መንግሥት በፀጥታ ሥጋት ምክኒያት የሚደረግ ፍተሻ ነው ብሏል

ጀማል ሰይድ
ቦርከና
ከሰሜንና ደቡብ ወሎ እንዲሁም ከዋግ ኽምራ ዞኖች ወደ አዲስ አበባ የሚጓዙ ተሳፋሪዎች ኦሮምያ ክልል ከተሞች ሲደርሱ “የአዲስ አበባ መታወቂያ አልያዛችሁም” በሚል ምክንያት ወደ መጡበት እንዲመለሱ መደረጋቸውን ለአሜሪካ ድምፅ ገለፁ፡፡
ተሳፋሪዎቹ “የምንኖርበት እየታወቀ የማንኖርበትን ከተማ መታወቂያ እንድናመጣ መጠየቁ አግባብነት የለውም” ይላሉ፡፡ የአማራ ክልል መንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ የተፈጠረው መጉላላት ከፀጥታ ጉዳይ ጋር የተያያዘ ቢሆንም አፈጻጸሙ ብዙሃኑን ተሳፋሪ ለእንግልትና ለአላስፈላጊ ወጭ የዳረገ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡
ከኦሮምያ ክልል እስካሁን በጉዳዩ ላይ የተሰጠ ማብራሪያ የለም፡፡ በጉዳዩ ላይ ምላሽ የሠጡት የመንግሥት ኮምዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዲኤታ ሠላማዊት ካሣ ሁኔታው ከጥብቅ የፀጥታ ቁጥጥር ጋር የተያያዘ መሆኑን ተናግረዋል። መታወቂያ ለመሥራት የሚያስፈልጉትን ጨምሮ የተለያዩ ሰነዶች በህወሓት ተይዘው ከነበሩ የአማራ ክልል አካባቢዎች መወሰዳቸው ደግሞ ለጥብቅ ቁጥጥሩ መነሻ መሆኑን ጠቅሰዋል።
አፈጻጸሙን በተመለከተ ግን ማሻሻያዎች መደረግ እንዳለባቸውና የደህንነት እና የፀጥታ መዋቅሩን ማጥራት እንደሚያስፈልግም ዛሬ የወጣውን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የደህንነት ምክር ቤት መግለጫ በመጥቀስ አብራርተዋል።
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena