spot_img
Friday, June 14, 2024
Homeነፃ አስተያየትበጎጠኝነት ኢትዮጵያን ማዳን አይቻልም።  (የመጨረሻው ክፍል)

በጎጠኝነት ኢትዮጵያን ማዳን አይቻልም።  (የመጨረሻው ክፍል)

ምላሽ ለአቶ ተስፋዬ ደምመላሽ፤ ኡመር ሽፋው፤ ዶ/ር ፈቃዱ፤ በቀለ እና ሌሎችም

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
ግንቦት 28, 2014 ዓ.ም.

                     “ከሥጋው ፆመኛ ነኝ፤ ከመረቁ አውጡልኝ”  ሃገራዊ ብሂል

“ቀደም ሲል “በጎጠኝነት ኢትዮጵያን ማዳን አይቻልም” በሚል ርዕስ በሁለት ተከታታይ ጽሁፎች አቶ ተስፋዬ ደምመላሽ፤ አቶ ኡመር ሽፋው እና ዶ/ር ፈቃዱ በቀለ በፃፉት ጽሑፍ ላይ ያለኝን ሃሳብ አካፍዬ ነበር። የጽሁፌ ዋና ዓላማ፤ ዶ/ር ዐብይ ዘረኛ ናቸው፤ ጨካኝ ናቸው፤ ደካማ ናቸው፤ ወዘተ እየተባሉ የሚቀርቡት ክሶች ምንም መረጃ የሌላቸው መሆኑን ለመጠቆምና፤ እንዲህ ዓይነት ክሶችን አንዳንድ የፖለቲካ ኃይሎች፤ “በኢትዮጵያዊነት ሽፋን” የራሳቸውን የጎጠኝነት ለማራመድ እና ሃገር ውስጥ ነውጥ ለመፍጠር የሚጠቀሙበት ድብቅ አጀንዳ በመሆኑ፤ በሃገር ላይ አደጋ ለመደቀን የሚደረጉ ሙከራዎች ለመሆናቸው ደውሉን ለመደወል ነው። የኦሮሞ ጽንፈኞች፤ ዶ/ር ዐብይን ለአማራ ብቻ ያደላሉ፤ ኦሮሞን በኦሮሞነት ያጠቃሉ ሲሉ ይከሳሉ፤ ሕወሃትና የትግራይ ጽንፈኞችም እንዲሁ፤ ዶ/ር ዐብይ ትግሬን ነጥለው በትግሬነቱ ያጠቃሉ ይላሉ፤ ጽንፈኛ አማሮች ደግሞ ዐብይ አማራን ብቻ ነጥለው በአማራነቱ ያጠቅሉ ይሉናል። አንባቢ እንደሚረዳው እነዚህ ሶስት የተለያዩ ነገሮች እርሰ በእርስ የሚጣረዙ ናቸው። አንድ ሰው ሶስቱንም ሊሆን አይችልም። ይህ ፀሃፍ ዶ/ር ዐብይ መነካት የለባቸውም፤ ሊወቀሱም ሆነ ሊወገዙ አይገባም የሚል እምነት የለውም። ዶ/ር ዐብይ በሚሰሯቸው ስህተቶች ሊወቀሱም ሊወገዙም ይገባቸዋል። ይህ ፀሃፍ ዶ/ር ዐብይ ሰሯቸው ብሎ የሚያምናቸውን ስህተቶች በመተቸት በተደጋጋሚ ያቀረባቸው ጽሁፎች ለሕትመት በቅተዋል። በተለይም ዶ/ር ዐብይ ሊወቀሱበት የሚገባ ሁለት ነገር አለ። አንደኛው፤ በአንድንድ ጉዳዮች ግልጽነት የጎደለው የፖለቲካ አካሄዳቸው ሲሆን፤ ሌላው አደንቋሪው ዝምታቸው ነው። በተለይ በተለያዩ አካባቢዎች በወገኖቻችን ላይ ጥቃት ሲደርስ እንደ ሃገር መሪ አደባባይ ላይ ወጥተው ሕዝቡን ለማረጋጋት ገለፃ አለማድረጋቸውና አጥቂዎች ላይ ምን እርምጃ እንደሚወሰድ እንዲሁም የፌደራል መንግሥቱ አጥፊዎችን በሕግ ቁጥጥር ሥር ለማዋል ምን ዓይነት ግብዓቶችን ለሕግ አስከባሪው ሃይል እንደሚያቀርብ በመጥቀስ ሕዝቡ የሰላም ተስፋ እንዲሰንቅ አለማድረጋቸው፤ በዚህ ዘርፍ የአመራር ውድቀት አሳይተዋል። አንድ የሃገር መሪ በአንድ ዘርፍ ድክመት አሳይቷል ወይም ወድቋል ማለት፤ የሰራቸውን በጎ ሰራዎች ሁሉ እንዳልተሰሩ ማራገብ ማለት አይደለም። በሚያሳዩት ማንኛውም ድክመትም ሆነ ጥፋት በመረጃ ተደግፎ ሊወቀሱም፤ ሊወገዙም ይገባል። ይህ ደግሞ በሃገራቸው ንቁ ተሳትፎ ከሚያደርጉ ዜጎች የሚጠበቅ ነው። “ሕፃኑን ከነታጠበበት ቆሻሻ ወኃ ጋር የመድፋት” የፖለቲካ ባሕላችን ግን ሊታረም ይገባዋል። 

ከዚህ እሳቤም በመነሳት ነው፤ በዚህ በመጨረሻ ክፍል፤ የዶ/ር ፈቃዱ በቀለን “ኋላ-ቀር አስተሳሰብ ባላቸውና በአረመኔዎች የሚመራ ምስኪን ህዝብና አገር!” በሚል ርዕስ በቦርከና ድሐረ ገጽ ላይ ያቀረቡት ጽሁፍ ላይ አስተያየቴን የምሰጠው። 

ዶ/ር ፈቃዱ፤ ዶክተርነታቸው በምን እንደሆነ ለማወቅ ያደረግኩት ጥረት አልተሳካም። ሆኖም፤ አንድ “ዶ/ር” የሚል የትምህርት ማዕረግ ያለው ሰው፤ አስተያየት ሲሰጥም፤ ያሉ ችግሮችንም ሲጠቁም ሆነ፤ መፍትሔ የሚለውን ሃሳብ ሲያቀርብ፤ መጠቅመ ያለበት ስርዓት (ዲስፕሊን) አለ። በትምህርት ደረጃው ከፍ ያለ ሰው፤ ከሌላው የተለየ የሚያደርገው፤ ለሕዝብ የሚያቀርባቸው ሃሳቦች፤ በመረጃ እና በማስረጃ የተደገፉ ሲሆኑና፤ ትንታኔውም በእነዚህ ጭብጥ ባላቸው መረጃዎች እና ማስረጃዎች ላይ መሰረት ሲኖረው ነው። የዶ/ር ፈቃዱ ጽሁፍ የሚጀምረው፤ ያለፍንበትን እና የኖርንበትን የወያኔን አገዛዝ በመግለጽ ሲሆን፤ ቀጥለው ያነጣጠሩት፤ የዐብይ አስተዳር ላይ ነው። ጽሁፋቸው በጥቅሉ፤ ብዙ ነገሮችን የነካካ፤ መንግስትንም፤ ይህንንም ትውልድ፤ ምሁሩንም በጥቅሉ የኮነነ ሆኖ፤ በጭብጥ እና በመረጃ ጠኔ የተመታ፤ ከመሆኑ አልፎ፤ ከጽሁፉ ርዕስ ጋር ምንም ግንኙነት የሌላቸው ነገሮች መካተታቸው፤ ጽሁፉን ሳይሰለቹ ለመጨረስ አያስችልም።  ዶ/ር ፈቃዱ፤ የኢትዮጵያ ምሁራን በጥናት ያልተደገፈ እና ሥራቸውን በአቦ ሰጡኝ የሚሰሩ ናቸው ብለው ሲተቹ፤ እራሳቸውን “በመስተዋት አልተመለከቱም”። ይህ ጽሁፋቸውም በምንም ዓይነት ጥናትም ሆነ መረጃ የተደገፈ አለመሆኑ፤ ክሳቸውን “አቦ ሰጡኝ” ያደርገዋል።  

የዶ/ር ፈቃዱ ጽሁፍ፤ ከጎጠኝነት ጋር የተያያዘ በመሆኑ፤ በዛው ርዕሴ ላይ አተኩሬ አስተያየቴን እገልፃለሁ። ዶ/ር ፈቃዱ ዶ/ር ዐብይን ሲገልፁ እንዲህ ይሉናል። ““በዶ/ር” አቢይ አህመድ የሚመራው አዲሱ  የለውጥ ኃይል  እየተባለ የሚጠራው ስልጣንን ሲጨብጥ ወያኔ ስልጣን ላይ በነበረበት ዘመን ምን ምን ዐይነት እርኩስ ስራዎችን ይሰራ እንደነበር የተገነዘበ መስሎን ነበር። በህዝባችን ላይ የፈጸማቸውን ጉዶች በሙሉና፣ በተለይም ደግሞ አገራችንን ያዳከመውን የጎሳ ፖለቲካ በመቀልበስ ወደ ተሻለና ወደ ስልጣኔ ጎዳና ያመራናል የሚል ዕምነት ነበርን። አለባበሱንና መልኩን ብቻ የተመለከተው ኢትዮጵያዊ በመፈንደቅ አዲስና ብሩህ የሆነ፣ እንዲሁም ደግሞ በአስተሳሰቡ ሊበራል የሆነ መሪ ስልጣንን ተቀዳጀ ብሎ ተስፋ አድርጎ ነበር። አንዳንዶች እጅግ በሚያሳፍርና በሚያሳዝን መልክ በማልቀስ የአቢይን ጫማ እስከመሳም የደረሱ ነበሩ። ይሁንና ሊበራል መስሎ የታየው፣ አሻግራችኋለሁ ብሎ የማለውና የተገዘተው፣ የኪነት ሰዎችን ሁሉ በመጋበዝ ስለኪነት አስፈላጊነት የተናገረው፣ አዛኝ መስሎ የቀረበውና ፈገግም እያለ የህዝብን ልብ የገዛው አዲሱ መሪያችን ይኸው እንደምናየው ሊበራልና ዲሞክራት ሳይሆን እጅግ አደገኛ እየሆነ የመጣ መሆኑን አስመስክሯል። ምኑን ታዩታላችሁ ገና ብዙ ሰው ይሞታል እያለ ርህራሄ የሌለው  መሆኑን አረጋግጧል። አስተሳሰቡና ድርጊቱ ከፋሺስቶች የማያንስ መሆኑን አስመስክሯል።” ዶ/ር ፈቃዱ ለዚህ ክሳቸው መረጃ አድርገው ያቀረቡት ዶ/ር ዓብይ ምኑን ታዩታላችሁ ገና ብዙ ሰው ይሞታል (ስርዝና ድምቀት የተጨመረ) ብለዋል ከሚል ከዶ/ር ዐብይ “መዘው ያወጧት” ዓረፍተ ነገር ነች። ዶ/ር ዓብይ ይህን ያሉት በምን የሃሳብ ዕቅፍ ውስጥ (context) እንደሆነ እንድንረዳ እንኳን፤ ዶ/ር ፈቃዱ፤ የዶ/ር ዓብይን ሙሉ ንግግር ለመጥቀስ ወይም በምን ዓይነት ሁኔታ ይህን እንደተናገሩ አልጠቀሱልንም። ለራሳቸው ክስ የሚመቻቸውን ብቻ መዘው ነው፤ ዶ/ር ዐብይን “አስተሳሰቡና ድርጊቱ ከፋሺስቶች የማያንስ መሆኑን አስመስክሯል።” የሚሉን። 

ዶ/ር ዐብይ ግን ከዶ/ር ፈቃዱ አገላለጽ የተለዩ ለመሆናቸው ድርጊታቸው ይመሰክራል። በየትኛውም ወቅት፤ የኢትዮጵያ መሪ፤ በውጭ ሃገር የታሰሩ ዜጎቹን አስፈትቶ ወደ ሃገር እሰረኞቹን ይዞ የገባ መሪ የለም። እኔ እስከማውቀው ድረስ፤ በየትኛውም የመንግስት አስተዳደር፤ በውጭ ሃገር ለኢትዮጵያውያን መብት የሚሟገት መንግሥት ኖሮ አያውቅም። ዶ/ር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ግን፤ በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራት እና በመካከለኛው ምሥራቅ የኢትዮጵያውያንን መብት ለማስከበር፤ በዶ/ር ዐብይ አስተዳደር ሥራ መጀመሩ የሚያበረታታ እና ተጠናክሮ መቀጠል ያለበትም ነው። የአዲስ አበባ አንደኛና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች በረሃብ ትምህርታቸውን ለመከታተል እንዳይቸገሩ፤ የቁርስና የምሳ አገልግሎት የተጀመረው፤ በዶ/ር ዐብይ አስተዳደር ነው። በሃገራችን የበጎ አድራጎት ሥራን ለማበረታታት፤ ዶ/ር ዐብይ፤ ሌሎች አመራሮችን በማስተባበር፤ የወዳደቁ የአቅመ ደካሞችን ቤቶች በማደስ እና በመገንባት፤ ምሳሌ በመሆን መንገድ ጠቁመዋል። ከዚህም አልፎ ችግኞችን በማስፈላት እና በመትከል፤ የበጎ አድራጊነት መንፈስ በሃገራችን እያደገ እንዲመጣም አድርገዋል። ዶር/ ፈቃዱ፤ ይህ የፋሽስት ወይም የአረመኔ መሪ መገለጫ አለመሆኑን የሚያውቁ ይመስለኛል። 

ከዛም አለፍ በለው፤ ዶ/ር ፈቃዱ እንዲህ ይሉናል “ብሄራዊ ባህርይ የሌለው፣ አብዛኛውን ህዝባችንን የሚንቅና፣ በተቃራኒው ደግሞ ለትግሬ ብሄረሰብ የሚቆረቆርና ወያኔን ናፋቂ መሆኑ በሚሰራው ስራ አረጋግጧል። ህዝባችንና አገራችን እዚያው በዚያው በጦርነትና በረሃብ፣ እንዲሁም በመፈናቀል ፍዳቸውን እንዲያዩ የሚያደርግ አዲስና ወጣት መሪ ነው ያጋጠመን። ከዚህም በላይ ደግሞ አገራችንን ለአረብ ቱጃሮችና ለኢምፔሪያሊስት ኃይሎች በመቸብቸብ ላይ ይገኛል። የነፃነቱንና የብልጽግናውን መንገድ ውስብስብ እያደረገውና፣ ህዝባችንም ለዝንተ-ዓለም በጨለማ ዓለም ውስጥ እንዲኖር ሁሉንም ነገር በማመቻቸት ላይ የሚገኝ ነው።”

የዶ/ር ፈቃዱን ጽሁፍ ለሚያነብ የሚያጭረው ጥያቄ፤ ዶ/ር ፈቃዱ የትኛው ዓለም ውስጥ ነው የሚኖሩት የሚያሰኝ ነው። የዶ/ር ዐብይ አመራር፤ ዶ/ር ፈቃዱ ከሚሉት ፍፁም የተቃረነ ነው። ዶ/ር ፈቃዱ ሃሳባቸውን ሲያቀርቡ፤ አንድም ያቀረቡት ጭብጥ ላይ የተመሰረተ መረጃ የለም። እንዲህ ዓይነት ጽሁፍ፤ እንኳን ዶ/ር የሚል የትምህርት ማዕረግ ያለው እና፤ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርትን ያጠናቀቀ ሰው እንኳን የማይጸፈው ዓይነት ጽሁፍ ነው። ዶ/ር ፈቃዱ፤ ስሜታዊ ከመሆን አልፈው፤ ውስጣቸው ጥላቻ የተጋገረበት ለመሆኑ ጽሁፋቸው ያሳብቃል። ፋሽስትና አረመኔ ያሉትን መሪ ነው “ለትግሬ ብሔረሰብ የሚቆረቆር” እያሉ የሚከሱት። 

ዶ/ር ዐብይ፤ ወያኔን ከሥልጣን ለማስወገድ፤ ዋጋ የከፈሉና በሕይወታቸው ቆርጠው፤ የታገሉ ለመሆናቸው ነጋሪ አያሻውም። ከዛም አልፈው፤ በወያኔ የሚጋለቡ መሪ ላለመሆን፤ እንዴት በብልሃት፤ የወያኔን ጉልበት ከደህንነቱ፤ ከፖሊስ፤ እንዲሁም ከመከላከያው፤ እየሸረሸሩ፤ የሥልጣንና የጉልበት ወንበሩን ከሥሩ እንዳነሱበትና በመጨረሻም ወያኔ ነቅሎ መቀሌ ለመግባት የተገደደበትን ሁኔታ እንደፈጠረ ለዶ/ር ፈቃዱ እንግዳ ይሆን ወይ ብሎ መጠየቅም ያስገድዳል። ያለፉት አራት ዓመታት ሂደታችንን ዞሮ ብሎ በቅንነት ላጤነ፤ ዶ/ር ዐብይ ወያኔ ናፋቂ ናቸው ሲባል፤ የስላቅ ፈገግታ ያጭርበታል ብዬ እገምታለሁ። የሃገር መሪ በመሆናቸው፤ ዶ/ር ዐብይ ለትግራይ ሕዝብ የመቆርቆርም፤ የትግራይን ሕዝብ የልብ ትርታ የማዳመጥ ሃላፊነትም ግዴታም አለባቸው። የዶ/ር ዐብይ ለትግራይ ሕዝብ መቆርቆር፤ ዶ/ር ፈቃዱን የሚያበሳጫቸው፤ እሳቸው ለትግራይ ሕዝብ ካላቸው አሉታዊ አመለካከት ለመሆኑ፤ ጠንቋይ መሆንን አይጠይቅም። 

ለመሆኑ ዶ/ር ዐብይን ብሔራዊ ባሕሪ የሌላቸው ማለት ምን ማለት ነው? ስለኢትዮጵያ ሌት ተቀን ከማስተማር፤ ኢትዮጵያዊ የሆኑ ተቋማትን ከመገንባት አልፈው፤ ወጣቱ ትውልድ በኢትዮጵያዊነት እንዲኮራ፤ ከትውልድ ትውልድ ሊተላለፉ የሚገባቸው ታሪካዊ ቅርሶችን፤ በተገቢ ሁኔታ በማደራጀት እና ቀጣዩ ትውልድ እንዲማርበት ከማድረግ ውጭ ምን ዓይነት ብሔራዊ ባሕሪ ነው የተፈለገው? እድሜያቸው 15 ዓመት ከሆነ ጊዜ ጀምረው በትግል ያለፉት እኝህ ሰው፤ የሃገራቸውን ድንበር ለማስከበር በጦር ግንባር በወታደርነትም ሆነ፤ የሃገር መሪ ከሆኑ በኋላ፤ ሕይወታቸውን ለሃገር አሳልፈው ለመስጠት ከመሰለፍ ውጪ ምን ዓይነት ብሔራዊ ባሕሪ መላበስ ነበረባቸው? ከካቢኔ አባላት እስከ ቀበሌ አመራር ድረስ፤ ከመንደርተኝነት ወጥቶ በኢትዮጵያዊነት ስሜት ሃገሩን እንዲመራ ከመጣር ሌላ፤ ምን ዓይነት ብሔራዊ ባሕሪ ነው የሚጠበቀው? በትምህርት አሰጣጥ እጅግ የተጎዳችውን ሃገርና ትውልድ፤ በተሻለ የትምህርት አሰጣጥ፤ ትውልዱ እውቀቱን እንዲያጎለብት ጠንክሮ ከመስራት ውጭስ ምን ዓይነት ብሄራዊ ባህሪ ነው የሚጠበቀው? የሃገራችንን የእርሻ ምርት ለማዘመን እና ሃገራችን በዝናብ ላይ ብቻ ከተመረኮዘ የእርሻ ምርት እንድትላቀቅ እና እራሷን እንድትችል ለማድረግ የሚጥር የሃገር መሪ ምን ዓይነት ብሔራዊ ባሕሪ እንዲኖረው ይጠበቃል? ዶ/ር ዐብይ በዓለም አቀፍ ደረጃ በብዙሃን መገናኛም ሆነ በምዕራባውያን ወከባ ያጋጠማቸው፤ እንዲሁም በዓለም ፍርድ ቤት “በዘር ማጥፋት” ክስ ይመሰረትበሃል እየተባለ ዛቻ የሚቀርብባቸው፤ ሃገሪቱን “ለኢምፔሪያሊስት ጥቅም አሳልፌ አልሰጥም” በማለታቸው አይደለምን? የዶ/ር ፈቃዱ መረጃ ምንድነው? በጽሁፋቸው ይህ ነው ብለው የጠቀሱት አንድ ምሳሌ እንኳን አለመኖሩ፤ ጽሁፋቸው በጥላቻ ላይ የተመሰረተ እንጂ በጭብጥ መረጃ ያልተመሰረተ ለመሆኑ ማሳያ ነው። 

ዶ/ር ፈቃዱ፤ በጽሁፋቸው፤ ስለኢትዮጵያ የትምህርት አሰጣጥ፤ ስለ ግሪክ ፍልስፍናና ሥልጣኔ፤ ስለጀርመን፤ ስለ ጨቋኝና ተጨቋኝ መደብ፤ እንዲሁም በርካታ ከርዕሳቸው ጋር የማይገናኝ እና፤ ምንም ዓይነት መረጃ የሌለው፤ የግል ትንታኔያቸውን ካጋሩን በኋላ፤ “ባለፉት አራት አመታት በፖለቲካ ስም የሚካሄደውን ድርጊት ስንመለከት የአቢይና የግብረአበሮቹ ፖለቲካ ህዝባዊ ቅራኔን ከማጥበብ ይልቅ የሚያስፋ፣ ሰላምን ከማስፍን ይልቅ ብጥብጥን የሚጋብዝ፣ በተለይም በዕድሜ የገፉ ሰዎች በፍርሃት ተውጠው እንዲኖሩ የሚያደርግ ነው። እንደተነገረን ከሆነ አቢይ ዶክትሬቱን የሰራው ሰላምና እርቅ (Peace and Reconciliation) በሚለው ዙሪያ ነው። ይህም ማለት በአገራችን ምድር ውስጥ ሰላም እንዲሰፍንና ይቅር በመባባል በአንድነት ለስራ እንዲነሳሳ ማድረግ ማለት ነው።” ይሉናል። ዶ/ር ፈቃዱ ግን፤ ይህንን ክስ ሲያቀርቡ፤ ጠብታ መረጃ እንኳን አላቀረቡም። የሆነውና እየሆነ ያለው ግን ከሳቸው ክስ በተቃራኒ ነው። ዶ/ር ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ ጀምሮ፤ የሚሰብኩን ብቻ ሳይሆን፤ በሥራ ላይ እንዲውል የሞከሩትም የእርቅ ባሕላችንን ነው። በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶች ሲነሱ፤ ሽማግሌዎች ችግሩን በእርቅ እንዲፈቱ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ከፍተኛ ጥረት አድርገዋል፤ ለዚህም በሶማሌያ እና በአፋር ክልል፤ በኦሮምያ ክልል፤ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፤ በሲዳማ፤ የተደረጉ የእርቅ ጉባኤዎችን እንደምሳሌ ማንሳት ይቻላል። በአንድ ወቅት ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ፤ ዐብይን ደካማ እያሉ ሲወቅሱት የነበረው፤ ዶ/ር ዐብይ ጉልበትን ከመጠቀም፤ ይልቅ ሃገራዊ የእርቅ እሴታችንን እንድንጠቀም፤ በመጣራቸው ነው። በተደጋጋሚ እንዳዳመጥነው፤ ዶ/ር ዐብይ “እባካችሁ መንግሥትን አምባገነነ አታድርጉ፤ ወደ ነበርንበት የመገዳደል አዙሪት አንመለስ፤” ወዘተ በማለት የተለያዩ የፖለቲካ ቡድኖች ሕግ እንዲያከብሩ ሲማፀኑ እንጂ፤ በአንድም ወቅት፤ በሕዝባችን መሃከል ቅራኔ እንዲፈጠር የተናገሩበት ወይንም የሰበኩበት ወቅት የለም። አለ ካሉ፤ ከሳሾቻቸው መረጃውን ይፋ ያድርጉ።  

ዐብይ ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላም ነው የሰላም ሚኒስትር በሚኒስትር መሥሪያ ቤትነት ተቁቁሞ፤ በተለያዩ አካባቢዎች በእርቅ ችግሮች እንዲፈቱ የተሞከረው። ከዛም አልፎ፤ የሰላምና የእርቅ ኮሚሽንን በአዋጅ በማቋቋም፤ ኮሚሽኑ እዚህ ግባ የሚባል ሥራ ሳይሰራ፤ የሥራ ጊዜውን የፈፀመው። ከዚህም አልፈው፤ ዶ/ር ዐብይ “መደመር” የሚለውን የእርቅ “ፍልስፍና” በሕዝብ ለማስረጽ መጽሐፍትን ጽፈው ለሕዝብ አበርክተዋል። በነገሬ ላይ፤ ከመጽሐፎቹ የተገኙትን ገቢዎች ለበጎ አድራጎት ሰጥተዋል። ይህ የጨካኝ መሪ መገለጫ አይመስለኝም። በኢትዮጵያ ውስጥ፤ ስለእርቅ፤ እና የእርቅ እሴታችንን እንድንጠቀም በተደጋጋም የጎትጎተ እንደ ዶ/ር ዐብይ ዓይነት መሪ እስካሁን የለም። 

የዶ/ር ፈቃዱ፤ እጅና እግር የሌለው ጽሁፋቸው ዋናው ዓላማ ወደ ዘር ፖለቲካቸው እንዲመራቸው ለመሆኑ ጽሁፋቸው ይጠቁመናል። “የአቢይ ዋና ዓላማም በተለይም የኦርቶዶክስ ሃይማኖትን መዋጋትና አማራ የሚባለውን ብሄረሰብ ማውደም ነው። በዚህ ዐይነት አካሄዱም አቢይ ለማረጋገጥ የቻለው የእነ መለስ ዜናዊንና የስብሃት ነጋን ዋና ዓላማ ነው ማለት ይቻላል።” ሲሉ ላቀረቡት ክስ ምንም ዓይነት መረጃ የለም። በተቃራኒው ግን ዶ/ር ዓብይ አሕመድ፤ በሁለት ተከፈላ አደጋ ላይ የነበረችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ወደ አንድ ያመጡ መሪ ለመሆናቸው በቂ መረጃ አለ። የየትኛውም የሃይማኖት ተከታይ፤ ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን አክብሮት እንዲኖረው የመከሩም መሪ ናቸው። የዶ/ር ዐብይ አመራር የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን እያጠቃ ነው የሚለው ክስ መሰረተ ቢስ ከመሆኑም በላይ ቤተክርስቲያኒቱን፤ የፖለቲካ ካባ በማልበስ፤ የራሳቸውን የፖለቲካ ጥቅም ለማራመድ፤ የወጠኑ ሰዎች የሚያራምዱት የፖለቲካ ቁማር ነው። በዐብይ አስተዳደር ነው፤ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን፤ መሪዎች የከተማ ባለሥልጣናትንም ሆነ የክልል መሪዎችን በመጥራት ያነጋገሩትና ባለሥልጣናትን የመገሰጽም “ጉልበት” ያገኙት። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያንን ለፖለቲካ በመጠቀም የሚገኝ ምንም ዓይነት የፖለቲካ ትርፍ እንደማይኖር፤ ሁሉም ሊገነዘብ ይገባዋል። 

 በተቀረው የዶር/ ፈቃዱ ሃሳብ ላይ አስተያየት መስጠት ጊዜ መግደል ነው፤ ምክንያቱም ምንም ምሁራዊ ሥርዓትን ያልተከተለ፤ በአሉባልታ በጥላቻና ከማህበራዊ ሚዲያ በተለቃቀመ ቅራቅምቦ የተሞላ መረጃ ቢስ ጽሁፍ ከመሆኑም አልፎ፤ ዋናው ዓላማ፤ በዐብይ አሕመድ አመራር የአማራው ሕዝብ ላይ ጥቃት እየተፈፀመ ነው የሚል መሰረተ ቢስ ክስ በማራገብ፤ በኦሮሞ እና በአማራ ሕዝባችን ውስጥ ቅራኔን ለማስፋት እና፤ አሁን ከተጀመረው የዲሞክራሲያዊ ሥልተ ስርዓት ውጭ፤ በነውጥ ሥልጣንን ለማስለቀቅ የሚደረግ ቅስቀሳ ነው። እራሱ በከፊል አማራ የሆነን መሪ፤ አማራ የሆኑ ሴት አግብተው፤ ከአማራ የተወልዱ ልጆች ያፈሩን መሪ፤ አማራው ሕዝባችን ላይ ጥቃት እንዲፈፀም ለምን ይፈልጋሉ? በመጀመሪያ ደረጃ፤ አማራን ማጥፋት ይቻላል ብሎ ማሰብ እራሱ፤ የጨነገፈ አስተሳሰብ ነው። 

አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር አለ። በአማራው ሕዝባችን ላይ ከፍተኛ ጥቃት ተፈጽሟል እየተፈጸመም ነው። ይህ ግን በመንግሥት የተፈጠረም ሆነ፤ በመንግሥት የሚበረታታ አይደለም። ይህ ማለት ግን፤ በተለያየ የመንግሥት እርከን ውስጥ የተሰገሰጉ ጽንፈኞች የሉም ማለት አይደለም። በአማራው እና በኦሮሞው ሕዝብ መካከል ችግሮችን በማስፋት እና ሁለቱ ሕዝቦች የማይታረቅ ቅራኔ ውስጥ እንዲገቡ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ ነው። ይህንንም ለማሳካት፤ በመንግስት ውስጥ የተሰገሰጉ ሰዎች ለመኖራቸው መረጃዊች ያሳያሉ። መንግሥት በተለያዩ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን እና በሺህ የሚቆጥሩ የብልጽግና አባላትን፤ ከድርጅቱ ማባረሩን ገልጽዋል። ይህ በቂ አይደለም። መንግሥት አቅሙን በማጠናከር፤ በተለያየ በወንጀል ድርጊት የተሰማሩና ወንጀልና ሁከት እንዲፈጠር ድጋፍ የሚሰጡ የመንግሥት ባለሥልጣናት ላይ እርምጃ ሊወስድ ይገባዋል። መንግሥት ሸኔ በተባለ ጽንፈኛ ድርጅት እና እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፤ የጉሙዝ ሕዝብ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ በሚባለው ጨካኝ ቡድን በአማራ፤ በሽናሽን እና የተለያዩ ብሄሮች ላይ እየተፈፀመ ያለውን ጥቃት ለመከላከል በሚያደርገው ዘመቻ፤ የእነዚህ ጽንፈኛ ኃይሎች ደጋፊ የሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናትንም ተጠያቂ ሊያደርግ ይገባዋል።  

ቀደም ባለው ጽሁፍ እንደገለጽኩት፤ ሃገራችን ዘርፈ ብዙ ችግር አለባት። ብዙ ወሳኝ የተባሉ ተቋማት እንደ አዲስ እየተገነቡ ነው፤ ገናም መገንባት አለባቸው። የደህነንቱ፤ መከላከያውም ሆነ የፖሊሰ ሰራዊቱ፤ ገና በቂ አቅም ያልገነባ ከመሆኑም በላይ በአንፃሩ፤ የሃገራችን ጠላቶች፤ በገንዘብ፤ በትጥቅ፤ በሰው ሃይል፤ በደምብ የተደራጁ ለዓመታትም ነውጥ ለመፍጠር የተዘጋጁ ናቸው። ይህ የለውጥ ሂደት ክግብ እንዲመታና ከትውልድ ትውልድ ሊተላለፍ የሚችል ስልተ ስርዓት ለመገንባት፤ የሁላችንንም አስተዋጽኦ ይጠይቃል። በራሳቸው የጎጠኝነት ደዌ ታመው፤ በአቋራጭ ሥልጣን ለመያዝ ለሚውተረተሩ ሰዎች ዕድል አንስጥ። ሲፈለግ የዶ/ር ዐብይን የአማራ ዝርያ፤ ሲያሻ ደግሞ የኦሮም ዝርያ በመምዘዝ አስተዳደራቸው ተቀባይነት እንዲያጣ በየጎጡ የሚራገበው ክስ ምንም መረጃ ሊቀርብበት ያለቻለ መሆኑ፤ ክሱ መሰረት የለሽ እንደሆነ ጠቋሚ ነው። በዘራቸው ሳይሆን፤ በሚሰሩት ሥራ ይመዘኑ። በቀበሌም ሆነ በወረዳ ወይም፤ በተለያየ የሥልጣን እርከን ለሚፈጠር ችግር፤ ዐብይን ብቻ ተጠያቂ እንደሆኑ ለማድረግ የሚደረግው ጥረት፤ አላማው አንድና አንድ ብቻ ነው፡ በአቋራጭ ሥልጣን መያዝ። በዘርና በጎጥ መቧደን ሳይሆን ዛሬ ሃገራችን የሁሉንም ልጆቿን ሕብረትና ሃገዝ ትፈልጋለች። ግን ሁሉም ለማገዝ ዝግጁ እንደማይሆን በእርግጠኝነት መናገር ይቻላል። በቅንነት ሃገራችንን ማገዝ የምንፈልግና የምንችል ግን ማንኛውንም ዜጋ በሥራው እንጂ በዘሩም ሆነ በሃይማኖቱ ሊመዘን አይገባውም ብለን እጅ ለእጅ ተያይዘን የሚጠበቅብንን እናድርግ። በመንግሥት በኩል እየተደረጉ ያሉ በጎ ሥራዎችን እያበረታታን፤ ስሀተቶችን እያረምን፤ ጥፋቶችን ደግሞ እያወገዝንና በቅንነት መፍትሔ እየጠቆምን፤ በነውጥ ሳይሆን በትብብር መንፈስ እንስራ። እንኳን ተከፋፍለን፤ ተባብረንም ልንወጣቸው የማንችላቸው ብዙ ችግሮች አሉብን። በአንድ ወቅት፤ ማይክ ዋለስ የተባለ የሲቤኤስ ጋዜጠኛ፤ የፊልም ተዋናዩን ሞርገን ፍሪመንን ዘረኝነትን እንዴት ማስቆም እንችላለን ብሎ ሲጠይቀው፤ ሞርገን ፍሪመን፤ አንተ ጥቁሩ ሞርገን ብለህ መጥራትህን አቁም እኔም ነጩ ማይክ ብዬ መጥራቴን ላቁም እና ከዛ እንጀምር ያለው ለእኛ ትምህርት ይሁነን። ማንም ለማንም ኢትዮጵያዊነትን የመስፈር ሥልጣን የለውም። ሰውን፤ በሰውነቱ ብቻ እንየው፤ በሥራውም ብቻ እንመዝነው።

ያለንበት ስልተ ስርዓት በዘር ፌደራሊዝም ሕገ መንግስት የሚመራ ሥርዓት ነው። ይህንን ዐብይ አሕመድ አልፈጠሩትም፤ እሳቸውም ሊቀይሩት አይችሉም። ዐብይ አሕመድ ሥልጣን ሲረከቡ፤ ሕገ መንግስቱን አከብራለሁ፤ በሕገ መንግሥቱም መሰረት እሰራለሁ ብለው ምለው ነው። ሕገ መንግሥቱ እንዲቀየር የሚፈልጉ በርካታ ሰዎች አሉ። እንዲቀየር የሚፈልጉ ሰዎች፤ ደግሞ ሕገ መንግሥቱ እንዲቀጥል የሚፈልጉ መኖራቸውን ይዘነጋሉ። መፍትሔው በሕገ መንግሥቱ ላይ ውይይት ማድረግ እና፤ በመጨረሻም ሕገ መንግሥቱን ለሕዝበ ውሳኔ ማቅረብ እና፤ የሕዝቡንም ውሳኔ መቀበል ነው። ለዚህም የምክክር ኮሚሽኑ ተቋቁሟል። ይህንን የብሔራዊ ምክክር ኮሚሽን በማጠናከር፤ ለተለያዩ ውስብሰብ ችግሮቻችን ተወያይተን መፍትሔ እንፈልግ። አንድ ግልጽ መሆን ያለበት ነገር አለ። ሁሉንም ሰው ማስደሰት አይቻልም። በዚህ የምክክር ኮምሽን መሳተፍ የማይፈልጉ ይኖራሉ። እነሱ ስላልፈለጉ ግን ሂደቱ መቋረጥ የለበትም። አብዛኛው ሕዝብ በተቀበለው እና ባፀደቀው ሕግ መገዛት የግድ ነው። አሁን ሃገራችን ያለችበት ሁኔታ የተረጋጋ ባለመሆኑ፤ አጋጣሚውን በመጠቀም ነውጥ የሚያራግቡ ሰዎችን ጆሮ እንንፈግ። የገበያ ግርግር ለሌባ ይመቻል ነውና፤ ሁላችንም ለሃገር ዘብ እንቁም። የኢትዮጵያን ባንዲራ ተጠቅልሎ የሙሾ ፖለቲካ በማራገብ እና ጎጠኝነትን በመስበክ፤ ሃገር ማዳን አንችልም።

በኢትዮጵያ የፖለቲካ ባሕል ውስጥ አንዱ አስቸጋሪና አደገኛ አስተሳሰብ፤ መንግሥትን መቃወም ብቻ እንደ ሃገር ወዳድነት መታየቱ ነው። መንግስትን በመደገፍ በጎ ሥራ የሚሰሩና የሰሩ በርካታ ሰዎች አሉ። ለእንደዚህ ዓይነት ሰዎች ታርጋ እየለጠፍን፤ ሌሎች ብቃት ያላቸው ሰዎች ወደ ፖለቲካውም ሆነ የመንግሥት አስተዳደር ሥራ ውስጥ እንዳይገቡ እናሸማቅቃለን። ሃገርን እንወዳለን እያሉ ሃገራችንን የገደሉ በርካታ ዜጎች እንደነበሩና አሁንም እንዳሉ እንዘነጋለን። ለሃገር ምንም ዓይነት አስተዋጽኦ ያላደረጉና የማያደርጉ፤ የተመቻቸ ወንበራቸው ላይ ቁጭ ብለው፤ ለሃገር የሚደክሙ ሰዎችን፤ ሆዳም፤ ባንዳ፤ ወዘተ በሚል ተራ ስድብ፤ ለሃገር መውደቅ ተባባሪ ባለመሆናቸው ሊያሸማቅቁ ይሞክራሉ። እነዚህ በሃሳብ ድርቀት የተመቱ የፖለቲካ ድንክዬዎች፤ ለሀገር የሚሰንቁት ራዕይ ውድቀትን ነው። እነሱን መሰል ሰው እና እነሱ የሚፈልጉት የፖለቲካ ኃይል ሥልጣን ካልያዘ፤ ለሃገር ውድቀት ተግተው ይሰራሉ። የሃገር ፍቅራቸውን የሚለኩትም፤ ‘ሃገር ለእኔ ምን አደረገችልኝ’ ከሚል የመከነ የግል ጥቅም በመነሳት እንጂ፤ ሃገር የምትጠበቅባቸውን ለማድረግ በመዘጋጀት አይደለም። አቅም ስለሌላቸው፤ በሃሳብ አይሞግቱም፤ ሌላው ሃሳብ እንዳያቀርብ እና ሃሳብ እንዳይለዋወጥ፤ ጋሬጣ በመሆንም የሰዎችን ሃሳብ ለመግደል ይተጋሉ። አስተሳሰባቸው ሁሉ ተለጣፊ እና የመንጋ በመሆኑም፤ ሁሉንም እንደተለጣፊ የማየት የተንሸዋረረ መነጽራቸውን ያጠልቃሉ። ሁሌም የሚጎተጉቱት መንግስትን እንድንቃወም ብቻ እንጂ፤ በጎውን እያበረታታን፤ ጥፋቱን እያረምን በትብብር እንድንጓዝም አይደለም። በእንደዚህ ዓይነት “ሃገር ወዳድነት” ሥም የጨነገፈ ሃሳብ የሚያራምዱ ሰዎችን ልንሞግት እና ልንጋፈጥም ይገባናል።   

መንግሥት፤ ከተለያዩ የፖለቲካ ሃይሎችና ከሕዝብ የሚቀርብለትን አቤቱታ በማዳመጥ፤ ለሕዝብ የልብ ትርታ ምላሽ ይስጥ። የሚወሰዱ ማናቸውም ሕግ የማስከበር ሥራ፤ ግልፀኝነት ይኑረው። ግልፀኝነት የጎደለው እና ሕግን ያልተከተል ማንኛውም አሰራር፤ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። የሃሳብ ነፃነት ይከበር፤ ያ ማለት ግን፤ ሃላፊነት የጎደላቸው ጋዜጠኛ አክቲቪስቶች ነውጥ ሲስብኩ እና ግጭት ሲቀሰቅሱ ይታለፉ ማለት አይደለም። የትም ሃገር፤ ግጭት የሚሰብክንና ግጭት ለማነሳሳት ተግቶ የሚሰራን ሰው ማንም ይሁን ምን፤ በዝምታ አያልፍም። የንግግር ነፃነት፤ ሕዝብን በሕዝብ ላይ ለማነሳሳት መብት አይሰጥም። ይህች ሃገር የሁላችንም ነች። ቀናነት በጎደለው አካሄድ፤ ለፖለቲካ ትርፍ የሚሰሩ ሸፍጦች የሚጎዱት ሁላችንንም ነው። እሳት አንዳጁንም ይለበልባል። ጎጠኝነትን እንጠየፍ፡ እኛ ጎጠኝነትን ሳንጠየፍ፤ የምናራመደው የጎጥ ፖለቲካ ወደ ቁልቁል ይወስደናል እንጂ ሃገር አያድንም። አስተያየት የሰጠሁባቸው ጸሃፊዎች፤ መድሃኒት ነው ብለው የጠቆሙን አደገኛ ጎጣዊ አስተሳሰብ፤ “በአላዋቂ” ሃኪም ለበሽተኛ እንደሚታዘዝ መድሃኒት ነው። በኢትዮጵያዊነት ካባ ተጠቅልሎ የሚሰበክ ጎጠኝነት ለኢትዮጵያ ጥፋት እንጅ ፈውስ ሊሆን አይችልምና እንጠንቀቅ።

 ቸሩ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ።

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here