spot_img
Saturday, July 13, 2024
Homeነፃ አስተያየትአድርባይነት ! የሞራል ዝቅጠት : የለውጥ መርገም ! (ኢዜማ?) (ከቴዎድሮስ ሐይሌ)

አድርባይነት ! የሞራል ዝቅጠት : የለውጥ መርገም ! (ኢዜማ?) (ከቴዎድሮስ ሐይሌ)

ከቴዎድሮስ ሐይሌ

አንድ ንጉስ ልጅ ይወልድና ታላቅ ደስታ በቤተመንግስቱ ይሆናል :: ንጉሱም የተወለደው ልጁ የወደፊት እጣ ፋንታእጅግ ያሳስበና በዘመኑ ያሉ አዋቂ የተባሉ ጠንቋዮች ኮከብ ቆጣሪዎችን ደብተራና አስማተኞችን አስጠርቶ ልጁሲያድግ ምን እንደሚሆን ይጠይቅ ጀመር:: ሁሉም በየተራ እየተነሱ ልጁ አድጎ የአባቱን ግዛት እንደሚያስፋፋበሃይለኝነቱ ጠላቶቹን የሚደመስስ የጦር ሰው እንደሚሆን ሌላም ሌላም የውዳሴ ትንቢት እያዘነቡ የንጉሱንመንፈስ በሃሴት ሞሉት ::  

 በዚህ የአድርባዮች በነገሱበት የንጉስ እልፍኝ በአዋቂነቱ ተጋብዞ የነበረ አንድ ፈላስፋ ካነበበው ታሪክከመረመራቸው መጽሃፍት አንጻር የንጉሱንን ልጅ የመጪ ዘመን እድል እንዲናገር በንጉሱ ይታዘዛል:: ፈላስፋውም ንጉስ ሆይ ሺ አመት ንገስ እኔ የማውቀው ቢኖር ልጁ ጎርምሶ ሆነ እርጅቶ እንድ ቀን ሟች መሆኑንአውቃለሁ:: ስለ መጪ ዘመኑ እድል ፋንታ ግን የማውቀው የለም ብሎ ይቀመጣል:: 

 በንጉሱ ስጦታና በግብዣው ወይን ጠጅ ልቡ የተደፈነው የአድርባይ መንጋ ይህ ፈላስፋ መጥፎ ተመኝቷል : በታላቁ ንጉሳችን ልጅ ላይ አሟርቷል:: ፍርድ ይገባዋል በሚል በእድርባዮች ተከሶ ንጉሱም በከንቱ ውዳሴ አይነልቦናው ታውሮ ሊሆን የሚችለውን ከመጽሃፍት ያነበበውን ከሕይወት የተማረውን እውነት የተናገረውን ፈላስፋበሞት እንዲቀጣ ወሰነበት ይባላል:: 

 የአድርባይ ምላስ ለሞላ መሶብ ስልጣን ለያዘ ሹም ሃብት ላካበተ ከበርቴ ለመነጠፍ ሃሰት ለመዝራት ከንቱውዳሴን ለማዝነብ የሚቀድማት የለም:: አድርባይ ለሞቀ ዙፉን ሰጋጅ ቀን የሞላለት አይጥ አንበሳ ጭለማውንብርሃን ብላ ለመግለጽ የሚለጉማት ሞራል የተባለው የሕሊና ጠፍር የላትም::  አድርባይነት የለውጥ እንቅፋትየፖልቲካ ቫይረስ ናት::  

 በተለይ ለሃገራችን መቆርቆዝ ዛሬ ለደረስንብት ውድቀት የአድርባዮች ሚና የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል:: ጃንሆይመቃብር ሲማስላቸው ሞት ተደግሶ ቀን ሲቆጠርላቸው : ስህተታቸውን አውቀው ለማረም እንዳይችሉበከበቧቸው መንጋ አድርባዮች ከንቱ ውዳሴ ታንቀው ላሳፋሪ ፍጻሜ በቅተዋል::  ሊቀመንበር መንግስቱምበተመሳሳይ ባቡር ተሳፍረው ለስደት እንደበቁም አይተናል:: 

 ለዚህ ነው መካሪ የሌለው ንጉስ ያለ አመት አይነግስ አባቶች የሚሉት:: ምክር ሰይፍ ናት ትቆርጣለች:: ትችትሞረድ ሆና ትስላለች:: ሂስ ኮንፖስ ሆና አቅጣጫዎችን ታሳያለች:: እውነት መስተዋት ነችና ጉድፍን ታሳያልች:: ልባም መካሪ እንዲህ ነው:: ይህን መሰል እስተዋይነት የተሞላው መካሪና ወዳጅ መሪዎች እያጡ ባልሆኑትእንደሆኑ : ከስረው እንዳተረፉ ተዋርደው እንደከበሩ በጣፈጡ ቃላት ተሽሞንሙነው ወደ አይቀሬው ውርደትያዘግማሉ:: 

 ለአድርባይነት ሰው የሚጋለጠው የስልጣን ጥማት ሕሊናውን ሲጋርደው : አፍቅሮት ንዋይ እረፍት ሲነሳው : ወኔሲያጥር ድፍረት ስትነጥፍ ፍርሃት ሲያይል ነው:: ሆዳምነት ለከት ሲያጣ ለቁሳዊ

አላፊና ጠፊ እንስሳዊ ባህሪ ይዳርጋል:: ሕሊና ሲደርቅ መንፈሳዊነት ሲሳሳ ስጋዊ አረም በላያችን ሲነግስ የአድርባይነት እርጉም መንፈስና የሞራል መርገምት የሃገር ደዌ ይሆናል::  

 ምሳሌዎች በሽ ናቸው ከጁንዲን ሳዶ እስከ አየለ ጫሚሶ : ከካሱ ኢላላ እስከ ታምራት ላይኔ : ብዙ አይተናል:: የሃይለማርያምን ባዶ ወንበር የነጋሶን መገለል : የገነት ዘውዴን ቅጥ ያጣ ምግባር በየፈርጁ አይተናል :: መርሕ እውነትና ሃቅ ይዘው እስከመጨሩሻው የጸኑ ጀግኖች በቁጥር እጅግ ቢያንሱም ለትውልድ ተምሳሌት የለውጥ ብርሃን ሆነውን ተስፋችን በአድርባዮች ጠውልጎ እንዳይጠፋ ጠል ሆነውናል:: 

 ዛሬ ሃገራችን ያለችበት ሁኔታም ታሪክ እራሱን ይደግማል እንዲሉ ከዛው አሮጌ አድርባይንት ከነገሰበት ዋሻ አልወጣንም:: አበው በካባ ላይ ደበሎ እንዲሉ ፖለቲካችን ላይ ጨለምተኛ የጎሳ እርዕዮት ተጨምሮበት አድርባይነት ሲታከልበት የሚፈጥረው ተጽዕኖ ለመገመት ከባድ ነው:: 

 አሁን ደግሞ በመደመር ወሽመጥ በአድርባዮች ሰልፍ ውስጥ እነ ዶር ብርሃኑን እያየን ነው::  ማህበራዊ ፍትህን የሚያህል ታላቅ ሕዝባዊ አጀንዳ ተሸክሞ የአማራጭ ፓርቲ ሚና ለመወጣት ተቋቁሚያልው የሚለው ኢዜማ እየተናጠ ያለበት ውስጣዊ ቅራኔ ዕሪዎታለማዊ ወይም እስትራቴጂያዊ ጥያቄ አይደለም:: በፓርቲው መርህና በሚከተለው ፍልስፍናም አይደለም:: ዋናው የፓርቲው ቀውስ ለገዥው ፓርቲ ለመንበርከክ ሱሪያቸውን ባወለቁና የሕዝብና የሃገርን ጉዳይ እናስቀድም የሚል ባርኔጣ ባጠለቁ መካከል እንደሆነ በገሃድ እየታየ ነው:: 

 የዛሬው የዶር ብርሃኑ አቋምና ሲያራምዱት የቆዩት ተግባር የፖለቲካ አድርባይነት የተጣባው ሃላፊነት ካለበት የድርጅት መሪ የማይጠበቅ ነው:: ግለሰቡ ባላቸው ስብዕና ከብዙ አቅጣጫ ብዙ ቢባሉም ሌሎች ያልሰሙ ትጥቂቶች የምናውቀው የሴራና የአሻጥር ፖለቲካ ተዋናይ ቢሆኑም ያለፈውን ሁሉ ትቶ ባለው የለውጥ ሂደት ውስጥ ተሽለው ይገኛሉ የሚል እምነት ነበረ :: ያ ቢቀር እንኳ በዚህ ደረጃ ወርደው የአድርባዮችን ካንፕ ይቀላቀላሉ ብሎ የሚገምትም አልነበረም:: 

 አብይን ዛሬም አምነዋለሁ የሚሉት ጎምቱው የሴራ ፖለቲከኛና የኢኮኖሚ ኤክስፐርቱ ብርሃኑ የአድርባይነትን ጥግጋት ከአንድ የታሪክ ኩነት ጋር ይመሳሰልብኛል:: 

 አድርባይነት በየዘመነ መንግስቱ የተለያየ ባህሪና ገጠመኝ አለው:: በ66 አብዮት ማግስት ገና በአፍላው የተፈጸመ ወደር የለሽ የአድርባይነት ጥግ በታሪክ ተሰንዶ ማየት ይደንቃል:: ከፈረሱ አፍ እንዲሉ ከጊዜው ተራማጆች አንዱ የሆኑት ዶ/ር አማረ ተግባሩ ኃይሌ ፊዳ እና የግሌ ትዝታ በሚል እርዕስ በጻፉት መጽሃፍ በገጽ 137 እንዲህ ብለውያሰፈሩት ይጠቀሳል:: 

 “’ኢሃፓ ፍቅሬ መርድን ከገደለ በሗላ ለደህንነትችን ሲባል ኮሎኔል መንግስቱ መኖሪያ ቤት እያመሸን በአጃቢ ወደቤታችን እንሸኝ ነበር:: አንድ ቀን እንደወትሯችን የፖለትካ ክርክሩ አብቅቶ ወደ ጨዋታና ቀልዱ አምርቶ እሳቸውም ዘና ብለው ከተቀመጡበት ሶፉ ላይ ሆነው ሰዓቱም እየመሸ በመሄዱ ይሆን የተለምዶ የወታደር ቡት ጫማቸውን ክር ለመፍታትና ካንጋቾቻቸው መካከል ለእግራቸው ሙቅ ውሃ ይዞ በመቅረብ ላለው ሰው እራሳቸውን ሲያዘጋጁ ሌላው አንጋቻቸው ጫማቸውን ለመፍታት ተንደረደረ:: ይህንን የተመለከተው ከሕብረቱ ድርጅቶች መሪዎች መካከል አንዱ ሰውም አብሮ ተንደርድሮ ካንጋቹ ጋር ትንቅንቅ ያዘ:: ይህን የተመለከቱት ኮሎኔል መንግስቱ ኧረ አይገባም ቢሉም .. ይህው ከህብረቱ

ድርጅቶች መሪ አንዱ የሆነው ሰው ጡንቸኛና ፍርጥም ያለ ስለነበር አንጋቹን ገፍትሮ ጫማቸውን አውልቆ እግራችውን አጠበ:: ግለሰቡ አጠባውን ጨርሶ ወደ መቀመጫው ሲመለስ የሚያስነውር ሳይሆን የሚያኮራ ተግባር እንደፈጸመ ፈገግ እንዳለ ወደ መቀመጫው ተመለሰ”  

 በዚያን ግዜ በኮሎኔል መንግስቱ ቤት አብረው የነበሩት የኢማሌድህ ድርጅት መሪዎች ነበሩ:: በግዜው የግራ ፖለቲካ እርዕዮተ አለም የሚጠበቡት የመኤሶኖቹ ሐይሌ ፊዳ አንዳርጋቸው አሰግድና ፖለቲካን የሚራቀቁባት ዶርነገደ ጎበዜን አቶ አሰፉ ጫቦ ዘገየ አስፉውና ዶር ሰናይ ልኬን የመሰሉ  አብዮተኞች የታደሙበት ስብስብ ነበር:: ጸሃፊው ተንበርካኪውን እግር አጣቢ የፖለቲካ መሪ እከሌ ነው ብለው በመጽሃፉቸው ስሙን ባይጠቅሱም ዶር ሰናይ ልኬ እንደነበር በወቅቱ እዛ አካባቢ ከነበሩ ሰዎች ሰምቻለሁ::  

 ዛሬስ እግር ለማጠብ የተሰለፉት ምሁራን የሉም ወይ? የእነ ዶር ብርሃኑ አብይን አምነዋለሁ የሚለው አቋም ከአድርባይነት የተቀዳ እምነት አይደለምን? አብይ የብሄር ፖለቲካን አስወግዶ ሃገራዊ አቋም እንዲጠናከር ያግዛል ሲሉም አልነበር? የታል ኢትዮጵያዊነት? ዛሬ ላይ ሰዎች በማንነታቸው በሺዎች ታርደው የሚያድሩበት ሃገር በዚህ ዓለም ላይ ከኢትዮጵያ ውጪ ማንም የለም:: ተረኝነት አፍጥጦ በሚታይበት ጄኖሳይድ የዕለት ዜና በሆነበት ገዥው ቡድንና ጠቅላይ ሚንስትሩ ከብሄር ፖለቲካ ቀኖናቸው ሳይላቀቁ ፖርቲያቸው ግጭት ጠማቂና ፍጅትፈጻሚ በሆነበት የሰቆቃ ምድር እንዴት ተስፉ ይሆናል:: በዚህ ሁሉ ሰቆቃ ውስጥ ዛሬም ለነዶር ብርሃኑ መንገድም ሕይወትም አብይ ነውን? ሕዝብ የሚጠይቀው ይህንን ነው?  

 አንድ አማራጭ ፓርቲ የሚመራ መሪ የመርከቧን ቀዳዳ ለመድፈን ከመታገል ይልቅ የካፒቴኑን ባዶ የተስፉ ኑዛዜ አምኖ አብሮ ለመስመጥ የሚያድርገው ምን ሃይል ይኖራል:: ከፍርሃት ከሞራል አልባነትና ከአድርባይነት ውጪ:: እንደ ዶር ብርሃኑ በኢትዮጵያ ፖለቲካ እድሜውን የጨረሰ ፖለቲከኛና ጥርሱን የነቀለ የአራዳ ልጅ እንደወረደ በባዶ የባልቴት ፕሮፓጋንዳ ሊነዳ የሚችልበት ምንም ምክንያት የለም:: ከላይ እንዳነሳንው ከተልዕኮው ውጪ በማይመልከተው የእግር አጣቢነት የተሰማራው የፖርቲ መሪ ለግርድና ያንብረከከው የሞራል ዝቅጠት የአድርባይነት መንፈስ ብቻና ብቻ ነው:: 

 የትግሉ እርዝማኔ በየፌርማታው የሚያወርዳቸው የጽናት ማጣት ትጥቃቸውን የሚያስፈትቸው የስልጣን ፍርፋሪ የቤተመንግስቱ እልፍኝ የሚያንበረክካቸው መርህ የለሾች በታሪክ ፊት ማየታችን ትላንትም ነበር ዛሬም ይቀጥላል:: በዛው ልክ የአቋም ሰዎች አሻራቸውን እያኖሩ በጥላቸው እያስበረገጉ በሃሳብ ሰይፍ እየመተሩ ምርኮኛና ምስለኔውን ብቻ ሳይሆን ገዢዎችንም እያራዱ ትግሉ ይቀጥላል:: ኢዜማ ውስጥ ሕዝባዊና ሃገራዊ ስሜት ያላችሁ ከየትኛውም ዘውግ ይሁን ሃይማኖት ውጡ በመርህ የምትመሩ ሞራልና እውነትን ትጥቅ አድረጋችሁ አድርባይነትን ልትጠየፉት ይገባል:: ለራሳችሁ ክብር ለልጆቻችሁና ለትውልድ የሚኖር አሳፉሪና አዋራጅ ታሪክ እንዳታወርሱ ተጠንቀቁ:: ለባለግዜ ዘረኛ ገዥዎች በአድርባይነት የሚታየው የፓርቲያችሁን አዋራጅ ምስል ለውጣችሁ ወደ ሕዝባዊነት ከፍታ ልትመልሱት ግድ ይላችሗል:: አለያ እውነት ጨልማ ሞራል ጠውልጋ አድርባይነት ደግፎት የሚጸና ወንበር አይኖርም::  መጨረሻውም ለሰጋጁም ለአሰጋጁም አያምርም:: የጨለመው መንጋቱ ሕዝብ የድሉ ባለቤት መሆኑ ዲሞክራሲ ሰፍኖ በዘረኝነትና በአድርባይነት መቃብር ላይ የሃሳብ የበላይነት በሃገራችን መረጋገጡ ቢዘገይም አይቀሬ ለመሆኑ አንጠራጠርም:: 

 በመጨረሻም ኢዜማዎች ከታሪክ ተማሩ በእራሳችሁ እንዳታፍሩ!!! 

 ድል ለሕዝባችን!!!

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here