
ጀማል ሰይድ
ቦርከና
“የራያ የማንነት እና የወሰን ጉዳይ የመላው አማራ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳይ ነው” ሲሉ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጅ ሚኒስቴር ሚኒስትሩ አቶ በለጠ ሞላ ተናገሩ።
የወሎ ራያ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ በራያ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ በደሴ ከተማ የምክክር መድረክ እያካሄደ ይገኛል። በምክክር መድረኩ ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች፣ የሃይማኖት አባቶች፣ ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ የራያ ተወላጆች እና የምሥራቅ አማራ ፋኖ አባላት ተገኝተዋል። በምክክር መድረኩ ላይ የደሴ ከተማ ነዋሪዎችም ታዳሚ እንዲሆኑ ለቀናት በከተማዋ ቅስቀሳ ሲደረግ ቆይቷል።
የውይይቱ ዓላማ የራያ የማንነት እና የወሰን ጉዳይ የመላው አማራ እና የኢትዮጵያ ሕዝብ ጉዳይ መሆኑን ማስገንዘብ መሆኑ ተጠቁሟል።
የራያ ሕዝብ ለበርካታ ዓመታት በማንነቱ ጫና ሲደርስበት መቆየቱና አሁንም በከፋ ችግር ውስጥ መሆኑ በምክክሩ ተነስቷል።
የራያ ሕዝብን አንድነት በማጠናከር የሕዝቡን ነጻነት ለመመለስ የወሎ ራያ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ እየሠራ መሆኑን የተናገሩት የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጅ ሚኒስትር እና የአብን ሊቀመንበር ዶክተር በለጠ ሞላ ኮሚቴውን በማገዝ የራያ ሕዝብ ነፃነቱን እንዲያገኝ በአንድነት መሥራት አለብን ብለዋል።
በውይይት መድረኩ ላይ የወሎ ራያ አማራ ማንነትና ወሰን አስመላሽ ኮሚቴ ባለፈው አንድ ዓመት ባከናወናቸው ተግባራት እና የወደፊት የትግል አቅጣጫዎች ላይ እየመከረ ነው።
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena