ተስፋዬ ደምመላሽ
ሚያዚያ 26 2014 ዓ.ም.
እንደሚታወቀው፣ ከአብዮቱ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ አማራው በማኅበረሰባዊና አገራዊ ህልወናው ከተለያዩ የውስጥም የውጭም ጠላቶች ለከባድ የርዕዮት፣ የስነልቦና፣ የፖለቲካ፣ የአገዛዝ እና የአሸባሪ ኃይል ጥቃት ኢላማ እንደሆነ አለ። ጥቃቱን ዛሬ ወራሪ የኦነግና ወያኔ ኃይሎች በአብይ ሙልጭልጭ አገዛዝ ይሁንታም ሴረኛ ተባባሪነትም ከመቸውም ጊዜ ይበልጥ ጨፍጫፊ፣ አውዳሚና ቀውስ ፈጣሪ አድርገው ቀጥለውበታል።
ዘርፈ ብዙውን ጥቃት መከላከልና ማምከን ማለት የአማራውን የመነመነና እየታመሰ ያለ ህልውና እንዳለ ከጥፋት ማትረፍ ሳይሆን መልሶ ማዳበር፣ ማረጋጋት፣ ማጠናከርና እንደገና እንዲያብብ ማድረግ ነው የሚሆነው። በጥልቅ ዕቅድና ዘዴ የአማራን የመኖር አለመኖር ትግል ዘላቂ አቅጣጫ ማስያዝ ማለት ነው። በዝች መለስተኛ ጽሑፍ ስለትግሉ ስልታዊ አቀራረጽ ጠቅለል ባሉ ጥቂት ርዕሰ ነገሮች ዙሪያ ሃሳቦችና አስተያየቶች እሰነዝራለሁ። በሌላ ቀጣይ መጣጥፍ ደግሞ ከአማራ ሕዝባዊ ኃይል፣ ፋኖ፟ አንፃር እንዲሁ የንቅናቄ ዕቅድና አፈጻጸም ላይ ያተኮሩ አስተያየቶች አቀርባለሁ።
ስልትና የጉዳዮች አቀራረብ ደረጃዎች፥ አማራው ማኅበራዊ ህልውናውን፣ ባህሉን፣ መንፈሳዊ ሕይወቱንና ዓለማዊ ኑሮውን ከዘረኞች ጥቃት ለመከላከል ሲንቀሳቅስ ደረጃው ከፍ ወዳለ አገር አቀፍ ስልታዊ ትግል የሚዘልቅበት አንዱ ዋና መንገድ የራሱንና የአገሩን ብርቱ ጉዳዮች አቀራረጹን በሃስብና ገቢር በማጥራት፣ በማሻሻልና በማጠናከር ነው። ሁለት የተለያዩ ግን የሚመጋገቡ የቀረጻ ደርጃዎችን መጠቆም እንችላለን።
አንደኛው፣ አማራው አፋጣኝ መልሶች እንዲሰጥና አስቸኳይ እርምጃዎች እንዲወስድ የሚያስገድዱትን ተለዋዋጭ ኩነቶች፣ ሁኔታዎችና ጥቃቶች የሚገጥምበት ደረጃ ነው። ሰሞኑን በጎንደርና በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ቤተ ክርስቲያናትን የማጋዬት ጥቃቶች በዚህ እርከን የሚከሰቱ ፈተናዎች ምሳሌዎች ናቸው። እነዚህ የአጭርና መካከለኛ ጊዜ ጉዳዮች በአንጻር ራሳቸውን ችለው የሚታዩና የተመጣጠነ ወቅታዊም አካባባዊም ምላሽ የሚፈልጉ ናቸው።
ሁለተኛውና ተያያዡ ደርጃ ደግሞ፣ ለተለዋዋጭ ማኅበረሰባዊና አካባባዊ ችግሮችም ሆነ ለነባራዊ ሁኔታዎች ጠቅለል ያሉ መዋቅራዊ መፍትሔዎች ለማበጀት አማራው በአንድነት ተሰባስቦ የሌሎች ባህላዊ ማኅበርሰቦች አካላት ከሆኑ አገር ወዳድ ስብስቦች ጋር ተባብሮ ራሱንም ኢትዮጵያንም ከጥፋት ላማዳን ምን ዓይነት የፖለቲካ ትስስር፣ አደረጃጀትና ንቅናቄ ያስፈልጉታል የሚል ጥያቄ የሚያስነሳ ነው። ይህ አቀራረብ፣ አስቸኳይ የሆኑ ተጨባጭ ችግሮችን ሥርዓታዊ ምንጮች አማራው በስልታዊ ትንተና ተረድቶ ዘላቂ መፍትሔያቸውን የሚተምንበትና የሚቀርጽበት ደረጃ እንደሆነም እንረዳለን።
እዚህ ላይ ጎሠኛ ፓርቲዎችም አገዛዞችም የኢትዮጵያን ሕዝብ ዘር ዘለል የጋራ መሠረታዊ ጉዳዮችና ጥያቄዎች በፀረ አማራ ዘረኛ ሴራ አጣበው፣ ሸራርፈውና ከፋፍለው የቀረጹባቸውን አምባገነናዊ የትርክት፣ የአስተሳሰብና የአነጋገር ዘይቤዎች ከተጠጨባጭ የሕዝብ ጥያቄዎች በግልጽ ለይቶ ማስቀመጥ ጠቃሚ ነው። ብሎም፣ ለወያኔና ኦነግ ወገንተኛ ፖለቲከኖች “ማንነት” መግለጫና ሥልጣን ማካበቻ በመሆን የላሸቁ የዜጎች ጉዳዮችን ለተሻለ፣ የግለሰብ መብቶችን በምር ታሳቢ ላደረገና የአገር መንፈስ ለተላበሰ አዲስ አቀራረጽ መከፋፈት ያስፈልጋል።
ስልት በሃሳቦች ዘርፍ፥ ድርጁ ጽንሳዊና ተግባራዊ ሃሳብ ለአማራው የህልውና ስልተ ትግል ጥራት ሰጪ፣ አጠናካሪና አዛላቂ ሊሆን እንደሚችል እውቅ ነው። ግን በዘረኛ ስሜት የተዋጠ አእምሮ ቢስ፣ ጠባብ፣ ጎጠኛ አገዛዝን – በትግሬም ሆነ በኦሮሞ ቅርጹ – በሃሳቦች ዘርፍ መቋቋም ምን ፋይዳ አለው፣ እንዴትስ ይከናወናል የሚል ጥያቄ ሊነሳ ይችል ይሆናል።
ማለትም፣ ከራሳቸው ብቸኛ ወገንተኝነት ባሻገር ለዓለም አቀፍ ሃሳቦች ቀርቶ ለአገራዊ የፖለቲካ እሳቤ ምንም ያህል ዋጋ ከማይሰጡ ጎሠኛ ፖለቲከኞችና ምሁራን ተብዬዎች ጋር የአስተሳሰብ ፉክክር ወይም ድርድር ማድረግ ለአገር ወዳዶች ምን ጉዳያቸው ነው? እዚህ ግባ በማይባል፣ እንደ እስስት ተለዋዋጭ በሆነ የአቢይ ኢመርሃዊ “አመራር” የሚጠመዘዘው ተልካሻ የአገዛዝ ተሽከርካሪ ከፕሮፓጋንዳና የቃላት ሽንገላና ውጪ በፖለቲካ ርዕዮት መስክ በምር ተወዳዳሪ ስላይደለ አገዛዙን በሃሳቦች ሜዳ መግጠሙ ጅምር የለሽ አይደለም ወይ? ከቶ ለምን ያስፈልጋል?
ጥያቄው ነጥብ አለው። ከጥቂት ዓመታት በፊት ከአገር ገዢነት የተባረረውን ወያኔን ተክቶ መንግሥትን ዛሬ እንደነገሩ የሚቆጣጠረው ኦነጋዊ ወገን ሃሳቦች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ የሚችለው በቀጥታ ግርድፍ፣ አፋኝ፣ አምባገነናዊ ኃይል በመጠቀምና ሴረኛ የፖለቲካ ቁማር በመጫወት ብቻ ነው። ሁሉ ነገር የኔ ነው ባዩ ስግብግብ ተረኛ ገዢ ወገን አገር ወዳድ ወገኖችን፣ ምሁራንን፣ ጋዜጠኞችንና ዜጎችን በቅጡ የሚያሳትፍ ምክንያታዊ ክርክሮችና የሃሳቦች ልውውጥ ማድረግ ፈቃደኝነቱም ሆነ ችሎታው የለውም። እንደ አገር መሪ ለደጉ ብቻ ሳይሆን ለክፉም ኃላፊነት መውሰድ የሚያስችል ተክለ ሰውነት ወይም ሥነ ምግባር የሌለው፣ ሁሉን አዋቂ ነኝ ባይ ጠቅላይ ሚንስትር ራሱን ከዕውቀት ፍንጭ አካቶ የከለለ ነው። ከዚህም ከዚያም እየቀነጫጨበ በየጊዜው የሚለግሰን ልቅምቅም የሃሳብ ውራጆችና ፍርፋሪዎች አገራዊ ይዞታም መንፈስም የራቃቸው ናቸው። ሥልጡኑን የኢትዮጵያ ሕዝብን አይመጥኑም።
ገዥው የኦነግ ፓርቲ እንግዲህ በሃሳብም ሆነ በገቢር ኢትዮጵያን መሪ ለመሆን ፈቃደኝነትና ብቃት ብቻ ሳይሆን ቁመናም እንደሌለው አሳይቷል። መሠረታዊ የተክለ አገርነት ችግር አለው። ስለዚህ የአማራው የህልውና ውጊያ በሃሳቦች ጎን አልፎ በቀጥታ ሰላማዊ የተቃውሞና አመጽ እርምጃዎች አገዛዙ ላይ በመውሰድ ገዢው ፓርቲ ከሥልጣን እንዲወርድ ግፊት ማድረጉ ይበልጥ ውጤታማ አይሆንም ወይ?
ቀጥታ ማህበርሰባዊ የተቃውሞ ጥረቶች፣ ለምሳሌ የሥራ ማቆም አድማ፣ እርግጥ በአማራው ሁለገብ ትግል ውስጥ ተገቢ ቦታ አላቸው፤ አስፈላጊ ናቸው። ድርጁ የፖለቲካ ሃሳብን፣ ዕቅድን፣ አመራርንና እንቅስቃሴን ግን የሚተኩ አይደሉም። መሠረታዊ የአስተሳሰብ ለውጥ የፖለቲካ ሥርዓት መቀየሪያ አይነታ መሣሪያ እንደሆነም መዘንጋት የለብንም። በኢትዮጵያ የተንሰራፋውን የጎሣ አገዛዝ መዋቅራዊ ሙጃ ከስራስሩ ለመመንገል ብቻ ሳይሆን የሚተካውን የተሻለ፣ ዜግነትን ያማከለ፣ የፍትሐዊ ሥርዓት ሰብል ዘርቶ ለማምረት አማራው በሃስቦች መስክ በብልኃት ጠለቅ ብሎ ገብቶ መንቀሳቀሱ ወሳኝ ነው።
በሃሳብ ሜዳ ላይ ስልታዊ ተጫዋችነትን አስፈላጊም ተገቢም የሚያደርገው በመሠረቱ የሃሳቦች ራሳቸው ተፈጥሮ ወይም ትርጉም አያያዝና አለቃቀቅ ባሕሪም ነው። ሃሳቦች (መርሆችን፣ እሴቶችንና እምነቶችንም አጠቃሎ) የመንገድ ካርታ እንደሚመራን በቀጥታ የትግል አቅጣጫዎችን የሚጠቁሙን አይደሉም። ራሳቸው ከኛ ግልጽ አላማ፣ ዘዴኛ አያያዝ፣ አተረጓጎምና አፈጻጸም፣ እንዲሁም መልካም አስተዳደር ካላገኙ ዓለም አቀፍ ይዘታቸውን በግብታዊ መንገድ አይለቁልንም። ለምሳሌ፣ በዘረኞች አገዛዝ “ሕገ መንግሥት” በጎ መርሃዊም ተግባራዊም ተጽዕኖ የሌለው፣ የሆነ ያልሆነ አገዛዝ እንዳሻው ገምድሎ የሚተረጉመው ወይም አካቶ ችላ የሚለው የወረቀት ነብር ሆኖ ቀርቷል።
የፖለቲካ ጽንሰሃሳቦች በጠቅላላ ራሳቸውን ቀራጭ፣ ገላጭ፣ ተርጓሚ፣ ፈጻሚና አስተዳዳሪ አይደሉም። እንዲያውም፣ አገራዊ መንፈስ በተላበሰ ንቃት፣ አስተውሎና ጽኑ እምነት ተቀርጸው ሥራ ላይ ካልዋሉ፣ በሂደትም ካልተስፋፉና ካልተጠናከሩ፣ የተዛባና የተወላገደ ፍቺ ወይም ተቃራኒ ትርጉም ያዥ ሊሆኑ እንድሚችሉ በኢትዮጵያ ድህረ አብዮት የፖለቲካ ልምድ በግልጽ ያየነው ነገር ነው። ለዚህ ነው ወረቅት ላይ የተጨነቋቆረ ሕገ መንግሥት ተብዬ ሰነድ የወያኔንም ሆነ የ“ኦርሚያ” ፓርቲን አምባገነናዊ አገዛዝ ሕጋዊ ሥርዓት ማስያዙ ቀርቶ የአገዛዞቹን እውን ሕገ ወጥነትና ሴረኝነት ሸፋፋኝ የሆነው።
የፖለቲካ ሃሳቦች እንግዲህ ከዘረኝነት የጸዱና ከአማራው ራስና አገር አድን ትግል ጋር ተግባቢ የሆኑ አዳዲስ የቀርጻ፣ የትርጎማ፣ የፍጸማና የአስተዳደር ጥረቶች ይጠይቃሉ ማለት ነው። ጽንሰሃሳቦች በዚህ መልክ የትግሉ ብርቱ መሣሪያ ሊሆኑ ይችላሉ፤ መሆናቸውም ለአማራው ብቻ ሳይሆን ለመ፟ላ ኢትዮጵያ መልሶ ማበብ፣ መጠናከርና መዳበር ወሳኝ ነው።
በትግሉ ስለሃሳቦች መሣሪያነት ስንናገር ግን አንድ ነገር በግልጽ መረዳት አለብን። በተለምዶ ግንዛቤ “መሣሪያ” ራሱ አድራጊ ሳይሆን ታጋዮችና ሌሎች ፈጻሚ ፈጣሪዎች እንዳስፈለጋቸው የሚጠቀሙበትን ነገር ሁሉ የሚያመላክት ቃል ነው። ሆኖም፣ በአማራው ሁለገብ ስልታዊ ንቅናቄ የሃሳቦች መሣሪያነት፣ ማለትም አያያዛቸውና አጠቃቀማቸው፣ ከወያኔና ኦነግ በመሠረቱ የተዛባ፣ ጠባብ፣ ጎጠኛና ወገንተኛ ያጠቃቀም ልምድ የተለየ አገራዊና ሥርዓታዊ ጎን የበልጥ ሊኖረው ይገባል።
በአምባገነናዊው የጎሣ አገዛዝ መዋቅር ውስጥ ጽንሳዊ፣ ተቋማዊና ተግባራዊ ይዞታ ሳይኖራቸው በአነጋገር ልምድ ብቻ ላይ ላዩን የሚዘዋወሩ ዓለም አቀፍ ተራማጅ ተብዬ “ሃሳቦች” እጥረት ኖሮን አያውቅም። እነዚህ “ነፃነትን”፣ “ዲሞክራሲን”፣ “እኩልነትን”፣ “ራስ ገዝነትን” እና “የሕግ በላይነትን” ያካትታሉ። ይሁን እንጂ፣ ለሂሳዊና ገንቢ ትችት፣ ክርክር፣ ውይይትና ድርድር በቅጡ ተከፍተው አያውቁም። ዜጎችንም ሆነ ፓርቲዎችን መሠረታዊ ስምምነት ላይ ማድረስ አልቻሉም።
ለምን? አንድ ዋና ምክንያት የጎሣ ፖለቲካና አገዛዝ አራማጆች ሃሳቦች የሚሏቸውን የሚጠቀሙባቸው ያለ ፍሬ ነገራቸው ነው። ማለትም፣ በድፍኑና በብቸኝነት የዘረኛ ራስነታቸው መቅረጫ ደነዝ ርዕዮታዊ መሣሪያ አድርገው ነው። ለምሳሌ፣ “ዲሞክራሲ” ከወያኔና ኦነግ ብቸኛ የ“ማንነት” ፖለቲካ ውጪ በሰፊው ለኢትዮጵያ መግሥትና ሕዝብ የሚተርፍ በጎ ፍቺ፣ እሴትና ተቋማዊ አካል የለውም። መርሃዊ ፍሬ ነገርም ሆነ ሥርዓታዊ ሕይወት ኖሮት አያውቅም።
በዚህ አውድ፣ የዘውግ አገዛዙ መዋቅር የሚያተኩረው የሃሳቦች ጽንሳዊ ይዘትና ጥራት ወይም ተጨባጭ ትርጉም ላይ ሳይሆን የጎሣ ማኅበረሰቦች ማንነት እና ልዩነት ገላጭነቱ ወይም አረጋጋጭነቱ ላይ ነው። ለምሳሌ ስለዲሞክራሲ መርህና አሠራር ምን እናስባለን ወይም እንላለን ከሚለው መሠረታዊ ጥያቄ የበለጠ አገዛዙ ክብደት የሚሰጠው ማን ነው አሳቢው “ብሔር” ወይም በሃሳቡ ተገላጭና ተጠቃሚ የሚሆነው “ብሔረሰብ” ለሚለው ጉዳይ ነው። በዚህ መልክ ወያኔና ኦነጋዊ ዘረኞች ምንጊዜም ብርቃችው የሆነማንነትን አለቅጥ አጉልተውና አጋነው ምንነትን ያደበዝዛሉ። ስለዚህ ጽንሳዊ ወይም መርኻዊ ሃሳብን ከጎሣ ፖለቲካ ባሻገር በአገር ደረጃ ሰፋና ጠለቅ አድርገው መጠቀም ወይም መረዳት ያዳግታቸዋል፤ ቢችሉም እንኳን ይህ ዓይነት አጠቃቀምም ሆነ አረዳድ አይዋጥላቸውም።
በተፃራሪ፣ አማራው ወደፊት ተመልካች ፖለቲካዊ ሃሳብን የመኖር አለመኖር ትግሉ መሣሪያ ሲያደርግ የሚነሳበት የተለየ ቅድመ ግንዛቤ አለው፣ ወይም ሊኖረው ይገባል። ይኸውም፣ በመሠረቱ ሃሳብ እንደሃሳብ መሣሪያ የሚሆነው በውስጣዊ ጽንሰ ምንነቱ ወይም ይዘቱ እንጂ ዝምብሎ የሆኑ ያልሆኑ አገዛዞችና ካድሬዎች ትርጉመ ገምድል ተቀባይ በመሆን አይደለም። በኃቀኛ አያያዝና መልካም አስተዳደር ሃሳቦች በአንጻራዊ ነፃነት በጎ ፍሬ ነገራቸውን እንዲለቁ ካላስቻልናቸው የአብርሆት ምንጭ ሊሆኑን አይችሉም። እንዲያውም፣ ዛሬ በኦነግ ቅጥ የለሽ፣ ስግብግብ አገዛዝ እንደምናየው፣ ሙስና፣ ድንቁርና፣ ቀውስና ሽብር አራቢ የጨለማ ኃይሎች ሊሆኑ ይችላሉ።
የአማራው ንቅናቄ ዕቅድ ከምክንያታዊ የፖለቲካ ሃሳቦችና ረቂቅ መርሆች ለየት ያለ እንደሁኔታው ሥራ ላይ ሊውል የሚችል የራሱ አመክንዮና ጥበብ፣ የራሱ መረጃ አሰባሰብ፣ አያያዝና አጠቃቀም አለው። አካቶ በይፋ ለሕዝብ ተገላጭና ታዋቂ ሊሆንም አይችልም። ነገር ግን ስልት ሃሳቦችን፣ መርሆችንና አገራዊ እሴቶችን ከላይ ወይም ከውጭ የሚጠመዝዝ ኃይል ሳይሆን እነዚህን በታማኝነት ውስጣዊ የውጊያ ቅኝት፣ ስምሪት፣ አቅጣጫና ሥነ ሥርዓት ያስይዛል። የትግል ዘርፎች (ለምሳሌ፣ የፖለቲካ፣ የስነልቦና፣ የሃሳብና የትጥቅ) ሲቀየሩ ወይም ሲተካኩ፣ ወይም ደግሞ ያልተጠበቁ ሁኔታዎች ሲከሰቱ፣ ስልትም ተመዛዝኖ ሊሸጋሸግና ሊስተካከል ይችላል፤ ያስፈልጋልም።
ጥልቅ ስልት፥ የአማራው ራስና አገር አድን ተጋድሎ ዕቅድ ለዘለቄታው ሰፋና ጠለቅ ብሎ እንዲቀረጽ የሚያስገድዱ የተለያዩ ነባርና ወቅታዊ ሁኔታዎች አሉ። እዚህ ባጭሩ ሁለት ዋና ምክንያቶች መጠቆም ይበቃል። አንዱ የፖለቲካ መዋቅር ወይም ሥርዓት ቅየራ አስፈላጊነት ነው። ዘላቂ ሥርዓታዊ ለውጥ ለማምጣት ደግሞ ጥልቀት ያለውና በተለያዩ የትግል ዘርፎች እንዳስፈላጊነቱ እየተስተካከለ ተፈጻሚ ሊደረግ የሚችል ተለማጭ ዕቅድ መቀየስ ግድ ይላል።
ይህን የምልበት መነሻ ሃሳብ ወይም ቅድመ ግንዛቤ አለኝ። የኸውም፣ ከጽንሱና መሠረቱ ፀረ አማራ በሆነው የጎሣ አገዛዝ መረብ ውስጥም ይሁን በጥጎቹና ዳርቻዎቹ ተወስኖ በመንቀሳቀስ አማራው ራሱንም ሆነ የሚወዳት አገሩን ኢትዮጵያን ከጥፋት ወይም ከቁም ሞት ሊያድን የማይችል መሆኑ ነው።
አገራችንን በቁሟ የሞት አፋፍ ላይ ያደረሳትና አማራውን በተለይ ደግሞ የህልውና አደጋ ላይ የጣለው ሁኔታ፣ በሆነ ያለሆነ አረመኔያዊ መንጋ ቀጥታ ወረራና ግድያዎች ክስተት የተወሰነ አይደለም። አደጋው በዚህ ወይም በዚያ ጎሠኛ ወገን አምባገነናዊ አገዛዝ ጥቃቶች ከፊት ለፊት ብቻ የሚታይም አይደለም። የተለያዩ ዘረኛ ፓርቲዎች ከሞላ ጎደል የሚጋሩትና በውጭ ኃይሎች የሚደገፍ ሥርዓታዊ ዳራ ወይም መነሻና መንደርደሪያ አለው። አማራውን ከነአገሩ በመሠረቱ የተጠናወተው ጠላት ትግሬና ኦሮሞ አገዛዞች በቅብብሎሽ ቀጣይ ያደረጉት፣ አማራ ግብረ አበሮችና ከዳተኞች ተሳታፊ የሆኑበት፣ ዘረኛ የፖለቲካ መዋቅር መሆኑን መዘንጋት የለብንም።
ሌላው ዋና የስጥም ስልተ ትግል አስፈላጊነት ምጣኔ ኃይልን የሚመለከት ነው። የፖለቲካና የጦር ኃይል እጅግ አባካኝ ከሆኑ፣ መቋጫ ከሌላው ውሃ ቅዳ ውሃ መልስ የርስ በርስ ውጊያዎች መቆጠብን ታሳቢ የሚያደርግ ነው። ማለትም፣ በተለያዩ ሁኔታዎች እየተስተካከለ በብልኃት ተፈጻሚ የሚሆነው የአማራው ሁለገብ ንቅናቄ ስልት፣ ምንም የጦርነት ስነ ምግባር የማይከተሉና ስብዕና አካቶ የሌላቸው ሕዝብ ጨፍጫፊ ወራሪዎችን ለዘለቄታው አደብ ሊያስገዛ ይችላል። ተደጋጋሚ ወረራቸውና ጥቃታቸው የሚያደርሱትን አላስፈላጊ ደም መፋሰስ፣ የንብረት ውድመትና የንጹሃን የዜጎች መፈናቀል ከወዲሁ ይቀንሳል፤ ብሎም ያስወግዳል።
ትግሉ በተለያዩ መንገዶችና ደረጃዎች ብዙ ዋጋ ያስከፍል ይሆናል፤ እርግጥ መስዋትነት ይጠይቃል። ነገር ግን መሠረታዊ የትግል ዕቅድ ለምጣኔ ኃይልና ድል አድራጊነት ያለውን አንድምታ በሚመለከት አማሮችና አገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን ታጋዮች በጠቅላላ ሰን ትዙ ከተባለው የጥንት ቻይናዊ ጦረኛ-ፈላስፋ ጠቃሚ አስተምህሮ መቅሰም የበጃቸዋል።
የአስተምህሮውን ይዞታ እዚህ በአማራው የትግል አውድ ባጭሩ ለመግለጽ፣ ሰፋና ጠለቅ ባለ ዕውቀት የተቀየሰ ስልት ውጤታማነት ዋና መገለጫው ኃይለኛ (ደም አፋሳሽ) ውጊያዎችን ምንም ያህል አስፈላጊ አለማድረጉ ነው። የአማራው ራስና አገር አድን ንቅናቄ እቅድ አቀራረጽ፣ አደረጃጀትና አመራር ጠልቀው ታሳቢና ተፈጻሚ እስከሆኑ ድረስ የጠላትን ዘረኛ ርዕዮትና የሃሰት ትርክቶች ያረክሳሉ፣ ዋጋ ያሳጣሉ፣ ይገረስሳሉ። የሆኑ ያልሆኑ ትብብሮቹን ያዳክማሉ፣ ይንዳሉ። የጦር ኃይሎቹንና መሪዎቹን ሞራል የሰብራሉ፣ ከግጥሚያ ውጭ ያደርጋሉ። በዚህ ዓይነት ዘዴኛ ንቅናቄ አማራው ጠላቶቹን በጦር ሜዳ ከመግጠሙ በፊት ለሽንፈት በማመቻቸት እምብዛም ሳይዋጋ ራሱን ዘላቂ ድል ማጎናጸፍ ይችላል።
አማራው በዚህ መንገድ የውጊያውን ውጣ ውረድ አስቀድሞ ሲቀይስ፣ ፊት ለፊት የተደቀኑበትን አጣዳፊ የመኖር አለመኖር ፈተናዎችን እርግጥ ትኩረትና ቀደምትነት መስጠት አለበት። ሆኖም፣ አስቸኳይ ተልዕኮዎቹንና መለስተኛ እንቅስቃሴዎቹን ዘላቂ ትግሉ ስሌት ዉስጥ በማስገባትና በማጠናከር የረጅም ጊዜ ንቅናቄው መረማመጃ ማድረግም ያስፈልገዋል። የእንቅስቃሴዎቹ ክንውኖችና ስኬቶች በታክቲክ ደረጃ ወይም በአካባቢዎች ተወስነው ከቀሩ ለጠላት ቅልበሳ ወይም ተቃራኒ ቅየራ ይጋለጣሉ።
ከዚህ አንጻር አማራው የጠላቶቹን ወረራ ሲቋቋምም፣ በየጊዜውና በየቦታው በቀጥታ የሚደርሱበትን አስከፊ ዝርዝር ወረራዎችና ጥቃቶች በምላሽ መከላከል ብቻ ሳይወሰን የደመኞቹን ወቅታዊም ዘላቂም እቅዶችና አዝማሚያዎች ከወዲሁ እየተረዳ በቅድመ ተነሳሽ እንቅስቃሴዎች በማሰናከል፣ የሃይል ክምችታቸውን በመበተን፣ ቅንጅታችውን በማፋለስና የውጊያ ሂደታቸውን በብልሃት በማደናገርም ነው። በዚህ መልክ አማራው ትግሉን አደራጅቶ ሲያካሂድ የጠላቶቹን የውጊያ አቅም ቀድሞ በዘዴ በመሸርሸርና በማመንመን ዝቅ ያደርጋል፤ ይገታል፣ ያኮላሻል።
በተለያዩ መስኮችና ደረጃዎች ሰፋና ጠለቅ ያለ ሁለገብ የትግል ስልት በመጠቀም እንግዲህ አማራው ራሱን ጠብቆና አጠናክሮ፣ ማለትም አሠልጥኖ፣ አደራጅቶ፣ አስታጥቆና አመራር በብቃት ሰጥቶ፣ ግን እምብዛም ሳይዋጋ፣ ለአሸናፊነት ሊበቃ ይችላል። ራሱንና አገሩን ከጥፋት ለማትረፍ አስፈላጊ ሆኖ ሲያገኘው ደግሞ፣ ታሪኩ እንደሚመሰክረውና ደመኞቹም እንድማይጠፋቸው፣ ጦር ሰብቆ፣ ሰይፍ መዞ በቆራጥነትና ጀግንነት ጠላቶቹን ከመግጠም ወደኋላ እንደማይልም ያሳያል።
የአማራና ኢትዮጲያ (ስልታዊ) ትስስር፥ እዚህ ላይ፣ አማራውን ከአሰቃቂ ግድያና መከራ ለማዳን ስንነጋገር የአገር ወዳድነትን (የኢትዮጵያዊነትን) ጉዳይ ማንሳት የአማራውን የመኖር አለመኖር ውጊያ ያደበዝዛል እያሉ የሚያላዝኑ አሉ። ሕያውና ውስብስብ የሆነውን የአማራና የኢትዮጵያ ትስስር አጉል አቃለው የሁለትዮሽ (binary) ቅርጽ በመስጠት የአማራን ራስ አድን ንቅናቄ ወዲህ፣ ኢትዮጵያን የመታደግ ውጊያን ወዲያ አድርገው ያያሉ። ይህ አተያይ ላይ ላዩን የአማራውን ትግል ለይቶ ግልጽ የሚያደርግና ቅድሚያ የሚሰጥ ይመስላል። ሆኖም፣ ከጥልቅ ስልት ቅየሳም ሆነ ከትግሉ ተጨባጭ አኪያሄድ አኳያ ሲታሰብ የተዛነፈ፣ ዝንጥል አመለካከት ነው።
በጦርነትም ሆነ በሰላም፣ የአማራው ህላዌ አንድም ሁለትም ነው፤ አማራ ራስነት ወይም ማንነት አገራዊ ወርድና ስፋት አለው። አማራነት ውስጥ ሕያው፣ ተንቀሳቃስሽ ኢትዮጵያዊነት አለ። ይህን ስንል ምን ማለታችን ነው? አማራው በህልውናው እና ንቃተህሊናው አገር ወዳድነትን በጥልቅ ስለሚያካትት ራሱን ከጥፋት ለመታደግ ተነስቶ ሲንቀሳቀስ በውስጡ ያዳበራቸው የአገር ወዳድነት እሴቶችና ፀጋዎች፣ ለምሳሌ ሥልጡን ሕዝብነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ አርበኝነትና ጀግንነት፣ ለራስ አድን ተጋድሎው ወሳኝ መሣሪያዎቹ ናቸው። የመኖር አለመኖር ትግሉን የሚበርዙ ውጨኛ ግባቶች አይደሉም። ይልቅስ የአማራው ሙሉ ህልውና የውስጥ አካላት ናቸው።
ይህን አስተሳሰቤን ይበልጥ ግልጽ ለማድረግ ስለ አማራው ውስጣዊ አገራዊነት አንድ ነገር አክየ ልበል። በአማራው የራስ አድን ትግል አገር ወዳድነት የተካተተ ነው ስንል በትግሉ ኢትዮጵያዊነት የግድ በይፋ የሚለፈፍ፣ የሚታወጅ የፖለቲካ አጀንዳ ወይም ርዕዮት ይሆናል ማለታችን አይደለም። አገር ወዳድነት የአማራውን ሕዝብ የሚያነሳሳውና ተወርዋሪ ኃይል ሊያደርገው የሚችለው ብዙ ሳይባልለት አንቂ፣ አነሳሽና አንቀሳቃሽ ኃይል በመሆንም ነው። በአገር ወዳድ አማሮች ዘንድ ኢትዮጵያዊነት እምብዛም የሚነገር፣ በዲስኩር መሰበክ የሚያስፈልገው አይደለም። በአመዛኙ፣ በጥልቅ የሚሰ፟ማን፣ የምንኖረውና የምናደርገው እንጂ ላይ ላዩን ወይም በረቂቁ የምንለውና የምናስበው አይደለም።
በተጨማሪ፣ የተለያዩ የአፍሪካ ቀንድ አካባቢ አገሮችንና ታላላቅ ምዕራባዊ መንግሥታትን ባካተተ የኃይሎች መረብ የሚደገፍን በመላ ኢትዮጵያ የተንሰራፋ የጎሣ አገዛዝ በትግል ሲገጥም ታላቁ የአማራ ሕዝብ ከአገራዊ መሠረቱና ልምዱ ተለይቶ በግልብ ነገዳዊ ማንነቱ ብቻ ይቆማል ተብሎ አየጠበቅም። በዚህ መልክ ተነጥሎና ተጣቦ የተከለለ ማንነት የአማራን ህልውናም ሆነ ንቃተ ኅሊና አይመጥንም። ይህ ዝምብሎ የኔ አስተያየት ሳይሆን ታሪካዊና ባህላዊ ኃቅ ነው።
ከትግል ስልት አመክንዮ አኳያም ቢሆን አማራው ራሱን ከኢትዮጵያ ጉዳዮች አርቆ፣ ኢትዮጵያዊነት የሚሰጠውን ልዩ አገራዊ አቅምና ልምድ ወደ ጎን ትቶ፣ እንደ ሕወሓት ወይም ኦነግ በብቸኛ የዘውግ “ነፃ አውጪ” ትግል ጎዳና መሄዱ ሩቅ አይወስደውም። ይህ የዘረኝነት ፍኖት እንኳን አማራውን በጠባብ ጎሠኛ ወገንተኝነት የተካኑትን ወያኔዎችንም አላዋጣቸውም። የፖለቲካና የሞራል ኪሳራ ነው ያከናነባቸው። ውሎ አድሮም ቢሆን የተረኛ ኦነጋዊያን መንጋ እጣ ፈንታም ከወያኔ ቢጤዎቻቸውና አጋሮቻቸው ምንም ያህል የተለየ አይሆንም።
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
ይህ የአቶ ተስፋዬ ደምመላሽ ጽሁፍ፤ የጭብጥ ጠኔ የመታው፤ በግምት እና በጥላቻ ላይ የተንጠለጠለ መጣጥፍ ነው። ሃገራችንን እየጎዳት ያለው፤ “ተማርን በሚሉ” የአማራ፤ ኦርሞ፤ እና ትግሬ ብሔርተኝነት አቀንቃኞች መካክል ያለን እርባነ ቢስ ፉክክር ወደ ሕዝቡ ለማውረድ በመሞከር፤ በሃገር እነሱን መስል፤ እራሳቸው የጠረቡት አገዛዝ በሕዝብ ላይ ለመጫን ከመሞከር የሚመጣ እሳቤ እንጂ፤ “አማራውን ለማዳን” ወይም “ኢትዮጵያን ለማዳን” አይደለም። ኦሮሞ ሁሉ ኦነግ ነው፤ ትግሬ ሁሉ ወያኔ ነው፤ አማራው እና ኦርቶዶክስ ክርስትያኑ ብቻ ሃገር ወዳድ ነው ከሚል ጽንፈኛ አስተሳሰብ የፈለቀው የአቶ ተስፋዬ አስተሳሰብ፤ ዶ/ር አብይን አስተዳደር “ገዥው የኦነግ ፓርቲ እንግዲህ በሃሳብም ሆነ በገቢር ኢትዮጵያን መሪ ለመሆን ፈቃደኝነትና ብቃት ብቻ ሳይሆን ቁመናም እንደሌለው አሳይቷል።” ሲሉ ይገልጹታል። ይህ ፍፁም ሃላፊነት የጎደለው ብቻ ሳይሆን፤ “ኦርሞ ሁሉ ኦነግ ነው” ከሚል የጥላቻና ዋልታ ረገጥ አስተሳሰብ የሚመነጭ ነው። ኢትዮጵያን ማዳን የሚችለው ሁልም ሲተባበር፤ በሚችለውም አቅም ሲሰራና የተጣመመውን ሲያቃና እንጂ፤ የአማራ ጎጠኝነትና ዘረኛ አስተሳሰብን በመስበክ አይደለም። ጎጠኝነትን በጎጠኝነት፤ እፈታለሁ ማለት፤ እነ አቶ ተስፋዬ ተጠግተው የማይሞቁትን ሌላ እሳት መለኮስ ይሆናል። በዚህ ጉዳይ፤ ነጥብ በነጥብ እያነሳሁ፤ የአቶ ተስፋዬ ጽህይፍ በቀል እና ጥላቻ የወለደው እንጂ፤ በእውነት ለኢትዮጵያም ሆነ ለአማራው ሰፊ ሕዝብ በመቆርቆር አለመሆኑን አሳያለሁ። ቸር ይግጠመን
አቶ ሳሙኤል፣ የተደራጁ ጎሠኛ ብሔርተኞች በፉክክርም ሆነ በትብብር “እርባነ ቢስ” ፉክክርራቸውን ወደ ሕዝቡ ካወረዱት እኮ አስርተ ዓመታት ተቆጥረዋል፤ እኔ ዛሬ እንደ አንድ ግለሰብ ለማውረድ መሞከር ምንም አይስፈልገኝም! በጽሑፌ ይህን ለማድረግም አልሞከርኩም። እርስዎ አክልው እንደሚወነጅሉኝም ጽሑፌ “ኦሮሞ ሁሉ ኦነግ ነው፤ ትግሬ ሁሉ ወያኔ ነው፤ አማራውና ኦርቶዶክሱ ብቻ ሃገር ወዳድ ነው ከሚል ጽንፈኛ አስተሳሰብ የፈለቀ” አይደለም። እኔ እንደዚህ አይነት ግምድል አስተሳሰብም ሆነ የደፍን ማኅበረሰቦች ጥላቻ ኖሮኝ አያውቅም፤ ዛሬም ፈጽሞ የለኝም። እርስዎ ተከላካዩ የሆኑለትን ኢትዮጵያ ላይ የተጫነ አፓርታይድ መሳይ ዘረኛ የአገዛዝ ሥርዓት ግን እርግጥ አልወደውም። ሥርዓቱ “ተጣሟልና” ይቃና የሚባል ሳይሆን በመሠረቱ፣ ከነሕገ መንግሥቱ፣ በጥልቅ የተዛባ ስለሆነ መለውጥ ያለበት እንደሆነ አምናለሁ።
በቅጡ ያልተረዱት አስተሳሰብ ላይ ግርድፍ ውንጀላና ወቀሳ በጅምላም ይሁን በችርቻሮ ማዥጎድጎድዎ ማንንም አይጠቅምም። ጽሑፌ “በቀል እና ጥላቻ የወለደው እንጂ፣ በእውነት ለኢትዮጵያም ሆነ ለአማራው ሰፊ ሕዝብ በመቆርቆር አለመሆኑን” ማሳየት የሚያስችልዎት አይደለም። ለመሆኑ ምን ሙያዊ ግንዛቤ ኖሮዎት ወይም ሰብአዊ ከፍታ ላይ ቆመው ነው የኔን ለሕዝቤና አገሬ ተቆርቋሪ አለመሆን ለማወቅ የበቁት?