spot_img
Sunday, September 24, 2023
Homeነፃ አስተያየትአደገኛው የበቀል ባሕልና የኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታ።

አደገኛው የበቀል ባሕልና የኢትዮጵያ ዕጣ ፋንታ።

advertisement

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
ሚያዚያ 22 2014

በቅድሚያ፤ በተለያየ መንገድ ሕይወታቸው ያለአግባብ ለተቀጠፉ ወገኖች ቸሩ እግዚአብሔር ነፍሳቸውን ይማር፤ ቤተሰብን ወዳጅ ዘመድንም ያጽናና።

“ጠንካራው፤ ኃላፊነት የተሞላበት እርምጃ በመውሰዱ፤ ደካማ የሚመስልበትና፤ ደካማው ደግሞ በሚወስደው ኃላፊነት የጎደለው እርምጃ ጠንካራ የሚመስለበት አስገራሚ ወቅት ላይ እንገኛለን” የቀድሞው የጀርመን ቻንስለር ኦቶ ቮን ቢስማርክ (Otto von Bismarck).

በቀል፤ በኢትዮጵያ ባሕል ውስጥ የተገመደና፤ ለዘመናት አንዱን ከአንዱ ጋር ሲያገዳድል የኖረ አደገኛ ባሕላዊ ክስተት ነው። ሌላው ቀርቶ ልጅ ሲወለድ የሚሰጡ ስሞች እና አንዳንድ ምሳሌያዊ አነጋገሮቻችን በቀልን የሚያወድሱ እና በቀልን የሚያበረታቱ ናቸው። በአንድ አንድ የሃገራችን አካባቢዎች፤ በቀል ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ እና በማህበረሰቡ ውስጥ ከፍተኛ ጉዳት ሲያመጣም ለዓመታት አስተውለናል። “ብድሩን የማይመልስ ወንድ ልጅ አይወለድ” የሚል ዓይነት ብሂል እና “ደም-መላሽ” የሚል ዓይነት ሥም፤ በባሕላችን እና በማህበረሰባችን በቀል ያለውን ተቀባይነት ያንፀባርቃል። ይህ የበቀል ባሕል፤ ፖለቲካችንን፤ ሃይማኖታችንን፤ ማህበራዊ ኑሯችንን እና የምጣኔ ሃብታችንን ጨምሮ አቃውሷል። እስካሁንም ትኩረት ተሰጥጦበት በጥናት የተደገፈ መፍትሔ ለማምጣት ብዙ ባይሞከርም፤ የበቀል ባሕልን ከሥሩ ለመንቀል ከመጣር ይልቅ፤ ስለ ሰላምና እርቅ መስበኩ፤ ዋነኛ አጀንዳ ሆኖ ቆይቷል። ይህ ፀሃፍ፤ የበቀል ባሕልን ከሥሩ እስካልነቀልን ድረስ፤ በሃገራችን ሰላም እና እርቅ ይኖራል በሎ ለመገመት ያዳግተዋል።

እስካሁን ድረስ ሃገራችን ከቀውስ አዙሪት ያልወጣችው፤ የፖለቲካ ባሕላችን በበቀል አስተሳሰብ የተመረዘ በመሆኑ ነው። ትላንትም ሆነ ዛሬም እየተገዳደልን የምንኖረው፤ ውስጣችን በበቀል ስሜት ስለጨቀየ እና፤ ይህን የበቀል ባሕል ለመቀየር ይህ ነው የሚባል ሥራ ባለመስራታችን ነው። ሃገራችን ብዙ ብርቅዬ ልጆቿን ያጣችው፤ ባልተቋረጠው በቀል በወለደው የግጭት እና የዓመጽ አዙሪት ለመሆኑ፤ ታሪክ ተንታኝ አያስፈልገንም። ለዘመናት ያካሄድናቸው የእርስ በእርስ ግጭቶች፤ መሰረታቸው በቀል ነው። ሌላው ቀርቶ፤ የፈጣሪን ፍቅር ማስተማር የሚገባቸው የሃይማኖት አባቶች፤ በበቀል ስሜት ታውረው፤ የሃይማኖት ተከታዮቻቸውን ለመግራት እንኳን ተነሳሽነት አያሳዩም። ምንም እንኳን በቃል በአደባባይ ስለ-ሰላም ቢሰብኩም፤ ከመጋረጃ ጀርባ ግን፤ በቀልን የሚያራምዱና የጥፋት ሴራ የሚጎነጉኑ ለመሆናቸው የአደባባይ ሚስጥር ነው። ሃይማኖቶች ከአፈጣጠራቸው ጀምረው የፖለቲካ መሳሪያ የነበሩ እና አሁንም የሆኑ ናቸው። ለዚህም ነው ዛሬ መስጊድ ሲቃጠል፤ በአደባባይ ውግዘት፤ ከጀርባ ደግሞ፤ የበቀል እርምጃ ግፊት የምናየው። በስልጤ ዞን፤ ቤተ ክርስቲያን የተቃጠለው፤ መስጊድ ውስጥ ጸሎታቸውን አጠናቀው ከመስጊድ በወጡ ሰዎች መሆኑ፤ መምህራኖቹ፤ ‘በቀል አያዋጣም፤ ከፈጣሪም ያጣላል’ ብለው አጽንተው ባለመምከራቸው ነው። ይህ ባይሆን ኖሮ፤ ከፈጣሪው ጋር በቤተ እምነቱ ተነጋግሮ (ፀልዮ) የወጣ ሰው፤ ምንም ቢሆን ወደ ጥፋት ጎዳና ባልሄደ ነበር። 

በጎንደርም የተከሰተው ከዚህ የተለየ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ፤ ስጡ እንጂ ንፉግ ሁኑ ብሎ አያስተምርም። ሕይወታቸው ላለፈው ሙስሊም አባት ቀብር፤ ድንጋይ ከተፈለገ፤ ቤተክርስቲያኗም ሆነ “አማኝ” ነን የሚሉት ሰዎች፤ ድንጋዩን መስጠት ብቻ ሳይሆን፤ ቀብሩ በሥርአት እንዲያልቅ ማገዝ ነበረባቸው። የሃይማኖቱም ትክክለኛ አስተምርሆት ይህ ይመስለኛል። ይህ በሃይማኖት ስም የተሰራ ሸፍጥ እንጂ ከሃይማኖቱ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። የተነሳውንም ግጭት ከማብረድ እና ለችግሩ መንሰኤ የሆኑ ሰዎችን ከመገሰጽ ይልቅ፤ በውስጥ ያለው የበቀል ስሜት ያነሳሳቸው “የሃይማኖት መሪ ነነ” ባዮች፤ ሁኔታዎችን ማባባሳቸው፤ ከክርስቶስ ትምህርት እና ክርስቲያን መርህ ያፈነገጠ ለመሆኑ፤ ፈላስፋ መሆንን አይጠይቅም። ድንጋይ አትርፎ፤ የእግዚአብሔር ፍጡር የሆነውን ክቡሩን የሰው ሕይወት የሚያጠፋስ በየትኛው ሃይማኖታዊ ትምህርት ታንጾ ነው? እኔ እንደሚገባኝ፤ ችግሩ፤ የሃይማኖቶቹ መርህ ሳይሆን፤ ችግሩ፤ የሃይማኖቱን አስተምርሆት ለምእመናን በተሳሳተ መንገድ ከማስጨበጥ የመነጨ ነው። 

በሰበታ ውስጥ፤ ማርያም ቤተክርስቲያን ባዋጣቸው መሬት እና ከሙስሊሙ ማህበረሰብ በተዋጣ ገንዘብ ትምህርት ቤት መገንባቱ፤ ያኮራንን ያክል፤ በጎንደር፤ በስልጤና በሌሎች አካባቢዎች በሃይማኖት ተቋማት ላይ የተፈፀመው ጥቃት እና፤ ከዛም ጋር ተያይዞ በጠፋው ሕይወት እና በወደመው ንብረት፤ ሁላችንም ልናፍር ይገባናል። ማፈር ብቻ ሳይሆን፤ የበቀል ባሕላችን ከሥሩ ሊበጠስ የሚችልበትንም መንገድ ማቀድ እና መተግበርም ይኖርብናል። እኔ እስከማቀው ድረስ የየትኛውም ሃይማኖት የተቀደሰ መጽሐፍ የሰዉን ሕይወት በከንቱ አጥፋ፤ ንብረት አውድም አይልም። በሁለቱም ወገን ለደረሰው ጥፋት፤ ዋና ተጠያቂዎቹ፤ የሃይማኖቶቹ መሪዎች ናቸው። የሃይማኖት መሪዎች፤ ምእመኖቻቸውን፤ የሚያስተምሩት ምንድነው? ይህ መልስ ማግኘት ያለበት ጥያቄ ነው። ፈጣሪ ሁሉንም የሰው ልጅ የሚያየው እኩል ነው። ሙስሊም፤ ክርስቲያን፤ ወዘተ የሚለውን ክፍፍል የፈጠርነው እኛ ነን። አላህ እና እግዚአብሔር አንድ ናቸው። “አላህ” አረብኛ እንጂ “እስላምኛ” አይደለም። በአማርኛ እግዚአብሔር፤ በእንግሊዝኛ God፤ በፈረንሳይ Dieu፤ በእብራይስጥ elo’ah፤ በአረበኛ ደግሞ አላህ ነው። በአረብ ሃገራት የሚኖሩ ክርስቲያኖች፤ እግዚአብሔርን የሚጠሩት “አላህ” ብለው ነው። የሰው ልጆች ተለያየ ሥም ቢሰጡትም፤ ፈጣሪያችን ግን አንድና አንድ ብቻ ነው። ሁሉም ሃይማኖቶች ክቡሩ የሰው ልጅ፤ የአንድ ፈጣሪ ፍጥረት መሆኑን እንደማስተማርና ፍቅርን እንደመስበክ፤ ለየራሳቸው “የሃይማኖት ችርቻሮ” ሲሉ፤ በሰዎች መካከል ልዩነትን በመፍጠር፤ በማስፋት እና፤ አንዳንድ ተከታዮቻቸው፤ በበቀል እንዲታወሩ በማድረግ፤ ላማያባራ ግጭት እየዳረጉን ለመሆኑ፤ በግልጽ፤ በድፍረት እና በተደጋጋሚ ሊነገር ይገባል። 

በአንድ ሃገር በሰላም ልንኖር የምንችለው፤ አንዳችን ሌላችንን እንደ ሰው ስናከብር፤ አንዳችን የሌላችንን እምነት ሳንጋፋ፤ ስንከባበር ነው። አባላት ለማብዛት በሚደረግ ፉክክር ውስጥ፤ በዚህም በሚገመድ ተንኮል ማንም አያተርፍም፤ ማንም አይፀድቅም። መጽሐፍ ቅዱስ  “እሱ እንዳደረገብኝ እንዲሁ አደርግበታለሁ፤ አጸፋውን እመልሳለሁ አትበል” ይላል (ምሳሌ 24:29)። ቅዱስ ቁርዓን በበኩሉ “ለዲያብሎሳዊ ሥራ የምትሰጠው የበቀል ምላሽ እራሱ ዲያቢሎሳዊ ነው፤ሆኖም ማንም ይቅር የሚል፤ ካሳውን የሚያገኘው ከአላህ ነው።” ይላል (ቁርዓን 42፡40)። የየሃይማኖቶቹ፤ የተቀደሱ መጽሐፍት የሚያስተምሩን፤ ይቅር ባይነትን ነው። ጥያቄው ግን የየሃይማኖቶቹ መሪዎችና አስተማሪዎች ይህንን ያስተምራሉ ወይ ነው። በየሃይማኖቶቹ የተሰገሰጉትንስ ጽንፈኞች እና ሃይማኖትን ለራሳቸው ፖለቲካ መጠቀምያ የሚያደርጉትንስ፤ የየሃይማኖቱ መሪዎች እንዴት ማጽዳት አቃታቸው? የማጽዳትስ ፍላጎት አላቸው ወይ? እነዚህ ጥያቄዎች በጥናት መልስ ሊገኝላቸው ይገባል። አንዱ ከሌላው የበላይ ለመሆን የሚያደርገው ፉክክር እና የአባላቶቻችውን የበቀል ስሜት በመቆስቆስ እየፈጠሩ ያሉት የማያቋርጥ የግጭት አዙሪት፤ መፍትሔው በሃይማኖት መሪዎቹ እንጂ በመንግሥት እጅ ብቻ አይደለም። 

በተደጋጋሚ እንደምንሰማውም፤ ከተራ “የሕብረተሰብ አንቂ” ጀምሮ፤ እስከ ከፍተኛ የሃይማኖት እና የፖለቲካ መሪዎች፤ ሁሌም የሚሉት አስገራሚ ነገር አለ። “መንግስት ዋና ሃላፊነቱ፤ የዜጎችን ሰላም የማስጠበቅ ነው፤ መንግሥት ሃላፊነቱን ይወጣ” የሚል። የመንግሥት ዋና ሃላፊነት ሰላም ማስጠበቅ ነው ማለት፤ ሁሌም መንግሥት ችግር ከመፈጠሩ በፊት፤ ችግሮችን ማስቆም ይችላል ማለት አይደለም። የሃይማኖት መሪውም፤ የፖለቲካ መሪውም ሆነ አንቂው፤ በየቦታው እሳት እየለኮሰ፤ መንግሥት እሳቱ እናዳይነሳ ማድረግ አልቻለም ብሎ መክሰስ ተገቢ አይደለም። በየትኛውም አለም ያለ መንግሥት፤ ሙሉ ለሙሉ ችግሮች ከመነሳታቸው በፊት ሊያስቆም አይችልም። ችግሮች ከተከሰቱ በኋላ ግን፤ መንግሥት አጥፊዎች ላይ እርምጃ የመውሰድ ግዴታና ሃላፊነት  አለበት። ይህ እንደተጠበቀ ሆኖ፤ ችግሩ ከመከሰቱ በፊት፤ ችግሩ እንዳይነሳ የማድረግ ሃላፊነቱ የማነው? በሃይማኖት መምህራን እና አመራሮች ያልተገራ አጥፊ ለሚያጠፋው ጥፋት፤ ተጠያቂ መሆን ያለበት የሃይማኖት መምህሩ እና አመራሩ ነው። በፖለቲካውም እንዲሁ። የፖለቲካ ድርጅቶች፤ አባላቶቻቸውን በተገቢው ሁኔታ በመግራት፤ በነውጥ እንዳይሳተፉ ከማድረግ ይልቅ፤ ነውጥን እየሰበኩ፤ አባላቶቻቸውና ደጋፊዎቻቸው፤ ጥፋት ሲፈጽሙ፤ መንግሥት ላይ ጣት መጠቆም ተገቢ አይሆንም። 

ኢትዮጵያ የሁላችንም ነች፤ ሰላሟን የማስጠበቅ ግዴታ የሁላችንም ነው። የመግሥት አካላት ከመሃላችን የወጡ እንጂ ከሰማይ የመጡ ተዓምር ሰሪዎች አይደሉም። ሕወሃት ስልጣን ከተቆናጠጠበት ጊዜ ጀምሮ፤ ከስልጣን እስከተወገደበት ጊዜ ድረስ፤ የሃገሪቱን በሔራዊ ተቋማት ያዳከመ እና በተለይም የፀጥታ መዋቅሩ፤ ለአንድ ፓርቲ ብቻ እንዲቆም ሆኖ የተገነባ እንደነበር መረዳት አለብን። ከለውጡ በኋላ ግንባታው እንደ አዲስ የተጀመረ በመሆኑ ጠንካራ ሆኖ ለመውጣት ብዙ ይቀረዋል። ተቋም መገንባት ጊዜ ወሳጅ ነው። በሃገራችን በተለያዩ አካባቢዎች ሽብር ለመፍጠር፤ የጅምላ ጭፍጨፋዎችን ለማካሄድ እና ሰላም ለመንሳት ቆርጠው የተነሱ የሽብር እና አጥፊ ሃይሎች መኖራቸውም የተዘነጋ ይመስላል። እነዚህን ኃይሎች መንግስት ሊቋቋም እና ሊያጠፋ የሚችለው፤ በህብረተሰቡ ትብብር ነው። እኛስ ችግር ከመፈጠሩ በፊት፤ ችግር እንዳይፈጠር የማድረግ ሃላፊነት የለብንም ወይ? ችግር ከተፈጠረስ በኋላ፤ ችግር ፈጣሪዎችን ለሕግ አካላት አሳልፈን የመስጠት ግዴታ የለብንም ወይ? ፋኖ አጠፋ ሲባል፤ ተከራካሪው አማራ ብቻ ከሆነ፤ ሸኔ አጠፋ ሲባል ተከራካሪው ኦሮሞ ብቻ ከሆነ፤ ይህ አካሄዳችን፤ በእውነት ለሃገራችን ይበጃል ወይ? ለሙስሊሙ ክርስቲያኑ ካልተከራከረ፤ ለክርስቲያኑ ሙስሊሙ ካልተከራከረ፤ የጋራ ሃገር ውስጥ በሰላም መኖር እንችላለን ወይ? መንግሥትን መውቀስ ቀላል ነው፤ እራሳችንንስ በመስተዋት ማየት የለብንም ወይ? ሃላፊነት እንደሚሰማው ዜጋ ሁላችንም ለሃገራችን ዘብ መቆም የለብንም ወይ? ወይስ በበቀል ደዌ ታመን፤ “የእኔ” የማንለውን ሃይል ለመጣል በምናደርገው እኩይ ተግባር ሃገርን በመጉዳት ዘላቂ ሰላም እናመጣለን ብለን እናስባለን? 

ዛሬ አዲስ አበባ ተቀምጠው ወንበር የሚያሞቁ እና “ጭብጨባ ፍለጋ” በመግለጫ የሚያደነቁሩን የፖለቲካ ሃይሎች ምን እየሰሩ ነው? መንግሥት የተቸገረውን እንዲረዳ የወቀሳ አለንጋቸውን ከመሞረድ ይልቅ፤ ሕዝቡን በማስተባበር፤ ለተቸገረውና ከየቀዬው ለተፈናቀለው ሕብረተሰብ እርዳታ ለምን አያደርሱም? ሕዝብን ለማገልገል፤ ከልብ ለማገልገል፤ የግድ ቤተ መንግሥት መገባት አለበት የሚል አስተሳሰብ ከየት  ነው የመጣው? ኢትዮጵያ ውስጥ በጦርነት ሕዝብ ሲፈናቀል ይህ የመጀመሪያው አይደለም። ከሱማሌ ጋር በተደረገ ጦርነት በደረሰው ጉዳትና መፈናቅል፤ በግል አነሳሽነት፤ እርዳታ ስናሰባስብ ለነበርን ሰዎች፤ አሁን በተሻለ ቴክኖሎጂ፤ የተሻለ ጥረት የማይደረግበት ምክንያቱ ግራ አጋብቶናል። በወሎ ረሃብ ጊዜ፤ በወቅቱ የወጣት መሪዎች የነበሩት እነ ረዘነ በየነ ገብረእግዚአብሔር፤ በብሔራዊ ሎተሪ አዳራሽ እርዳታ ያሰባሰቡበት የኢትዮጵያዊነት መንፈስ የተ ገባ? በጋሽ ጳውሎስ ኞኞ አስተባባሪነት፤ አባቴም የተሳተፈበት፤ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች፤ በራሳቸው አነሳሽነት፤ ለወሎ እና ለትግራይ ረሃብተኞች ያሰባሰቡት እርዳታስ፤ መንፈሱ የታለ? ከእነዚህ ልምዶች እንዴት ትምህርት አልተወሰደም? አንዳንድ የዛሬ “ጋዜጠኞቻችን” ስለተቸገረው ሕዝብ የአዞ እንባ እያፈሰሱ፤ ስህተት ፍለጋ ከማነፍነፍ እና አንዱን ብሔር ከሌላው ጋር ለማጋጨት፤ ተግተው ከመስራት ይልቅ እናስብለታለን ለሚሉት ተፈናቃይ ሕዝብ ምን ሰሩ? እነዚህ ኃይሎች፤ በበቀል ስሜት የታመሙ በመሆናቸው፤ የመገናኛ ብዙሃንን ለራሳቸው ጠባብ ፍላጎት ሲጠቅሙብት እያየን፤ እና እያበረታታን፤ መፍትሔ ማግኘት እንዴት እንችላለን? 

ለዚህ ሁሉ የሰው ሕይወት መጥፋት፤ ንብረት መውደም፤ ምክንያቱ የበቀል ባሕላችን ነው። ችግሩን ካባባስነው፤ ስለመንግሥት ጥፋት ነጋ ጠባ ካወራን፤ መንግስትን ብቻ ተጠያቂ ካደረግን፤ የማንፈልገው ቡድን ከሥልጣን ይነሳል፤ በሚል የበቀል ስሜት የተገመደ ሃገር አጥፊ የበቀል ባሕል። በመንግሥት በኩል ያሉ ጥፋቶችን ተገቢና ገንቢ በሆነ መንገድ ከማረም ይልቅ፤ “ልጁንም፤ የታጠበበትንም ቆሻሻ ወኃ” የመድፋት የቂም አስተሳሰብ ሃገራችንን እየጎዳ ነው። አመራር ላይ ያሉ ሰዎችን፤ በአስተሳሰባቸው ወይም በስራቸው ሳይሆን፤ የምንመዝናቸው በሃይማኖታቸው እና በዘራቸው በመሆኑ፤ የእኔ ካልናቸው እንደግፋቸዋለን፤ የእኔ ካላልናቸው ደግሞ አምርረን እንጠላቸዋልን። ስንጠላቸው ደግሞ በሥራቸው ስኬታማ እንዳይሁኑ ግጭት እናራግባለን። መልሰን ስለሰላም የምንጠይቀው ደግሞ እኛው እንሆናለን። 

“ትኋንን ለማጥፋት ቤትን የማቃጠል” እርምጃ በሃይማኖቱም በፖለቲካውም የምናየው የሃገር ጠንቅ፤ ሊወገድ የሚችለው የበቀል ባሕላችንን ከሥሩ ነቅለን ስንጥል ብቻ ነው። በአንድ ጉንጭ ስለሰላም እየሰበኩ፤ በሌላ ጉንጭ ጥፋትን ማስተማር የሚያጠፋው ሁላችንንም መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል። እንደዚህ ፀሃፍ እምነት፤ የወደፊት አብሮነታችንን እና ዘላቂ ሰላም ልናሰፍን የምንችለው፤ አደገኛውን የበቀል ባሕል ለመቀየር፤ በጥናት የተደገፈ መሰረታዊ ለውጥ የሚያመጣ ሥራ ስንሰራ ብቻ ነው። በተለይም የተቋቋመው የሰላምና የእርቅ ኮምሺን፤ የበቀል ባሕላችንን ለመለወጥ ተግቶ ካልሰራ፤ ስበሰባው ብቻውን፤ ለውጥ ያመጣል ብሎ ማመን አስቸጋሪ ነው። ገና ከጅምሩ፤ በርካታ የፖለቲካ ኃይሎች እንቅፋት ሲፈጥሩ የምናየው፤ ውስጣቸው ባለው የበቀል ስሜት ነው። ዛሬም ዓላማቸው የሃገር ፅናት ሳይሆን፤ በአቋራጭ ሥልጣን መያዝ ነው። ሃሳብ አቅርበው፤ በሃሳብ ተሟግተው የሕዝብን ልብ ለማሸነፍ አቅም የሌላቸው፤ ገና ክ70ዎቹ የበቀል የፖለቲካ አስተሳሰብ ያልተላቀቁ እና የሙሾ ፖለቲካ ላይ የተቸነከሩ ፖለቲከኞች፤ አርቀው የሚያዩት እስከ ሥልጣናቸው እንጂ፤ ከሥልጣን ባሻገር፤ ለሃገር ዘላቂ ሰላም እና ከትውልድ ወደ ትውልድ የሚሸጋገር ስልተ ሥርዓት የመገንባት አዎንታዊ ሥራ ላይ አይደለም። ይህም የሆነው፤ ውስጣቸው በበቀል የተሞላ በመሆኑ ነው። ለዚህም ነው ሃገራችንን በጥናት በተደገፈ ከፍተኛ ሥራ የበቀል ባሕልን ከሃገራችን ማጽዳት ያለብን። ለዚህም ነው፤ ከበቀል የፀዳ ኅብረተሰብ ስንገነባ ሃገራችን ኢትዮጵያ ከግጭት አዙሪት የምትወጣበት ዕጣ ፈንታ የሚሆነው።

ሰላም ለኢትዮጵያ፤ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን እግዚአብሔር ይጠብቅ፤ ይባርክ። 
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,682FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here