spot_img
Sunday, May 19, 2024
Homeአበይት ዜና"የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ባለፉት አራት ዓመታት በሁሉም መስክ ዕድገት አሳይተዋል" የኢትዮጵያ...

“የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ባለፉት አራት ዓመታት በሁሉም መስክ ዕድገት አሳይተዋል” የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ

ዶ/ር ይናገር ደሴ የብሔራዊ ባንክ ገዢ (ፎቶው የተወሰደው ከኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ነው)

ጀማል ሰይድ
ቦርከና

የኢትዮጵያ ንግድ ባንኮች ባለፉት አራት ዓመታት በሁሉም መስክ የተሻለ እድገት ያሳየበትና በፋይናንስ አፈፃፀማቸውም ጤናማነት የተስተዋለበት መሆኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገለጸ።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ፤ ከባንክ ተወካዮች ጋር በ2014 በጀት ዓመት የዘርፉ አፈፃፀም ዙሪያ ውይይት አድርጓል። ኢትዮጵያ ባለፉት አራት ዓመታት መልከ ብዙ ውስጣዊና ውጫዊ ፈተናዎች ቢኖሩም በተለይም በፋይናንስ ዘርፍ ዕድገት ማስመዝገቧ በመድረኩ ተገልጿል።

መንግስት በፋይናንስ ዘርፍ ባደረገው ሪፎረምና የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያ እርምጃዎች በመውሰዱ በፋይናንስ ሴክተሩ ለውጥ እንደተመዘገበ ተገልጿል። 

ለአብነትም የወለድ አልባ ባንኮች መቋቋም፣ የተንቀሳቃሽ ንብረት የብድር አገልግሎት መፈቀድ፣ የውጭ ዜግነት ያላችው ኢትዮጵያዊያን በባንኩ ዘርፍ እንዲሰማሩ መፈቀዱ፣ የካፒታል ገበያ መፈቀዱና የማይክሮ ፋይናንስ ተቋማት ወደ ባንክ እንዲያድጉ መደረጉ ተጠቅሷል። በዚህም የባንኮች ቁጥር በ67 በመቶ፣ የባንኮች ቅርንጫፎች ብዛት በ61 በመቶ፣ ጠቅላላ ሀብታቸው በየዓመቱ በአማካይ 24 በመቶ፣ ተቀማጭ ገንዘብ 93 በመቶ፣ የብድር አቅርቦታቸው 73 በመቶ፣ ጠቅላላ ካፒታላቸው ደግሞ 101 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ተብሏል።

በመንግስትና በግል ባንኮች የገበያ ድርሻ ረገድም የተቀራረበ እንደሆነ በባንክ እድገት ጤናማነት ሲመዘንም ጥሩ ደረጃ ላይ ይገኛል ነው የተባለው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶክተር ይናገር ደሴ፤ በተቀማጭ ገንዘብና በብድር አመላለስ በሁሉም መስኮች ከፍተኛ ዕድገት በመምጣቱ ባንኮች ውጤታማ አፈፃፀም አሳይተዋል ብለዋል።

በተለይም በዲጂታል ባንኪንግ ከፍተኛ ዝውውር መታየቱን በተለይም የቴሌብር ወደ ገበያ መቀላቀል ለዲጅታል ባንኪንግ መነሳሳት ጥሩ ጅምር መሆኑን ገልጸዋል። የኤሌክትሮኒክ ግብይት አፈፃፀምም በ2025 ዲጂታል ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ የተያዘውን ግብ ለማሳካት ጉልህ ሚና ይኖረዋል ነው ያሉት።

ባለፉት አራት ዓመታት የኢትዮጵያ ባንኮች በበርካታ ተገዳሮቶች ውስጥ ሆነው እንኳን ከመደበኛ የባንክ አገልግሎቶቻቸው ባሻገር ማህበራዊ ኅላፊነታቸውን በሚገባ እንደተወጡም ገልጸዋል።

ለአብነትም በገበታ ለሀገር ፕሮጀክት ከተሰበሰበው ውስጥ ግማሹ ከባንኮች የተሰበሰበ እንደሆነ አንስተዋል።

ምንም እንኳን ባለፉት ዓመታት ባንኮች ያሳዩት ዕድገት በጥሩ ደረጃ ላይ ቢሆንም ይበልጥ መሰራት ያላባችውና የወደፊት ስጋቶችን ታሳቢ ያደረገ እንቅስቃሴ ማድረግ እንዳለባቸውም አመላክተዋል።

ከብድር አቅርቦት አንፃር ባንኮች ብድር ከትልልቅ ባለሀብቶችና ከተማ አካባቢ ከመታጠር ተሻግሮ በገጠር ማህበረሰቡንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እና ታችኛውን ማህበረሰብን መድረስ እንዳለባቸው ገልጸዋል።

በፋይናንስ ተደራሽነት በተመለከተም ባንኮች ከቅርንጫፍ ከፈታ ባሻገር በሞባይል ባንኪንግና በሌሎች ዲጂታል የባንክ አገልግሎቶች በማስፋት በገጠር ያለውን ማህበረሰብ ተጠቃሚ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

በሌላ በኩል ሕገ ወጥነት እና ማጭበርበር ድርጊቶች በመግታት እና ከባንኮች ውጭ በንግዱ ውስጥ ያለውን ገንዘብ በማሰባሰብ ባንኮች የአሰራር ስርዓት መዘርጋትና ከህግ አካላት ጋር በትብብር መስራት ይጠበቅባቸዋል ነው ያሉት።

 ወደፊት የውጭ ባንኮች ወደ አገር ቤት ከገቡም አገር በቀል ባንኮች ሰፊ ውድድር ስለሚጠብቃቸው ከወዲሁ ስትራቴጂ ቀይሰው ሊሰሩ እንደሚገባ ተናግረዋል።

አስተያየታቸውን የሰጡት የባንክ ስራ አስፈጻሚዎች ባለፉት አራት ዓመታት የመጣው አወንታዊ ውጤት ባንኮች በዲጂታል ባንኪንግ እየዘመኑና አቅማቸውን እያጎለበተ ተደራሽነታቸውንም እያሰፉ በመምጣታቸው መሆኑን ገልጸዋል።

በብሔራዊ ባንክ የወጡ የሕግ ማዕቀፍ ማሻሻያዎችና ከባንኮች ጋር የተናበበ የቁጥጥር ስራ ለፋይናንስ ዘርፉ ዕድገት አወንታዊ ሚና ነበራቸው ብለዋል። 

የውስጥ ደህንነትን ቁጥጥር ማሳደግ፣ በቴክኖሎጂ ማሻሻል፣ በገጠር ተደራሽነትና በብድር አቅርቦት  እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የባንክ ብድር እስከታችኛው ህበረተሰብ ተዳራሽነት ለማስፋትም ቴክኖሎጂን መጠቀም፣ ብሔራዊ መታወቂያ እንዲሁም አስተማማኝ ማንነት ሰነዶች ጉዳይ ሊታሰብብት እንደሚገባ ገልጸዋል። 

በባንኮች የሚስተዋለውን የደንበኞች መታለልና ህገ ወጥ ድርጊት በተመለከተ ባንኮች ሪፖርት የሚያደርጉት መሰረት የፍትህ ተቋማት ጠንካራ ህጋዊ እርምጃ ሊወስዱ ይገባል ብለዋል።

__

በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር
 ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here