ጥበበ ሳሙኤል ፈረንጅ (ሃምሌ 14 2014)
“አውቆ የተኛን፤ ቢቀሰቅሱት አይሰማም” (ሃገራዊ ብሂል)
የኢትዮጵያ ሕዝብ፤ ከ50 ዓመታት በላይ የጮኸው፤ የታገለው እና ከፍተኛ የሕይወት መስዋዕትነትም የከፈለው፤ እራሱ ወዶና ፈቅዶ በመረጠው መንግሥት እንዲተዳደር ነው። ይህ ሁሉ ትግልና መስዋዕትነት፤ በሰኔ 2013 መልስ አግኝቶ፤ ሕዝቡ ሊያስተዳድረኝ ይችላል ብሎ ያመነበትን፤ መርጧል። ምንም እንኳን ይህ ምርጫ በአብዛኛው የኢትዮጵያ ሕዝብና በገለልተኛ አካላትም፤ተአማኒ የሆነ ምርጫ መሆኑ ቢገለፅም፤ በሕዝብ የተመረጠውን መንግስት ሕጋዊነት ጥያቄ ውስጥ ለማስገባትና ለመጣል፤ ከፍተኛ ዘመቻ በመደረግ ላይ ነው። ምርጫው በብዙዎች ዘንድ ተዓማኒ ነበር ማለት ግን፤ ምርጫው እንከን አልባ አልነበረም ማለት አይደለም። በአለማችን፤ በየትኛውም አገር ሙሉ ለሙሉ እንከን አልባ የሆነ ምርጫ የተካሄደበት ቦታ ለመኖሩ ምንም መረጃ የለም። በሕዝብ ድምጽ ለመገዛት ፈቃደኛ ያለሆኑ ኃይሎች፤ ምርጫውን ለማጣጣል ተግተው ቢሰሩም፤ ሕዝቡ በፈቀደውና በነፃነት ድምጽ በሰጠው የፖለቲካ ኃይል እየተዳደረ መሆኑን ውድቅ አያደርገውም።
በአብዛኛው ሃገራት እንደምናየውና ፤ ባለፈው የአሜሪካን ምርጫም ብዙዎችን ያስተማረው ነገር፤ ምርጫውን “አንቀበልም” የሚሉ የኅብረተሰብ አካላት፤ ተመራጩ መንግስት “ሕጋዊንት የተላበሰ” (legitimate) እንዳልሆነ የሚስሉት ሰዕልና፤ ሥርዓቱንም እንቀይራለን በሚል ምኞት የሚፈጥሩት ሁከትና፤ ነውጥ ሃገርን ወደ አለማረጋጋት፤ አልፎም ወደ ከፋ ግጭት የሚወስድ መሆኑን ነው። በተለይ የኢትዮጵያ የብሔር ፌደራል አወቃቀር ሥርዓት፤ “ትናንሽ የብሔር ነገስታትን” የፈጠረ በመሆኑ፤ ሃሳባቸውን ለሕዝብ አቅርበው፤ በብሔራዊ የፖለቲካ መድረክ ላይ የሕዝብን ልብ ማሸነፍ የማይችሉና የማሸነፍ አቅም መገንባት የማይችሉ ኃይሎች፤ ነውጥ በመፍጠር፤ በአቋራጭ ወደ ሥልጣን ለመምጣት የማይፈነቅሉት ድንጋይ የለም። በጥቂት ተከታዮቻቸው ጭብጨባ ሰክረው፤ ከእኔ በላይ “ለብሔሬ ተቆርቋሪ የለም” በሚል የትዕቢት መንፈስ ተወጥረው፤ ብሄር ተኮር ጥቃቶችን በመቀስቀስና፤ ብሔር ተኮር ጥቃቶችን፤ በማራገብ፤ በሃገር ላይ በውጥረት ላይ ውጥረት በመጨመር፤ መንግሥት መሥራት የሚገባውን ሥራ እንዳይሰራ ያደርጋሉ።
ከዚህም አልፈው፤ በተለይ በሙስናና ከዚህ በፊት በሰሩት ወንጀል እጃቸው በደም የተነከረ፤ አሁንም በሥልጣን ላይ ያሉ፤ የበላይና የበታች ሹማምንትን በመመልመል፤ የእኩይ ተግባራቸውና ዓላማቸው አካል በማድረግ፤ በንፁሃን ዜጎች ላይ ጭፍጨፋ እንዲካሄድ ሁኔታዎችን ያመቻቻሉ፤ ሥምሪት ይሰጣሉ፤ አጋጣሚ በፈጠረ ቁጥርም በቀጥታ ይሳተፋሉ።ታድያ እነዚህን ኃይሎች ይዘን እንደኤት ወደ ብሔራዊ ዕርቅ መሄድ እንችላለን? በጎ እሳቤ ከሌላቸውና እራሳቸውን ብቻ “በሥዩመ እግዚአብሔር የተቀባን መሪዎች ነን” ብለው ከሚያሰቡ የፖለቲካ ኃይሎች ጋር አብሮ መሥራት ይቻላል ወይ የሚሉና መሰል ጥያቄዎች መልስ ሊበጅላቸው ይገባል።
በተለይ ደግሞ “እኛ ለመግዛት ነው የተፈጠርነው” (We are destained to rule) የሚል እሳቤ ያላቸውና እራሳቸውን ከማንም በላይ አግዝፈው የሚያዩ፤ የአሰተሳሰብ ድዊዎች፤ በአቋራጭ ሥልጣን ለመያዝ በሚያደርጉት እኩይ ሥራ፤ ሕዝባችን ለዓመታት እጅግ ብዙ ዋጋ ከፍሏል።እነዚህ “በአዳራሽ ጭብጨባ” የሰከሩ እኩይ ኃይሎች፤ በሕይወታቸው አንድ የረባ ተቋም መርተው የማያውቁ፤አንዳንዶቹም፤ ሃገርን ለማስተዳደር በተሰጣቸው ኃላፊነት፤ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡና፤ የራሳቸውን የገዥነት ቅዠት ለማሳካት፤ ከጠላት ጋር በመተባበር፤ ኢትዮጵያን ከጀርባ ያስወጉ ሰዎች መሆናቸውም ሊስተዋል ይገባዋል።
ሕወሃት ለ27 ዓመታት ሕዝባችንን ረግጦ ሲገዛ፤ ይህ ነው የሚባል አስተዋጽኦ ያላበረከቱና፤ ሕወሃት የመውደቅ አፋፍ ላይ ሲደርስ፤ ትግሉን ጠልፈው፤ “እኛ ነን ትግሉን የመራነው” በሚል የሃሰት ትርከት፤ በኀዳሴው ለውጥ ግርግር ውስጥ ተሸለኩልከው፤ የሥልጣን ኮርቻ ላይ ለመቀመጥ ያልተሳካላቸው ሰዎች፤በምናባቸው ያዩት የነበረውን የቋመጡለትን የሥልጣን ወንበር በማጣታቸው፤ የኅዳሴው ለውጥ ከግብ እንዳይደርስ፤ በሚችሉት አቅም ሁሉ እየተንጠራሩ፤ ከሕዝባችን ታሪካዊ ጠላቶችም ጋር በተጋመደ ሰንስለት፤በሕዝባችን ላይ ከፍተኛ ሰቆቃ እየፈፀሙ በሚገኙበትና ዓላማቸውን ኢትዮጵያን ማፍረስ ወይም ማዳከም መሆኑን እያወቅን፤ ከእነዚህ ኃይሎች ጋር ምን ዓይነት ብሔራዊ ምክክር ማድረግ ይቻላል? እነዚህ ኃይሎች፤ እራሳቸው ነውጥ ፈጣሪዎች፤ እራሳቸው ጨፍጫፊና አስጨፍጫፊ ሆነው ሳለ፤ ከሳሾችም፤ የአዞ እንባቸውን እያነቡም አዛኞች ሲመስሉ ይታያሉ። ይህ ከጡት አባታቸው ከሕወሃት የተንኮል “መጽሔት” የወረሱት፤ “ገሎ አብሮ ንፍሮ የመቀቀል ባሕሪም” እረጅም መንገድ ያስጉዘናል ብለው ስለሚያስቡ፤ ዛሬም፤ በሕዝባችን ላይ እልቂት ለመፈፀም ትንኮሳዎችን፤ ሲያበረታቱ፤ ለትንኮሳም ሲያሴሩ፤ የሚጽፏቸው ጽሁፎችና በየማህበራዊ ሚድያ የሚለቁት “ተውሳክ” ያሳብቅባቸዋል።ለዚህም ነው ገና ከጅምሩ የብሄራዊ ምክክር አጀንዳውን ማጣጣልና ሕዝባችንን በመከፋፈል አገራችንን አደገ ላይ ለመጣል ተግተው የሚሰሩት።
የእነዚህ ኃይሎች ዋና ዓላማ፤በሃገር ውስጥ አለመረጋጋት መፍጠርና፤ በሚፈጠረው አለመረጋጋትም፤ በግርግር ሥልጣን የመያዝ ነው። ለዚህም ደግሞ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ እርዳታ የሚያገኙ በመሆናቸው፤ ገና ተቋማትን እንደ አዲስ በመገንባት ላይ ላለችው ኢትዮጵያ እጅግ ፈታኝና አደገኛም ሆኖ እየታየ ነው። የእነዚህ ኃይሎች በተለያዩ ብሔር ውስጥ ያሉ ጽንፈኞችን እና ገና ያልበሰሉ ወጣቶችን በምመልመል፤ እራሳቸውን የሕዝብ ድምጽ እና የሕዝብ መብት ተቆርቋሪ በማስመሰል ሕዝባዊ የሚመስሉ ግን እጅግ አደገኛ የሆኑ አጀንዳዎችን በማንሳት፤ በተለይም በአማራው እና በኦሮሞው ሕዝብ መካከል ግጭቶች እንዲነሱ ተግተው ይሰራሉ። አማራው የኦሮሞን መሬት እንደወረረ በማስመሰል፤ እንዲሁም አማራው ለሌሎች ብሔሮች መብት አለመከበር ምክንያት እንደሆነ አድርገው በሚረጩት መርዝ፤ ለዘመናት ዛሬ “ኦሮሞ ክልል” ተብሎ በተሰመረው መልክአ ምድር የኖረውን አማራ ሕይወት የምድር ገሃነም አድርገውታል።
በአማራው ሕዝብ ላይ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ ከፈፀሙና ካስፈፀሙ በኋላ፤ ቀጣዩ ሥራቸው፤ አዛኝ በመምሰል፤ ሕዝብ በመንግሥት ላይ እምነት እንዳይኖረውና፤ በመንግሥት ውስጥ ያሉም የሥራ ኃላፊዎች እርስ በእርስ በጥርጣሬ እንዲተያዩ ለማድረግ፤“አስጨፍጫፊው መንግሥት ነው፤ መንግሥት የዜጎችን ሕይወት ለመታደግ እየሰራ አይደለም፤ዐብይ ቢፈልግ ኖሮ ሽመልስን ከሥልጣን ማንሳት ይችል ነበር፤ሰው እየተገደለ ችግኝ ይተከላል” ወዘተ ወደ የሚሉ የሕዝብን ስሜት የሚኮረኩሩ በማር የተጠቀለለ መርዛቸውን ይወረውራሉ። በንፁሃን ዜጎች እልቂት ስሜቱ የተነካው ሃገር ወዳድ ዜጋ፤ እነዚህን ሃሳቦች በመግዛት፤ በሚያገኘው አጋጣሚ ሁሉ ያስተጋባል። የእነዚህ እሳቤዎች መለቀቅ፤ ሕዝቡን ስሜታዊ ለማድረግ እና፤ ቢቻል የበቀል እርምጃ እንዲወሰድ፤ ካልተቻለ ደግሞ መንግሥት ላይ ተጨማሪ ውጥረት በመፍጠር፤ በተለይም የፀጥታ መዋቅሩን የበለጠ ማላላት ነው።
የአቶ ሽመልስን ጉዳይ ካነሳሁ ዘንድ፤ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ እንደገለፅኩት፤ አቶ ሽመልስ፤ የኦሮምያን ክልል የመመራት አቅም እንደሌላቸው በተጨባጭ አሳይተዋል። ይህንን ገምግሞ ከሥልጣን ሊያነሳቸው የሚጭለው ጨፌ ኦሮምያ ነው።ዶ/ር ዐብይ አቶ ሽመልስን ከሥልጣን ማንሳት እንደሚችሉ ተደርጎ የሚነገረው ትርከት፤ ፍፁም የተሳሳተና፤ በየትኛውም የፌደራል ሥርዓት ሊተገበር የማይችል ነው። ዶ/ር ዐብይ አቶ ሽመልስን ከሥልጣን የማንሳት ምንም ዓይነት ሕጋዊ ሥልጣን የላቸውም። የየትኛውም የፌደራል አስተዳደር ያለው ሃገር፤ የክ/ሃገር (ክልል) መስተዳደር ወንጀል ሲሰራ እጅ ከፍንጅ ካልተያዘ በሰተቀር፤ ከሥልጣን ሊያነሳው አይችልም። በሕገ መንግሥቱ መሰረት፤ እያንዳንዱ ክልል እራሱን የቻል “ሏአላዊ ግዛት” ሆኖ ነው የፌደራል መንግሥቱ አካል የሆነው። በቅርቡ ኢኮኖሚስቱ ዶ/ር ዮናስ ብሩ፤ ከጋዜጠኛ ሃርሜላ አረጋዊ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስም፤ ዶ/ር ዐብይ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድራንን እንደቀያየሩ ተደርጎ የቀረበውም ፍፁም አሣሣች ነው። በአማራ ክልል፤ አቶ ገዱ አንዳርጋቸው በፈቃዳቸው ሥልጣን ሲለቁ፤ የተኳቸው ዶ/ር አምባቸው ደግሞ በአረመኔዎች ተቀጠፉ። እሳቸውን የተኩት አቶ ተመስገን ጥሩነህም ተሹመው ወደ ኢንሳ ተዘዋወሩ፤ ልክ አቶ ለማ መገርሳ፤ ወደ መከላከያ እንደተሾሙት ማለት ነው። አቶ ተመስገንን የተኩት አቶ አገኘሁ ተሻገር ደግሞ በአማራ ክልላዊ መስተዳድር ተሹመው ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት በመላካቸው ዶ/ር ይልቃል ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሆነው በክልሉ ምክር ቤት ተሹመዋል። ጭብጡ ይኽው ነው። ዶ/ር ዐብይ በምንም መልኩ የክልል ርዕሰ መስተዳደር የመሾምም የማንሳትም ምንም ሕጋዊ ሥልጣን እንደሌላቸው ሊሰመርበት ይገባል።
ወደ ጀመርኩት ሃሳብ እንድቀጥል ይፈቀድልኝ። የሃገራችንን የፀጥታ መዋቅር ለማላላትና፤ በንፁሃን ዜጎቻችን ላይ በሚፈፀም ጥቃት፤ መንግሥት ውስጥ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ ሰዎች የሉም ማለትና ከጠላት ጋር ተባባሪ የሆኑ የመንግሥት ባለሥልጣናት የሉም ማለት አይደለም። ሃገር ወዳድ ዜጎች በቅንነት፤ በመንግሥት በኩል ተጠያቂነት እንዲኖር የሚያነሷቸውና፤በሃገር ላይ ነውጥ ለመፍጠር ተግተው የሚሰሩ ኃይሎች የሚያነሷቸው ጥያቄዎች እጅግ ይለይያሉ። የሳትነውና ለእነዚህ አደገኛ ኃይሎች በር የከፈተው፤ብዙዎቻችን፤ አሁን ሃገራችን ያለችበትን የኅዳሴ ለውጥ በቅጡ አለመገንዘባችንና፤ ብዙ ነገሮችም በአስቸኳይ እንዲለወጡ ካለን ጉጉት ነው።ሌላው ቀርቶ እንደ ኢሰመጉ እና ኢሰመኮ ያሉ ተቋማት የሚሰጧቸው መግለጫዎችና የሚያወጧቸው ሪፖርቶች፤ ሃገራችን በጦርነት ውስጥ መሆኗን ከግንዛቤ ያላካተተ ነው። ጦርነት ስንል፤ ከሕወኃት ጋር ያለውን ጦርነት ብቻ አይደለም። ሕወሃት እና የውጪ ጠላቶቻችን በቅንጅት የከፈቱብን የውክልና ጦርነት ጭምር ማለት ነው። “መንግሥት ሕግ የማስከበር ኃላፊነቱን አልተወጣም” ስንል፤ ነገሮችን የምናይበት መነፅር እየተፈፀመ ያለውን ጭፍጨፋ፤ “መደበኛ ወንጀል” ያስመስለዋል። ይህ መደበኛ ወንጀል አይደለም፤ምንም እንኳን የዚህ ገፈት የመጀመሪያው ተጠቂ የአማራው ሕዝባችን ቢሆንም፤ ጥቃቱ ያነጣጠረው፤ በኦሮሞና በአማራ ሕዝብ መሃከል የእርስ በእርስ “ጦርነት” ለመፍጠር እና፤ እነዚህ አረመኔዎች ከቻሉ ሥልጣን ይዘው ረግጠው ሊገዙን፤ ካልተቻለ ግን፤ ኢትዮጵያን እንደሃገር እንዳትቀጥል፤ ግብ ተደርጎ የተሰላ የጭካኔ ቀመር መሆኑን ልብ ልንል ይገባል።
በሃገራችን ለዓመታት የቆየውን የፖለቲካ ችግር ለመፍታት በሚል እሳቤ፤ የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን ተቋቁሟል። ይህ ኮሚሽን ግን በሚያደርገው ብቸኛ ጥረት፤ እና በተወሰኑ ኃይሎች ተሳትፎ ብቻ፤ የምንፈልገውን ውጤት እናገኛለን ወይ የሚለው ለሁላችንም አሳሳቢ ጥያቄ ሊሆን ይገባዋል። በዚህ ፀሃፊ እምነት ከሞላ ጎድል፤ ሃገራችን በሶስት በሚከፈሉ የፖለቲካ ኃይሎች ተወጥራለች። አንደኛው ኃይል፤ ለሃገሩ ፍፁም ቀናኢ የሆነና፤ በመቻቻል ፖለቲካ ሃገራችንን ወደፊት ለማራመድ ጠንክሮ የሚሰራ ነው። ሁለተኛው ኃይል፤ምንም ዓይነት የተሻለ ሃሳብ ማመንጨት የማይችል፤ሙሾ እያወረድ፤እሱ ያልተቆጣጠራትና ያልመራት ኢትዮጵያ፤ ተረጋግታ እንዳትኖር የሚሻና ለዛም ባለችው አቅም እና አሉኝ በሚላቸው፤ ከሃገሪቱ ሕዝብ 2 እጅ የማይሞላ ድጋፍ የሚኩራራ፤ በአዳራሽ ጭብጨባ የሰከረና፤ እራሱን ከአቅሙ በላይ አግዝፎ የሚያይ ነው። እነዚህ ኃይሎች በተደጋጋሚ እንዳየነው፤ “የሽግግር መንግሥት በሚል ደዌ” የታመሙና፤ሃገር ውስጥ ምንም ዓይነት በጎ ነገር ቢሰራ፤ ወርቅን ፋንድያ ለማለት የማይቦዝኑ ናቸው። የሚገርመው፤ እነዚህ ኃይሎች አንድ ተቋም ለመምራት የማይችሉ፤ ሌላው ቀርቶ የመዋዕለ ኅፃናት የማስተዳደር እንኳን አቅም የሌላቸው ናቸው። ሦስተኛው ኃይል ደግሞ፤ ሃገር ለማፍረስ ተግቶ የሚሰራ ኃይል ሲሆን፤ ምንም ነገር ቢደረግለት የማይጠረቃ፤ በሕዝብ መካከል ግጭቶችን በመፍጠር፤ ኢትዮጵያን ለመከፋፈልና ለማዳከም ጠንክሮ የሚሰራ የፖለቲካ ኃይል ነው።
በሁለተኛ ረድፍ የተቀምመጠው የፖለቲካ ኃይል፤ ለሃገራዊ ምክክሩ እንቅፋት ለመሆን መሞከሩ የማይቀር መሆኑና በምክክሩ ላለመሳተፍ ከአሁኑ ሰበብ እየደረደረ ይገኛል።በሃገር ውስጥ ያሉት እነዚህ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ በተወሰነ ደረጃ “ውጋት” ቢሆኑም፤ ሃገር ወዳድ ኃይሎች፤ አመርቂ የፖለቲካ ሥራ ከሰሩና በአብዛኛው ሕዝብ ዝንድ የምክክር ኮምሽኑ ሥራ ተቀባይነት ካገኘ፤ የሚኖራቸው የፖለቲካ ሕይወት አጭር ነው። በተለይ እንደ ኦፌኮ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች፤ አሁንም የፖለቲካ አቅማቸው በሥስ ክር ላይ የተንጠለጠለ በመሆኑ፤ ለምክክር ኮምሽኑ እንቅፋት ለመሆን ከሰራ፤የኦፌኮን አወዳደቅ ያፋጥነዋል። በሁለተኛው ጎራ ውስጥ ያሉት በውጭ የሚገኙ የፖለቲካ ኃይሎች፤ በማህበራዊ ሚድያ፤ ከማጓራት እና የሚቻላቸውን ከማድረግ ውጭ፤ አንድ ስንዝር እንኳን መራመድ የሚችሉ አይሆኑም።
አደገኛውና በጥንቃቄ መታየት ያለበት ግን በሦተኛው ጎራ ያለው የፖለቲካ ኃይል ነው። ከላይ እንደተገለፀው፤ ይህ ኃይል፤ የፈሪ ዱላውን በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚያሳርፍ፤ ከውጭና ከውስጥ ጠላቶች የተደገፈ ከመሆኑም በላይ በተለይ ንፁሕ አማሮችን በመጨፍጨፍ፤ በኦሮሞና በአማራ ሕዝብ መካከል ግጭት ለመፍጠር ተግቶ የሚሰራ ነው። የዚህ ኃይል አረመኔያዊ ድርጊት የብዙዎችን ስሜት እየተፈታተነ ያለና በተወሰነ ደረጃም፤በመካከላችን መከፋፈሎችን ለመፍጠር መቻሉ እየታየ ነው። ይህንን አድገኛ አካሄድ የምናይበት ሁኔታና ለመፍትሔውም የሚሰሩ ሥራዎች፤ የሃገራችንን የወደፊት ዕጣ ፋንታ የሚወስን በመሆኑ፤ ይህን በጥንቃቄ ማየት ከሁላችንም ይጠበቃል። ይህ ኃይል፤ በምክክር ኮምሽኑ መሳተፍ ይችላል ወይ የሚለው ጥያቄ እራሱ ገና ከጅምሩ አወዛጋቢ ነው። አብዛኛው ሕዝብ፤ ይህ ኃይል ትጥቁን ፈቶ በሰላማዊ የፖለቲካ መድረኩ ለመሳተፍ ፈቃደኛ ካልሆነ በስተቀር የሃገራዊ ምክክር ውስጥ መካተት የለበትም የሚል ሲሆን፤ የውጭ ኃይላትና፤ አንዳንድ ሃገር ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ድርጅቶች ግን፤ ካለእነዚህ ኃይሎች ተሳትፎ’ የሃገራዊ ምክክር መደረጉ ፋይዳ የለውም የሚል አቋም አላቸው።
ይህ ፀሐፍ፤ የዚህ አደገኛ ኃይል በምክክር ኮምሽኑ ውስጥ መሳተፍም አለመሳተፍም፤ ለምክክር ኮምሽኑ እንቅፋት ከመሆን ውጭ ጥቅም የለውም ብሎ ያምናል። ይህ ኃይል የመጨረሻ ግቡ አንድና አንድ ብቻ ነው። ይህም ኢትዮጵያን ማፍረስ፤ አልያም ደካማ ኢትዮጵያን እንደ ሃገር ማስቀጠል ነው። ምንም ቀናዒ የሆነ ፍላጎት የሌለው በመሆኑ፤ ይህን ኃይል ለኢትዮጵያ አደጋ የማይሆንበትን አቅም ማሳጣት ቀዳሚ አጀንዳ ሆኖ፤ በጥናትና በትኩረት ሊሰራበት ይገባል። በተለይ ሕወኃት፤ በዳኡድ ኢብሳ የሚመራው ኦነግና፤ ኦነግ ሸኔ እየተባለ የሚጠራው የአስተሳሰብ ድኩማን ጥርቅም በዚህ ጎራ የሚመደቡ ናቸው። ምንም እንኳን የእነዚህን ኃይሎች ደጋፊዎችና አባላት በተወሰነ ደረጃ አስተሳሰባቸውን መለወጥ ቢቻልም፤ አብዛኞቹ ግን በጥላቻ የታወሩ፤ ያልበሰሉና ጽንፈኛ የሆነ አቋም ያላቸው በመሆናቸው፤ በተቀናጀና ጥንቃቄ በተሞላበት ሕግ የማስከበር ሥራ ማዳከምና ማምከን ብቸኛው አማራጭ ነው ብሎም ይህ ፀሃፍ ያምናል።
በዚህ ፀሐፊ እምነት፤ በሁለተኛው ጎራ የተካተተው የፖለካ ኃይል፤ ፖለቲካው ወደ አጋደለበት፤ ዘምበል የማለት ባሕሪ ስላለው እንደ ጊዜው የፖለቲካ ነፋስ፤ ምን አልባት፤ በብሔራዊ ምክክሩ እሳተፋለሁ ሊል ይችላል። ግን አዎንታዊ የሆነ አስተዋጽኦ የማበርከቱና፤ በኋላም ለአብዛኛው ሕዝብ ድምጽ ተገዥ መሆኑ አጠያያቂ ነው። ብሔራዊ የምክክር ኮምሽኑ፤ በሚችለው አቅም ሁሉ፤ ሁሉንም የፖለቲካ ኃይሎች “እያስታመመ” ወደ የምንፈልገው የብሔራዊ ዕርቅ ሊመራን ይችላል ተብሎ ቢታመንም፤ ሁሉም የሃገራችን የፖለቲካ ችግር አካል የሆኑ ኃይሎች፤እራሳቸውን ከትዕቢት አፅድተው በቀናነትና ለሃገር ቅድሚያ በመስጠት፤ ለብሔራዊ ዕርቅ አዎንታዊ አስተዋጽኦ ያደርጋሉ ብሎ መጠበቅ የለውን እውነታ ያለመገንዘብ ስለሚሆን፤ የችግሩ አካል የሆኑ ሁሉ የመፍትሔው አካል ይሆናሉ ብሎ መጠበቅ ብዙ ዋጋ ሊያስከፍል ይችላል። በጽኑ መገንዘብ ያለብን፤ ሁሉንም ማስደስት እንደማይቻል ነው። ስለዚህ የብሔራዊ ምክክር ኮምሽኑ ከአሁኑ ይዘጋጅበት እላለሁ። አውቆ የተኛን፤ በተፈለገው መልኩ ቢቀሰቀስ፤ አይሰማምና፤ ይህንን ከግምት ውስጥ ማስገባት፤ ከብሔራዊ ምክክር ኮምሽኑ ይጠበቃል።
ቸሩ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይጠብቅ።
__
በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
I second it.
This writer is Always biased against Ethiopians who try to seek justice for innocent Ethiopians murdered in broad daylight. Gaslighting is a tactic used to silence and shame people who are trying to be voice for the voiceless. This tactic is used to silence dissent. He is telling us not to say anything about the pitfalls of the current govt . Scare tactic of state collapse to silence people. We will continue to speak truth to power and one day justice will be served. One fact, prime minister Abiy had removed the former Somali kilil president. The current president of Oromia has done far worse things. Teregna!!! It’s scholars like this writer who alienate people and make things work for the better.
Correction on the comment I wrote in response to above article.
I want the last sentence to read ‘against the betterment of Ethiopia’
Thanks!