spot_img
Wednesday, May 29, 2024
Homeነፃ አስተያየትበጎጠኝነት ኢትዮጵያን ማዳን አይቻልም። (ክፍል 2)

በጎጠኝነት ኢትዮጵያን ማዳን አይቻልም። (ክፍል 2)

ምላሽ ለአቶ ተስፋዬ ደምመላሽ፤ ኡመር ሽፋው፤ ዶ/ር ፈቃዱ፤ በቀለ እና ሌሎችም (ክፍል 2)
ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
ግንቦት 15 2014 ዓ. ም.

በመጀመሪያው ክፍል፤ የአቶ ተስፋዬ ደምመላሽን ጽሁፍ እያጣቀስኩ፤ የመልዕክታቸውን አደገኛነት ለማሳየት ሞክርያለሁ፤ ዛሬ ደግም ክፍል ሁለትን ለማቅረብ ይፈቀድልኝ። በዚህ አጋጣሚ ጽሁፌ ሌላ የመጨረሻ ክፍል እንደሚኖረው በትህትና እገልፃለሁ።

አቶ ተስፋዬ በጽሁፋቸው እንዲህ ይላሉ፤  “በኢትዮጵያ የተንሰራፋውን የጎሣ አገዛዝ መዋቅራዊ ሙጃ ከስራስሩ ለመመንገል ብቻ ሳይሆን የሚተካውን የተሻለ፣ ዜግነትን ያማከለ፣ የፍትሐዊ ሥርዓት ሰብል ዘርቶ ለማምረት አማራው በሃስቦች መስክ በብልኃት ጠለቅ ብሎ ገብቶ መንቀሳቀሱ ወሳኝ ነው።”  በእሳቸው አመለካከት፤ በኢትዮጵያ የተንሰራፋውን “በኦሮሞ” እየተመራ ያለውን የጎሣ አገዛዝ፤ “በአማራ” በተመራ የጎሣ አገዛዝ በመቀየር፤ “የፍትሐዊ ሥርዓት ሰብል ዘርቶ ለማምረት አማራው በሃስቦች መስክ በብልኃት ጠለቅ ብሎ ገብቶ መንቀሳቀሱ ወሳኝ ነው” ሲሉ ከአማራው በስተቀር ለኢትዮጵያ የሚቆረቆር የለም የሚል ለመሆኑ ግልጽ ነው። የእነ አቶ ተስፋዬ ዓይነት ሰዎች፤ ዘረኝነታቸውን በኢትዮጵያ ባንዲራ በመጠቅለል፤ “ዜግነትን ለሌላው የመስፈር መብት” እንዳላቸው ስለሚያምኑ፤ አማራውን የበኩር ልጅ፤ ሌላውን ደግሞ የእንግዴ ልጅ አድርጎ የማስላት፤ ጽንፈኛ አመለካከታቸውን በአደባባይ ሲገልፁ ሃፍረት እንኳን አልተሰማቸውም። ሁሉም በዘሩ ያስባል አስተሳሰቡም አንድ ነው የሚሉን ሰዎች፤ ዘረኞቹ እራሳቸው መሆናቸውን አያስተውሉም። ታሪካችንን ዞር ብለን ስንፈትሽ ግን በኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ፖለቲካ እንዲጎለብት ብቻ ሳይሆን፤ ሃገራችን ላይ አደጋ የደቀኑና አሁንም እየደቀኑ ያሉ አማሮች አሉ። በጥቂት አማሮች፤ ሁሉንም አማራ እንደ አንድ ያስባል ብሎ መፈረጅም፤ ተገቢ አይደለም። እንኳን እንደ አማራ ያለ ትልቅ ሕዝብ ቀርቶ፤ አንድ ቤተሰብ ውስጥ እንኳን የሃሳብ ልዩነቶች አሉ። የሕወሃት አመራር ውስጥ በነበረው ጌታቸው ሴኩትሬ ሌላውን አማራ እንደማንለካ ሁሉ፤ በምንም ሂሳብ ኦሮሞን ሁሉ በእነ ዳውድ ኢብሳና በጥቂት የኦሮሞ ብሔር አቀንቃኞች ልንለካ አይገባም። ከዚህ በተፃራሪ የሚያስቡ ሰዎች፤ እራሳቸው በዘረኝነት ደዌ የታመሙ ለመሆናቸው፤ ብዙ መጽሐፍትን ማገላበጥ አያስፈልግም። እነ አቶ ተስፋዬ ሌላውን ጎጠኛ አድርገው የሚከሱት፤ ሁሉንም ሰው፤ በራሳቸው “ድንክዬ ቁመትና፤ ከጥጥ የቀለለ ክብደት” ስለሚመዝኑ ነው።  

በ1983 የዓፄ ምኒሊክን ሃውልት ለማፍረስ ተሞ የነበረውን ጽንፈኛ ኦሮሞ እኮ የተከላከሉት ኦሮሞዎች በልባቸው ኢትዮጵያን ስለያዙ ነው። እነ ጃጋማ ኬሎ፤ ባልቻ አባነፍሶ፤ ራስ ጎበናና ሌሎቹ የታገሉትና ዋጋ የከፈሉት ለኢትዮጵያ እንጂ፤ ለአንድ ብሔር አልነበረም። በተለያዩ ሃገር የመመከት ትግል ውስጥም ሆነ ሕዝብን ከጭቆናና ከአምባገነን ገዥዎች ለማላቀቅ፤ በርካታ ኦሮሞዎች፤ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ነፃነት ሕይወታቸውን ገብረዋል። አንድ ሚሊዮን የማይሞላ ጽንፈኛ ኦሮሞ ከ 30 ሚሊዮን በላይ የሚሆነውን የኦሮሞ ሕዝብ አይወክልም። ይህ አሁን እየጎለበተ የመጣው፤ “አማራ ካልሁንክ፤ ለኢትዮጵያዊነትህ “ማረጋገጫ” ማምጣት አለብህ” የሚል የጽንፈኞች ታምቡር በጽኑ ልንታገለው የሚገባ አገር አፍራሽ ሃሳብ ነው። ማንም ኢትዮጵያዊ ሊመዘን የሚገባው በራሱ ሥራ እንጂ በብሔር አይደለም። ለዚህም ነው ዛሬ መንግስት ሕግ ለማስከበር እርምጃ ሲወስድ፤ በሕግ የሚፈለጉ ሰዎች የብሔር ካርድ እየተመዘዘ፤ የዚህ ወይም የዛ ብሔር አባል ስለሆኑ ነው እየተባለ የሚቀነቀነው፤ ከተጠያቂነትም ለማምለጥ የሚሞከረው። እነ አቶ ተስፋዬም ይህንን አደገኛ አመለካከት የሚያጠናክር ሃሳብ ነው ይዘው ብቅ ያሉት።፡ አንባቢ እራሱን አንድ ጥያቄ ይጠይቅ፤ በእርግጥ የአማራውን ሕዝብ፤ ከሌላው ሃገር ወዳድ ኢትዮጵያዊ በመነጠል ኢትዮጵያን ማዳን ይቻላል ወይ? 

አቶ ተስፋዬ ወኃ የማይቋጥር ሃሳባቸውን ሲያጠናክሩ እንዲህ ይላሉ። “በጦርነትም ሆነ በሰላም፣ የአማራው ህላዌ አንድም ሁለትም ነው፤ አማራ ራስነት ወይም ማንነት አገራዊ ወርድና ስፋት አለው። አማራነት ውስጥ ሕያው፣ ተንቀሳቃስሽ ኢትዮጵያዊነት አለ። ይህን ስንል ምን ማለታችን ነው? አማራው በህልውናው እና ንቃተህሊናው አገር ወዳድነትን በጥልቅ ስለሚያካትት ራሱን ከጥፋት ለመታደግ ተነስቶ ሲንቀሳቀስ በውስጡ ያዳበራቸው የአገር ወዳድነት እሴቶችና ፀጋዎች፣ ለምሳሌ ሥልጡን ሕዝብነት፣ አርቆ አሳቢነት፣ አርበኝነትና ጀግንነት፣ ለራስ አድን ተጋድሎው ወሳኝ መሣሪያዎቹ ናቸው። የመኖር አለመኖር ትግሉን የሚበርዙ ውጨኛ ግባቶች አይደሉም። ይልቅስ የአማራው ሙሉ ህልውና የውስጥ አካላት ናቸው።” (ድምቀት የተጨመረ)። አቶ ተስፋዬ“አማራነት ውስጥ ሕያው፣ ተንቀሳቃስሽ ኢትዮጵያዊነት አለ።” ሲሉ ሌላው ብሔር ብሔረሰብ ውስጥ ኢትዮጵያዊነት የለም ማለት ነው? እንዲህ ዓይነት ዘረኛ አስተሳሰብ በምንም ዓይነት መረጃ የተደገፈ አይደለም። መንዝ ያለው አማራ፤ ሰዮ ካለው ኦሮሞ ወይም ውቅሮ ካለው ትግሬ በምን ይለያል? በእንዲህ ዓይነት ደካማ አስተሳሰብስ ነው ኢትዮጵያን ማዳን የሚቻለው? 

የአቶ ኡመር ሽፋው “የኢዜማ መኢሶናዊ ጉዞ” የሚለው ጽሁፍም በመልዕክቱ፤ ከአቶ ተስፋዬ የተለየ አይደለም።አቶ ኡመር ጽሁፋቸውን ሲጀምሩ፤ ታሪክን አጣመው ነው የጀመሩት፤ አሳዛኙ ነገር ደግሞ፤ ፍፁም ከታሪክ ያልተማሩ መሆናቸው ነው። የቀድሞ የኢትዮጵያ ምክትል ፕሬዝዳንት ኮሎኔል ፍስሐ ደስታ (ነፍሳቸውን ይማር) “አብዮቱና ትዝታዬ” በሚለው መጽሐፋቸው፤ በቁጭት ያስታወሱት አንዱ ነገር፤ ኢሕአፓ፤ መኢሶንና፤ ደርግ ተባብረው አለመስራታቸው ኢትዮጵያን ምን ያክል እንደጎዳ ነው። ይህ ፀሃፍ ኢሕአፓን የተቀላቀለው ታዳጊ ወጣት በነበረበት ጊዜ ነበር። ግን፤ ኢሕአፓ የተከተላቸውን አደገኛ መንገዶችና፤ መኢሶን ይዞት የነበረው ትክክለኛ አቅጣጫን ለመካድ አይችልም። አቶ ኡመር ጽሁፋቸውን ሲጀምሩ “መላ ኢትዮጵያ ሶሻሊስት ንቅናቄ (መኢሶን) ተብሎ ይጠራ የነበረው የፖለቲካ ድርጅት በደርግ ወይም በወታደራዊው አገዛዝ ጊዜ ከመንግሥት ጋር ተለጥፎ በኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) አባሎች ላይ ምን ዓይነት ግድያ፣ እሥራት፣ አፈናና ድብደባ እንዳስፈጸመ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን ነው።” ብለው ሲያስታውሱ፤ ኢሕአፓ በመኢሶን አባላትና ከደርግ ባለሥልጣናት እስከ ቀበሌ አመራር የፈፀመውን ግድያ ግን ባላየ አልፈውታል።

በዛን ወቅት፤ እርስ በእርስ ከመጠላለፍ ይልቅ፤ በሰከነ አዕምሮ፤ በትብብር መንፈስ ለሀገር የሚበጀው ቢሰራ ኖሮ፤ ዛሬ የደረስንበት ቀውስ ላይ እንደርስ ነበር ወይ ብሎ መጠየቅ ተገቢ ነው። ኮሎኔል ፍስሐ ይህንን ጠይቀው የደረሱበት መልስ፤ ትብብር ቢኖር ኖሮ፤ የዛሬ ውድቀት ላይ ባልደረስን ነበር የሚል ለመሆኑ ከመጽሐፋቸው መገንዘብ ይቻላል። መኢሶንም ሆነ ኢሕአፓ ውስጥ የነበሩት የኢትዮጵያ ብርቅዬ ልጆች ነበሩ። ችግራቸው፤ የመቻቻል የፖለቲካ ባሕል አለማዳበራቸው፤ በችኮላ፤ ኢትዮጵያን በአንዴ ለመለወጥ የነበራቸው የወጣትነት ጉጉት እና፤ በተለይም ኢሕአፓ፤ ለውጥ በነውጥ ለማምጣት፤ ሌላው ቀርቶ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር መተባበሩ ነበር። መኢሶን ከደርግ ጋር ሲስራ የነበረውም፤ የደርግ መንግስት አቅጣጫ እንዳይስት እና ለውጡም የተፈለገውን ውጤት እንዲያስገኝ ለማገዝ እንደነበር አቶ ተስፋዬ መኮንን “ይድረስ ለባለታሪኩ” በሚለው መጽሐፋቸው አስፍረውታል። እንደ እኔ ግምት፤ በወቅቱ የነበረው የፖለቲካ አለመብሰል እና፤ በሃሳብ ከመሟገት ይልቅ፤ ሰዎችን በመቅጠፍ ሃሳብን መግደል ይቻላል በሚል የተሳሳተ ስሌትና ጀብደኝነት በሁሉም በኩል የተከሰቱ ስሕተቶች ናቸው። ስሕተቱ የመኢሶን ብቻ ነበር ማለት ግን፤ ከራሳችን ታሪክ አለመማር፤ ወይም በበቀል ስሜት የታመመ አዕምሮ ስሜት መሆኑን ያሳብቃል። 

አቶ ኡመር በጽሁፋቸው “ታሪክ ራሱን ይደግማል እንዲሉ ባለፈው አራት ዓመት የኢትዮጵያ ዜጎች ለማህበራዊ ፍትህ ፓርቲ  (ኢዜማ) ከለየለት ዘረኛና ተረኛ የአብይ አህመድ መንግሥት ጋር ድንበር የለሽ ቅርርብ በማድረግ ከሞላ ጎደል መኢሶን የሄደበትን ጎዳና ለታክቲክም ይሁን ለስትራትጂ ተጉዞበታል ማለት ይቻላል።” ሲሉ ዘረኛም ሆነ ተረኛ ለሚሉት ክስ ያቀረቡት አንድም መረጃ የለም። የአብይ አሕመድ መንግሥት፤ ኢትዮጵያዊ ተቋማትን ከመገንባት፤ ኢትዮጵያን ከፍ ከፍ ከማድረግ፤ ከሚኒስትሮች ጀምሮ፤ የምክር ቤት አባላትንም ሆነ መላው ኢትዮጵያዊ ከዘረኝነት እና ከመንደርተኝነት ወጥቶ፤ ስለኢትዮጵያ ትልቅነት እንዲያስቡና፤ ለኢትዮጵያ እንዲሰሩ፤ ከመምከር እና ከማስተማር፤ እንዲሁም ኢትዮጵያን መጠቀምያ ለማድረግ ቆርጠው ከተነሱ ባዕዳን የተሰነዘረውን አደጋ ከመከላከል ውጭ፤ ዘረኛ ለመሆናቸው፤ ማንም ምንም ዓይነት መረጃ ማቅረብ እንደማይችል በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። ቀደም ብዬ እንደገለፀኩት፤ አብይ አሕመድ ከሰሩት አንዱ ትልቅ ሥራ፤ ከ-40 ዓመታት በላይ የተሸረሸረውን የኢትዮጵያዊነት ስነ ልቦና እየገነቡ መሆናቸው ነው። አብይ አሕመድ በጽንፈኛ ኦሮሞዎች ተቃውሞ እያጋጠማቸው የሚገኘው፤ ኢትዮጵያን በማለታቸው ለመሆኑ ነጋሪ አያሻውም። ወያኔ እንኳን ዶ/ር አብይ አሕመድን የሚከሰው “አሕዳዊ” ነው እያለ ነው። ታድያ፤ አቶ ኡመር፤ አብይ አሕመድ ዘረኛ ነው የሚሉን ያለምንም መረጃ መሆኑ፤ ያለምክንያት አይደለም። ይህ ቢሆንማ ኖሮ፤ የዜግነት ፖለቲካን በማራመድ ከተለያዩ ጽንፈኞች “በሚወረወርበት ጦር” ብዙ ዋጋ የከፈለው ኢዜማ፤ አሁን ያለውን የፖለቲካ ሚና ባልተጫወተ ነበር። ይህ ደግሞ ሃላፊነት ከሚሰማው የፖለቲካ ፓርቲ የሚጠበቅ ነው። 

በየትም ሃገር አንድ መንግሥት ተወግዶ፤ ሌላ ሲተካ፤ የሚያልፈው በነውጥ ነው። ለሃገር ቅድሚያ የሚሰጡ የፖለቲካ ሃይሎች፤ ትኩረታቸው ሊሆን የሚገባው ሃገርን ለማረጋጋት ገንቢ ሚና መጫወት እንጂ፤ ሌላ ነውጥ በመቆስቆስ፤ እራሳቸው ችግር በመሆን ሊሆን አይገባውም:: ምንም እንኳን በአንድ ሃገር የተቃዋሚ ፓርቲ ሥራው ቀን ተቀን መንግሥት የሚሰራውን ሥራ ማጣጣል ቢሆንም፤ ሃገር ቀውስ ውስጥ ስትሆን ግን፤ ከመንግሥት ጋር በመስራት፤ ቀውሱን ማርገብ ይጠበቅበታል። በቀውስ ወቅትም ጥያቄው መሆን ያለብት፤ እኔ ምን የፖለቲካ ጥቅም አገኛለሁ ሳይሆን፤ በሃገር ውስጥ መረጋጋት በመፍጠር ሃገር እንዴት ልትቀጥል ትችላለች የሚል መሆን አለበት። በዘር ጥላቻ ልባቸው ለታወሩ ሰዎች ግን፤ ጥቅማቸው፤ ሃገርን ሰውተው፤ እነሱ የፖለቲካ ትርፍ ማግኘት ነው። ዛሬ ሃገራችን ባለችብት ሁኔታ፤ ትከሻዋ የፖለቲካ ቁማር መሸከም አይችልም። ለዚህም ነው እንደነ አቶ ኡመር ያሉ ሰዎች፤ በፈጠራ ክስ እንደ ኢዜማ ያሉ ድርጅቶች ላይ ጫና ለመፍጠር እና፤ ሌላ ቀውስ፤ ሌላ ግጭት የሚደግሱልን።  

አቶ ኡመር፤ ብሔራዊ አጀንዳ አቅነቃኝ መስሎ የተጀመረው ሃሳባቸው፤ ወደ ጎጠኝነት ለመውረድ ጊዜ አልፈጀበትም። ለዚህም ነው በጽሁፋቸው “የኢዜማ አመራሮች የአብይ መንግሥት ሕብረብሔራዊ ነው፣ ያሻግራናል፣ በአብይና በታከለ ኡማ ላይ እምነት አለን እያሉ ሲምሉና ሲገዘቱ ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፈው አራት ዓመት ከሆነው ይልቅ ያልሆነውን የግፍ ዓይነት መቁጠር ሳይቀል የሚቀር አይመስለኝም። አማራው በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል-ግሙዝ ክልሎች በገፍ ታርዷል፣ በጅምላ ተቀብሯል። አሸባሪው ሕወሃት በከፈተው ጦርነትና መንግሥት በፈፀመው ሴራ በአማራና በአፋር ክልሎች ከተሞች ፈራርሰዋል፣ ሴቶች ተደፍረዋል፣ በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል፣ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በበሽታና በረሃብ በማለቅ ላይ ይገኛሉ። የሁለቱ ክልልሎች መሠረተ ልማቶች እንዳሉ ወድመዋል። ታሪካዊ አብያተክርስቲያናትና መስጊዶች ተቃጥለዋል፣ ረክሰዋል፣ ቅርሶቻቸው ተዘርፈዋል። የሁለቱ ክልሎች ልማት ወደኋላ ሰላሳ ዓመት ሂዷል ቢባልም መልሶ ለመገንባት መቶ ዓመት ሊፈጅ ይችላል። ምን ያልደረሰ ስቆቃና ግፍ አለ?” የሚሉን። 

ከአቶ ኡመር አንድ የተረዳሁት፤ እሳቸው እና እሳቸውን መሰል ሰዎች እጃቸውን አጣጥፈው ተቀምጠው፤ ሃገሪቱ በመንግሥት ብቻ ወደ ተሻለ ሥርዓት እንድትሻገር ነው። የዜግነት ግዴታና ሃላፊነት ምን እንደሆነ የገባቸው አይመስሉም። ዛሬ ሃገራችን ከገባችበት ቀውስ ለማውጣት፤ ሁሉም መተባበር ሲኖርበት፤ እንደ ኢዜማን የመሰለ የፖለቲካ ፓርቲ ለማሸማቀቅ የሚደረገው ሙከራ በሃገር ተጨማሪ ቀውስ ለመፍጠር ነው። በአንድ ወቅት የአሜሪካ የሪፓብሊካን ፓርቲ፤ ኦባማ ስኬታማ እንዳይሆኑ ምንም ነገር ላለማገዝ የወሰኑትን ዘረኛና እኩይ ውሳኔ ያስታውሰኛል። እነ አቶ ኡመር ኦሮሞ ዝርያ ያለበት ኢትዮጵያዊ የሚመራት ኢትዮጵያ ስኬታማ እንድትሆን እንደማይፈልጉ ሃሳባቸው ያሳብቃል። ለዚህም ነው በኢትዮጵያ ውስጥ የዘር ፍጅትና መፈናቀልን አዲስ ለማሰምስል የሚሞክሩት። ርሃብስ ለኢትዮጵያ አዲስ ነው? አቶ ኡመር “ታይቶ የማይታወቅ ረሃብና በሽታ ሲሉ” የ1960ዎቹ ነው ወይስ የ1970ዎቹ ኢትዮጵያን ጠኔ ያመሰበት ወቅት የተዘነጋቸው? እነ አቶ ኡመር፤ የ1980ዎቹን፣ 90ዎቹን እና ከዛም በኋላ የነበሩ ዘር ተኮር ግድያዎችን እና መፈናቀሎቹን ዘንግተውት ነው? በተለይ ሕወሃት ሥልጣን ከተቆናጠጠ በኋላ በመንግሥት ድጋፍ የተደረጉ ማፈናቀሎች፤ ግድያዎች፤ አዲስ ናቸው እንዴ? እነ አቶ ኡመር፤ የኢትዮጵያ እስር ቤቶች፤ ወንዱ ወንድን፤ ሴቱ ሴትን በወሲብ እንዲደፈር ይግደድ የነበረበት እና በመጥረጊያ ዱላ ወንድና ሴቶች በየእስር ቤቱ በወሲብ ጥቃት ይደፈሩ እንደነበር ዘነጉት እንዴ? በሃገራችን፤ በርካታ ግፍ እየተፈፀመ መሆኑ የየዕለቱ የዜና መዋዕል ነው። ለዚህ ግን ተጠያቂው የዐብይ አስተዳደር ነው ወይ? ከዚህ በፊትስ እንዲህ ዓይነት ጥቃት አልተፈፀመም ወይ? የጥቃቱ ሰለባስ አማራው ሕዝባችን ብቻ ነው ወይ? በደርግ ጊዜ በኦጋዴን፤ በአሶሳ፤ በትግራይ እና በኤርትራ የተፈፀመው ዘር ተኮር ጥቃት፤ በጎንደር በወሎ፤ ወጣቶች በአደባባይ ተሰቅለው በግፍ የተገደሉበት ለእነ አቶ ኡመር እንግዳ ይሆን እንዴ? ኢትዮጵያ በአምስት አቅጣጫ (አዲስ አበባ ከተማን ጨምሮ) ጥቃት ላይ የነበረችበትና አንዱ ሌላውን በጥርጣሬ ያይበት የነበረበት ወቅት፤ እንዴት ተዘነጋ? እነ አቶ ኡመር ችግሩ በቅጡ አልገባቸውም ስለዚህ ከእንደዚህ ዓይነት ሰዎች መፍትሔ መጠበቅ አይቻልም። ለመሆኑ፤ ዶ/ር ዐብይ ከሕወሃት ጋር ጦርነት ውስጥ ላለመግባት የሄዱበት መንገድ እልህ አስጨራሽ አልነበረም እንዴ? ለጦርነቱ ተጠያቂ እንዴት ሊሆኑ ይችላሉ? ምን አልባት ለአቶ ኡመር እንግዳ እንደሆነ አላውቅም እንጂ አሁን ግጭት ያለውና የኢኮኖሚና ማህበራዊ ቀውስ የመጣው አማራና ትግራይ ክልል ውስጥ ብቻ አይደለም። ወይስ የመልእክታቸው አንድምታ፤ ‘የኦሮሞ ክልል እያደገ ሌላው እየተጎዳ ነው’ ለማለት ነው? 

አቶ ኡመር፤ ያለምንም ሃፍረት “አሸባሪው ሕወሃት በከፈተው ጦርነትና መንግሥት በፈፀመው ሴራ በአማራና በአፋር ክልሎች ከተሞች ፈራርሰዋል፣ ሴቶች ተደፍረዋል፣ በብዙ መቶ ሺ የሚቆጠሩ ንፁሃን ዜጎች ተገድለዋል፣ በሚልዮኖች የሚቆጠሩ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለው በበሽታና በረሃብ በማለቅ ላይ ይገኛሉ።” ሲሉ ይከሳሉ። “መንግሥት በፈፀመው ሴራ” ሲሉ ግን ያቀረቡት የጠብታ መረጃ የለም። ሴራው ምንድ ነው? ማንንስ ለመጥቀም ነው? እንዲሁ በደመ ነፍስ ያልተገባ ውንጀላ ማንን ይጠቅማል? በመንግሥትና በሕዝብ መሃከል መጠራጠርን ከመፍጠርና ሃገራችንን ለተጨማሪ አደጋ ከማጋለጥ ሌላ አላማውስ ምንድ ነው? መንግሥት አሲሯል ካሉ፤ አቶ ኡመር መረጃውን ያቀብሉን። እንዲሁ “የመንጋ” ጭብጨባ ፍለጋ የሚወረወሩ ውንጀላዎች የማንንም ቀልብ አይገዙም።፡አልካይዳ የአሜሪካ ጥቅም ላይ ጥቃት ሲፈጽም፤ ቦኮሃራም በናይጄርያ፤ አልሸባባ በሶማልያ፤ አይሪሽ ሪፓብሊካን በአየርላንድ ወዘተ በሰላማዊ ዜጎች ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ፤ ጥቃቱን በጥቂት ዓመታታ የመከተ ማንም መንግሥት የለም። ጥቃቱም የተፈፀመው ከመንግስታቱ ጋር በማሴርም አልነበረም። አሜሪካ ከዚህ ሁሉ ጉልበቷ፤ ምርጥ የስለላ እና የመረጃ ተቋሟ ከአልካይዳ ጋር ከ 20 ዓመታታ በላይ ታግላለች፤ ቦኮሃራም ለ20 ዓመታታ ናይጄርያ ውስጥ ሽብር እየነዛ ነው፤ PKK በመባል የሚታውቀው የኩርዲሽ ሰራተኛ ፓርቲ ለቱርክ የጉሮር አጥንት ከሆነ 40ኛ ዓመቱን ሊይዝ ነው። 

ከእነዚህ ሁሉ የኢትዮጵያን የተለየ የሚያደርገው ምን አለ? የራሳቸው የፖለቲካ ፍላጎት ያላቸው ሃይሎች በሃይል ለውጥ ለማምጣት የሚፈፀሙት ጥቃት ለኢትዮጵያም እንግዳ አይደለም፤ ታሪካችን አብዛኛውን የሚያሳየው ይህንኑ ነው። ዛሬ በኢትዮጵያ ውስጥ በተየለያዩ አካባቢዎች የሚፈፀሙት ጥቃቶች ከበስተጀርባቸው፤ የሕወሃት እና የግብጽ እጅ እንዳለባቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ። ዐብይ ከኢትዮጵያ ጠላቶች ጋር እየተመሳጠሩ ነው የሚያሰኘው እና “ለሃገራቸው ኢትዮጵያ ያለቸው ፍቅር ጥያቄ ውስጥ የሚገባው” ምክንያቱ አንድና አንድ ብቻ ነው። ይኸውም፤ የኦሮሞ ዝርያ ያለበት ኢትዮጵያዊ፤ በመሪነት ቦታ መቀመጡ ሕመም የፈጠረባቸው ሰዎች፤ የፈበረኩት ትርከት መሆኑ ነው። ለመሆኑ፤ አቶ ኡመርና መሰሎቻቸውን፤ ከዐብይ “የበለጠ” ኢትዮጵያዊ የሚያደርጋቸው ምንድ ነው? ለመሆኑ እነዚህ ሰዎች ለአማራው ሕዝብም ሆነ ለኢትዮጵያ ያበረከቱት ምንድ ነው? George Orwell Animal Farm በሚለው መጽሐፉ “All animals are equal, but some animals are more equal than others.” እንዳለው እነ አቶ ኡመርም “ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው፤ አማራው ግን ከሌላው የበለጠ ኢትዮጵያዊ ነው” በሚል ጽንፈኛ አስተሳሰብ በመጠመቃቸው፤ “እነሱን ከሚመስል” ስው በስተቀር ኢትዮጵያ ውስጥ አመራር ላይ እንዲቀመጥ ስለማይፈልጉ፤ እንቅፋት ለመሆን የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደሌለ፤ ሃሳባቸው ይመሰክራል። 

ዋና ዋና በሚባል በአለም የመገናኛ ዘዴዎችም ሆነ በምእራቡ ዓለም መንግስታት በዶ/ር ዐብይ ላይ ወከባ፤ ዘለፋ፤ ጫና፤ ዛቻና ማስፈራርያ እየደረሰባቸው ያለው የኢትዮጵያን ጥቅም አሳልፌ አልሰጥም በማለታቸው አይደለም እንዴ? ይህ ለእነ አቶ ኡመር እንግዳ አይደለም። ዓላማቸው ግን ሃቅን ይዘው መፍትሔ ለመጠቆም ሳይሆን፤ አላማቸው ነውጥ በመፍጠር የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት ነው። ታድያ የእነዚህ ዓይነት ሰዎች አስተሳሰብ “እኛ ካልገዛናት፤ ኢትዮጵያ ገድል ትግባ’’ ከሚል ወያኔያዊ አስተሳሰብ በምን ይለያል? አቶ ኡመርን መሰል ሰዎች፤ ትኩረታቸው የኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት አይደለም። ለዚህም ነው በዐብይ አመራር ምንም ዓይነት በጎ ለውጥ ቢመጣ ሊዋጥላቸው እንደማይችል ጽሁፋቸው የሚያሳብቀው። 

አቶ ኡመር “ኢዜማ አልፎ አልፎ ብቅ እያለ መግለጫ በማውጣት ሕዝቡን ለማስተኛት ከመሞከርና ከብአዴን የበለጠ የኦሮሙማ አገልጋይ መሆኑን ለማሳየት ከመፎካከር በስተቀር የአብይ አህመድ መንግሥትን የተሳሳተ አቅጣጫ ለማረም አንድም መሬት ላይ የወረደ ሥራ ሲሠራ አልታየም። እንዳውም የይስሙላውን ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ነበር ለማሰኘትና የአብይ አህመድን ገጽ ለመገንባት በምርጫው ቢሳተፍም ጥረት ያደረገው ግን ለራሱ ወንበር ለማሸነፍ ሳይሆን ሌሎች ተቃዋሚ ፓርቲዎችን የማሸነፍ ዕድል ለመንፈግ እንደነበረ በተደጋጋሚ ክስ ይቀርብበታል።” ይሉናል (ድምቀት የተጨመረ)። ለመሆኑ የዐብይ የኦርሙማ አገልጋይ መሆን ምን ማለት ነው? አቶ ኡመር በኢትዮጵያ የተደረገውን ዲሞክራሲያዊ ምርጫ አይናቸውን በጨው አጥበው ሲክዱ የሚነግረን ብዙ ነው። መንግሥቱ ኃይለማርያም “ወርቅ ሲነጠፍላቸው፤ ፋንድያ የሚሉ” ያሏቸው እንዲህ ዓየነቶቹን ሰዎች ነው። ለመሆኑ፤ ኢትዮጵያ ወስጥ የትኛው የፖለቲካ ፓርቲ ነው እንደ ኢዜማ በቁጥርም ይሁን በጥራት የምርጫ ተወዳድሪ እጩዎችን ያቀረበ? አቶ ኡመር ይህን ጭፍን ክሳቸውን ሲስነዝሩ፤ ኢዜማ ለእነ እከሌ እንቅፋት ለመሆን ነው ሲሉ የጠቀሱት የድርጅትም ሆነ ግለሰብ ስም የለም። በተቃዋሚ ደረጃ እንደ ኢዜማ የተሻለ ቁመና ያለው ማንም አልነበረም አሁንም የለም:: ይህንን በሙሉ ድፍረት መናገር ይቻላል።

ብዙዎቻችን መጠየቅ ያለብን ጥያቄ፤ ለመሆኑ ዐብይ አሕመድ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ሃገራችን ምን ዓይነት ሁኔታ ላይ ነበረች የሚለውን ነው። እርስ በእርስ ልንተራረድ የተዘጋጀንበት ወቅት እንደነበርም ልንዘነጋ አይገባም። ምን ዓይነትስ ተቋማት ነበሩ ብለን መጠየቅም አለብን። ምርጫ ቦርድ፤ የኢትዮጵያ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን፤ ፍርደ ቤቶች፤ ነፃና ገለልተኛ ሆነው እንዲሰሩ አቅጣጫ የተቀመጠውና በአዲስ መልክ የተዋቀሩት፤ በዐብይ አስተዳደር አይደለም እንዴ? ዓብይ አሕመድ እና ቡድናቸው የተረከበው መንግሥታዊ አስተዳደር ከሥር መሰረቱ የበሰበሰ የፖለቲካ አመራር እና ቢሮክራሲ መሆኑንስ እንዴት ዘነጋን? ይህንን ከስር መሰረቱ የበሰበሰን፤ በዘር አድልዎ፤ በፖለቲካ ተውሳክና በሙስና የተጨማለቀን ቢሮክራሲ በ4 ዓመታታ አይደለም፤ በአስር ዓመታት ለማጽዳት የሁሉንም ተሳትፎና ቁርጠኝነት ይጠይቃል። በሴራ፤ በመጠላለፍ እና ነውጥ በማራገብ ሃገር መገንባት አንችልም። እንደ እነ አቶ ኡመር ያሉ ሰዎች፤ እጃቸውን አጣጥፈው፤ ሁሉም ለውጥ በአንድ ሰው መምጣት እንዳለበት የሚሰብኩን፤ ሃገሪቱን እንዴት ኦሮሞ ይመራል ከሚል የውስጥ ደዌ ከፍተኛ ሕመመ እንጂ፤ ለአማራው ሕዝብ በመቆርቆር አይደለም። ለዚህም ነው ሕዝቡ የብሔርና የሃይማኖት ነጋዴዎችን በንቃት ሊመክት እና ጆሮ ሊነፍግ የሚገባው።  (ይቀጥላል)። 

__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here