spot_img
Saturday, May 25, 2024
Homeነፃ አስተያየትለሁሉም ነገር መልሱ ነውጥና አብዮት ሊሆን አይችልም። (ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ )

ለሁሉም ነገር መልሱ ነውጥና አብዮት ሊሆን አይችልም። (ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ )

ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ
ሰኔ 30, 2014 ዓ. ም.

ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ጊዜ አብዮት ተካሂዷል። ሁለቱም አብዮቶች፤ የሕዝባችንን ስቃይ ከማባባስና የሃገራችንን ቀውስ ከማራዘም ውጭ፤ የሕዝቡን ጥያቄ አልመለሱም። በኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን በበርካታ ሃገሮች እንዳየነው፤ በአብዮት ለውጥ ለማምጣት የሚደረግ ጥረት፤ ትርፉ የሃገር ቀውስ፤ ከዛም አልፎ የሃገር መፍረስ መሆኑን ነው። ለዚህም ይህ ትውልድ ቋሚ ምስክር ነው። በሊብያ፤ በየመን፤ በሶሪያ፤ የተደረጉት አብዮታዊ ለውጦች፤ መጨረሻቸው፤ ሃገር፤ እንደሃገር እንዳይቆም ያደረጉ ናቸው። በግብጽና በሱዳን ዛሬም የምናየው ትርምስ፤ አብዮት የወለደውና፤ የሃገራቱን ዕጣ ፋንታ መተንበይ የሚያስቸግርበት ሁኔታ የፈጠረ ነው። 

ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ፤ የሕዳሴ ለውጥ (Reform) ያደረገችው፤ በ2010 ዓ.ም. ሲሂን፤ ለዚህ ያደረሰንም የ1983 አብዮት፣ ለሃገር ደንታ በሌላቸው ዘረኞችና፤ ሃገር ጠል በሆኑ “አብዮተኞች” ለ27 ዓመታት የደረስብንን ግፍና በደል፤ ሕዝቡ አልሸከምም በማለቱ ነው። እነዚህ ሃገር ጠል አብዮተኞች፤ ከሥልጣን መንበራቸው ሲነሱ፤ ለህዳሴው ለውጥ የጉሮሮ አጥንት እንደሚሆኑ ሳይታለም የተፈታ ነበር። የሕዳሴው ለውጥ መሪዎች፤ ጅምራቸው በፈተና የተሞላ ብቻ ሳይሆን፤ የፀጥታ፤ የመከላከያ፤ የሕግ አስከባሪውንና ሌሎች ወሳኝ የሚባሉ መዋቅሮችን፤ ፀረ-ኢትዮጵያ ኃይሎች ተቆጣጥረውት ስለነበር፤ የህዳሴውን ለውጥ በፈተና የተሞላ እንዲሆን፤ መንገድ ላይ ወቅት እየጠበቀ የሚፈነዳ ቦምብ ተክለው እንዲሄዱ እድል ሰጥቷቸዋል። በመጨረሻም ጓዛቸውን ጠቅልለው፤ ወደ መቀሌ ሲሄዱ፤ ለሃገራችን፤ የእልቂት ድግስ ደግሰው፤ የእራሳቸውን ቀጣይ እርምጃ ደግሞ አመቻችተው ነበር የሄዱት። 

እነዚህ ኃይሎች፤ ከሃገር የዘረፉትን አንጡራ ሃብት፤ ለሃገር ጠላት የሆኑ ኃይሎችን ለመመልመል፤ ለማደራጀትና ለማስታጠቅ ብቻ ሳይሆን፤ ለፕሮፖጋንዳውና አለም አቀፍ ዲፕሎማሲያዊ ተጽእኖም ለመፍጠር ይጠቀሙበታል። በሥልጣን ላይ በነበሩ ጊዜ “እኛ ኢትዮጵያን ካልገዛን፤ ትበታተናለች” ይሉት የነበረውን፤ ቅዠት እውን ለማድረግ ተግተው በመስራት ላይ ይገኛሉ። እራሳቸውን አግዘፈው የሚያዩ በመሆናቸው፤ በጦርነት ሕዝብ አንበርክከን ወደ ሥልጣን እንመጣልን በሚል ሕልም፤ የሞከሩት ቀጥተኛ ጦርነት ሲከሽፍ፤ አዘጋጅተውልን ወደ ነበረው የእርስ በእርስ የግጭት ስትራቴጂያቸውን (Plan B) እውን ለማድረግ፤ ንፁሃን ዜጎችን በመግደልና በማስገደል፤ አረመኔያዊ ድርጊታቸውን እየፈፀሙ ነው። ይህ አደገኛ ሃይል፤ በተለያዩ የመንግሥት መዋቅራት እና በገዥው ፓርቲ ውስጥ፤ ያሰማራቸው የአምሰተኛ ረድፍ ተዋንያን፤ መረጃ በማቀበል፤ በቀጥታና በተዘዋዋሪ፤ ለሽብርተኞች መመሪያና ስምሪት በመስጠት፤ በተለይም በአማራው ሕዝባችን ላይ አሰቃቂ ጥቃት እንዲፈፀም አድርገዋል። 

የአማራው ሕዝብ ላይ ጥቃት የሚፈፀመው፤ ዋናው ዓላማ፤ በአማራው እና በኦሮሞ ፖለቲካ ሃይሎች ብቻ ሳይሆን፤ በሕዝቡም ውስጥ አለመተማመን ለመፍጠርና ሁለቱን ታላላቅ ብሔሮች ማጋጨት ከተቻለ፤ ሃገር ለማፍረስ ቀላል መሆኑንም ስለሚያውቁ ነው። የአሁኑ የሕወሃት “ቃል አቀባይ” ባለሥልጣን በነበረበት ወቅት፤ ከአንድ ባልሥልጣን ቀርቶ፤ ከአንድ ቦዘኔ በማይጠበቀ ያልተሞረደ አንደበቱ “አማራና ኦሮሞ እሳትና ጭድ ናቸው” ማለቱ ያለምክንያት አልነበረም። ሕወሃት ብቻ ሳይሆን፤ የውጭ ጠላቶቻችንም፤ በአማራውና በኦሮሞው ሕዝባችን መካከል መከፋፈልና ግጭት ከተፈጠረ፤ ኢትዮጵያን ወደ የሚፈልጉት አቅጣጫ መውሰድ እንደሚችሉ ያውቃሉ። ለሕወሃት የ27 ዓመታት አሰቃቂ አገዛዝ፤ አንዱና ዋነኛው ምክንያትም፤ በኦሮሞው እና በአማራው “ምሁራን” መካከል የነበረው አለመተማመን እና የርስ በእርስ ቁርቋሶ እንደነበር ነጋሪ የሚያሻው አይመስለኝም። በጠላቶችችን እምነት፤ “ኦሮሞ” የሆነው ጠቅላይ ሚንስትር ስኬታማ እንዳይሆንና፤ በአብዮት ከሥልጣን እንዲነሳ ለማድረግ፤ አማራውን እና ኦሮሞውን ከማጋጨት ውጭ አማራጭ አላገኙም። 

በአማራውና በኦሮሞ መካከል የሚፈጠር ግጭት፤ ለዘመናት የማይበርድ እንዲሆንም ጠንክረው ይሰራሉ።                                                                    ይህ እኩይ ዓላማ ሊሳካ የሚችለው፤ እኛ ከተባበርናቸው ብቻ ነው። ስለዚህ፤ ሁላችንም ስሜታችንን በመግራት፤ በነውጥ እና በአብዮት ሳይሆን፤ የሕዳሴው ለውጥ ከግብ እንዲደርስ ተግተን መስራት የሚኖርብን። ይህ የህዳሴ አብዮት፤ የዶ/ር ዓብይ አሕመድ ወይም የብልፅግና ፓርቲ አይደለም። ውድ የኢትዮጵያ ልጆች፤ ከፍተኛ መስዋዕትነት የከፈሉበት የለውጥ ሂደት እንጂ። ብዙ ጊዜ ስለሕዳሴው ለውጥ ግብ ስናወራ፤ አንዳንዶች፤ ጉዳዩን፤ የዶ/ር ዐብይን ሥልጣን ከማስቀጠል ጋር ብቻ ያያይዙታል። በዚህ ጎዶሎ አመለካከታቸውም ትልቁን ስዕል ይዘነጋሉ። ማንም ይሁን ማን፤ ቋሚ አይደለም፤ ዐብይም ነገ ሂያጅ ናቸው። ቋሚና ቀጣይ ሊሆን የሚችለው ግን ከትውልድ ትውልድ የሚሸጋገር ስልተ ሥርዓት ስንገነባ ነው። ይህንን፤ ሕዝብን የሥልጣን ባለቤት ያደረገ ሥልተ ሥርዓት ግን ባካሄድናቸው የአብዮታዊ ለውጦች ልናሳካ አልቻልንም። ተግተን፤ አስበን፤ ተባበርን ከሰራን ግን፤ ለዘመናት የተጮኸንበትን፤ ስንት ብርቅዬ ዜጎቻችንን የገበርንበትን፤ ሥልጣን የሕዝብ የማድረግ ዓላማችንን ከግብ ማድረስ እንችላለን። ይህ ማለት ግን፤ ለማንም ጭፍን ድጋፍ እንስጥ ማለት አይደለም። ተጠያቂነት የሌለበት ሥልተ ስርዓት፤ ሥልጣንን የሕዝብ አያደርግም። ተጠያቂነት እንዲኖር እና የሕግ የበላይነትም እንዲከበር፤ ዜጎቻችንን ከአላሰፈላጊ እልቂት ለመታደግ፤ ሁላችንም የተጣለብንን ኃላፊነት መወጣትና እጅ ለእጅ ተያይዘን፤ እንክርዳዱን ከስንዴ እየለየን፤ በአንድ ላይ ሆነን የውስጥም የውጭም ጠላቶቻችንን ተባብረን በቁርጠኝነት መታገል አለብን።                                            

መረዳት ያለብን፤ ከእነዚህ እኩይ ኃይሎች ጋር ጦርነት ውስጥ ነው ያለነው። ነገም ደግመው ንፁሃን አማሮችን ሊገድሉ ይችላሉ። በተለይ በኦሮምያ እና በቤሻንጉል ክልል የአማራውን ሕዝባችንን መሳደድንና መጨፍጨፍን ማስቆም፤ ለነገ የሚባል መሆን የለበትም። በኦሮምያ ክልልም ሆነ በፌደራል መንግሥቱ በኩል፤ ፈተናዎቹ እንደተጠበቁ ሆነው፤ከፍተኛ ድክመቶች አሉ። የፌደራሉም ሆነ የክልሉ አስፈፃሚው አካል፤ የፌደራል ምክር ቤቱና የኦሮምያ ጨፌ ሥራቸውን በሚገባ አይሰሩ ነው ለማለት አያስደፍርም። እኛም እንደዜጋ ሃላፊነታችንን አልተወጣንም። ዜጎቻችን በተጨፈጨፉ ቁጥር ማዘን፤ ማልቀስ፤ እና ሻማ ማብራት፤ ለዜጎቻችን ሕይወት የሚፈይደው ምንም የለም። ቀጣዩ ጥያቄ፤ ሽብርተኞችን አይቀጡ ቅጣት ለመቅጣትና፤ ድል ለማድረግ ምን መደረግ አለበት የሚል መሆን አለበት። በእኔ እምነት ጊዜ ሳይሰጠው መደረግ ያለባቸው ነገሮች የሚከተሉት ናቸው።

-የፌደራል መንግሥቱ፤ ልክ በቤኒሻንጉልና ጉሙዝ ክልል እንዳደረገው፤ ከተለያዩ ክልሎች የተውጣጡ ልዩ ኃይል አባላትንና የፌደራል ፖሊስን በኦሮምያ ክልል ውስጥ፤ በተለይም ጥቃት ሊፈጽምባቸው ይችላሉ የተባሉ ቦታዎች ተለይተው፤ ማዝመትና ለነዋሪዎች ጥበቃ ማድረግ። በእኔ እምነት አንዱ የሕወሃት እቅድ፤ የመከላከያውን ሰራዊት፤ በተለያዩ አካባቢዎች እንዲወጠር በማድረግ፤ “ሥስ” ቦታዎችን መፍጠር በመሆኑ፤ መከላከያው “ከዋናው ኳስ” ላይ ዓይኑን እንዳያነሳ ማድረግ ያስፈልጋል።

-ጉዳት ለደረሰባቸው እና የቤተሰብ አባላቶቻችውን ላጡ ተጎጂዎች፤ እንዲሁም ከቤት ንብረታቸው ለተፈናቀሉ መንግሥት አስቸኳይ ድጋፍ ያድርግ።

-የፌደራሉ ምክር ቤት በአስቸኳይ፤ የፀጥታ ባለሙያዎችን ያካተተ፤ ገለልተኛ ኮምሽን በማቋቋም፤ ምርመራ እንዲደረግ ማድረግ፤ ውጤቱን ለሕዝብ ይፋ ማድረግ፤ እንዲሁም ሥራቸውን ባልሰሩና ከጠላት ጋር የተባበሩ ባለሥልጣናትን ለይቶ ሕጋዊ እርምጃ መውሰድ። 

-የኦሮምያ ጨፌ፤ በዚህ ጉዳይ ትኩረት ሰጥቶ፤ የክልሉን ርዕሰ መስተዳድር፤ የፖሊስ ኮሚሽነሩንና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸውን ባለሥልጣናት ጠርቶ እንዲጠይቅ፤ አስፈላጊም ከሆነ የፌደራሉ ምክር ቤት ከኦሮምያ ጨፌ ጋር በጋራ ምርመራ (investigation) ለማድረግ ሁኔታዎችን ማመቻቸት።

-እያንዳንዱ ክልል፤ የየክልሉን ነዋሪ በማስተበበር፤ በአማራው ሕዝብ ላይ የተደረገውን ዘር ተኮር ጭፍጨፋ፤ እንዲያወግዝ ማድረግ። በአማራው ሕዝባችን ላይ የተደረገው ጭፍጨፋ፤ የአማራው ጉዳይ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም መሆኑን መግለጽ፤ እና አንድነታችንን ማሳየት ያስፈልጋል። 

– ከዚህ በተጨማሪ፤ በተለይም በአማራና በኦሮሞ ልሂቃን መካከል ውይይቶችና ጥናቶች ላይ የተመረኮዝ ሰነድ ለሕዝብ ይፋ ማድረግና በአማራው ሕዝባችን ላይ የሚደረገውን ጭፍጨፋ በማውገዝ የአቋም መግለጫ ማውጣት። 

– እኛም እንደዜጋ፤ የምክር ቤት አባላት፤ የጨፌ አባላት፤ እንዲሁም ልሂቃን ላይ ግፊት በማድረግ፤ የተሻለ ሥራ እንድሰራ፤ ለዜጎቻችንም አስፈላጊው ጥበቃ እንዲደረግ ማድረግና፤ ሕዝቡ ከፀጥታ ኃይል ጋር በመተባበር አጥፊዎችንና ለጥፋት የሚዘጋጁ ኃይሎችን እንዲያጋልጥ፤ ግፊት እንፍጠር። ከሁሉም በላይ ደግሞ ሕግ እንዲከበር የበኩላችንን እናድርግ። በነውጥ እንዲመጣ የምንፈልገው ለውጥ የከፋ ሊሆን እንደሚችልም እንገምት፤ በስሜት ሳይሆን በእውቀት እንራመድ። 

ዶ/ር ዐብይ ከሥልጣን እንዲነሱ የምትፈልጉ ሰዎች ምርጫዎች አሏችሁ። ፓርላማው ከሥልጣን እንዲያነሳቸው ማድረግ፤ አልያም፤ በቀጣዩ ምርጫ ተደራጅታችሁ በምርጫ እንዲሸነፉ ማድረግ ነው። ከዚህ ውጭ፤ በአቋራጭ ሥልጣን ለመያዝ የሚደረግ ሙከራ፤ አደጋው የከፋ መሆኑን እና ከግጭት አዙሪት የማንወጣበትን መንገድ መምረጥ መሆኑን መረዳት ያስፈልጋል። አሁን የተጀመረውን፤ ሰላማዊ የሥልጣን ሽግግር አጠናክረን መቀጠልና ለዲሞክርሲያዊ ስልተ ስርዓት መገንባት ተግተን ልንሰራም ይገባል። ያለንበት የትግል ወቅት፤ ሰዎችን በመቀያየር ሽብርተኝነትን የምናሸፈበት ወቅት አይደለም። ሕወሃት፤ ወደ ሥልጣን እስካልመጣ ድረስ፤ ሃገር ውስጥ መረጋጋት እንዳይኖር ተግቶ እንደሚሰራ እና፤ ለዚህም የመረጠው መንገድ አማራውን በመጨፍጨፍና በማስጨፍጨፍ፤ በኦሮሞና በአማራ ሕዝብ መካከል ጠላትነትን ማስፈን ነው። ይህ የማናውቀው ወይም ድብቅ ነገር አይደለም። ይህንን እያወቅን፤ የእነዚህ እኩይ ሰዎች ዓላማ እንዲሳካ፤ ለምን እንደምንከፋፈል አይገባኝም። አምስተኛ ረድፎችን ማጥራት የምንችለው ስንተባበር ነው፤ ዋልጌና ቸልተኛ ባለሥልጣናትን የምናነሳውና በሕግ ተጠያቂ እንዲሆኑ የምናደርገውም ስንተባበር ነው። ስለዚህም ከነውጥና ከአብዮት ይልቅ ለሕዳሴው ለውጥ መሳካት፤ ተግተን እንስራ። 

ቸሩ እግዚአብሔር፤ ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ።  
__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here