spot_img
Wednesday, June 12, 2024
Homeነፃ አስተያየትየኢትዮጵያ ሕዝብ ለመብቱና ነፃነቱ ለጋራ ብሄራዊ ዓላማ ሲል በጋራ እንዲቆም አደራ እንላለን

የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመብቱና ነፃነቱ ለጋራ ብሄራዊ ዓላማ ሲል በጋራ እንዲቆም አደራ እንላለን

ከኢትዮጵያ የውይይትና መፍትሄ መድረክ(EDF) የተሰጠ መግለጫ

ያለንበት ጊዜና ወቅት ይበልጥ ይፋ አደረገው እንጂ የዘር ፖለቲከኞች፤ ጠባብ ብሄርተኞች፤ የብሄር ጽንፈኞችና ተራው የኔ ነው የሚሉ ፀረ ኢትዮጵያና ጸረ ኢትዮጵያዊነት ኃይሎች የኢትዮጵያን መንግስት ሥልጣን እየተፈራረቁ ሲይዙ፤ ሲገዙና ኢኮኖሚውን፤ ባጀቱንና የተፈጥሮ ኃብቱን ለቡድን ጥቅም ሲያውሉት አመታት አሳልፈዋል።

አንዱ መሰረታዊ ክስተት በኢትዮጵያ ረዢም ታሪክ ተዋልዶና ተጋብቶ በአንድ አገር ጥላ ስር የኖረውንና በጨዋነቱ የሚታወቀውን ሕዝብ ከገነባው አብሮነትና ከገመደው አንድነቱ እንዳናጉትና አገር አልባ እንዳደረጉት ግልጽ መሆኑ ነው።

በተለይ ጠቅላይ ሚኒስቴር ዐብይ አህመድ የዛሬ አራት ዓመት ሥልጣን ከጨበጡ ወዲህ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለዘመናት በጋራና ባንድነት ኖሮ የማያውቅ አስከሚመስል ድረስ፤ የዕርስ በርስ መጠፋፋትና የግጭት ሰለባ እንዲሆን ተደርጓል። ያለፉት አራት ዐመታት የአገዛዝ ታሪካቸውና ጠቅላይ ሚንስትሩ በቅርቡ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት “በአዲስ አበባ ከተማ ኦሮሞ ጠልነት አለ” ብለው የተናገሩት ንግግር ሃላፊነት የጎደለው እና ጥላቻን ፈጣሪ ሆኖ አግኝተነዋል።

በጥቅል ስናየው ሰላም ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለይ ደግሞ ለኢትዮጵያ ግዛታዊ አንድነትና ነጻነት

ከፍተኛ ሚና በተጫወተው በዐማራው ህብረተስብ ላይ የጥፋት ዕጃቸው ያነጣጠረ መሆኑን ብዙ ታዛቢዎችና የአገር ተቆርቓሪዎች በማስተጋባት ላይ ይገኛሉ። ድርጅታችን-EDF- ይህንን ብሂል ትክክል አይደለም ለማለት የሚደፍርበት መስፈርት የለውም።

ለመብትና ለነፃነት የሚደረግ ትግል የሰው ልጆች የሰውነት መለኪያ ነው።

ለወላጆች የልጆቻቸው፤ለልጆች፤ የወላጆቻቸው እንዲሁም የትውልዱ፤ እጣፈንታ በዘረኞችና በቂመኞች መቀጠፉን ዕለት በዕለት ማየት ምንኛ ነፍስንና ሥጋን የሚያሰቅቅ ይሆን? እያልን እንጠይቃለን። የሰቀቀንና የስጋት መሰረት ይህ ካልሆነ ከቶ ምን ሊሆን ይችላል! ??

በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የሚመራው የብልጽግና ፓርቲ አገዛዝ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከትርፉ ሳይሆን ከጉድለቱ በሚያወጣው የግብር /ታክስ/ ገንዘብ የሚያስተዳድረው መንግስትና ያደራጀው የፌደራል መከላከያም ሆነ የክልል ልዩ ሐይል፤ አገሪቱንና ሕብረተሰቡን ከማናቸውም ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ጉዳቶች እንዲጠበቅ፤እንዲከላከል፤ወደላቀ የዕድገት ደረጃ በተስፋና በፍቅር እንዲያሸጋግር እንጂ፤ የአንድ ፖለቲካ ፓርቲ ወይንም ቡድን ወይንም ግለሰብ መሳሪያ ሆኖ ተስፋችንን በማመንመን ህይወታችንን እንዲያመሰቃቅለው አይደለም።

የዐማራው ዘውግ ተኮር እልቂት

June 18/19, 2022, 1,500 በላይ በሚገመት የዐማራ ሕዝብ ላይ በወለጋ፤ ኦሮምያ ክልል የፈጸሙትን አሰቃቂ እልቂት ለማውገዝና ይህንን ወንጀል የፈጸሙት ግለሰቦች፤ ቡድኖች፤ መሪዎች፤ ተባባሪዎችና የበላይ አካላት በአስቸኳይ በሕግና በህዝብ ሊጠየቁ ይገባል ብለን እናምናለን።

በድርጅታችን እምነትና ግምገማ የኢትዮጵያ የፌደራል መንግሥት ባለሥልጣናትና የኦሮሞ ክልል መሪዎች ይህንን ዐማራ ተኮር እልቂት በማጣራት ወንጀለኞችን ለፍትህ ለማቅረብ የሚያበቃቸዉ፤ የሞራል ብቃትና ሰብአዊ ርህራሄ አላገኘንባቸዉም።

ስለሆነም፤ ድርጅታችን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሸል ባርትሌት የዐማራውን ጭፍጨፋ በሚመለከት ከመንግሥትና ከፓርቲ ባለሥልጣናት ቁጥጥር ውጭ የሆነ እና በነጻነትና በችሎታ የተዋቀረ መርማሪ ቡድን እንዲመሰረትና በአስቸኳይ ጥናትና ምርምር አካሂዶ በሃላፊነት የሚጠየቁትን ግለሰቦች ለፍርድ ያቅርብ የሚለውን ሐሳብ፣ድርጅታችን ይደግፋል።

ስለሆነም ከኢትዮጵያዊያን ባለሞያዎች የተዉጣጣ መርማሪ ቡድን በአስቸኳይ እንዲቋቋም እናሳስባለን። የሚሰየሙት ግለሰቦች በሞያቸው የታወቁና የሕዝብን አመኔታ የሚያንጸባርቁ እንዲሆኑ እናሳስባለን።

ኢትዮጵያ በዐብይና በሺመልስ አብዲሳ አስተሳሰብ ውስጥ የምትወሰን ሳይሆን በራሷ የዘመናት ህልውና ያላት እውነት ናት

በመጨረሻ፤

· የኢትዮጵያ የውይይትና የመፍትሄ መድረክ/EDF/በዐማራው ሕዝብ ላይ የተካሄደውን ብሄር ተኮር እልቂት በጥብቅ ያወግዛል። ወንጀሉን የፈጸሙት ግለሰቦች፤ መሪዎችና ድርጅቶች በሃላፊነት እንዲጠየቁ ይጠይቃል። ለሟች ቤተሰቦች፤ ወዳጆችና ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ መፅናናትን ይመኛል።

· ድርጅታችን የኢትዮጵያና የኦሮሞ ክልል መንግሥታት ለተጎዱት ካሳ እንዲከፍሉ ይጠይቃል።

· ድርጅታችን የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ከፍተኛ ኮሚሽነር የሰጡቱን መግለጫ ያደንቃል። በተመሳሳይ፤ የዐለም አቀፍ ሰብአዊ መብት አስከባሪ ድርጀቶች ይህንን በንፁሀን ዜጎች ላይ የተፈጸመ አሰቃቂ የዘር ጭፍጨፋ ወንጀል በሚመለከት ግዴታቸዉን በመወጣት ድርጊቱን እንዲያወግዙ ጥሪ ያደርጋል።

· ድርጅታችን የዐብይ አህመድ መንግስት በወለጋ በሰጋት ላይ የሚኖረውን የዐማራውን ሕብረተሰብ፣ ህይወቱንና ንብረቱን የጥፋት ተልዕኮ ካላቸው ፀረ-ዐማራ ሃይሎች የመጠበቅና የመንከባከብ ግዴታው የሆነዉን መንግስታዊ ሃላፊነት ባለመወጣቱ ምክንያት፣ የዐብይ መንግሥት እና በሽመልስ አብዲሳ የሚመራው የኦሮሞ ልዩ ኃይልና ፖሊስ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ በክልሉ ጥላቻ እንዲነግስና እልቂቱ እንዲባባስ አድርጓል ለማለት እንገደዳለን።

EDF- የኢትዮጵያ ተቋማዊና መዋቅራዊ ተግዳሮቶች ግዙፍ መሆናቸውን በተደጋጋሚ በማሳሰብ አማራጭ የመፍትሄ ሀሳቦችን ሲያቀርብ ቆይቷል። የኢትዮጵያን ሕዝብና በመላው ዓለም የሚኖረውን ዲያስፖራ ለማሳሰብ የምንፈልገው በዐማራው ሕዝብ ላይ የተፈጸመው እልቂት እንዳይደገም የምንመኝ፤ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት የዜግነት መለያዎች የምናምነው ሁሉ በተለይም የተደራጃችሁ አብሮነትን ፈላጊ ሃቀኛ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ንቅናቄዎች፤ ህዝባዊ ድርጅቶችና የሙያ ማህበራት ለህዝባችን በዚህ መራራ አደጋ ወቅት መድረስ ዜግነታዊ ግዴታችሁ ነው። የጋራ ህብረት መስረታችሁ በመተጋገዝና አገርን በማዳን መንፈስ ሁሉን አቀፍ የሆነ የዴሞክራሲያዊ የሽግግር መንግስት ይመሰረት ዘንድ ጥያቄው ወደህዝባችን ዘልቆ እንዲገባ ታሪካዊ ሀላፊነታችሁን እንድትወጡ መድረካችን /EDF/ከአደራ ጭምር አበክሮ ያሳስባል።

ኢትዮጵያ ክሁሉም ልጆቿ ጋር ለዘላለም በሰላም ትኑር!!!

June 23, 2022

የኢትዮጵያውያን የውይይትና መፍትሄ መድረክ (Ethiopian Dialogue Forum – EDF)

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here