አልማዝ አሸናፊ
ዊሚንግ, አሜሪካ
Imzzassefa5@gmail.com
በመጀመሪያ ይህንን ሳቀርብ ስለራሴ ግልፅ ማደርገው እኔ ኢትዮጵያ ውስጥ ከዘመዶች በስተቀር ምንም ሀብትና የግል ጥቅም ያለኝ ሴት እመቤት አይደለሁም:: ካለው መንግስት ጋር ሆነ ከክልሎች አስተደዳረሮች የሚያሞዳሙደኝ ግኑኝነትና ዝምድና የለኝም:: ይህ መንግስት ሲመጣም ያለፈው ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ ኢትዮጵያዊነት መንግስት ከአሸዋ እንደተሰራ ማማ ሲፈርስም ከእሩቅ ሆኜ ከመስማትና ከማንበብ ከቅርብ ሆኜ አላየሁም:: ኢትዮጵያን ከረገጥኩ አመታት አልፈዋል:: ሄዶ የመኖርም እቅድም ሆነ ሕልም የለኝም:: ስለጠቅላይ ሚኒስትሩ የምለው ከእሩቅ ሆኜ የምሰማውንና የማነበውን አመዛዝኜ ካለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ጋር በማነፃፀር አብዛኛው ስራቸው መልካም መሆኑን መገንዘብ በመቻሌ ነው:: የኢትዮጽያ ችግሮች በአንድ ሰው ወይም በእንድ አስተዳደር ወይም በአምስት ዓመት ይፈወሳሉ የሚል ብዥታም የለኝም:: ስለዚህ አንባቢ እንደፈለገችው ወይም እንደፈለገው ልትረዳ ወይም ሊረዳ ይችላል:: በዚህ አቅጣጫ እይው ወይም እየው ለማለትም አልጥርም:: ምክንያቱም እኔም የአመለካከቴ ነፃነት እንዲጠበቅ ስለምፈልግ የአክብሮትን መስመር ያልጣሰ የሰዎች የአስተሳሰብ ነፃነትን ስለማከብር ነው::
የአሁኑን የኢትዮጵያ ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ አህመድን ለጎሳዎች ውዝግቦች ተጠያቂ ለማድረግ ያለው ሩጫ በኢትዮጵያና በሕዝቦቿ የውስጥና የውጭ ጠላቶች የተቀናጀና የተዶለተ ሴራ መሆኑ እየታወቀ በሶሻል ሚዲያዎች የሚራገበው ክስ አዳማጭ ማግኘቱ ምን ያህል ሰዎችን ለግጦሽ እንደወጡ ከብቶች መንዳት እንደሚቻል መገመት አይሳነኝም:: ጥያቄው ኢትዮጵያውያን በተለይ ቀለም የቀመሰው አንብቦ ማስተዋልና እድል ቢሰጠው አገር ሊመራ ይችላል ተብሎ የሚገመተው የማህበረ ሰብ ክፍል እውነትን ከውሸት አበጥሮ መለየት እንዴት ተሳነው? ነው:: በተለይ በዲያስፖራ የሚኖሩበትን አገራት ዜግነት አግኝተው ምቹ ኑሮ እየኖሩ ደሃውን የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰላም ሲነሱት ማየት እነዚህ ጎሰኞችና ፅንፈኞች በእውነትስ ስብእና አላቸው? ወይስ ያሰኛል:: አንድ በዚህ ነጥብ ላይ የኢትዮጵያ መንግስት ያለበት ድክመት የኢትዮጵያን ዜግነትን ክብር አለማስጠብቁና አለማስከበሩ ነው:: ይህን ስል ምን ማለቴ ነው?
ትውልደ ኢትዮጵያዊ መሆንና የኢትዮጵያ ዜጋ መሆን ልዩነት አላቸው:: ትውልደ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ከኢትዮጲያ ዜጋዎች እኩል መብት ሊሰጠው አይገባም:: ማንኛውም አገር የዜግነት መብትን እጅግ ያስከብራል:: የኢትዮጵያ መንግስትም ዜጋ ያልሆኑ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ ዜግነት የሚሰጠው መብቶችና ግዴታዎች ሳይሰጣቸው በመንግስት ቸልተኝነት እንደዜጋ ሆነው በአገርቷ የውስጥ ጉዳዮች ጣልቃ እንዲገቡ አድርጏል:: የእነዚህ የኢትዮጵያ ዜግነታቸውን በሌሎች አገሮች ዜግነት የለወጡ ግለሰቦች ጣልቃገብነት ኢትዮጵያ ላጋጠማት የፖለቲካ አስቀያሚ ችግሮች በተለይ ዛሬ በአሁኑ ሰዓትና ደቂቃ ጎልቶ ለሚታየው የኦሮሞና የአማራ ጎሳ ሽኩቻ ታላቅ ሚና ተጫውቷል:: እየተጫወተም ነው:: ጥሩ ምሳሌ የሚሆነው ከአሜሪካ ሚኒሶታ ግዛት ተነስቶ በአማራ ኢትዮጵያውያን ላይ የኦሮሞ ፅንፈኞች ጥላቻ እንዲሲፋፋ እሳቱን ለኩሶ ቤንዝን ሲያርከፈክፍበት የነበረው አክራሪ የጥላቻ ፅንፈኛውን ጀዋር “ከበቡኝ” መሐመድ ሊጠቀስ ይገባል:: ይህንን ስብእና የተሳነውን ምንም የማይገባቸውን ኦሮሞ ኢትዮጵያዊያንን አማራ ጠላትህ ነው መሬትህን ቀምቶሃል አዲስ አበባ የኦሮሞ ነች ኦሮሞ ነህ እንጂ ኢትዮጵያዊ አይደለህም እያለ ከውጭ ሆኖ በኢትዮጵያ ላይ ረብሻ ሲያስነሳ የነበረውን በልመና ገንዘብ በGOFUNDME የሚተዳደረውን ያለገደብ ኢትዮጵያ እንዲገባ ጊዜያዊ የነበረው የዶ/ር አቢይ አህመድ አስተዳደር መፍቀዱ የኢትዮጵያን የዜግነት ሕግ እለማስከበር ነው:: ኢትዮጵያም ከገባ በሗላ ለዜግነት ሕግ ያሳየው ንቀት ባደረገው “የከበቡኝ” ጥሪ ሊገለፅ ይችላል:: በእሱ ምክንያት በአገሪቱ ውስጥ የተከሰተው የጎሳ ግድያና የንብረት ውድመት ሌላ ተራ ሰው ቢሆን የሞት ወይም የእድሜ ልክ እስር ቅጣት ይፈረድበት ነበር:: የሟቿች ደም ይበቀለው እንጂ መንግስትማ ነፃ ለቆት በሚኖርብት የአሜሪካ እገር ግዛት በመንግስት ዱጎማ በሚኖሩትና በመላው ዓለም እንደአይጥ እየተልከሰከሱ በሚገኙ ኦሮሞነትን በሚያዋርዱ ኦሮሞነትን በሚያሰድቡ ጠባብ የኦሮሞ ጎሰኞችና ፅንፈኞች እጨብጫቢነት እንደ ዝነኛ ሰው በስብሰባ መልክ ገንዘብ እየለመነ እየኖረ ይገኛል::
ይህ ሰው የአሜሪካንን ዜግነት አስወግዶ ያስጨፈጨፍውና ንብረቱን የያስወደመበት የኢትዮጵያ ዜግነት ማግኘቱን እስኪያረጋግጥ ድረስ በኢትዮጵያ የውስጥ ፖለቲካ ጉዳይ እንደገና ጣልቃ ከገባ ወተት ውስጥ እንደገባች እርጎ ዝንብ ተንጠልጥሎ ለሕግ መቅረብ ይገባዋል:: ይህ የስብእና ዱክማን የሆነው ብቻ ሳይሆን ማንኛውንም ትውልደ ኢትዮጵያዊነት በስተቀር የኢትዮጵያ ዜግነት የሌለው ሰው ከጃወራዊ ፀረ-ኢትዮጵያዊ ጥፋት መንግስት ማገድ አለበት:: በኢትዮጵያ አገር ውስጥ የፓለቲካ ጉዳይ ላይ በግልፅ ለመሳተፍ የሚፈልግ ሁሉ የኢትዮጵያን ዜግነት ማግኘት ይኖርበታል::
ፖለቲካን በገሃድ ለማራመድ ከፈለጉ እነዚህ ልውጥ ኢትዮጵያውያን የያዙትን የሌላ አገር ዜግነት ትተው የኢትዮጵያን ዜግነት ሲቀበሉ መንግስት ለሕዝብ ማሳወቅ ይኖርበታል እላለሁ:: ልማትንና ለአገር እድገት የሚያስፈልጉትን ስራዎች የሚሰሩ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የውጭ ዜጎች እንደማንኛውም የውጭ ዜጋ መታየት ይኖርባቸዋል:: ካስፈለገ እነዚህ ትውልደ ኢትዮጵያውያን የተወለዱበት አገረ ኢትዮጵያ ኖረውም ሆነ እየተመላለሱ የተወለዱበትን አገር እንዲያለሙና እንዲያሳድጉ መንግስት የማደፋፈርና የማነቃቃት ስራ እጅግ መስራት ይገባዋል:: ግን በኢትዮጵያ ፖለቲካ ጉዳይ ዜጋ ያልህነ ጣልቃ ከገባ በሕግ መጠየቅ አለበት::
በተጨማሪ ጀዋር “ከበቡኝ” መሐመድ የዛሬ ስድስትና ሰባት አመት በፊት በሚኔሶታ ስቴት ውስጥ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆኑትን ጠባብና ፅንፈኛ የኦሮሞ ጎሰኞችን ሰብስቦ ክርስትያኖችን በኦሮምያ አርደን ማባረር ይኖርብናል ብሎ የተናገረውን ማስታወስ እፈልጋለሁ:: ይህ የየመኔ ስደተኛ ወንድና የኦርቶዶክስ ሃይማኖት ተከታይ ኢትዮጵያዊት ልጅ በዚህ አነጋገሩ ዛሬ ምን ይሰማዋል? ለጥቅም ሲል ክርስትያን እናቱን ለምሳረድ እንዴት አሰበ? ለእናት ያልሆነ ልጅ ለሌላ ሰው ይጠቅማል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው:: ከ500 በላይ ሰዎችና ኢትዮጵያውያን እሱ በሚያራምደው የጎሳ ጥላቻ በስመ አማራ በተወለዱበት ወለጋ በአረመኔው ሸኔና ኦነግ ሲገደሉ እንደሰው ስብእና ተሰምቶት ይህ እግባብ አለመሆኑን የተናገረው ነገር አለ? የለም:: ተምሮ ደንቆሮ የሆነው የጀዋር “ከበቡኝ” መሐመድ ፖርቲ መሪ መራራ ጉዲና የ500 ንፁሃን ሰዎች ደም መፍሰስና ሕይወት መጥፋት ሳይሰማው የኦሮሞ ወጣቶች ተበድለው አውሬ መሆናተቸውን ለመሸፈን የጎሳ ፖለቲካውን ሲያራምድ ጀዋር ተናግሯል ወይ? በቀለ ገርባ በመላው የኢትዮጵያ ደሃ ላብ ተምሮ ዛሬ ያስተማረውን ሕዝብ በጎሳ ፅንፈኝነት ኦሮሞ ተበድሏል በማለት ሰላም ሲነሳ ማየት ድህነቱን በፖለቲካ ልመና ገንዘብ ለማሸነፍ መሯሯጡ ምን ያህል ቀፎ እንደሆነ ያሳየናል:: አብዛኛዎቹ ፖለቲከኞች ውሸታሞችና የግል ጥቅም አጠባቂዎች መሆናቸውን መረዳት አስፈላጊ ነው:: እነዚህ የኦነግ ሸኔ አራማጆች በኦፌኮ ፓርቲ ሕጋዊነት አሸባሪነትን ከለላ የሚሰጡ እራሳቸው አሸባሪዎች ናቸው:: መንግስት ሕግ ማስከበር ላይ ጠንከር ማለት ይገባዋል::
ጀዋር “ከበቡኝ” መሐመድም የአገር ማጥፋት ቅዠቱን አስወግዶ በኢትዮጵያ ሕዝብ አንድነት አምኖ ኢትዮጵያዊነትን ተቀብሎ በእጉል የጠባብ ኦሮሞ ጎሰኝነትና ፅንፈኝነት የተለከፉትን ጆሌዎቹን በጠበል ሆነ በእርኩስ መንፈስ ማስለቀቂያ EXORCISM አስፀድቷቸው ካመጣ በልማትና በእድገት መስክ የበደላትን አገር የጎዳውን ሕዝብ በአገልግሎት መካስ ይችላል:: ያኔ እውነትም ስብእና ትጎናፅፏል እንላለን::
በኢትዮጵያ ውስጥ ላለው የጎሳ ችግር እንደኦሮሞ ጎሳ ፅንፈኞች የአማራ የትግራይ የቤንሻንጉል ጉምዝ ወዘተ ጠባብ ጎስኞችና ፅንፈኞችም ተጠያቂዎች ናቸው:: በተለይ የኢትዮጵያ የጎሳ ጠባብነትና ፅንፈኛነት አራማጅ ኃያላን ኃይሎች የሆኑት የትግራይ የኦሮሞና የአማራ ዘረኞች ናቸው:: ለትግራይ ኢትዮጵያውያን ደንታ ሳይሰጣቸው በትግራያን ስም በመነገድ የእራሳቸውን ስልጣን በማጠናከር የሕዝብ ሀብት ሲዘርፉ የነበሩት የወያኔ ጅቦች አገራችንና ሕዝባችንን በማሰቃየት ዛሬ ላለንበት አስቀያሚ የጎሳነትና የፅንፈኝነት ፖለቲካ ቁሪኝት በትልቁ አስተዋፅኦ አድርገዋል:: የአማራ ኢትዮጵያውያንና የፋኖ ስም እየተጠቀሙ ለተፈናቀለውና ለተቸገረው አማራ ኢትዮጵያ ርዳታ በማለት በውጭም የተሰበሰበውን ገንዘብ ለጦር መሣሪያ መግዣ በማዋል በአማራ ስም የጎሳ ጦርነት ለማካሄድ የሚፈልጉ ፀረ-አማራ ኢትዮጵያውያን እንዳሉ ግልፅ ነው:: እነዚህ በአማራ ስም የሚነግዱና የሚያጭበረብሩ ፀብ ጫሪዎች መረዳት ያለባቸው የያዙት የጎሳ ጥላቻ ከኦሮሞና ከትግራይ ፅንፈኞች ጋር እንደሚያመሳስላቸውና የያዙት አማራ ኢትዮጵያውያንንና መላውን የኢትዮጵያ ሕዝብ የሚጠቅም ሳይሆን ሰቆቃውን የሚያበዛና የሚያዳብር አካሄድ መሆኑን ነው:: የሌላውን ጎሰኝነትንና ፅንፈኝነትን እየተቃወሙ የእራስን ጠባብ ጎሰኝነትንና ፅንፈኝነትን ትክክል አድርጎ ማየት የድንቁርና ምልክት ነው:: በዚህ አኳያ የኦሮሞ የአማራና የትግራይ ጠባብ ጎሰኞችና ፅንፈኞች የአንድ ሳንቲም ተገለባባጭ ገፆች ናቸው:: ላለንበት የአገራዊ ሀዘን ምክንያት በመሆናቸው ሶስቱም የፅንፈኞች ቡድኖች በኢትዮጵያ የጎሳ ኃያላን ለመሆን በጎሳ ስም በሚያካሂዱት የጎሳ ጦርነት በግልፅ መወገዝ አለባቸው:: ሁላችንም መጀመሪያ የሰው ልጆች መሆናችንን እንወቅ:: አገር ጎሳና የማንነት መታወቂያ ገላመለኔ ከሰው ልጅነት በላይ አይደለም:: የሰው ልጆች እየፈጀን አገርና ጎሳ ብንል ትርጉም የሌለው ነገር ነው:: አገርና ጎሳ የሚኖረው የሰው ልጆች ሲኖሩ ብቻ ነው:: ይህንን የማይረዳ የተማረም ያልተማረም ካለ ማሰብ የማይችል የሰው አተላ ነው:: አውሬ እንኳን ወገኑን ለይቶ በማወቅ አምሳያውን እንደማያጠቃ እንዴት የሰው ልጆች ልንገነዘብ አልቻልንም? እንዴት የስው ልጆች ሆነን በድርጊታችን ከአውሬ እንሰሳ አነስን? እንዴት የትግርይ የአማራና የኦሮሞ ዘረኞች ከእንሰሳ በታች እንደዘግጡ አንባቢዎች ይግምቱ!!
በእርግጥ ያለው የጎሳ ንትርክና ንክሻ የተጀመረው በዶ/ር አቢይ የአስተዳደር ጊዜ እንዳልሆነ ሁላችንም እናውቃለን የሚል ግምት አለኝ:: ፀረ-ኢትዮጵያና ፀረ-ኢትዮጵያዊ የሆነው መሪዎቹን በውርደት ያጣው ውዳቂ የወያኔ ድርጅት ወደስልጣን ሲመጣ የዛሬው ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ አህመድ ገና የ14/15 ዓመት ወጣት ነበሩ:: እኝህን ሰው ዛሬ ኢትዮጵያ ላለችበት የጎሳ ጥላቻ ውዝግብ ተጠያቂ ማድረግ አባትና እናት ለፈፅሙት ወንጀል ልጆቻቸውን መክሰስ ይሆናል:: ዛሬ በኢትዮጵያ ላይ መከራ የሆነውን የጎሳ ጥላቻ ፖለቲካ በዶ/ር አቢይ አህመድ ምክንያት ነው የሚል አስተሳሰብ የሚያራምድ ማንኛውም ሰው እውነትንና ሃቅን ያልተጎናፀፈ ፈስፋሻ ደደብ ነው ብል አልሳሳትም::
ምንም እንኳ በኢሐደግ አስተዳደር ውስጥ ባልኖርም ከእርቀት ሆኜ የኢሐደግ የክልል አገዛዝ በትውልድ አገሬ ኢትዮጵያ ያመጣው ከፋፍለህ ግዛ አስተዳደር ዛሬ ከ50 እድሜ በታች ያላቸውን ኢትዮጵያውያን ጎሳን የመጀመሪያ የማንነት መገለጫ አድርጎ ኢትዮጵያውያንነትን በሁለተኝነት ደረጃ አስቀምጦታል:: ይህንን የማንነት መገለጫ ለመቀልበስ ስለአንድነትና ስለኢትዮጵያዊነት ትልቅ ትምህርታዊ ስራ መሰራት ይኖርበታል:: ኢትዮጵያዊነትን ለማጉላት የአንድ ሙሉ ትውልድ ጊዜ ያስፈልጋል እላለሁ:: ይህ ሸክም ያንድ መሪ ያንድ ፓርቲ ስራ ብቻ ሳይሆን የመላው ሕዝብና የማንኛውም በአገር ቤትም ሆነ በዲያስፖራ ያለ ኢትዮጵያዊ ግዴታ መሆን አለበት:: በጎሳ ስም ሆነ በፓለቲካም ምክንያት የሚሞተው የሰው ልጅ ነው:: ለሞቱት ለሚሞቱት ማዘን ማልቀስ መጮህ ያለብን የሰው ልጆች በመሆናቸው እንጂ የአንድ ጎሳ የአንድ ሃይማኖት ተከታዮች በመሆናቸው ብቻ መሆን የለበትም:: የኦሮሞ ጠባብ ጎሰኞችና ፅንፈኞች በአማራ ስም የሰው ልጆችን ሲጨፈጭፉ ኦሮሞ ኢትዮጵያውያን የሰው ልጆች ሞት እንደሚያማቸው እንደሚያስለቅሳቸው እንደሚያሳዝናቸው መገንዘብ ይኖርብናል:: የአማራ ጠባብ ጎሰኞችና ፅንፈኞች ድንገት ተነስተው ኦሮሞ ኢትዮጵያውያንን ቢገድሉ አማራ ኢትዮጵያውያን የሰው ልጆች በከንቱ በመገደል ጥልቅ ሃዘን እንደሚገባቸውና እንደሚያለቅሱ ማሰብ አይከብድም:: ይህንን የምልበት በኢትዮጵያ ውስጥ በሚደረጉ ጎሳ ነክ ግድያዎች በእርግጥም የጎሳ ጦርነት በተለይ በአማራና በኦሮሞ ኢትዮጵያውያን መሃል እንዳለ በየመድረኩ ስለሚናፈስ ነው:: ሃቁ ከሁለቱም ጎሳዎች እንዲህ ዓይነት የእርስበርስ ጦርነት እንዲፋፋም የሚመኙና የሚቶነክሱ በእርግጥም አሉ:: በተለይ በዲያስፓራ ተቀምጠው ይህ እውን እንዲሆን የሚቋምጡ አልጠፉም:: ይህንን የጥላቻ ትረካ NARRATIVE ማራገብ ካላቆምንና የትም አካባቢም ሆነ ክልል ያለአግባብ የሚያልቀው ሁሉ የሰው ልጆችና ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን መሆናቸውን ተገንዝበን ለሰው ልጅነታቸውና ለኢትዮጵያዊነታቸው መጮህ ካልቻልን የእራሳችንን ስብእናን መሳት ይሆንብናል:: በስመ ኦነግ ሸኔና በእነ ጀዋር “ከበቡኝ” መሐመድ በቀለ ገርባ መራራ ጉዲናና በሌሎች ጥቂት ጎሰኞችና ፅንፈኞች ምክንያት መላውን ኦሮሞ ኢትዮጵያዊ ማጥላላት ሚዛናዊና ተገቢም አይደለም:: በተመሳሳይ በሰው በላ በመጨረሻም ራሱን ያስበላና ያስቀበረው የእርኩሶች ስብስብ ዛሬ እንደአይጥ ከጉድጏድ ወደ ጉድጏድ እየተንቀዠቀዠ ያለው እርምጥምጥ ወያኔ ምክንያት መላውን ትግራይ ኢትዮጵያዊያንን የሚጠላው በጭንቅላቱ ሳይሆን በመቀመጫው የሚያስብ ገለባ ነው:: የአማራው ክፍል አካል ነኝ በማለት ለአማራ ቆሜያለሁ በማለት እየወሸከ ሕዝብን ከሕዝብ የሚያገጨውም የመጨረሻ ቀኑ የደረሰበት የኦኔግ ሸኔና በሞት አፋፍ ላይ ተንጠንጥሎ ሞቻለሁ ብዬ አልዋሽም የሚለው ወያኔ ዕጣ እንደማይቀርለት ቀኑን መቁጠር መጀመር አለበት:: እነዚህ ሶስት ተውሳኮች ሲደመሰሱና ሲቀበሩ ለኢትዮጲያና ለኢትዮጵያውያን ሰላምና ደህንነት ይከፈታል በሩ::
ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር አብይን በተመለከተ:- መገንዘብ ያለብን እኝህ መሪ አንድ ሰው ናቸው:: እንደማንኛችንም የአንድ ሰው ችሎታና አቅም ውስን ነው:: ሁልገብ ለመሆን የሰው ፍጥረታችን አይፈቅድም:: እንደ መሪ ማድረግ የሚችሉት በስልጣን ላይ ካሉት ኃላፊነት ከተሰጣቸው ግለሰቦች ጋር ተመካክረው የስራ እቅዶች መንደፍና መትገበራቸውን መከታተል ነው::እነዚያም ሕዝቧን ሶስት ጊዜ በቀን ማብላት በማትችል አገር እንዲያገለግሉ ኃላፊነት የተጣለባቸው ግለሰቦች ስብእና ተሰምቷቸው የአደጉበትን ሕብረሰብ ከችግር ለማውጣት በሙሉ ልብ የተቻላቸውን መስራት ይኖርባቸዋል:: መሪ ጥሩና ታታሪ ሆኖ ከስሩ ያሉት በመሃላ የተቀበሉትን ኃላፊነት ለግል ጥቅማቸው ማሳደጃ ያደርጋሉ:: ከሚኒስትርነት አንስቶ እስከ ወረዳ ተቀጣሪ ያለውን የስልጣን ሰንሰለት መሪው መቆጣጠር አለበት የሚል አስተሳሰብ ማሰላሰል አንድ ሰው ላይ የማይቻል ከባድ ኃላፊነት መጣል ይሆናል:: ሙስናንና በስልጣን የተሸፈነን ስርቆት መከላከል የሚቻለው የመንግስት ሰራተኞች ሃቀኞችና ሃቅ አራማጆች ሲሆኑና ሕዝቡ ለግል ጥቅሙ ሲል በመንግስት መስሪያ ቤት በነፃ መፈፀም ላለበት ጉዳይ ሕገውጥ የሆነ ጉቦ ሲጠየቅ አልሰጥም ብሎ መብቱን ሲያስከብር ብቻ ነው:: እዚህ ላይ መሪው በመንግስት ደረጃ የተቋቋመው የሙስና መከላከያ መስሪያ ቤት የተቋቋመበትን ዓላማ ማሳካቱን ማለትም የተሰጠውን መመሪያ በስራ ላይ ማዋሉን መከታተላቸውና አለመከታተላቸው ተጠያቂ ያደርጋቸዋል:: በተቀረ የክልል አስተዳደሮች በየክልሉ ውስጥ ለሚታየው እድገትና ልማት : ጥፋትን ሸፍጥ ከጠ/ሚኒስቴሩ በላይ ተጠያቂ በመሆን ለጥሩና መልካም የክልል አስተዳደር እየተመሰገኑ : ለተዛባና ምግባረ ብልሹ ለሆነው አስተዳደር ዋነኛ ተጠያቂና ተወቃሽ መሆን ይኖርባቸዋል:: በዚህ ነጥብ ላይ ክቡር ጠ/ሚ ዶ/ር አቢይ ቢወቀሱ ይገባችዋል የምለው : ብልፅግና ምርጫውን እንዳሸነፈና ስልጣን እንደተረከቡ ከፍተኛ ሹመት የሰጧቸውን ሹማምንት በ2 ወይም በ3 ወራት ጊዜ ውስጥ እነዚህ ሹማምንቶች ያላቸውን የግል ሀብት እንዲያስመዘግቡ የተሰጠውን ትእዛዝ የሙስና ኮሚሽኑ በተባለው የጊዜ ገደብ አለማስፈፀሙ ነው:: በአሁኑ ሰዓት ሙስና በመንግስት ደረጃ ብቻ ሳይሆን በግል ንግዶች አስተዳደሮች ውስጥ ይታያል:: አንድ በቅርብ ጊዜ የሰማሁት አንድ ሰው ከአሜሪካ ሄዶ ቤት ገዛ:: የመግዣ ገንዘቡንም በሌብነት ማለትም በጥቁር ገበያ በመመንዘር ሳይሆን በሕጋዊ መንገድ በባንክ (የነበረው የምንዛሬ ልዩነት በአንድ ዶላር 15 የኢትዮጵያ ብር ) አስገብቶ ነው:: በጥቁር ገበያ ባለማስገባቱ 3 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ብር አጥቷል:: ለምን እንዲህ አደረክ ሲባል እኔ በምቾት አገር ኖሬ ከደሃ የኢትዮጵያ ሕዝብ አልሰርቅም:: ያስተማረኝንና ለዚህ ያበቃኝን ደሃ ሕዝብ በሌላ መንገድ አረዳሁትም:: የእራሴን ሕይወት በምቾት ስመራ ቆይቻለሁ:: ስለዚህ አልሰርቀውም : አላጭበረብረውም አለ:: ቤቱን ሙሉ ዋጋውን ከፍሎ ከሪልእስቴቱ ኩባንያው ቁልፉን ተቀበለ:: ግን የባለቤት ካርታውንና ምስክር ወረቀቱን TITLE ማስጨረስ ያለበት ኩባንያው ስለሆነ ከስር ያሉት የኩባንያው ሰራተኞች ዛሬ ነገ እያሉ ሲጎትቱበት ምክንያቱን ሲመረምር የሻጩ ኩባንያ ሰራተኛዎች ጉቦ እንደሚፈልጉ ተረዳ:: ይህንን ለኩባንያው ዋና አስተዳዳሪ በማቅረብ ጉዳዩን ያለጉቦ ማስፈፀም ቻለ:: ይህ ግለሰብ በተቻለው አቅም እውነትንና ሃቅን ለማስከበር ችሏል:: ከዚህግለሰብ ያገኘሁት አንድ አገር ነክ ትምህትት አለ:: ይህም ዲያስፖራ ያለነው ኢትዮጵያውያን ምን ያህል ነው ለአገር በማሰብ በጥቁር ገበያ ገንዘብ አልለውጥም በማለት በባንክ የምንልከው? የግል ጥቅማችንን እንጂ በጥቁር ገበያ አገር እንደምንጎዳ ተረድተናል?ማነው አገር ቤት ኗሪ ሆኖ አዲስ አበባ አዲስ የሚገነቡትን ቤቶች የሚገዛው? አብዛኛው ገዢ የዲያስፖራ ሰዎች ናቸው:: ቤቶቹ በየጊዜው ዋጋቸው እየጨመረ የሚሄደው ለምንድነው? ምክንያቱም የጥቁር ገበያ ገንዘብ ምንዛሬ ሲጨምር የቤቶችም ዋጋ ይነርታል:: ይህ ኗሪዎቹ ላይ የዋጋ ጭማሪ በማድረጉ ቤት የመግዛት አቅማቸውን አድክሞባቸዋል:: ይህንን የሌብነት ስራ ዲያስፖራው እያራመደ : በአገር ቤት ኗሪዎች ላይ የመግዛት አቅማቸውን እያዳከመ አቢይ አህመድን የሚወቅስና የሚያንቋሽሽ ዲያስፖራ አቢይ አህመድን ለመተቸት የሞራል ብቃት የለውም:: መጀመሪያ በጥቁር ገበያ እየመነዘረ ገንዘብ እያስገባ ቤት የሚገነባውንና የሚገዛውን አቁሞ በሕጋዊ መንገድ ገንዘብ ሲያስገባ ያኔ አቢይ አህመድ የሚሰራውን ስህተት መተቸት ይችላል:: ይህ አርእስት በሰፊው መነገር ያለበት ነው:: እንዲያውም ዲያስፖራ የሚኖረው ትውልድ ኢትዮጵያውያን ንብረት ኢትዮጵያ ውስጥ ሲገዙ መንግስት ገንዘብ ከየት እንዳመጡ መመርመር ይገባዋል:: ከቤተሰብ ውርስም ከሆነ ማስረጃ እንዲቀርብ : ከውጭም ከሆነ በባንክ ማስተላለፋቸውን ማረጋገጥ ይኖርባቸዋል:: በጥቁር ገበያ የሚወጣው ገንዘብ ለወያኔ ለኦነግ ሸኔ ለፅንፈኛው ፋኖ አገር መበጥበጫ የጦር መሳሪያ መግዣና በዲያስፖራ ለሚኖሩት ጎሰኞች መኖሪያ ምንጭ ነው::
ውደ ሙስና ኮሚሽን ልመለስና እስከ አሁን ስንቶቹ ከፍተኛ ሹማማንቶች የግል ሀብታቸውን በእርግጥ አስመዝግበዋል? አገር ጤናማ ልማት እንድታራምድ ከተፈለገ ሙስናና የባለስልጣናት ሌብነት በቅድሚያ መጥፋት አለባቸው:: የእንግሊዝኛው ተረት TELL ME YOUR FRIENDS & I WILL TELL YOU WHI YOU ARE እንዳይተረትባቸው በዚህ ጉዳይ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ መተኛት የለባቸውም:: በምንም ዓይነት ጠቅላይ ሚኒስቴሩ ይሰርቃሉ ጉቦ ይቀበላሉ የሚል አስተሳሰብና አመለካከት ፍፁም የለኝም:: የትኛው የኢትዮጵያ መሪ ወይስ የትኛው የጎሳ ፖለቲካ አቀንቃኝና አራማጅ በGOFUNDME ያሰባሰበውን ለሕዝብ አገልግሎት ያዋለው? ጠ/ሚ የመደመር መፅሐፋቸውን ሸጠው እስከአሁን ድረስ ወደሃያ ትምህርት ቤቶችና ስንት ዳቦ ቤቶች በየክልሉ አሰርተው ከፍተዋል:: በቀለ ገርባ የማርቲን ሉተርኪንግ ጁንየርን ጥቅሶች ስብስቦ ወደአማርኛ ተርጉሞ መፅሐፍ አሳትሞ አልሸጠም? ሲበጠብጥ ያለውን የኦሮሞ ሕዝብ በመፅሐፍ ሽያጩ እረድቷል? ካለ ልወቀው:: የሚገርመው በቀለ ገርባ አማራን እየጠላ ለምን መፅሐፍ በአማሪኛ አወጣ? መልሱ ግልፅ ነው:: ጥቅም!!! በኦሮሚኛ ቢፅፈው ገበያው እጅግ አነስተኛ ስለሆነ:: ይህች ትንሽ ነገር የጎሰኞችን ዓላማ ትመሰክራለች:: ትግላችው በሰፊው መድረክ ላይ ለማሸነፍ ያላቸው አቅም አነስተኛ ስለሆነ መንደርና ጎሳን ተንተርሰው በገዢነት ለመጠቀም ብቻ ነው:: ኢትዮጵያ ቢሉ ከእነዚህ የጎሳ ዶማዎች የላቁ ኢትዮጵያውያን ስላሉ ለመወዳደር ሐሞት የሌላቸው አይጦች ናቸው:: ጀዋር “ከበቡኝ” መሐመድም ሆነ መራራ ጉዲና ኦሮሞ ኢትዮጵያዊያንን ከማስለቀስና ስቃዩን ከማብዛት በስተቀር ያደረጉት በጎ አድራጎታዊ አገልግሎት ፍፁም የለም:: በዚህ አጋጣሚ ለጀዋር “ከበቡኝ” መሐመድ አንድ መልእክት አለኝ:: ይህም በቅርቡ በአንድ የዩቱብ ቃለመጠይቅ ታስሮ በነበረበት ወቅት የሁለት መፅሐፎች ረቁቆች እንዳዘጋጀና አንድቀን እንደሚያሳትም ሲናገር ሰማሁ:: መልእክቴ በጥያቄ መልክ ስቀርብ መፅሐፎቹ ሲሸጡ ገቢውን እንደ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወይስ እንደአጃቢው በቀለ ገርባ ነው?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር እቢይ አህመድ የገንዘብ ፍቅር የሌብነትና የጥቅም ሰው ሳይሆኑ አገራቸውንና ሕዝባቸውን ለማገልገል ቆርጠው የተነሱ ለመሆናቸ ምንም አይነት ጥርጣሬ የለኝም:: ግን ሹማምንቶቻቸውን ከስልጣን ብልግናና ከጉበኝነትና ሙስና አስፀያፊ ተግባር ካልገሰፇቸው ከወቀሳና ከሐሜት ክቡርነታቸውም ነፃ ሊሆኑ አይችሉም:: ምክንያቱም እንደመሪ THE BUCK STOPS WITH HIM ተረት ይጠቀስባቸዋል:: ጠቅላይ ሚኒስትሩ ብዙ ኃላፊነት እንዳለባቸው ባውቅም የባለስልጣናት ሌብነትና ሙስና የሚያመጣው መዘዝ ከጦርነት አያንስም:: እሳቸው ይሰራሉ ሕዝብ ያገለግላሉ ብለው የተማመኑባቸው ሹማምንቶች በስግብግብነታቸውና በተረኛነት ስሜት እየተመሩ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለአስቀመጡት ዓላማዎችና ለነደፉት መልካም እቅዶች እንቅፋት ከሆኑ ሕዝብ የሚወቅሰው ጠቅላይ ሚኒስትሩን መሆኑን መገንዘብ አይሳንም:: ስለዚህ ጠ/ሚ ዶ/ር አብይ አህመድ ይህ እንዳይከሰት ሹማማምንቶቻቸው ሀብት ማስመዝገባችውን የሙስና ኮሚሽን ትእዛዙ መፈፀሙንና አለመፈፀሙን ገሃድ ማድረግ አለባቸው:: “ተሸፋፍኖ ቢተኙ : ገልጦ የሚያይ ጌታ አለ” እንደሚለው ተረት ይህንን የመልካም አስተዳደር እንቅፋት ለመሸፋፈን ከተሞከረ እውነትንና ሃቅን ማጥፋት ይሆናልና ፈርሐ እግዚአብሔር ካላቸው ጠቅላይ ሚኒስትር እውነትንና ሃቅን ከፍ ማድረግ ይገባቸዋል::
አንድ ቤተሰብ ማስተዳደር የማይችል ሁሉ በሶሻል ሚዲያ አውታሮች ዩቲውብ ፌስቡክ ቲውተር ኢንስታግራምና ሌሎች መድረኮች ላይ እየወጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አብይ አህመድን በመሳደብ ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያውያንን ከገጠማቸው ችግሮች አያድኑም:: እነዚህ ሰርተውና ለፍተው መኖር የተሳናቸው ድኩማን ዩቲውበርስ የኪልክ ለማኞች የሚለጥፉትን አስፀያፊ ስድብና አነጋገር በማዳመጥና በማንበብ አገርና ሕዝብን ችግር ላይ ለመጣል: መልካም ሥራ የሚሰራውን ቀና መሪ በደቦ የምትዶቅሱ ጀሌዎች ስለማንነታችሁና ስለአስተሳሰብ ችሎታችሁ በረጋ ቀልብ አስቡ:: የተንኮለኞች መጠቀሚያ መሣሪያ አትሁኑ:: ኢትዮጵያና ሕዝቦቿ የሚፈልጉት ሰላምና ፀጥታ ነው:: ኢትዮጵያ ሰላምና ፀጥታ ካገኘች እንኳን ሕዝቧን ይቅርና ዓለምን ለመቀለብ የትችልበት እምቅ ሀብት አላት:: ያጣችው የልጆቿን ድጋፍ ነው:: ሩዋንዳ በ1994 ከነበራት 7 ሚሊዮን ሕዝብ በጎሳ ጥላቻ በሶስት ወራት እልቂት 1 ሚሊዮን አጥታለች:: ዛሬ ግን ያንን ሁሉ ተቋቁማ ጎሰኝነትና ፅንፈኝነትን አስወግዳ ሁቱና ቱቲሲ ሳይሉ ርዋንዳዊ ነኝ ብሎ የሚኮራ 12.5 ሚሊዮን ሕዝብ ልታፈራ ችላለች:: ይህም የሆነው ፕሬዝዳንት ፖል ካጋሜ ራዋንዳነት እንጂ የመጣበትን የቱቲሲን ጎሳ ስላቀፈ አይደለም:: ኢትዮጵያ ዛሬ ያላት መሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር አቢይ አህመድ የጎሰኝነት ስሜት የሌላቸው ኢትዮጵያዊነትን አጉልተውና አጥብቀው የያዙ መሪ መሆናቸው ከእሩቅ ሆኜ በማየት ኢትዮጵያን እንዲያራምዷት መደገፍ አለባቸው እላለሁ::
ያለመስማማት ላይ ልንስማማ እንችላለን:: ስላልተስማማን ማንነትን የሚነካ የሰብአዊነት አክብሮት የተሳነው ትችትን በምንም አይነት የማስተናገድ ትግስት ሊኖር አይገባም::
ኢትዮጵያና ኢትዮጵያዊነት ይበለፅጋሉ!! ያብባሉ!!
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
It is great to read this kind of positive assessment. I always want to believe the notion this writer brought forth. But, sometimes I hear directly from the PM speeches very divisive language so this days I can’t blame the FANNO and most Amhara activists to push back the PM. After all he had great support from Amhara as he came to power. So he has to re-earn acceptance rather than blindly supporting him.
This article reads good but it is very flawed in every way. The writer didn’t want to acknowledge the innocent Ethiopians who were slaughtered and murdered in broad daylight. She didn’t not criticize the government’s failed policies to protect civilians. She tried to gaslight Ethiopians who don’t support the prime minister as ignorant. First acknowledge the failure and the abysmal record of the prime minster’s record to protect civilians. No matter what Amhara nationalists have done, that doesn’t justify others to murder civilians. Period! I’m ashamed this article is written by a woman who didn’t even express her condolences to the hundreds of orphans left parentheses by this tragedy .