
ጀማል ሰይድ
ቦርከና
በደቡብ ወሎ ዞን በአሸባሪው የትህነግ ቡድን ወረራ ዉድመት የደረሰባቸውን ቤቶች መልሶ መገንባት ተጀምሯል።ለግንባታው ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ እንደሚደረግ ተገልጿል፡፡ በዞኑ በሚገኙ 11 ወረዳዎች ውስጥ ዉድመት የደረሰባቸውን ቤቶች መልሶ ለመገንባት ታቅዶ ወደ ሥራ ተገብቷል፡፡
ዛሬ በተሁለደሬ ወረዳ 07 ቀበሌ 12 ለሚኾኑ አባወራዎች የግንባታ ቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ የመልሶ ግንባታ ሥራዉ ተጀምሯል፡፡
በቦታዉ ተገኝተዉ ጉዳት የደረሰባቸውን አርሶ አደሮችን የጎበኙት የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አብዱ ሁሴን፤ ለመልሶ ግንባታዉ ሥራ ከ40 ሚሊዮን ብር በላይ ወጭ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
አቶ አብዱ ግለሰቦቹ የደረሰባቸዉን ጉዳት ለመካስ እና የጠላትን አንገት ለማስደፋት ድጋፉ መደረጉን አስረድተዋል፡፡ የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ተጠሪ ጽሕፈት ቤት ኅላፊ ኢብራሂም ይመር፤ በዞኑ ባሉ 11 ወረዳዎች 2ሺህ 600 ቤቶችን መልሶ ለመገንባት መለየታቸዉን ተናግረዋል፡፡ ዛሬ የ12 አርሶ አደሮችን ቤት መልሶ ለመገንባት የተደረገው የግንባታ ቁሳቁስ ድጋፍ ቀጥሎ በቀሪ የክረምቱ ወቅትም ሁሉም ተደራሽ ይኾናሉ ነው ያሉት፡፡
ቤታቸዉ የወደመባቸው እና ድጋፍ የተደረገላቸዉ አርሶ አደሮችም ለተደረገላቸዉ ወገናዊ ትብብርና ድጋፍ አመስግነው ‟ከተደረገው ድጋፍ በላይ ያለንበትን ለማየት መምጣታችሁ አስደስቶናል” ብለዋል፡፡
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena