
ጀማል ሰይድ
ቦርከና
በመጪው መስከረም ራስ ገዝ የሚሆነውን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲን ሳይጨምር በቀጣዮቹ ሁለት ዓመታትም 10 ዩኒቨርሲቲዎችን ራስ ገዝ ለማድረግ መንግሥት አቅጣጫ ማስቀመጡን የትምህርት ሚኒስቴር ገልጿል።
መንግስት ያስቀመጠውን አቅጣጫ በተመለከተ መግለጫ የሰጡት የከፍተኛ ትምህርት ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ሳሙኤል ክፍሌ (ፒኤችዲ) ናቸው።
ሚኒስትር ዲኤታው ትግበራው ለትምህርት ጥራት፣ በተቋማቱ መካከል የትብብር እና የፉክክር መንፈስ በማምጣት ልሕቀትን ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ጠቁመው በዚህ ምክንያትም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲን ዕውን ለማድረግ እንደሚረዳ ገልፀዋል።
ዩኒቨርሲቲዎች ራስ ገዝ ሲሆኑ ተወዳድረው ከውጭም ሀብት ያገኛሉ፤ ከአገር ውስጥ ከንግዱም ማኅበረሰብ በምርምርና በማማከር ገቢ ያስገባሉ፤ ብቁ ተማሪ ስለሚያወጡ ከመንግሥትም ተጨማሪ በጀት ያገኛሉ ነው ያሉት ሚኒስትር ዲኤታው።
ውድድሩ ልህቀት እንደሚያመጣ እና በአገር ውስጥ ሳይገደብ በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ የሆነ ተቋም መፍጠር እንደሚያስችልም ተመላክቷል።
ለመምህራኖቹ የተሻለ የደመወዝ ክፍያ እና ጥቅማ ጥቅም አሟልተው እንዲቀጥሩ የሚያስላቸው ይሆናል፤ ለሚቀጥሯቸው መምህራንም እንደ አቅማቸው የሚከፍሉበት ዕድል ይሰጣቸዋል ብለዋል ዶ/ር ሳሙኤል ደስታ።
ሚኒስትር ዲኤታው “በዓለም አቀፍ ተወዳዳሪ የሆነ ተቋም መፍጠር ያስፈልጋል፤ ዩኒቨርሲቲን በሰፈር አጥረነው መቀጠል የለብንም፤ ዩኒቨርሲቲ ዓለም አቀፍ በመሆኑም ራስ ገዝነት በጣም ወሳኝ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena