spot_img
Wednesday, March 22, 2023
Homeነፃ አስተያየትበጎጠኝነት ኢትዮጵያን ማዳን አይቻልም። ምላሽ ለአቶ ተስፋዬ ደምመላሽ፤ ኡመር ሽፋው፤ ዶ/ር ፈቃዱ፤ በቀለ...

በጎጠኝነት ኢትዮጵያን ማዳን አይቻልም። ምላሽ ለአቶ ተስፋዬ ደምመላሽ፤ ኡመር ሽፋው፤ ዶ/ር ፈቃዱ፤ በቀለ እና ሌሎችም

- Advertisement -

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ  
ሚያዚያ 30 2014 ዓ.ም.

Politics that’s based solely on a tribe and ethnicity is politics that’s doomed to tear a country apart, it is a failure, a failure of imagination.” Barack Obama

ይህንን ጽሁፍ እንድፍ ያነሳሳኝ፤ ሰሞኑን በቦርከና ድሕረ ገጽ ላይ የተፃፉ የተለያዩ ጽሁፎችን በማንበቤና፤ በተለይም ደግም የአማራው ራስና አገር አድን ትግልዘላቂ ስልታዊ ንቅናቄ እንዴት?” በሚል ርእስ በአቶ ተስፋዬ ደምመላሽ፤የኢዜማ መኢሶናዊ ጉዞበሚል ርዕስ በአቶ ኡመር ሽፋው፤ እንዲሁም / ፈቃዱ በቀለ ኋላቀር አስተሳሰብ ባላቸውና በአረመኔዎች የሚመራ ምስኪን ህዝብና አገር!በሚሉ ርዕሶች የታተሙት መጣጥፎች ናቸው።እነዚህ ሦስት መጣጥፎች የተለያየ ርዕስ ኖሯቸው በሶስት የተለያዩ ሰዎች ይፃፉ እንጂ፤ መንፈሳቸውም፤ ይዘታቸውም፤ መልዕክታቸውም ተመሳሳይ ነው።  

ሶስቱም ፀሃፊዎች፤ ምንም ጭብጥ የሌላቸው፤ የጽሁፋቸው ርዕስ፤ ከጽሁፋችው አጠቃላይ መልዕክት ጋር ምንም ግንኙነት የሌለው፤ ዛሬ ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ፍፁም ያላገናዘበ፤ ጎጠኝነትን የሚያራግብና በጭብጥ ጠኔ የተጠቃ መሆኑ ደግሞ አሳዛኝ ብቻ ሳይሆን አደገኛም ያደርገዋል። ሌላውን ለማስተማርም ሆነ፤ ሃገር ከተደቀነባት አደጋ፤ ሃሳቡን በቅንነት ለሕብረተሰብ የሚያጋራ ማንም ቀለም የቆጠረ ሰው፤ ቢያንስ ጽህፎቹ፤ ከስሜት የፀዱ፤ በመረጃ የተደገፉ እና ተገቢ መፍትሔን የሚጠቁሙ ሊሆኑ ይገባል እንጂ፤ አንዱን የበኩር ልጅ፤ ሌላውን ደግም፤የእንግዴ ልጅአድርገው የሚያዩበት የተንሸዋረረ መነጽራቸው፤ የሚመራን ወደ የማያባራ የእርስ በእርስ ግጭት እንጂ ወደ መፍትሔም አይሆንም። እነዚህን ከላይ የጠቀስኳቸውን መጣጥፎች፤ በሃሳብ ለመሞገት፤ ጽሁፌን በሁለት ክፍሎች ከፍየወላሁ። በመጀመሪያ፤ የአቶ ተስፋዬ ደምመላሽ ጽሁፍ ላይ አስተያየት እንድሰጥ ይፈቀደልኝና፤ ሌሎቹን ሁለት ጽሁፎች ደግሞ ላይ ያለኝን አስተያየት አስከትላለሁ። 

አቶ ተስፋዬ ደምመላሽ፤ የአማራው ራስና አገር አድን ትግልዘላቂ ስልታዊ ንቅናቄ እንዴት?” በሚል ጽሁፋቸው አማራውእራሱንም ሆነ ኢትዮጵያን እንዴት እንደሚያድንም ሆነ ዘላቂ ስልታዊ ንቅናቄ የሚሉት ምን እንደሆነ፤ በጽሁፋቸው ያስቀመጡት አቅጣጫም ሆነ ትንታኔ አለመኖሩ፤ ርዕሳቸው ጩኸት ለመጨመር የታሰበ መሆኑን ያሳብቅባቸዋል። 

እኝህ ፀሃፊ ሲጀምሩ፤እንደሚታወቀው፣ ከአብዮቱ ዘመን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ አማራው በማኅበረሰባዊና አገራዊ ህልወናው ከተለያዩ የውስጥም የውጭም ጠላቶች ለከባድ የርዕዮት፣ የስነልቦና፣ የፖለቲካ፣ የአገዛዝ እና የአሸባሪ ኃይል ጥቃት ኢላማ እንደሆነ አለ። ጥቃቱን ዛሬ ወራሪ የኦነግና ወያኔ ኃይሎች በአብይ ሙልጭልጭ አገዛዝ ይሁንታም ሴረኛ ተባባሪነትም ከመቸውም ጊዜ ይበልጥ ጨፍጫፊ፣ አውዳሚና ቀውስ ፈጣሪ አድርገው ቀጥለውበታል።” ይሉናል። 

“የኢትዮጵያን አብዮት” አመራር፤ ዘር ተኮር ያልነበረና፤ ሃገሪቱን በመደብ የከፋፈለ እንደነበር፤ የኖርንበትና ያለፍንበት ታሪክ ነውና፤ አቶ ተስፋዬ፤ ከአብዮቱ ጀምሮ “አማራው” ላይ ጥቃት ደርሷል ሲሉ፤ ሌላው ማህበረሰብ አልተጠቃም ለማለት ነው፤ ወይስ፤ የሌላው ሞትና ስቃይ ከቁጥር አለገባላቸው ይሆን ወይ ያሰኛል። አብዮቱን ይመራው የነበረው ወታደራዊ አገዛዝ፤ ተራማጅና አብዮታዊ ከሚለው የሕብረተሰብ ክፍል ውጪ፤ ያላሰረው፤ ያላጠቃውና ያልገደለው፤ የኅብረተሰብ ክፍልስ አለ ወይ ብሎም መጠየቅም ተገቢ ነው።  በአማራው ሕዝብ ላይ ከፍተኛ በደልና ግፍ ተፈጽሟል፤ ግን ግፉ በአማራው ሕዝብ ላይ ብቻ አልነበረም። 

ደርግ ከሥልጣን ተወግዶ፤ ሕወሃት፤ የገዥነቱን ቦታ ሲረከብ፤ ጫካ ውስጥ ከነበረበት ጊዜ ጀምሮ፤ በአማራ ሕዝብ ላይ የነበረውን ጥላቻ፤ በመንግሥት ፖሊሲ ነድፎ፤ በአማራው ሕዝብ ላይ ከፍተኛ ግፍ ፈጽሟል፤ በተለይም በመጀመሪያ 3 የግዛት ዓመቱ፤ ሌላው ብሔር አማራውን እንዲያጠቃ በመገናኛ ብዙሃን ጭምር ሲስብክና፤ በወቅቱ ሥልጣን ላይ የነበሩ፤ የአማራ ተወካይ ነን ባዮች ሳይቀሩ፤ ሌላው ብሔረሰብ በአማራው ሕዝብ ላይ እንዲነሳ ከፍተኛም ቅስቀሳ ሲያደርጉና አማራውን ሲያስጠቁ ነበር። ሆኖም፤ በተለይ ከሰኔ 1984 ኦነግ እራሱን ከሽግግር መንግሥት ካገለለ በኋላ፤ ወያኔ በኦሮሞውም ብሄር ላይ ከፍተኛ ግፍና በደል ፈጽሟል። በወያኔ አገዛዝ፤ እስር ቤቱ “ኦሮሞ፤ ኦሮሞ ይሸታል” ይባል እንደነበርም የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው። ከዚህም አልፎ፤ በወላይታ፤ በጋምቤላ፤ በሶማሌና ሌሎች ብሔሮች ላይም ከፍተኛ ግፍና በደል ተፈጽሟል። 

የአማራው ሕዝባችን ላይም ሆነ ሌሎች ላይ ጥቃት ሲፈፀም፤ ጮኸናል፤ እንደ የአቅማችን ደግሞ በምንችለው ታግለናል። እንደማንኛውም ሌላው የኢትዮጵያ ብሄር፤ የአማራም ሕዝብ እጣ ፈንታው እንደ ሌሎች ወንድሞቹ እና ከሌሎች ወንድምና እህቶቹ ጋር እንጂ፤ “አማራን ለብቻ በጎጥ አደራጅቶ አማራንና ኢትዮጵያን እናድን” የሚል ወኃ የማይቋጥር እይታ፤ በሃገር ላይ ሌላ ነውጥ በመፍጠር፤ ዐብይን የሚጠሉ ኃይሎች፤ ዐብይን ከሥልጣን አስወግደን፤ እኛ የምንፈልገውን የፖለቲካ ኃይል ወደ ሥልጣን እናመጣለን የሚል ቅዠታቸውን ለማሳካት የሚጭሩት እሳት ነው። 

የአማራው ሕዝብ፤ ወያኔ በቀደደልን፤ ኋላቀር አስተሳሰብ ተተብትቦ “በልሂቃኑ” መሃከል ያለን ሹክቻ፤ በሕዝቡ ውስጥ ዘልቆ እንዲገባ ለማድረግ የሚደረግ ጉትጎታ፤ ለአማራው ሕዝብ እንዲሁም ለኢትዮጵያ ከማሰብ የሚመነጭ አይደለም። ይህ ቢሆንማ፤ የዚህ ዓይነት ድንክዬ አስተሳሰብ አራጋቢዎች፤ መላውን ኢትዮጵያዊ ለማስተባበር ተግተው በሰሩ ነበር። አማራው ሕዝብ ላይ የሚደርስ ጥቃት ሁላችንም ላይ የሚደርስ ጥቃት ነው። ይህንን ለመመከትም በርካታ ኢትዮጵያውያን መስዋዕትነት ከፍለዋል፤ አሁንም እየከፈሉ ነው። እነ አቶ ተስፋዬ የሚያቀነቅኑት ጎጠኝነት፤ ይህንን መስዋዕትነት ዝቅ የሚያደርግ ነው። የአቶ ተስፋዬ ጽሁፍ ለአማራው በማሰብ ሳይሆን፤ አብይ ላይ ያነጣጠረ ለመሆኑ፤ ርቆ መሄድ አያስፈልግም። 

አቶ ተስፋዬ ያለምንም መረጃ እና ምንም ዓይነት ለናሙና የሚሆን ምሳሌ እንኳ ሳያነሱ፤ “ጥቃቱን ዛሬ ወራሪ የኦነግና ወያኔ ኃይሎች በአብይ ሙልጭልጭ አገዛዝ ይሁንታም ሴረኛ ተባባሪነትም ከመቸውም ጊዜ ይበልጥ ጨፍጫፊ፣ አውዳሚና ቀውስ ፈጣሪ አድርገው ቀጥለውበታል።” ይሉናል (ድምቀትና ሰረዝ የተጨመረ። አንድ ሌላውን “አስተምራለሁ” በሚል ስሜት ጽሁፍ የሚያወጣ ሰው ቢያንስ “ሙልጭልጭ ባሕሪም ሆነ ሴረኛ ተባባሪነት” ለሚል ውንጀላ ምሣሌና መረጃ መስጠት መቻል አለበት። ተማርኩ የሚል ሰው፤ ከሌላው የሚለየው፤ በአሉባልታ የምሰማውን በአደባባይ ከማንፀባረቅ ይልቅ፤ በመረጃ የተደገፈ ሃሳብ ሲያቀርብ ነው። በነገሬ ላይ፤ “አብይ አማራ ጠል ነው” ብለው የሚሰብኩን ሰዎች፤ ዶ/ር ዐብይ በከፊል አማራ መሆኑን እንዲሁም አማራ ሚስት እንዳላቸውና ከአማራ አብራክ የወጡ ልጆች እንዳላቸው እያወቁ መሆኑ፤ እንዲህ ዓይነት ወኃ የማያቋርጥ ክስ የሚሰነዝሩ ሰዎች፤ ጎጠኞቹ እነሱ እንደሆኑ እንደሚያሳብቅባቸው አለመረዳታቸው ነው። 

በተደጋጋሚ፤ በተለያዩ መድረኮች እንደገለፅኩት፤ ዶ/ር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ ትልቁ የሰሩት ሥራ ክ40 ዓመታታ በላይ የተሸረሸረውን የኢትዮጵያዊነት ሥነ ልቦና መገንባት ላይ ነው። ዶ/ር ዐብይ፤ የሚወቀሱባቸው ነገሮች አሉ፤ ብሔርተኝነት ግን አንዱ አይደለም። ለረጅም ጊዜ ወዳጅ ከሆኑዋቸው የትግል አጋራቸው ከነበሩት ከአቶ ለማ መገርሣ ጋር የተለያዩበት ዋናው ምክንያት፤ ዶ/ር ዐብይ ኢትዮጵያዊነት መቅደም አለበት በማለታቸውና አቶ ለማ ደግሞ፤ መጀመሪያ ኦሮሞን እናጠናክር በማለታቸው ለመሆኑ፤ የአቶ ለማ መገርሳ ለአሜሪካ ድምጽ ሪርድዮ ከሰጡት ቃለ ምልልስ ሌላ በቂ መረጃ ሊኖር አይችልም። ግንባር ድረስ ሄዶ ሰራዊቱ የሚበላውን በልቶና፤ ሰራዊቱ የሆነውን ሆኖ፤ ከወያኔ ጋር በግልጽ የተፋለመን ሰው፤ ከወያኔ ጋር ተባባሪ ነው ብሎ መክሰስ ያስኬዳል ወይ?

አቶ ተስፋዬ “ዘርፈ ብዙውን ጥቃት መከላከልና ማምከን ማለት የአማራውን የመነመነና እየታመሰ ያለ ህልውና እንዳለ ከጥፋት ማትረፍ ሳይሆን መልሶ ማዳበር፣ ማረጋጋት፣ ማጠናከርና እንደገና እንዲያብብ ማድረግ ነው የሚሆነው። በጥልቅ ዕቅድና ዘዴ የአማራን የመኖር አለመኖር ትግል ዘላቂ አቅጣጫ ማስያዝ ማለት ነው።” ይላሉ፤ ይህ ዓይነት አስተሳሰብ፤ በብሔርተኝነት የተደራጁ የፖለቲካ ኃይሎች ሁሌም የሚያቀነቅኑት ሃሳብ ነው። ለዓመታት የተለያዩ ብሔር ተኮር ድርጅቶች ሲያነሱት ለነበረው ጥያቄ፤ መፍትሔው ችግሮችን በኢትዮጵያዊነት መፍታት ነው እያልን ለዓመታት ጮኸናል። ሁሉም የራሱ ተገቢም ሆነ ያልሆነ ቅሬታ አለው። ማንንም፤ ለምን ቅሬታ ተሰማህ ማለት አይቻልም። ሁሉም የሚሰማውን ቅሬታም ሆነ “በብሔሬ” ላይ ጥቃት ተፈፀመ ሲል የሚያነሳውን ስሞታ፤ በጥሞና ማዳመጥና፤ ለዚህም መፍትሔ መፈለግ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ነው። አሁን የተቋቋመው የእርቅ ኮምሽን ሥራው ይህ ይመስለኛል። የኦሮሞ ሕዝብ አለኝ የሚለውን ጥያቄ መፍታት የሚቻለው በኢትይጵያ እቀፍ  (context) እንጂ፤ ለብቻው የተለየ የሚያበጀው መፍትሔ የለም፤ የአማራውም፤ የትግራዩ፤ አፋሩም ሆነ ሌላው፤ ዘላቂ መፍትሔ ሊያገኝ ይሚችለው፤ ሁሉን ኢትዮጵያው አቀፍ በሆነ የመፍትሔ ሃሳብ ነው። ይህንን ከኤርትራ መማር እንኳን ይቻላል። የብሔር አቀንቃኞች፤ በየራሳቸው “ክልል” ትንንሽ ነገሰታትን ከመፍጠር ውጪ፤ ለሕዝብ የሚያመጡት ምንም ፋይዳ እንደሌለ፤ ከራሳችን ታሪክ መማር እንችላለን። አቶ ተስፋዬ ያላስተዋሉት ነገር ወይም አስተውለው የገደፉት ነገር፤ የአማራው ሕዝብ ለብቻው፤ ኢትዮጵያንም ሆነ እራሱን ማዳን እንደማይችል ነው። ምክንያቱም፤ ሁሉም “ለራሴ” በሚል ደዌ ከታመመ፤ ከግጭት አዙሪት ልንወጣ አንችልም። የእነዩጎዝላቪያ ታሪክም የሚያስተምረን ይህንኑ ነው። 

አቶ ተስፋዬ “ስልትና የጉዳዮች አቀራረብ ደረጃዎች፥  በሚል ንዑስ ርዕስ ሥር “አማራው ማኅበራዊ ህልውናውን፣ ባህሉን፣ መንፈሳዊ ሕይወቱንና ዓለማዊ ኑሮውን ከዘረኞች ጥቃት ለመከላከል ሲንቀሳቅስ ደረጃው ከፍ ወዳለ አገር አቀፍ ስልታዊ ትግል የሚዘልቅበት አንዱ ዋና መንገድ የራሱንና የአገሩን ብርቱ ጉዳዮች አቀራረጹን በሃስብና ገቢር በማጥራት፣ በማሻሻልና በማጠናከር ነው። ሁለት የተለያዩ ግን የሚመጋገቡ የቀረጻ ደርጃዎችን መጠቆም እንችላለን።” (ድምቀት የተጨመረ)። አንድ በበሔር የተደራጀ ኃይል፤ እንዴት ነው ስለአገሩ ብርቱ ጉዳዮች ሊያስብ የሚችለው? በብሔር እደራጃለሁ የሚልበት ምክንያት እኮ ከሌሎች ብሔሮች ጋር የሚያጋጨኝ ጥቅም አለ፤ ሌሎች ብሔሮች እያጠቁኝ ነው ከሚል እሳቤ ነው የሚደራጀው፤ የሥልጣን ባለቤት ሲሆንም፤ የሚያስቀድመው የራሱን ብሔር ነው፤ ለዚህም አዲስ አይደለንም፤ አሁንም እዚህ ምስቅልቅል ውስጥ የከተተን፤ እንዲህ ዓይነት ኋላ የቀረ አስተሳሰብ አይደለም ወይ? በቅርቡ ጄነራል ተፈራ ማሞ በሰጡት አንድ ቃለ ምልልስ ላይ የሰጡት አስተያየት፤ የአቶ ተስፋዬ ደምመላሽን ደካማ አስተሳሰብ የሚጋራ ነው። ጄነራሉ ሲናገሩ፤ “አማራው ሲዋጋ፤ ለኢትዮጵያ እያሰበ ነው” የሚል አንድምታ ያለው ጎጠኛ አስተሳሰብ አንፀባርቅዋል። ሌላው ሲዋጋ ማንን እያስበ ነው? ድንበር ላይ እየሞተ ያለው አፋር፤ ሶማሌ፤ ሲዳማ፤ ኦሮሞ ወዘተ፤ ከክልሉ ተሻግሮ መጥቶ የአማራ ክልል ውስጥ እየሞተ ያለው ማንን እያሰበ ነው?  እንዲህ ዓይነት፤ ‘እኔ የበኩር ልጅ ነኝ፤ ሌላ ግን “የእንግዴ ልጅ” ነው’ የሚል ጽንፈኛ አስተሳሰብ መሰረት የለሽ መሆኑ ብቻ ሳይሆን፤ በውስጣችን መርዝ በመርጨት የሚያተራምሰን ነው። በተሳሳት እይታ እንዲህ ዓይነት አስተሳሰብ የሚያራምዱ ሰዎች ቆም ብለው ሊያስቡ ይገባል።  

አቶ ተስፋዬ ሲቀጡል እንዲህ ይሉናል፤ “አንደኛው፣ አማራው አፋጣኝ መልሶች እንዲሰጥና አስቸኳይ እርምጃዎች እንዲወስድ የሚያስገድዱትን ተለዋዋጭ ኩነቶች፣ ሁኔታዎችና ጥቃቶች የሚገጥምበት ደረጃ ነው። ሰሞኑን በጎንደርና በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች ቤተ ክርስቲያናትን የማጋዬት ጥቃቶች በዚህ እርከን የሚከሰቱ ፈተናዎች ምሳሌዎች ናቸው። እነዚህ የአጭርና መካከለኛ ጊዜ ጉዳዮች በአንጻር ራሳቸውን ችለው የሚታዩና የተመጣጠነ ወቅታዊም አካባባዊም ምላሽ የሚፈልጉ ናቸው።” አቶ ተስፋዬ፤ አማራው ምን ዓይነት አፋጣኝ መልሶች እንዲሰጥና ምን ዓይነት እርምጃዎች እንዲወሰድ እየመከሩ እንደሆነ አልጠቆሙንም፤ የሰነዘሩት ጥቅል ሃሳብ በመሆኑ፤ እሳቸውን ሆኖ መናገር አይቻልም፤ ሆኖም ስለጎንደር ቤተ ክርስቲያን መጋየት ሲነግሩን፤ ስለተቃጠሉት መስጊዶችም ሆነ፤ በጎንደር በሙስሊሙ ማህበረሰብ ላይ የተፈፀመውንም ግድያም ሆነ ንብረት ውድመት አለመግለፃቸው፤ የልባቸውን መስኮት ወለል አድርጎ አሳይቷል ለማለት ይቻላል። በየትኛውም የሃይማኖት ተቋማት ላይ የሚደረግ ጥቃት፤ በሁላችንም ሊወገዝ ይገባዋል። ሃይማኖት እና ብሔር እየመረጥን፤ ሳይሆን፤ ሁሌም አጥቂዎችን ማውገዝና ከተጠቂው ጎን መቆም ከኢትዮጵያዊነት የሚጠበቅ ብቻ ሳይሆን፤ ሰዋዊ አመለካከትም ነው። 

አቶ ተስፋዬ ያነሷቸው፤ አማራውን ጎጠኛ በማድረግ ሃገራዊ መፍትሔ ያመጣሉ ያሏቸው “ሃሳቦች” በተለያዩ ጽንፈኛ ኃይሎች በየማህበራዊ ሚድያው የሚንሸራሸር ወኃ የማይቆጥር ሃሳብ ለመሆኑ፤ መጣጥፉን ያነበበ ይረዳል ብዬ አምናለሁ። የአቶ ተስፋዬ ሃሳብ ያነጣጠርው፤ የዐብይ “ኦሮሞነት” ላይ ለመሆኑ፤ ችግሩ የአቶ ተስፋዬ የራሳቸው ጎጠኝነት አስተሳሰብ እንደሆነም ጽሁፋቸው ያሳብቃል። አቶ ተስፋዬ፤ ዶ/ር ዐብይን ለመግለጽ የሚጠቀሙባቸው የተለያዩ ሃሳቦች፤ በመረጃ ያልተደገፉ ብቻ ሳይሆኑ፤ ተራ አሉባልታ መሆናቸውንም አንባቢ በቀላሉ ሊረዳ ይችላል።

አቶ ተስፋዬ፡  ከጥቂት ዓመታት በፊት ከአገር ገዢነት የተባረረውን ወያኔን ተክቶ መንግሥትን ዛሬ እንደነገሩ የሚቆጣጠረው ኦነጋዊ ወገን ሃሳቦች ላይ ተጽዕኖ ሊያሳርፍ የሚችለው በቀጥታ ግርድፍ፣ አፋኝ፣ አምባገነናዊ ኃይል በመጠቀምና ሴረኛ የፖለቲካ ቁማር በመጫወት ብቻ ነው። ሁሉ ነገር የኔ ነው ባዩ ስግብግብ ተረኛ ገዢ ወገን አገር ወዳድ ወገኖችን፣ ምሁራንን፣ ጋዜጠኞችንና ዜጎችን በቅጡ የሚያሳትፍ ምክንያታዊ ክርክሮችና የሃሳቦች ልውውጥ ማድረግ ፈቃደኝነቱም ሆነ ችሎታው የለውም።” (ድምቀት የተጨመረ) ይሉናል። መረጃው ምንድነው? ሃቁ፤ በሥልጣን ላይ ያለው መንግሥት በየወቅቱ፤ በሃገር ጉዳይ ያገባናል ከሚሉ የተለያዩ የሕብረተሰብ አካላት ጋር፤ ከዚህ በፊት አይተን በማናውቀው ሁኔታ ከምሁራንም፤ ከጋዜጠኞችም፤ የሃይማኖት አባቶችም ሆኑ ሌሎች አካላት ጋር ውይይት እያደረገ ነው። ይህንን እንዴት መካድ ይቻላላል?  የዶ/ር አብይንስ አስተዳደር “ኦነጋዊ” የሚያደርገው ኦሮሞ በመሆናቸው ነው? ለመሆኑ፤ አቶ ተስፋዬ በኦነግና በዶ/ር ዐብይ መካከል ያለውን ሰፊ ልዩነት ጠንቀቀው ያውቃሉ? የዶ/ር ዐብይ አስተዳደርስ ኦነጋዊ የሚያደርገው ምንድነው? ስለ ኢትዮጵያዊነት ማቀነቀን ከመቼ ወዲህ ነው ኦነጋዊ የሆነው? ወይንስ የኦነግን ስም በማንሳት ሃሳቤ ገዥ ያገኛል በሚል ስሜት የተጫረ ነው? ስለ ዶ/ር ዐብይ ሴራ እስቲ አቶ ተስፋዬ አንድ ምሳሌ፤ አንድ መረጃ ይስጡን። እስቲ አፋኝ እና አምባገነናዊ ለሚሉት ክስ አንድ መረጃ ያቅርቡ። 

ለመሆኑ፤ ዶ/ር ዐብይ ወደ ሥልጣን ሲመጡ፤ የሃገሪቱ አቅም ምን እንደነበረ የጠየቀ ሰው አለ? የሃገሪቱ ወታደርዊ ሃይል፤ የደህንነቱ፤ የፖሊስ፤እንዲሁም የሃገሪቱ አጠቃላይ ግብአት (Resource) ምን ደረጃ ላይ እንደነበር የጠየቀ አለ? በሃገሪቱ ዶላር የሚባል ነገር እኮ አልነበረንም፤ እረሳነው እንዴ? ያንን ክፍተት ለመሸፈን፤ እነ አረብ ኢምሪት፤ ሳውዲ አረብያና ሌሎችም እኮ ተለምነው ነው፤ የውጪ ምንዛሪ የተገኘው። ለመሆኑ የወታደሩን አቅም ጠይቀናል። በወታደሩ ውስጥ የነበሩ አመራሮችም ሆኑ ወታደሮች እኮ 60% የሕወሃት የነበሩ ናቸው። ከሕወሃት ጋር ጦርነት ሲጀመር እኮ የኢትዮጵያ ሠራዊት 40 ሺህ ብቻ እንደነበር ጄነራል አበባው ከጥቂት ወራት በፊት ገልፀዋል። የሃገሪቱ መረጃና ስለላ ድርጅት እኮ ባዶ ሆኖ ነው ዶ/ር አብይ የተረከቡት። የሃገሪቱ 80% የጦር መሣሪያ እኮ በሕወሃት ቁጥጥር ሥር ነበር፤ ፖሊሱስ በብዛት ማን ነበር? ዶ/ር ዐብይ ወደ ሥልጣን ሲመጡ እኮ ገደል አፋፍ ላይ የነበረች ሃገር ነው የተረከቡት። ይህን እንዴት እንረሳለን? “በሽተኛ ሲድን፤ እግዚአብሔርን ይረሳል” ይባላል። ሃገር መገንባት ማለት ሃገራዊ ተቋማትን መገንባት ማለት መሆኑ እነ አቶ ተስፋዬ ይገባቸው ይሆን? የመጀመሪያው የሁለት ዓመት የዶ/ር ዐብይ አስተዳደር እኮ በወያኔ ባለሥልጣናት ተንኮል ሲታመስ የነበረ ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት የተገነቡትን ወታደራዊ፤ የመረጃና የሕግ አስከባሪ ተቋማትን አስተውለናል? ያለማጋናን በሌላ ሃገር ወደ አስር ዓመታት የሚፈጅ ሥራ ነው ከሦስት ዓመታት ባነሰ ጊዜ ውስጥ የተሰራው። የእንዱስትሪው፤ እርሻው እና አገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ለማጠናከር፤ በዚህ ሁሉ ነውጥ ውስጥ በመንግሥት በኩል የተሰሩ መሰረተ ልማቶች፤ ተቋርጠው የነበሩ የተለያዩ መንግሥታዊ ፕሮጀክቶች (ሕዳሴ ግድቡን ጨምሮ)፤ በምን ዓይነት ፍጥነት እያለቁ መሆናቸው ነጋሪ ያሻዋል እንዴ? ዶ/ር ዐብይ የአዲስ አበባን መሰተዳደር የጠየቁትን እዚህ ላይ መልሼ ልጠይቅ። አዲስ አበባ መብራት የሚያገኘው በፈረቃ ነበር፤ አሁን ግን ያ ፈረቃ የለም፤ ለምን ብሎ የጠየቀ አለ? ለነ አቶ ተስፋዬ ቢዋጥም ባይዋጥም፤ ሃቁ፤ የዶ/ር ዐብይ አስተዳደር፤ በምርጫ በሕዝብ አዎንታ ሥልጣን የተረከበ ነው፤ ምኑ ነው አምባገነናዊ የሚያደርገው?

 አቶ ተስፋዬ “ገዥው የኦነግ ፓርቲ እንግዲህ በሃሳብም ሆነ በገቢር ኢትዮጵያን መሪ ለመሆን ፈቃደኝነትና ብቃት ብቻ ሳይሆን ቁመናም እንደሌለው አሳይቷል።” ይሉናል፤ ለመሆኑ፤ አቶ ተስፋዬ በምናባቸው የሚያዩት እየገዛ ያለው “የኦነግ ፓርቲ” እንዴት የኦነጉን መሪ ዳውድ ኢብሳን በቤት ውስጥ እስሮ ለወራት እንዳቆያ ያስረዱን፤ ወይስ ኦሮሞነት ያለበት ሁሉ “ኦነግ” ነው ከሚል ጽንፈኛና ደካማ አስተሳሰብ የመነጨ ክስ ነው? እንደ አቶ ተስፋዬ ያሉ፤ ዳር ሆነው እሳት ለኩሰው እሳቱን የማይሞቁ ሰዎች፤ ከልብ ለሃገራቸው መስራት ከፈለጉ፤ ጊዜው አሁን ነው። እንኳን እንደ ኢትዮያ ዓይነት ውስብስብ ችግር ያለባት ሃገር ይቅርና፤ አንድ ቤተሰብ ማሰተዳደር ፈተና ነው። የሃገራችን ችግር በመከፋፈል፤ አማራውን በጎጥ በማደራጀት፤ ወይም በአንድ ሰው፤ በአንድ ትውልድ አይፈታም። ይህንን በመገንዘብ፤ አንድነታችን ላይ መስራት እና፤ በምንችለው ሁሉ በማገዝ፤ የሕዝባችንን ችግር እናቃልል። ሁሉም የአቅሙን እንዲያደርግ፤ የሃገር ጥሪ አለ፤ ጣት ከመጠቆም፤ በጎደለው እንሙላ፤፡ የተሻለ አመራር እንሰጣለን አቅም አለን የሚሉ ሰዎች፤ ከመሰሎቻቻው ጋር ይደራጁ፤ ሃገር ለመምራት የሕዝብን አዎንታ ለማግኘት ደግሞ በፖለቲካ መድረኩ ይሳተፉ እንጂ አማራውን ከሌላው ለይተን ኢትዮጵያን እናድናል የሚል ቅዠት ጥፋት እንጂ፤ ላለብን የተወሳሰብ ችግር መፍትሔ ሊሆን አይችልም። በተንሸዋረረ የዘር መነጽር እያየን፤ ጥላቻ በመረዘው አመለካከት፤ ለኢትዮጵያ በጎ ራዕይ ሊኖረን አይችልም። 

 (ክፍል ሁለት ይቀጥላል)

__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com     

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,440FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

4 COMMENTS

  1. እናመሰግናለን ጥበበ ሁኔታዋችን እንዲ በሙላት አገርን ወደፊት በሚያራምድ መንገድ መተንተን ሲገባ አይናችሁን ጨፋኑና ላሞኛቹህ አይነት በሴራና በአሉባልታ የተሞላ ጽሁፋ ያቀረቡትን አቶ ተስፋዬን ሳይቀር ወደቀልባቸው የሚመልስ እይታ ነው

  2. የሰዎቹን ጽሁፍ አላየሁትም፡፡ቢሆንም ከዚህ የመልስ ጽሁፍ ይዘቱን ተረድቼዋለሁ፡፡ ከእነዛ ወገን ሲታይ የመማር ትርጉም ምን ይሆን ያሰኛል፡፡ ከዚህ ጽሁፍ አቅራቢ አንጻር ሲታይ ደግሞ የመማር ምንነት እና ጠቀሜታ በጉልህ ይታያል፡፡
    ዶ/ር አብይ ወደ ሥልጣን በመጡ ማግስት ባደረጉት የሀገር ውስጥ ጉብኝት ባህር ዳር ላይ ይመስለኛል እባካችሁ ምሁራን በየሙያችሁ ሰብሰብ እያላችሁ ሀሳብ አቅርቡልን ምከሩን ወዘተ ብለው ነበር፡፡እነዚህ ነቃፊ ሰዎች በግልም ሆነ በቡድን ያደረጉት ነገር ይኖር ይሆን፡፡
    ከየትኛው የኢትዮጵያ ብሄር ይባል ብሄረሰብ በላይ አንድነት የሚጠቅመው አማራውን ነው፡አማራ የሌለበት የሀገራችን ክፍል አለ ለማለት ይቸግራል፤በሌላ በኩል ደግሞ ስሙ አማራ ክልል ይባል እንጂ በክልሉ የሚኖሩ ብሄረሰቦች ብዙ ናቸው ፤ስለዚህ አማራው በያለበት በሰላም ለመኖርም ሆነ ብክልሉ ውስጥ ካሉት ሌሎች ብሄረሰቦች ጋር ለመኖር የሚያስችለው ልዩነትን በጌጥነት የሚያተናግድ አንድነት ነው፡፡
    ወያኔ በዘር ተደራጅታ በትግረኛ ተናጋሪው ተንጠላጥላ ነው ለቤተ መንግስት የበቃቸው የሚል አስተሳሰብ ከአለ ማስተዋል የጎደለው ነው፡፡ከእንግዲህ በኢትዮጵያ ከምርጫ ውጪ ሥልጣን ማለም ያውም አሜሪካ ተቀምጦ ዘመኑን ያለመዋጀት ነው፡፡

  3. ነገሮችን ከተባሉበት አውድ አውጥጦ አንባቢን በሚያሳስት መልክ ማቅረብ፡ የተለመደው የምሁራን ቅጥፈት ነው።
    ጅ. ተፈራ ‘አማራ ሲዋጋ ኢትዮጵያን እያሰበ ነው’፡ ማለት ሊሎች አያስቡም ማለት አይደለም። ደርግ አማራን ጨፍጭፏል ማለትም ሌላውን አልነካም ማለት እንዳልሆን አቶ ጥበበ እያወቀ ለምን ብዙ ሊተችበት ፈለገ?
    ለማንኛውም፡ ቢቀባቡት፡ ቢያሰማምሩት፡ ሊደበቅ የማይችል፡ ሳይለወጥ ከኢሕአዴግነት ወደ ብልጽግንናነት ያደገ ዘረኛ፡ ውሸታም፡ አድሎኛ፡ ኢትዮጵያ ጠል፡ አማራ ገዳይ፡ ኦርቶዶክስ የዋራጅ መንግሥት ለመኖሩ ፡ ኦሮሞ ክልል እስካለ ድረስ፡ ማስረጃ አቅርብ እንደማልባል እርግጠኛ መሆን እችላለሁ።
    በመጨረሻ፡ የአብይ እናት አማራ ናቸው፡ ያለው ልብወለድ ታሪክ ነው። ነገሩ የተምታታ ቢሆንም እስካሁን የሚታወቀው የሰውየው እናት የአምቦ ኦሮሞ ፡ ሃይማኖታቸው ኦርቶዶክስ፡በኋላ የሰለሙ መሆናቸው ነው። ፕሮ ገመቹ እንደቀባጠረው፡ ኦርቶዶክስ መሆን አማራ መሆን ካላልክ።

    ለማንኛውም፡ ምሁራን ሰው እያለቀ አላግጡ። ቱ!

  4. ይህ ጽሁፍ በቀላል ቌንቌ ለሁሉም በሚገባው መልኩ የቀረበ ነው:: በማስረጃም የተደገፈ ነው::

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here