
ጀማል ሰይድ
ቦርከና
ነሃሴ 5, 2014 ዓ. ም.
የባልደራስ ሊቀመንበር አቶ እስክንድር ነጋ ለፓርቲያቸው ፃፉት በተባለውና ዛሬ በማህበራዊ ሚዲያ ሲዘዋወር በቆዬው ደብዳቤ “መስራት የማልችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ።” ሲሉ ገልፀዋል።
ለፓርቲያቸው የፃፉት ደብዳቤ እንደሚከተለው ቀርቧል።
“ለባልደራስ ለእውነተኛ ዴሞክራሲ የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ
—
ኢትዮጵያ ወደ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት እንድትሻገር ለዓመታት የበኩሌን አስተዋጽዖ ሳደርግ መቆየቴ ይታወሳል። በአሁኑ ጊዜ ግን፣ ተረኛው ጨቋኝ መንግስት በባልደራስም ሆነ በሃገር አቀፍ ደረጃ በፈጠረው የለየለት አምባገነናዊ ጫና ሳቢያ፣ በአባልነትም ሆነ በአመራርነት መስራት የማልችልበት ደረጃ ላይ ደርሻለሁ።
በመሆኑም የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ፣ አባላት፣ በየደረጃው ያሉ የፓርቲው አመራር አባላት፣ መላ አባላትና ደጋፊዎች፣ እንዲሁም መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ከፓርቲው ምክትል ፕሬዝደንት አቶ አምሃ ዳኘው ጋር ሙሉ ለሙሉ በመተባበር ስራቸው የተቃና እንዲሆን እንድትተባበሯቸው በትህትና እጠይቃለሁ።
በመጨረሻም፣ እቅድ የተያዘለት የባልደራስ ጠቅላላ ጉባኤ በተሳካ ዝግጅት እንዲከናወን ያለኝን ብርቱ ተስፋ እየገለጽኩ፣ ባልደራስ በሃገር አቀፍ ፓርቲነት አድጎ የማየት ተስፋችን ወደ ተግባር ተተርጉሞ ለማየት የፈጣሪ መልካም ፈቃድ ይሁን።”
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena