spot_img
Sunday, May 26, 2024
Homeአበይት ዜናበጉራጌ ከተሞች የሥራ ማቆም አድማ ተደረገ

በጉራጌ ከተሞች የሥራ ማቆም አድማ ተደረገ

 ጉራጌ ከተሞች

ጀማል ሰይድ
ቦርከና

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ውስጥ የተካተተው የጉራጌ ሕዝብ እራሱን በቻለ ክልል እንዲዋቀር ጥያቄ ሲቀርብ ቆይቷል። ይህን ጥያቄ በተለይ ከአራት ዓመት በፊት የዞኑ ምክር ቤት ጭምር ለፌደራል መንግሥቱ ማቅረቡ ይታወሳል።

ነገር ግን ይህ በክልል የመደራጀት ጥያቄ ዓመታትን ያስቆጠረ ቢሆንም እስካሁን ድረስ ለጥያቄው ምላሽ ማግኘት እንዳልቻሉ የዞኑ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የጉራጌ ዞን በክልል የመደራጀት ጥያቄን ተከትሎ ማክሰኞ ዕለት በዞኑ መዲና ወልቂጤ እና በሐዋርያት ከተማ የሥራ ማቆም አድማ ተደርጓል።

ይህን ነሐሴ 03/2014 ዓ.ም. የተካሄደውን የሥራ ማቆም አድማ ማን እንደጠራው በትክክል ባይታወቅም ሰኞ ነሐሴ 02/2014 ወረቀት ከተበተነ በኋላ ወልቂጤ ከተማ ከሥራ እንቅስቃሴ ውጪ ሆና መዋሏን ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በጉራጌ ጉዳዮች ላይ በማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ሐሳቦችን የሚያቀርበው አቶ ተስፋ ነዳም የሁለቱ ከተሞች ነዋሪዎች ከቤቱ መዋላቸውን “ከዳቦ ቤት እና ከሕክምና ተቋማት ውጪ ሙሉ በሙሉ የንግድ እንቅስቃሴ ቆሞ ውሏል” ሲሉ ተደምጠዋል፡፡

እንደ አቶ ተስፋ ከሆነ በዞኑ ባሉ አንዳንድ አካባቢዎች የመንግሥት አስተዳዳሪዎች ነዋሪዎችን ለውይይት ቢጠሩም ነዋሪዎች ለመሰብሰብ ፍቃደኛ ሳይሆኑ በመቅረታቸው የታቀዱት ስብሰባዎች ሳይካሄዱ ቀርተዋል ብለዋል። የሥራ ማቆም አድማ የተደረገው የጉራጌ ዞን ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር በመሆን በክላስተር መደራጀት ሳይሆን በክልልነት እንዲዋቀወር የቀረበው ጥያቄ ምላሽ እንዲያገኝ ጫና ለማሳደር መሆኑን አቶ ተስፋ ያስረዳሉ።

ጨምረውም ከሦስት ዓመታት በፊት የጉራጌ ዞን ምክር ቤት በክልል የመደራጀት ጥያቄውን ለክልሉ በይፋ አቅርቦ እንደነበረ በማስታወስ፣ የዞኑ አስተዳደርም በአሁን የቀረበውን የአወቃቀር አማራጭን አይቀበልም ሲሉ ይናገራሉ።

የጉራጌ ሕዝብ እራሱን በክልልነት የማደረጀት ሙሉ ሕገ-መንግሥታዊ መብት እንዳለው የሚናገሩት አቶ ተስፋ፤ “መንግሥትም ቢሆን በዚህ አደረጃጀት ተደራጁ ወይም የምፈቅደው ይህ ነው የማለት መብት የለውም” ሲሉ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

‘የክልልነት ጥያቄ የቀረበው ከዓመታት በፊት ነው’

የጉራጌ ዞን ራሱን ችሎ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ማቅረብ ከጀመረ ዓመታት መቆጠራቸውን የሚናገሩት ደግሞ የጉራጌ ባህላዊ ሸንጎ መሥራችና ሰብሳቢ ወ/ሮ ዛይዳ ግዛው ናቸው። “ለውጡ ከመምጣቱ በፊት ህወሓት አገር ሲመራ ከሌሎች ጋር በክልል አልዋቀርም ብሎ ለመጀመሪያ ጊዜ ተቃውሞ ያሰማው የጉራጌ ማኅብረሰብ ነው” በማለት ይናራሉ።

ለዘመናት የዘለቀው ጥያቄ ፍትሐዊ በሆነ መንገድ ምላሽ አላገኘም የሚሉት ወ/ሮ ዛይዳ፤ “ሕዝቡ ቁጭት ውስጥ ገብቷል። የፖለቲካ አሻጥርም በዝቶበታል” በማለት ወ/ሮ ዛይዳ ያስረዳሉ።

የክላስተር አወቃቀር ተቃውሞ ለምን ገጠመው?

ጉራጌ አሁን ተደራጅቶ የሚገኝበት ሁኔታ “የራሱን ቋንቋ፣ ማንነቱን፣ ባህሉን ማሳደግ እናመጠበቅ አልቻለም። የጉራጊኛ ቋንቋ ሊጠፋ ከጫፍ ድርሷል። ቋንቋው ለመማሪያነት አልበቃም እነዚህ ሁሉ መስተካከል ስላለባቸው ነው የክልል ጥያቄ የተነሳው” ይላሉ አቶ ተስፋ። ጉራጌ በክላስተር የሚደራጅ ከሆነ ሕዝቡ ከሁለት በላይ ወደ ሆኑ ዞኖች ተከፋፍሎ ስለሚገባ የጉራጌ ማንነትን ሊያሳጣ ይችላል በማለት ስጋታቸውንም ጨምረው ይናገራሉ።

ወ/ሮ ዛይዳ በበኩላቸው፤ ክላስተሩ የሕገ-መንግሥት መሠረት የሌለው እና ሕብረተሰቡ ሳይቀበለው በግድ የሚጫንበት ሃሳብ በመሆኑ አንቀበለውም ይላሉ።

“የጉራጌ ማኅብረሰብን ቋንቋ፣ ባህል የሚያጠፋ ነው። እስከ ዛሬ ድረስ በቋንቋው ማስተማር እና አካባቢውን ማልማት ያልቻለ፣ የፖለቲከኖች አሻጥር አድክሞት የኖረ ማኅብረሰብ ከአሁን በኋላ በክላስተር ይደራጅ ቢባል በፍጹም ሊያንሰራራ የማይችልበት ደረጃ ላይ ይገባል” ሲሉ ወ/ሮ ዛይዳም ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

“በትግል የማይለወጥ ነገር የለም” የሚሉት ደግሞ አቶ ተስፋ፤ “የተቀረውን ሕዝብ የሚጎዳ ነገር ሳይኖር አሁንም ቢሆን ሕጋዊ መስመሩን በመከተል የዞኑ ምክር ቤት ጥያቄ እንዲከበረ ጥረታችንን እንቀጥላለን” ሲሉ አቶ ተስፋ ሃሳባቸውን ሰጥተዋል።

__

በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር
 ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here