከፈላቸው በማድረግ ከሥራ ውጪ እንዲሆኑ ማድረግ፤
≠ ከእጅ ወደአፍ በሆነ የኑሮ ደረጃ የሚኖሩና የሌላ ብሔረሰብ አባል የሆኑ የከተማዋ ነዋሪዎችን በየመንገዱ ገበያ ነግደው እንዳይሠሩ ማባረር ንብረት መቀማት እና ማሰር
≠ ወንጀል የሠሩ የአንድ ብሔረሰብ አባላትን የይስሙላ እስር ካሰሩ በኋላ መፍታት
≠የብዙኃን ፡ መኖሪያ ፡ የሆነችውን ፡ የአዋሳ ፡ ከተማ ፡ ውበት ፡ በሚያበላሽ ፡ መልኩና ፡ የአንድን ብሔረሰብ ፡ ማንነት ፡ በሚያጎላ ፡ መልኩ ፡ ቀለም ፡ መቀባት ፡ እና( ፡ መንገዶችና ፡ ቤቶችን) ፡ ታሪካዊ ቦታዎችን ፡ ሆን ፡ ብሎ ፡ ማፈራረስ
≠የልማት ሥራዎች በአግባቡ እንዲሠሩ የተመደበ ገንዘብን መዝረፍ ፤ የተጀመረ ፕሮጀክት ካለ እንዳያልቅ ማስተጓጎል
≠ ጉቦ እየተቀበሉ ሕጋዊ ያልሆኑ መኖሪያ ቤቶች እንዲሰሩ ማድረግ ከዋና መንገዶች ውጪ ፤ ውስጥ ውስጡን ያሉ መንገዶችን ባለማሰራት ሕጋዊውን መንገድ ጥሰው ቤቶች እንዲሠሩ መፍቀድ
≠ለሐዋሣ ከተማ ተብለው በመንግሥት ገንዘብ የሚገዙንብረቶችን ከአጭበርባሪ ነጋዴዎች ጋር በመተባበር ( ብረት፣ ቆርቆሮ ) የመሳሰሉትን በመሸጥ የመንግሥት ገንዘብ ለግለሰቦች እንዲውል የማድረግ ብልሹ አሠራር
በከተማዋ ተንሰራፈቷል፡፡
መሰል ጉዳይ በከተማዋ መከሰቱን በመግለጽ ደጃዝማች ወልደ ሰማዕት በወቅቱ በተመሣሣይ ሁኔታ የተፈጠረውን እንደሚከተለከው በግለ ታሪካቸው ጠቅሰውታል
…ለከተማዋ ዕድገት ከባድ እንቅፋት የነበረው በሐይቁ ዳርና በከተማዋ ዋና ዋና መንገዶች ግንባር ቦታ በአድሎ እያንዱን (sic) ለሌላው መስጠት ብቻ ሳይሆን ቦታ ተሻምቶ ለመያዝ ሲባል አቅመ አዳም ላልደረሱና ተወልደው ሥም ላልወጣላቸው በፅንስ ደረጃ ለነበሩ ሕፃናት ጭምር ሥም ሰጥቶ ቦታ መያዝ ያሉ ውስብስብ ችግሮችን ማቃናት ያስፈልግ ነበር፡፡ በተለይ ገና ወደዚህ ዓለም ላልመጣ በፅንስ ደረጃ ለነበረ ወይም ለነበረች ሕፃን ቦታ ተይዞ ስለነበረ የቦታው ባለቤት ፎቶግራፍ በግንባር ይዞ ይቅረብና ከፋይሉ ጋር ይያያዝ ሲባል ጉድ ፈላ፡፡ ( ገጽ 429- 430)
ይህን ነጥብ የሚያሳየን ችግሮች በየጊዜው ዓይነትና ውስብስብነታቸውን ጨምረው የሚመጡ መሆኑን ሲሆን የአሁኑ የበለጠ ከባድ የሚያደርገው ሌላው የደከመበትንና እድሜ ልኩን ጥሮ ያፈራውን ንብረት ሥራ ጠል ወገኖች በብሔረሰብ ሥም በመነገድ ለመዝረፍ ማሰፍሰፋቸውና እየዘረፉም መሆኑ ነው፡፡
መፍትሔ
_
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
መፍትሔው አዋሳን የፌዴሬል ከተማ ማድረግ ብቻ ነው። አለበለዚያ ከተማው ለሀገሪቱ ነዋሪዎች የማትጠቅም የሌቦች እና የዘረኞች ምሽግ ሆና ትቀጥላለች።