spot_img
Thursday, May 30, 2024
Homeአበይት ዜናበአማራ ሕዝብ ላይ የሚካሄደውን ግፍና በደል በሚመለከት ከቪዥን ኢትዮጵያ የተሰጠ መግለጫ

በአማራ ሕዝብ ላይ የሚካሄደውን ግፍና በደል በሚመለከት ከቪዥን ኢትዮጵያ የተሰጠ መግለጫ

ግንቦት 13፣ 2014

ቪዥን ኢትዮጵያ (ራዕይ ለኢትዮጵያ)፣ ሰሞኑን በኢትዮጵያ ውስጥ፣ በተለይም በአማራው ሕዝብ ላይ፣ በጠቅላይ ሚንስትር አብይ አሕመድ መንግሥት እውቅና፣ እየተከሰቱ ያሉትን አስከፊ የግፍና የበደል እርምጃዎችን አጥብቆ ያወግዛል።

ምንም እንኳን አሁን እየተከሰቱ የሚታዩትን ዘር-ተኮር የወንጀል ድርጊቶች የራዕይ ለኢትዮጵያ ድርጅት በተደጋጋሚ ባወጣቸው ፅሁፎች ሲያስጠነቅቅ የቆየ ቢሆንም፣ በአሁኑ ሰዐት በሰላማዊ ዜጎች ላይ፣ ከመቸውም ጊዜ በከፋና በተቀነባበረ ሁኔታ በመተግበር ላይ ያለውን በደል፣ ማንኛውም ለፍትህ የቆመ ግለ-ሰብ፣ ወገን፣ ቡድን፣ መዋቅር ወይም አገር፣ በማያሻማ ሁኔታ ሊቃወመዉና ሊታገለው ይገባል ብለን በጽኑ እናምናለን::

ለ27 ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ ሲገድል፣ ሲያስር፣ ሲበዘብዝና ሲያሳድድ የቆዬው የወያኔ አረመኔአዊ አገዛዝ በኢትዮጵያ ሕዝብ አመፅ ከስልጣን ከተወገደበት ጊዜ ጀምሮ፣ የዐቢይ አሕመድ መንግሥት በዘረኛ አመለካከቱና ፍላጎቱ፥ በአገሪቱ ዙሪያ በአማራ ተወላጆችና ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖች ላይ በገፍ እየተፈፀሙ የነበሩትን ኢሰብአዊና አሰቃቂ ግድያዎችና ጅምላ የዘር-ፍጅት ድርጊቶች፣ እንዳላየ በማስመሰል፣ ለማስቆም አለመፈለጉን በተግባር ሲያሳይ ቆይቷል::

ከዚህም በባሰ ደረጃ፥ ያለጊዜውና ያለበቂ ምክንያት የመከላከያ ሀይሉን ለወያኔ በሚያመች መንገድ ከትግራይ በማስወጣት የአማራውንና የአፋሩን ህዝብ ለወያኔ የጥቃት ጦርነትና አሰቃቂ የጦርነት ወንጀሎች አጋልጦ ብዙ ከግምት ውጭ የሆኑ ሰብኣዊና ቁሳዊ ጉዳቶች በአማራና የአፋር ህብረተሰቦች ላይ እንዲደርሱ አድርጓል።

 ከዚያም አልፎ፣ ብዙ የሚዲያ አባላትን፣ የሰብአዊ መብት ታጋዮችንና ሌሎችን የተራኛነት አላማን ለማራመድ እንቅፋት ይሆናሉ ብሎ የገመታቸውን ግለ-ሰቦችና ቡድኖች፣ በእስራትና በማዋከብ ሲያሰቃይ ቆይቷል:: ቀደም ሲል በመዐዛ መሃመድ፥ ታምራት ነገራ፥ ጎበዜ ሲሳይና ታዲዎስ ታንቱ ላይ የተወሰዱትን፥ ዛሬ ደግሞ መስከረም አበራንና ሰለሞን ሹምዬን በመሳሰሉት ላይ እየተፈጸመ ያለውን ግፍ መጥቀስ ይቻላል። ይህ የሚዲያ ባለሙያዎች አፈናና የማሕበረ-ሰብ አንቂዎች ጥቃትና ማጎሳቆል፣ ዐላማውና ዉጤቱ ምን እንደሆነ ለማስገንዘብ ቪዥን ኢትዮጵያ ሲታገል ቆይቷል። 

ዛሬ እንዲህ በከፋ መልኩ አግጥጦ የወጣውና፣ በአማራውና በኦርቶዶክስ ክርሲቲያኖች ላይ የታወጅው የዐቢይ አሕመድ ጦርነት፣ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ሲታቀድበት የነበረው የኦሮሙማና የወያኔ ፕሮግራም መሆኑ ግልጽ ነው። የእነመስከረም አበራ አፈናና መታሰር፣ የዚሁ የታላቁ የኦሮሙማና የወያኔ ሴራ አካል ነው።

በአሁኑ ጊዜ፣ ሙሉና ይፋ ጦርነት በአማራው ህዝብ ላይ ታውጇል። የአማራ ልዩ ኅይል መሪ የነበረው ጀግናው ጀኔራል ተፈራ ማሞ ታፍኖ በባሕር-ዳር እስር ቤት እየተሰቃየ ይገኛል። የአማራ ፋኖ መሪዎች እየተሳደዱ፤ እንዲሁም የአማራ ፋኖዎች በያሉበት እየተከበቡ፥ እየታደኑና እየተገደሉ ይገኛሉ። ያልታጠቁና ለማንም ስጋት ያልሆኑ ንፁሃን ወጣቶች በጅምላ በጎጃም፣ በወሎ፣ በሽዋና በጎንደር በጠራራ ፀሀይ እየተረሽኑ ይገኛሉ። በአዲስ አበባ ከተማ፣ ወጣቶች በግፍና በጭካኔ እየተለቀሙና ባልታወቁ እስር ቤቶች እየታጎሩ ይገኛሉ።

 ስለዚህ፥ ቪዥን ኢትዮጵያ፥

  1. እነኝህ ጨካኝና ኢትዮጵያን አፍራሽ የሆኑትን የኦሮሙማንና የወያኔን አረመኔያዊ ተግባሮችን በሙሉ ልቡ ያለምንም ማወላወል ያወግዛል፥ ይታገላል። 
  1. በአማሮች ላይ የፍጅት ጦርነት የከፈተው የኦሮሙማ ልዩ ሃይልና አብረውት ያሉት አፋኝ ቡድኖች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከአማራ ክልል በአስችኳይ እንዲወጡ፣ ለሰላምና ፍትሕ ከቆሙ ወገኖች ጋር በመተባበር፣ ያለማቋረጥ ይታገላል።
  1. በተለይም፣ መምህርት መስከረም አበራ ያለምንም ቅድመ – ሁኔታ እንድትፈታና፣ ጨቅላ ልጇን ለማሳደግ እንድትበቃ፣ የሰብአዊ መብቶችን ለመጠበቅ ከቆሙ ድርጅቶች ጋር በመተባበር፣ ያለመትጋት ይታገላል።
  1. ሌሎች ያለህግ፣ በማን ኣለብኝነትና በትእቢት የታሰሩትና የተሰወሩት የሚዲያ ባለሙያዎች፥ የአዲስ አበባ ወጣቶችና ሌሎችም ንፁሃን ዜጎች በአስቸኳይ እንዲፈቱ የማያቋርጥ ጥረት ያደርጋል።
  1. መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፥ በተለይም በውጭና በአገር ውስጥ ያሉት የመብት ተቆርቋሪዎች፥ በሙሉ በአንድነትና በመተባበር፣ ይህንን በኢትዮጵያ ህልውና ላይ የመጣውን አደጋ ለመግታትና ለማሸነፍ፣ በጋራ እንዲቆሙና እንዲታገሉ ጥሪ ያቀርባል።
  1. በመጨረሻም፣ የአማራ ብልጽግና በሚል ስያሜ የሚታዎቀው የአብይ አሕመድ ጸረ-አማራ አጀንዳ አስፈጻሚና ተባባሪ ቡድን፣ በታሪክም ሆነ በሀግ ተጠያቂነቱን ተገንዝቦ፣ ክዚህ የወንጀል ተግባር እንዲቆጠብና፣ የአማራ ወገኑን ከተደቀነበት አደጋ ለማዳን በሚደረገው ጥረት ተሳታፊ እንዲሆን ጥብቅ ጥሪ እናቀርባለን። 

ድል ለተበደለ ሕዝብ

ቪዝን ኢትዮጵያ (ራዕይ ለኢትዮጵያ)

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here