spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትከረዳት ወደ ዋና ሕዝባዊ ኃይል - የፋኖ፟ ትግል ሲስተካከል   

ከረዳት ወደ ዋና ሕዝባዊ ኃይል – የፋኖ፟ ትግል ሲስተካከል   

ተስፋዬ ደምመላሽ
ሰኔ 23 , 2014 ዓ.ም.

ፊት ለፊት የሽንገላ ቃላት ሠራዊት ማሰማራት ሳይቦዝን ከኋላ አማራ አፋኝ እውን ጦር ሲያዘጋጅ የከረመው በአብይ አሕመድ የሚመራው የኦህዴድ አገዛዝ ይኸው ባለፈው ሰሞን ወደማይቀረው ፀረ አማራ የኃይል አፈና ዘመቻ “አሸጋገረን”። በአሰልቺ ዲስኩር ሲደልል፣ ሲያስመስልና የፖለቲካ ቁማር ሲጫወት ለነገ የማይለውና ቀውስ የሚመቸው አብይ፣ በአንድ በኩል ከጎሣ ፖለቲካ ተባባሪውና አገር ከዳተኛው ሕወሓት ጋር “ድርድር” እያለ በሌላ በኩል ደግሞ የአገር መከታው ፈኖ፟ ላይ የጦር ዘመቻ እያኪያሄደ ነው።  

ፋኖ፟ የተመዘዘበትን ሰይፍ ለመመከት በጀግንነት ክንዱን አንስቶና ልቡን አደንድኖ እየተንቀሳቀሰ ነው። ከዘረኛው የኦህዴድ አገዛዝ ጋር አዲስ የህልውና ትግል ምዕራፍ መክፈት ተገዷል። የፋኖ፟ አርበኞች እንደ ቅድመ አያቶቻቸው “ኧረ ጥራኝ ጫካው ኧረ ጥራኝ ዱሩ፣ ላንትም ይሻልሃል ብቻ ከማደሩ” ብለው ደን ገደሉን መከታ አድርገው የአገዛዙን ፋሽስታዊ አፋኝ ጥቃቶች መመከት ጀምረዋል። 

የኦህዴድ አገዛዝ ለይስሙላ “የኢትዮጵያ መከላከያ” የተባለ ኃይሉ ከሰሜን እዝ ጥቃት በኋላ ያካሄደውን “ሕግ አስከባሪ” ተብዬ ጦርነት ትግራይ ውስጥ የሚያስፈልገውን ያህል ጊዜ ቆይቶ በአግባቡ እንዳይቋጭ ያገደ ነው።  የአማራና ትግሬ መናቆርና በጦርነት መማቀቅ ምንጊዜም የሚመቸው የ“ኦሮሚያ” ገዢ ፓርቲ ራሱ ያወጀውን አስመሳይ ሕግ የማስከበር ዘመቻ ራሱ እንዳጨናገፈ ይታወሳል። የኢትዮጵያ መሬት በሱዳን ተወሮ ሲያዝ ዝምብሎ ያየውን “መከላከያ” ከሰሜን ኢትዮጵያም በማሸሽ በወሎ፣ አፋርና ሸዋ ንፁሃን ዜጎችን ለወያኔ ወራሪዎች ወደር የሌለው የሽብር ጥቃት ሰለባ አደረገ።     

ፋኖ የተባበረው አገራዊ መሰል ሠራዊት እንግዲህ በሰሜን እዝ ላይ ብቻ ሳይሆን በአማራና አፋር ማህበረሰቦች ላይም አሰቃቂ የጦር ወንጀሎች ፈጽመው ወደ ትግራይ የሸሹ ወያኔ ሽብርተኞችን ከገቡበት ገብቶ ትጥቅ እንዳያስፈታና ለፍርድ እንዳያቀርብ የኦህዴድ አገዛዝ ከለከለ። ተሸናፊውን “ጁንታ” ዛሬ በሰሜን ጎንደር ለድጋሚ የወረራ ጦርነት መታጠቅ የሚያስችል አቅም፣ ብሎም በፍጹም የማይገ፟ባውን በኢትዮጵያ ጉዳዮች “ተደራዳሪ” የመሆን ወይም የመምሰል ቁመና ቸረው።     

በተጻራሪ፣ ሴረኛው የኦህዴድ አገዛዝ ዛሬ በአማራው ላይ የሚፈጽመው “ሕግ አስከባሪ” የተባለ ዘመቻ በሰሜኑ ጦርንት የተባበረውንና የአማራም የኢትዮጵያም መከታ የሆነውን ፋኖ፟ን “ትጥቅ ለማስፈታት” አማራ ግዛቶች ውስጥ ሰተት ብሎ ገብቶ ሰፍሮ በፋኖ፟ አባላት ላይ ብቻ ሳይሆን ባልታጠቁ ወጣቶች፣ ጋዜጠኞች፣ ምሁራን፣ የአማራ ተቆርቋሪዎችና ማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ ግብስብስ የአፈና፣ የግድያና የእገታ ዘመቻ ያካሂዳል። ይህ አሸባሪ የጦር ዘመቻ አገር ወዳድ የፋኖ፟ ኃይሎች ዛሬ ለሚተምኑት የትግል አላማ፣ አቅጣጫና መዳረሻ አንድምታ አለው።

የፋኖ፟ አነሳስ ፈተና – የትግሉ ሜዳ ክፍልፋይነትና ጥበት 

ፋኖ፟ የተጠናከረ ድርጁ የትግል ቁመና እና ዘላቂ አቅጣጫ ለመያዝ ማለፍ ያለበት ብርቱ ፈተናዎች አሉ። ከነዚህ አንዱ ዋና ተግዳር የትግሉ አውድ ወይም ሜዳ ከጅምሩ የሚያሳርፈው አሉታዊ ተጽዕኖ ነው።

ለፋኖ፟ ይህ የመነሻ ፈተና የሆነበት እንዴት ነው? በኢትዮጵያ ምድር ቀደም ብሎ አብዮቱ የጠረገው ሙሉ፣ ዘር ዘለል የሕዝባዊ ትግል ሜዳ በኋላ አብርሆት በራቃቸው “ብሔር ነፃ አውጪ” ተብዬ ዘረኛ ፖርቲዎች ተቆራርሶ፣ ተተልትሎ፣ ከማኅበራዊም ሆነ ከፖለቲካዊና አገራዊ አንድነት “የተከለለ” መሆኑ ነው። ዛሬ ያለንበት የጨለማ ዘመን በሁሉም የባህል፣ የህብረተሰብና የመንግሥት ዘርፎች ከአንድነት መንፈስ ርቆ ምድሩም ሰማዩም የኔ የብቻዬ ነው በሚል የተደናቆረና በሙስና የተበከለ ጎጠኝነት ከተዋጠ ሦስት አስርተ ዓመታት አልፈዋል። 

የመከፋፈልና የሴራ አረንቋ የሆነው የውጊያ መሬት ወይ የለየለት ጦርነት ተካሄዶ ዘላቂ፣ አገር አቀፍ የፖለቲካ ሥርዓት በአሸናፊነት የማይወጣበት (ለምሳሌ እንደ አሜሪካ ወይም ቻይና የርስ በርስ ጦርነት)፣ ወይ ደግሞ ቀና መንፈስ በተላበሰ ፍትሐዊ ድርድር ዘላቂ ስምምነት፣ እርቅና ሰላም የማይሰፍንበት፣ ከሁለት ያጣ ጎመን ሆኗል። የትግሉ ሜዳ፣ አንሰው ኢትዮጵያን በሚያሳንሱ፣ አገርን መቆጣጠር ፈልገው ግን አገራዊ መሆን በማይፈልጉ ወይም በማይችሉ ደናቁርት የማንነት ፖለቲካ አምላኪ ወገኖችና የውጭ ተባባሪዎቻቸው የተጥለቀለቀ ነው።     

ይህ አገርን በቁም ገዳይ የሴረኝነት፣ የመጠ፟ላለፍና የሥርዓት አልበኝነት ጥላ የማይለ፟የው የተቃወሰ የውጊያ መስክ ተባብሶ ወደ “አማራ ክልል” ተብዬውም የወረደ መሆኑ (ለምሳሌ፣ ‘ቅማንት’፣ ‘አገው’፣ ወዘተ በሚል የወያኔ ልዩነትና መከፋፈል ፈጠራ) ዛሬ የፋኖ፟ን ትግል ወጥ አነሳስ ተፈታታኝ አድርጎታል። 

የተረኞቹ ጎሠኛ አገዛዝ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ዘር ዘለል አገራዊ ትስስርና አንድነት ጠንቅ መሆኑ እንዳለ ሆኖ፣ በተለየ መልክና መጠን ደግሞ አማራውን ማኅበረሰብ – በቅጥ፟ያም ፋኖ፟ን – የሚፈራ፣ የሚጠላ፣ የሚከፋፈልና የሚያገል እንድሆነ ከማንም ስውር አይደለም። ብሎም አማራውን ከሌሎች የአገሪቱ ነገዳዊና ባህላዊ ማኅበረሰቦች ለይቶ በገሃድ ከመጨፍጨፍም ሆነ ውስጥ ውስጡን ከመቦርቦር፣ ከመበደልና ከመጉዳት አይቦዝንም።  

የዚህ አንድ ዋና መገለጫ አማራው በእውን የራሴ ነው ብሎ መከታም ሆነ የትግል መነሻ ሊያደርገው የሚምችል “ክልል” (ግዛት) እንኳን በወያኔዎችና ኦህዴድ/ኦነግ/ሸኔ ተረኛ ገዢዎች ያልተቸረው መሆኑ ነው። “የአማራ ክልል” ከጅምሩ በኤርትራዊ ነኝ ባዩ ትግሬ በረከት ስሞን፣ በኦሮሞው አዲሱ ለገሰ፣ ፍልቀቱ ጉራጌ በሆነው ታምራት ላይኔና በሌሎች አማራ ያልሆኑ ግለሰቦች የበላይ ጠምዛዥነት የተገዛ ነበር።ዛሬም ብአዴን በተባለ፣ ስሙን በየጊዜው ቢለዋውጥም በቀጣይነት የፀረ አማራ ዘረኛ ጌቶቹ ተለጣፊ ሆኖ በቀረ ባንዳዊ ድርጅት ቁጥጥር ስር ነው። ለስም ብቻ የተሾሙ ተወካይ አማራ ባለሥልጣናትና ካድሬዎች ከውስጥ ተተብትቦ የተያዘ ነው።     

ስለዚህ፣ በትግሬ ክልል የሕወሓት መሪዎች ራሳችውን ችለው አድራጊ ፈጣሪ በሆነበት መጠን ወይም በ“ኦሮሚያ” አብይ የሚመራው የኦህዴድ ፓርቲ በተረኝነት አዛዥ የሆነበትን ያህል እንኳን ባይሆን “አማራ” የተባለው ክፍለ ሃገር ለአስርተ ዓመታት ራሱን የቻለ መለስተኛ ገዢ ፓርቲ ወይም የረጋ፣ ቀጣይ ርዕሰ መስተዳደር ኖሮት አያውቅም። እንዲኖረውም አልተፈለገም። አማራው ከኦሮሞ፣ ከትግሬና ከሌሎች ክልሎች ተለይቶ አምስት ጊዜ “ርዕሰ መስተዳደሮች” (ጉልቻዎች) የተለዋወጡበት አለምክንያት አደለም። 

አማራው ተባብሮ ተገቢ ማኅበራዊና አገራዊ ጥቅሞቹን ማስከበር ፈጽሞ ያላስቻለው ይህ ሁኔታ የፋኖ፟ ትግልን ወጥ አንድነት አዳጋች አድርጎት ቆይቷል። ዛሬ የሁኔታው አስቀጣዮቹ ተረኛ ገዢዎች ህሊናቸውን በሸጡ ባንዳዊ አማራ የጦር መኮንኖች ግብረ አበርነት እየታገዙ የፋኖ፟ ታጣቂዎችን ብቻ ሳይሆን የአማራውን ማኅበረሰብ በጠቅላላ የአሸባሪ ወረራ፣ ግድያ፣ አፈና እና እገታ ኢላማ አድርገውታል። 

ስለዚህ ትናንት ጠላቶቹ የራሳቸውን ክልል ሲፈጥሩ፣ አማራው በተጻራሪ በእውን ራሱ የሚያስተዳድረው ግዛት አካቶ መነፈጉ፣ ዛሬ ደግሞ ፋኖ፟ እስከ አፍንጫቸው ታጥቀው በጎንደር፣ በጎጃም፣ በወሎና በሸዋ በሚንቀሳቀሱ ደመኞቹ ትጥቅ ፍታ መባሉ፣ በቀጥታ የተያያዙ ፀር አማራ የዘረኛ ፖለቲካ ዕቅዶችን አመላካች ናቸው። አማራው በፋኖ፟ መከታነት እነዚህን ዕቅዶች ለማክሸፍና ህልውናውን ለመጠበቅ ዛሬ ቆርጦ ሲነሳ ወሳኙ የመጀመሪያ እርምጃው ከራሱ ጋር ታግሎ የፖለቲካ ቤቱን ከውስጥ አጥቂዎችና አስጠቂዎች ማጽዳት ነው መሆን ያለበት። ይህን ሳያደርግ ሊያጠፉት የተነሱ ዘረኛ ጠላቶቹን ማሸነፍ ቀርቶ ፈርጠም ብሎ ሊቋቋማቸው እንኳን አይችልም።

ፋኖነት – ባህላዊ ዘማችነትና ዘመናዊ አቅጣጫው 

ፋኖ፟ አንድነቱን በጥልቅ ድርጅታዊ ሥነ ሥርዓትና አመራር አጠናክሮ በመጠበቅ የአገር ውስጥና የውጭ ከፋፋይ ሃይሎችን የፊት ለፊት ጥቃቶችንም ሆነ የበስተጀርባ ወይም ስውር የማፍረስ ሙከራዎችን በአሰፈላጊው ሁሉ መንገድ እየመከተ ምንጊዜም ሙሉነቱን (ሐቀኝነቱን) እና ደህንነቱን በንቁ ትግል ማረጋገጥ መቻሉ ወሳኝ ነው። 

ነገር ግን የትግሉ ሜዳ የተከፋፈለ፣ በለት ተለት ሚዲያ አሉባልታ የተደናገረ፣ እንዲሁም በሴራ የተጠላለፈ መሆኑ ለፋኖ፟ ንቅናቄ የተረጋጋና በምር የተስተዋለ አቅጣጫ ያዥነት መነሻ ፈተና ሲሆን፣ ንቅናቄው በሂደት መወጣት ያለበት የራሱ ተግዳሮችም አሉት። እነዚህ ፈተናዎች ጠቅለል ብለው ሲታዩ፣ የትናንቱ (ባህላዊው) ፋኖ፟ነት ከዛሬው (ዘመናዊ) ቅርጽና ይዘቱ ጋር ያለውን፣ አለያም ሊኖረው የሚችለውንና የሚገባውን በጎ መስተጋብር ይመለከታሉ።

ኢትዮጵያ በረጅም ታሪኳ ቋሚ የጦር ሠራዊት ሳይኖራት ከውጭ ወራሪዎችና የውስጥ ጠላቶች መከላከያ ኃይሏ ባመዛኙ ራሳቸውን ያሰለጠኑና ያስታጠቁ፣ በአገር ወዳድ ስሜትና ፈቃደኝነት ተነሳሽ የሆኑ፣ የዜጋ ወይም የሕዝብ ጦረኞች (ፋኖ፟ዎች) ነበሩ። በተለይ በ19ነኛው ምእተ ዓመት መጨርሻ በአድዋ ጦርነትና በኋለኛው የጣሊያን ወረራ ጊዜም በጎበዝ አለቆችና መኳንንት አርበኞች እየተመሩ የኢትዮጵያን ነፃነት ጠብቀዋል። የነገሥታት ጦር አመራርን አለመኖር ወይም መጓደል በማሟላት እና ተጨማሪ ሕዝባዊ ኃይል በመሆንም አገራቸውንና ማኅበረሰባቸውን አገልግለዋል። በዚህ መልክ በኢትዮጵያ በዳበረው ምግባረ ጥሩ አገር ጠባቂ የጦረኝነትና ጀግንነት ባህል ወሳኝ ተጽእኖ አሳርፈዋል።

የዛሬዎቹ ሕዝባዊ ዘማቾች (ፋኖ ታጋዮች) ከቅድመ አያቶቻቸው ይህንኑ አኩሪ፣ አገር ወዳድ የዘማችነትና የጀግንነት ቅርስ የወርሱ ናቸው፣ ምንም እንኳን ውርሱን ከዘመናዊ የትግል አውድ ጋር አዛምደው፣ ማለትም ይበልጥ ተደራጅተው፣ ሠልጥነው፣ ታጥቀውና ዘዴኛ ሆነው መነቃነቅ ግድ ቢላቸውም።

የዛሬው የ”ዘመነ” ፋኖ፟ነት (በኅብር ለመናገር) ከተነሳባቸው ባህላዊ-ታሪካዊ የፋኖ፟ ትግል አደራጅ መርሆች ጥቂቶች ልጠቁም፥

  1. ፋኖ፟ ከመንግሥት ጋር በመደበኛ አስተዳደር ወይም ቁጥጥር ያልተገናኘ፣ ግን ከመንግሥት እውቅናን ያገኘና በአማራው ማኅበረሰብ የሚታመንበት፣ በመሠረቱ የራስ አሰልጣኝና አስታጣቂ ፈቃደኛ ዜጎች ጦረኝነት ልምድ መሆኑ፤ 
  2. ፋኖ፟ በአገርና መንግሥት ውስጥ በየጊዜው የሚፈጠሩ ውጥረቶችን ወይም አስጊ ሁኔታዎችን ለመወጣት የሚወ፟ሰዱ የጦር እርምጃዎችን የሚያሟላ ረዳት፣ ተባባሪ ወይም ተጨማሪ ኃይል መሆኑ (ለምሳሌ፣ በመጨርሻው የአገር ውስጥ ጦርነት ፋኖ፟ መከላከያ ከተባለ፣ ኦህዴድ በበላይነት ከሚያዘው ጦር ጎን ተሰልፎ ሕወሓትን ተግቶ በመዋጋት የአብይን ሥልጣን ማስቀጠሉ)፤
  3. በጠቅላላ፣ የፋኖ ዘማችነት የፖለቲካ ኃይል ይዞ መግሥትን ከመቆጣጠር ፍላጎትና ዓላማ ወይም ዕቅድ ጋር ያለተገናኘ መሆኑ፣ ምንም እንኳን የዛሬው ፋኖ፟ ዘመቻ ይህን ዕቅድ ታሳቢና ተፈጻሚ ማድረግ እየተገደደ ቢሆንም (በጎንደር የሚንቀሳቀሰው ፋኖ ባለፈው ሰሞን በመግለጫው እንዳስታወቀው)፤
  4. አማሮች በቀውጢ ጊዜያት ለመንግሥትና አገር ከሚሰጡት ተጨባጭ የጦረኝነት አገልግሎት ባሻገር፣ ለአማራው ማኅበረሰብ ፋኖ፟ነት ራሱን የቻለ ቋሚ ባህላዊ እሴት መሆኑ – የነፃነትን፣ ስብዕናን፣ አገር ወዳድነትን፣ ጨዋነትን፣ መንፈሳዊነትን፣ ጀግንነትን፣ እና የሕዝብ አለኝታነትን እሴቶች ማካተቱ፤ እነዚህ እሴቶች ከጦር ሜዳ ዘልቀው ወደ ሌሎች የሰላማዊ ኑሮና እንቅስቃሴ ዘርፎች (ሞራላዊ፣ ምሁራዊ፣ መንፈሳዊ፣ ፖለቲካዊ ወዘተ) የፋኖነትን መንፈስ የሚያዛመቱ ወይም ሊያዛመቱ የሚችሉ መሆናቸው፣ 
  5. በዚህ እሴታዊ ቅርጽና ይዘቱ፣ የፋኖ፟ ሥልጡን ሕዝባዊ ጦረኝነት የማንነት ፖለቲካ አምላኪ ወገኖች ከሚያራምዱት፣ አረመኔያዊ፣ ንጹሃንን ጨፍጫፊ የቡከኖች “ውጊያ” ልምድ አካቶ የተለየ መሆኑ፤ የፋኖ፟ ጦረኞች የጦር ግዳጃቸውን በቆራጥነትና ጀግንነነት ሲወጡም ፍልሚያቸውን በመርህ መጥነውና ገድበው (ከፋኖ፟ ባህላዊ እሴቶች ጋር አገናዝብውና አጣጥመው መሆኑ)፤

እነዚህና ሌሎች ባህላዊ-ታሪካዊ የፋኖ፟ነት ገጽታዎች የዛሬው ዘመናዊ ፋኖ፟ ተጋድሎ መሠረታዊ ግብአቶችና ገጽታዎች ናቸው። ይሁን እንጂ፣ አስተባበራቸው ከወቅቱ የትግል ሁኔታና ፋኖ፟ነት ጋር ተዛምዶ፣ ሲያስፈልግም ተስተካክሎ ነው ሥራ ላይ መዋል የሚችለው።

አሁን የትግሉ ሁኔታዎች በጣም ተለውጠዋል። በዘመነ ዘረኞች፣ “መንግሥት” ከጅምሩ የፋኖ፟ን አገር ወዳድ ተባባሪነትና አጋዥነት ምንም ያህል ተቀብሎ አያውቅም፤ ከአፈጣጠሩና ከተነሳበት ዘረኛ ዓላማ ሐቀኛ አገራዊነትንም ሆነ የነፃ ሕዝባዊ ኃይል እገዛን መቀበል የሚፈልግ ወይም የሚችልም አይደለም። በተለይ ዛሬ የገዢው ኦህዴድ እና የሥልጣን ተቀናቃኙ ሕወሓት ተባባሪም ተፎካካሪም ፀረ አማራነት ኢትዮጵያን እያወዛገበ ባለበት ጊዜ ደግሞ፣ የፋኖ፟ መሪዎችና አባላት “ትጥቅ የማስፈታት” ዘመቻ ታውጆባቸው የሚታደኑበት፣ የሚዋከቡበት፣ የሚታፈኑበትና የሚገድሉበት ውቅት ሆኗል። 

የሁኔታዎች መቀየር፣ መባባስም፣ ለፋኖ፟ ህልውና በጣም አደገኛ ነው፤ በቅጥ፟ያም የአማራውን ማኅበረሰብ መከታ በማጥፋት ማኅበረሰቡን ለዘረኛ ደመኞቹ ጥቃቶችና ጭፍጨፋዎች ይበጥ ያመቻቻል። እነዚህን አደጋዎች በምር ታሳቢ በማድረግ፣ የፋኖ፟ ትግል መሪዎችና ዕቅድ አውጪዎች ሁኔታውን በሚገባ ተገንዝበው፤ የትግሉን አቅጣጫ መልሰው መቀየስና የራሳቸውን ተገቢ ስልታዊ ማስተካከያዎች ማድረግ ግድ ሊላቸው ይገባል።

ይህን ግዴታ ለመወጣት ትግሉን ይበልጥ የአስተሳሰብ ወይም የርዕዮት ንቃት ሰጥቶ ዘላቂ አቅጣጫ በማስያዝ ከፍ ወዳለ የፖለቲካ ደረጃ ማሸጋገር የጠይቃል። ማለትም፣ የባህላዊ-ታሪካዊ ፋኖ፟ነትን ውስንነቶች (ለምሳሌ፣ የፖለቲካ ስልጣን መያዝ አፋርነቱን ወይም ችላ ባይነቱን) ከትውልድና ዘመን ተሻጋሪ ጥንካሬዎቹ (እንበል፣ አገር ወዳድ፣ ሥልጡን ጦርኝነቱን) እየለዩ ካለንበት ዘመንና ሁኔታ ጋር አስማምቶ ማዳበርና ወደፊት ማራመድ ያስፈልጋል። 

ከዚህ ግንዛቤ ተነስቼ ለፋኖ፟፣ በሰፊው ደግሞ ለአገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያንን ትግል መሪዎችና ተማ፟ኞች የሃሳብና የስልት ማዳበሪያ ሊሆኑ የሚችሉ መላ ምቶች ወይም ማስታወሻዎች ቀጥዬ አቀርባለሁ። ማስታወሻዎቹ የአንድነት፣ የሥርዓት ለውጥና የፖለቲካ ጉዳዮችን ይመለከታሉ።  

የአንድነት ፈተና – የፋኖ፣ የአማራውና የኢትዮጵያ

1. ዛሬ ባለንበት ዘመን፣ በጠቅላይ ግዛቶችና አካባቢዎች (በጎንደር፣ ጎጃም፣ ወሎ፣ ሸዋና ሌሎች ክፍለ ሀገራት) ያልተከፋፈለ የፋኖ (አማራዊ) አንድነት በቀጥታና ባንዳፍታ በታሪክ ተሟልቶ የተሰጠ ወይም በባህላዊ ቅርስነት ብቻ የምንቀበለው አይደለም። ይልቅስ፣ በሁለገብ ትግል አጠናክረን የምንገነባው፣ የምንዋጋለት ነገር ነው። ጽኑ አንድነት ዝምብሎ የፋኖ፟ ዘመቻ መነሻ  ሳይሆን መዳረሻም ነው።

2. የአማራው/የፋኖ ራስነት ውይም ህልውና የዘውግ አገዛዙ መዋቅር ከተቋቋመበትና ከሚያራምደው በዘር ወይም በቋንቋ የተከለለ ብቸኛ ማንነት ወይም “አንድነት” የሚለይ መሆኑን አውቆ ለሕዝብ ማሳወቅ ጠቃሚ ነው። የፋኖ፟ አንድነት ዋና መለያው የአማራን ማኅበረሰባዊ ማንነት በድፍኑ ከኢትዮጵያዊነትም ሆነ ከሌሎች ባህላዊ ማኅበረሰቦች በማራቅ አገራዊ ህላዌን በጎሣ ማንነት ፖለቲካ የመቃረንና የመተካት ልምድ ወይም ዕቅድ የለውም። አማራው በኢትዮጵያ ክፍለ ሀገራትና አካባቢዎች የባህል፣ የቋንቋና የሃይማኖት ብዝሃንነትን ጨፈላልቆ በዘረኛ አምባገነንነት ወይም የበላይነት ተለጣጣፊ የጎሣ “ክልሎች” ፈጣሪ ሆኖ አያውቅም፤ ዛሬም አይደለም፤ ለወደፊትም አይሆንም።

3. በአገር ደርጃ አማራው፣ በቅጥ፟ያ ደግሞ ፋኖ፟፣ የሚከተለው የኢትዮጵያን አንድ ሕዝብነት ያማከለ የአብሮነት መርህ የዘር አገዛዝ ሥርዓቱ “መደ፟መር” ከሚለው፣ ትስስር የሌሽ የተነጣጠሉ ደሴታዊ “ሕዝቦች” ጥርቅምን ከሚያጎላ ተልካሻ እሳቤ በግልጽ መለየት ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ሕዝብ ከዘውግ ክልሎች የቁጥር ድምር ያለፈ አንድነትና ሉአላዊነት አለው። ኢትዮጵያ የሆነ ያልሆነ ዘረኛ ስብስብ ወይም ወገንተኛ ቡድን እንዳሻው የሚያነሳትና የሚጥላት፣ የሚቀንሳትና የሚደምራት፣ እንደተመቸው ወይም እንድተመኘው የሚሠራትና የሚያፈርሳት አይደለችም። 

በዕቅድም ሆነ በውጤት፣ የ“መደ፟መር” ከንቱ አስተሳሰብ በኢትዮጵያ የእውን አንድነትን ቦታ ያዥ በመሆን የአብሮነትን (የአገራዊ መንግሥትን) አለመኖር ወይም መጓደል ሸፋፋኝ ነው፤ እውን አንድነትን በአስመሳይ፣ ጎደሎ ግልባጩ ከመተካት ያለፈ ፋይዳ የለውም። የመደመር ፈሊጥ ከዚያም አልፎ፣ ይህ ነው የሚባል ፖለቲካዊ ወይም አገራዊ ይዞታ የሌለው፣ በጅ አዙር አገዛዛዊ ሥርዓተ አልበኝነትንና ሽብርተኝነትን አመቻች እሳቤ መሆኑን ተረድቶ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ ማድረግ አስፈላጊ ነው። 

ማለትም፣ አስተሳሰቡ አገር መሪ ነኝ ባዩን፣ በኦህዴድና ኦነግ-ሸኔ የሚደገፍ፣ የአብይ አገዛዝ በአሸባሪነት ተጠያቂ ከመሆን ማምለጫ መሣሪያ እንደሆነ እንረዳለን። ባለፉት አራት ዓመታት በተደጋጋሚ እንዳየነው፣ ሰሞኑን በወለጋ የተፈጸመው የንጹሐን አማሮች አረመኔያዊ ጭፍጨፋ የሚያሳየን ይህንኑ የመደመር ፈሊጥ መሣሪያነትን ነው። በሽመልስ አብዲሳ የሚመራው ተደማሪ ተብዬ “ኦሮሚያ” አማራ ቀናሹን የታጠቀ አሸባሪ ወገን ሸኔን ከተጠያቂነት ማምለጫ (የሽብር ብቸኛ ማመካኛ) አድርጎ በውስጡ ያካተተ ክልል ነው። 

በ“ፌደራል” ደረጃም አብይ በአማራ ግዛቶች ዛሬ እያካሄደ ያለውን ፋኖ፟ን “ትጥቅ የማስፈታት” አሸባሪ ዘመቻ አካቶ የተደማሪው “አማራ ክልል” መሪዎች እቅድና ሥራ ነው በሚል አይን ያወጣ ቅጥፈት ራሱ የሚመራውን የኦህዴድ “መከላከያ” ኃይል ከአፈናው ኃላፊነት ለማስመለጥ የሞከረውም የመደመር እሳቤን ከለላ አድርጎ ነበር። የአማራ ነው የተባለው ክልል “ፕሬዚደንት” የአብይ አገዛዝ ተላላኪና ሥራ አስፈጻሚ መሆኑ የተሰወረ ሳይሆን የአደባባይ ምስጢር ነው።    

4. ሆኖም፣ ለይስሙላ ፌደራላዊ የተባለው የ”ብሔሮች” ቁጥር “ድምሩ” ራሱ በተደማሪ ተብዬዎቹ የዘር ክፍሎች ዳርቻ ወይም ጎን ሥፍራ የተሰጠው እንጂ የጎሣ ክልሎችን ተሻጋሪ የሆነ በጎ አገራዊ ቁመና ወይም መዋቅር የለውም። በዚህ መልክ የተደራጀው የኦህዴድ ዘረኛ አገዛዝ የኢትዮጵያን ሕዝብ ደህንነት በቅጡ የማይጠብቅ፣ በየጊዜው ለሚጨፈጨፈው አማራ ማኅበረሰብ ዘብ ሊቆም የማይችል እንደሆነ ደግሞ ደጋግሞ በግልጽ አሳይቷል። የአገራችን መሬት በአረብ ነኝ ባዩ ሱዳን ብቻ ሳይሆን ትናንት በተፈጠረችው፣ ትንሿ፣ ደቡብ ሱዳንም ሰሞኑን ተወሮ ሲያዝ “መከላከያ” ዝምብሎ ማየቱ የአብይ አገዛዝ ከሸንጋይ ዲስኩሩ ባሻገር የኢትዮጵያ ደህንነትና ሉአላዊነት ግድ እንደማይለው ሕዝቡ መረዳት አለበት።  

5. ወያኔ የፈጠረውና የዛሬው አገር ገዢ “ኦሮሚያ” ፓርቲ ውርስ የሆነው አስመሳይ “ፌደራላዊ” የአገዛዝ ሠርዓት ራሱ አንድ ዘረኛ ወገን በበላይነት የተንሰራፋበት ፖለቲካዊ  “ክልል” መሆኑ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በደንብ ሊያውቀው ይገባል። ሕዝብ ከፋፋይና አጋጪ የጎሠኛ ክልሎች መራባት ለአገር ህልውና ጠንቅነት መልክዓ ምድራዊ ብቻ ሳይሆን ተቋማዊም ነው። ጠንቅ የሆነው ክፍለ ሀገራትንና አካባቢዎችን ወሮ እንዳልነበሩ በማድረጉ፣ ከብዝሃንነት በማጽዳቱ፣ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያን ማኅበራዊ፣ ባህላዊ፣ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ተቋማት አገራዊ ተጽዕኖ በማቀጨጩም ጭምር ነው። 

የአገዛዝ መዋቅሩ ለስሙ የኢትዮጵያ መንግሥት ቢባልም፣ ከጠ/ሚንስትሩ አፈ ጮሌ ‘ኢትዮጵያ’ ‘ኢትዮጵያ’ ባይነት ባለፈ የአገሪቱን ዜጎችና ባህላዊ ማኅበረሰቦች በእውን የእኩልነት መርህ አንድ ሊያደርግ ወይም ሊያስተባብር የሚችልበት ፖለቲካዊ ዳራና ልምድም ሆነ ይህ ነው ይሚባል ርዕዮታዊ ይዘት የለውም። ሆኖም፣ በበላይነት የትግሬና ኦሮሞ ዘረኛ ወገኖች የተቀባበሉት አገዛዝ፣ ከኢትዮጵያ አብዮታዊ ልምድ በዘረኝነት አወላግዶና አጣ፟ቦ የወሰዳቸው ርዝራዥ መዋቅራዊ (ፓራዳይማዊ) የፖለቲካ አስተሳሰብ፣ አነጋገርና አሠራር ገጽታዎች አሉት።    

ለዘለቄታው፣ ለኢትዮጵያ አንድነትና ሰላም ብቻ ሳይሆን ለየትኛውም የኢትዮጵያ ነገዳዊ ማኅበረሰብ የማይበጀው “ፌደራላዊ” አገዛዝ ከነ“ኢመደበኛ” ወኪሎቹ ከሥልጣን መወገድ አለበት። ድፍን አገር አሸባሪ የሆነውን፣ በተለየ መልክና መጠን ደግሞ አማራ ጨፍጫፊና አፋኙን የአገዛዝ መዋቅር መለወጥ ለአማራው ማኅበረሰብም በጠቅላላ ለኢትዮጵያም የመኖር አለመኖር ጉዳይ እንደሆነ እንረዳለን። ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህን የተቃወሰ ሥርዓታዊ መንፈስ በተክለ ሰውነቱ የተላበሰ ነው፤ የአገዛዙን ሥርዓተ አልበኝነት በአስተሳሰቡ፣ አነጋገሩና ባህሪው ያንጸባርቃል።  

የህልውና ትግል ሥርዓታዊ ለውጥ አቅጣጫ

6. የሥርዓታዊ ለውጥ አቅጣጫ መያዝ የሚያስፈልገው የህልውና ትግል እንግዲህ አንድም ሦስትም ነው – የፋኖ ሕዝባዊ ኃይል፣ የአማራው (እንደማኅበረሰብ) እና የድፍን የኢትዮጵያ። የአስርተ አመታት እድሜ ያለው ዘረኛ የአገዛዝ መዋቅር በነዚህ የተያያዙ ሦስት እርከኖች በሚካሄዱ ንቅናቄዎች ቅንብር ላንዴም ለሁሌም ካልተደቆሰ በተያያዥ የህልውና አደጋነቱ ይቀጥላል።    

7. በባህላዊ ልምድ፣ የፋኖ ዘማችነት በውስጥም ሆነ የውጭ ጠላቶች የሚፈጠሩ አስጊ ሁኔታዎችን ወይም ውጥረቶችን ለመወጣት መንግሥት የሚውስዳቸውን እርምጃዎች በማገዝና ጉድለቶችን በሟላት የተወሰነ ነበር። ዛሬ ፋኖ፟ ይህን ታሪካዊ የአጋዥ የጦረኝነት ሚና የሚጫወትበት ወቅት ሳይሆን ራሱን ከ‘መንግሥት’ ተብዬው አፈና መከላከል የተገደደበት የሞት ወይም የሽረት ፈተና ጊዜ ነው። 

ፈተናው የአጭር ጊዜ፣ ቀጥታና አጣዳፊ፣ ራስን ከጥፋት የማትረፍና የመጠበቅ ሁለገብ እንቅስቃሴዎችን ቀደምትነት መስጠት ያስገድዳል። አያይዞም በረጅም ጊዜ ስልታዊ ትግል ደረጃ የአገዛዝ ሥርዓቱን ተገዳዳሪና ለዋጭ የሆነ ዘላቂ የአማራ (በሰፊው ደግሞ የአገር ወዳድ ኢትዮጵያዊያን) ንቅናቄ ማኪያሄድ የሚያስችል የመዋቅራዊ ለውጥ ዕድል ፈጥሯል፤ አዲስ የፋኖ፟ነት ምእራፍ ከፍቷል። 

8. ከረጅሙ ጊዜ የሥርዓት ለውጥ ንቅናቄ አንጻር፣ የፋኖ፟ነት ቋሚ እሴቶች ከጦረኞች ውጊያ ጋር ካላቸው ቀጥታ ግንኙነት ባሻገር በሰላማዊው ትግል መስክ ወጣቶችን፣ ምሁራንን፣ ሙያተኞችን፣ መንፈሳዊ መሪዎችን፣ ማህበረሰብ አንቂዎችን፣ ፖለቲከኞችን፣ ወዘተ ለንቅናቄው ቀስቃሽና አነሳሽ መሣሪያ ሊሆኑ ይችላሉ። በዚህ የነፃነትን፣ ጀግንነትን፣ አገር ወዳድነትንና ጨዋ ዘማችነትን እሴቶች በሚያካትት የፋኖነት መንፈስ መላ፟ ኢትዮጵያዊያን በለውጡ ንቅናቄ መሳተፍ እንችላለን።

9. የለውጡ ንቅናቄ ዘላቂ አቅጣጫ በነባሩ ጎሠኛ የአገዛዝ መዋቅር ውስጥ የተፈጠሩ እና የሚፈጠሩ ውጥረቶችን ማርገብ፣ ውዝግቦችን ማረጋጋትና ቀዳዳዎችን መሙላት አይደለም። ይልቅስ፣ መዋቅሩን ከነሃሰት ትርክቱ እንዳለ መናድና በተሻለ፣ ከዘረኝነት የጸዳ፣ ለመላ የኢትዮጵያ ዜጎችና ባህላዊ ማኅበረሰቦች በሚበጅ፣ መልካም ታሪካዊ ትስስራቸውን በሚመጥን፣ አዲስ ሥርዓተ መንግሥት መተካት ነው። 

መሠረታዊ የአንድነት፣ አካባባዊነት፣ ነፃነት፣ እኩልነት፣ የዲሞክራሲና የልማት ጉዳዮችን አስመልክቶ ንቅናቄው የሚያዳብረው ግንዛቤ የማንነት የፖለቲካ ሥርዓቱ በጉዳዮቹ ካለ፟ው ነባር የተወላገደ ዘረኛ አረዳድ ጋር ሊስማማ ቀርቶ በምክንያታዊ ክርክር ሊግባባም አይችልም። በጥልቅ ስልት ሥርዓታዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስፈልገው ለዚህ ነው። 

የለውጥ ትግሉ ፖለቲካ

10. በአንዳንድ የአማራ ተቆርቋሪ ወገኖች ዘንድ ፖለቲካን ከአማራው የመኖር አለመኖር ትግል ለይቶ እንደ ትርፍ እንቅስቃሴ (እንደ ቅንጦትም) የማየት አዝማሚያ አለ። ሆኖም፣ ፖለቲካ አየነት አይነት አለው፤ በድፍኑ መደበኛ ወይም ዋና የተቃውሞ ንቅናቄ ላይ ታካ፟ይ፣ የምቾት እንቅስቃሴ ሆኖ ሊታይ አይችልም።  

ፖለቲካ የፋኖም ሆነ የአማራው ማኅበረሰብ ህልውና ትግል ተጨማሪ ጥረት ሳይሆን የትግሉ ዋና አካል፣ አደራጅ መርህና መሣሪያ ሊሆን የሚችል ነው። የመኖር አለመኖር ተጋድሎውን ጽኑ ድርጃታዊ ሥርዓትና ዘላቂ አቅጣጭ ያስይዛል። ፖለቲካ ለአንድነት እንቅፋት በሆነ ዘረኝነት ወይም አጉል በረቀቀ ርዕዮት አማካኝነት ከውጭ በፋኖ ትግል ጣልቃ የሚገባ ሳይሆን ትግሉን ከውስጥ አግባብ ባለው አስተሳሰብ የሚያጠራ፣ በድርጅት የሚያጠነክርና በስልት የሚያዳብር በጎ ተጽዕኖ ማሳረፍ ይችላል።

የፋኖ፟ ንቅናቄ የአማራውና የኢትዮጵያ መከታ ስለሆነ ዘላቂ የፖለቲካ ድርጅትና አመራር በጥልቅ ማካተቱ ግድ ይላል። ንቅናቄው ዛሬ እንዳለ፣ ማለትም ለተለያዩ የህልውና አደጋዎች እንደተጋለጠ በመቀጠል ዘመኑ የጣለበትን ከባድ ኃላፊነት በብቃት መወ፟ጣቱ ቀርቶ ራሱን በአንድነት ከጥፋት መታደግም ያዳግተዋል። 

ትግሉ የተማከለ ፖለቲካዊ ቅርጽ ካልያዘ የያካባቢዎች ተነጣይ ፋኖ፟ ጓዶች (ወገኖች) ጥርቅም ከመሆን ባሻገር የአንድነት ግቡን ማሳካት ይከብደዋል። ወይም ደግሞ በሰፊ አገር አቀፍ መጠንና በረጅም ጊዜ ደረጃ የመነቃነቅና በሂደት የመዳበር አቅሙ እንደተወሰነ ሊቀር ይችላል። ስለዚህ የፋኖ ንቅናቄ ሁነኛ ስልታዊ የፖለቲካ አስኳል ፈጥሮ በቀጣይነት የራሱን ደህንነት ነቅቶ መጠበቁ፣ ድርጅታዊ ኃይሉን መገንባቱ፣ እንዲሁም ከሌሎች አገር ወዳድ ወገኖች ጋር ያለውን ትብብር ማጠናከሩ ለትግሉ ዘላቂነትና አሸናፊነት ወሳኝ ክንውኖች ናቸው።     

 

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here