
ጀማል ሰይድ
ቦርከና
መንግስት አሸባሪ ሲል የሰዬመው ሸኔ የደቡብ ዞን ምክትል ሀላፊ የሚል ሀላፊነት የተሰጠው ተጠርጣሪ በቤት መኪና ወደ መሀል አገር ሲጓዝ በቦረና ዞን ሞያሌ ወረዳ መያዙን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ ገልጿል፡፡
የመምሪያው ኮሚኒኬሽን ረዳት ዲቪዥን ሀላፊ ኢንስፔክተር ግርማ ሹሚ ተጠርጣሪው መኪና ተኮናትሮ ወደመሀል አገር ለመግባት ተዘጋጅቶ መኪናውን በመጠባበቅ ላይ እንዳለ በሞያሌ ወረዳ ልዩ ስሙ ቦቆላ በተባለ ስፍራ መያዙን ተናግረዋል።
ተጠርጣሪው ከአዳማ ከተማ በተላከለት የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 3 B-37253 አአ በሆነ መኪና በመጓዝ ላይ እንዳለ በፖሊስ በተደረገ ድንገተኛ ፍተሻ ሐምሌ 30 ቀን 2014 ዓ.ም ከቀኑ 8 ሰአት አከባቢ ተይዟል ብለዋል፡፡
በቁጥጥር ስር የዋለው ተጠርጣሪ ቀድሞ የሚታወቅበትን ‘መሀመድ አሜ’ የሚለውን የመጠሪያ ስሙን አብዱ ኡመር ሁሴን በሚል ቀይሮ መታወቂያ በማሰራት ሲንቀሳቀስ እንደነበር ጠቁመዋል፡፡ ግለሰቡ “ከአሸባሪው የሸኔ ቡድን” ጋር ብቻ ሳይሆን አልሻባብን ከመሳሰሉ ከአለም አቀፍ አሸባሪዎች ጋር ግንኙነት እንዳለው የሚጠረጠር እንደሆነም ጠቁመዋል፡፡
የቦረና ዞን ፖሊስ ተጠርጣሪውን ጭኖ የነበረውን መኪና ከነአሽከርካሪው በቁጥጥር ስር አውሎ ጉዳዩን በመከታተል ላይ እንደሆነ ተገልጿል።
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena