spot_img
Monday, May 29, 2023
Homeነፃ አስተያየትየኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት መቀየር አስፈላጊነት (ታዬ ብርሃኑ ዶ/ር )

የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት መቀየር አስፈላጊነት (ታዬ ብርሃኑ ዶ/ር )

- Advertisement -
Ethiopian politics _ constitution

ታዬ ብርሃኑ ዶ/ር 

በኢሕአዴግ መንግሥት በአዋጅ ቁጥር 1/1987 ነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም የጸናው የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት አጠያያቂነት እና ተቃውሞ የተነሳው ገና ከጥንስሱ ጀምሮ ነው፡፡ በርካቶች የሕገ መንግሥቱን የመለወጥ አስፈላጊነት ሲደግፉ በአንጻሩ ሕገ መንግሥቱ ካስፈለገ አንዳንድ ማሻሻሎች እንጂ መለወጥ የለበትም የሚሉ አሉ፡፡ የሁለቱ ወገኖች አሰላለፍ እንደተጠበቀ ሆኖ የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ ሕገ መንግሥቱ እንዲቀየር የሚያስፈልግበትን ምክንያቶች በመረጃዎችና በአምክናዊነት ለማቅረብ ነው፡፡ 

በመሠረታዊነት ዛሬ አገራችን ላለችበት አስከፊ߹ አሳዝኝ እና ውስብስብ ሁኔታ እና የድቅድቅ ቀቢሰ ተስፋ ግርዶሽ መንስዔ በዋነኝነት የአገራችን የፖለቲካ߹ የኢኮኖሚና የማሕበራዊ ሥርዓት መሠረት የሆነው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ነው፡፡ በሌላ በኩል በረጅሙ ጉዞው በ2008ዓ.ም ተጠናክሮና ገንፍሎ የመጣው የሕዝብ ብሶትና ቁጣ በ2010 ዓ.ም ይፋ ለሆነው የለውጥ ተስፋ ፈርጥ መሠረት የሆነው የሕገ መንግሥቱን መቀየር አስፈላጊነት በማመን ነበር፡፡

በዚች አጭር ጽሑፍ የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ይቀየር ሲባል ምን ማለት እንደሆነ እና የሕገ መንግሥቱ መቀየር አስፈላጊነትን ከሕገ መንግሥት ምንነት አረዳድ እና ከሕገ መንግሥቱ ይዘት አንጻር እንደሚከተለው ለማቅረብ ተሞክሯል፡፡ 

1. ሕገ መንግሥቱ ይቀየር ሲባል ምን ማለት ነው? 

ሕገ መንግሥቱን በይቀየር እና በይሻሻል የሚንሸራሸሩ ተጻራሪ ሃሳቦችን በዝርዝር ማየቱ ጠቃሚ ቢሆንም ለጊዜው ሁለቱም ተወራራሽ መሆናቸውን መጥቀሱ ብቻ ይበቃል፡፡ መሻሻል የመቀየር፤ መቀየርም የመሻሻል አካል ናቸው፡፡ ሁለቱን የሚለያቸው መሻሻል ብዙ ወይም ትንሽ ሊሆን ሲችል፤ መቀየር ግን መሻሻልን በዋናነት በይዘት እና በብዛት ልቆ የሚገኝ ነው፡፡ 

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ካዘለው ግዙፍ ችግር አንጻር ከመሻሻል ይልቅ ጨርሶኑ የመቀየር አስፈላጊነት አጠያያቂ አይደለም፡፡ ሕገ መንግሥቱ መቀየር አለበት ሲባል በውስጡ ጥሩ ይዘት የለውም ማለት አይደለም፡፡ የአሁኑ ሆነ ቀደምት የአገራችን ሕገ መንግሥታት ከአገራችን ተጨባጭ ሁኔታዎች߹ከውጭ መንግሥታት እና ከዓለም አቀፍ ድርጅቶች ለምሳሌ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሕዝብን የጋራ እና የግል ሰብዓዊ߹ ማሕበራዊ߹ ፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ መብቶችን ከግዴታ ጋር በማስተሳሰር የተቀዱ በርካታ ቁም ነገሮችን አቅፈዋል፡፡ 

የሕገ መንግሥቱ መቀየር ከማሻሻል የሚመረጥበት ምክንያት የሕገ መንግሥቱ መሠረት የሆነው ፖለቲካዊ߹ ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ሥርዓቱ እጅጉን የተሳሳተ እና አገሪቱን ወደ አንድነት ሳይሆን ወደመበታተንና ወደ አገር መፍረስ የሚያንደረድር አደገኛ በመሆኑ ነው፡፡ በአገራችን የተቀጣጠለው ሰንካላ ፖለቲካዊ ሰደድ ግፈኛ የዘር ማጥፋት ወንጀልን ጨምሮ የዚህ ሕገ መንግሥት መዘዝ መሆኑ አሌ የማይባል ሀቅ ነው፡፡ ለአገራችን ሕልውና መጠበቅ እና ከመፍረስ ለመዳን በሕገ መንግሥት የተደነገገው የጎሣ ፌዴራሊዝም ሥርዓትን በማስወገድ እንጂ በማሻሻል አይሆንም፡፡

2. የሕገ መንግሥቱ መቀየር አስፈላጊነት – አጭር ምልክታ 

በአገራችን የጎሣ ፖለቲካ ሥርዓትን መሠረት ያደረገው የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በንድፈ ሀሳብ ሆነ በተግባር ከፍተኛ ችግር እንዳለበት ይታወቃል፡፡ ለሕገ መንግሥቱ መቀየር አስፈላጊነት በርካታ ምክንያቶች አሉ፡፡ የአገርን አንድነት እና የነጻነት ታሪክን አጠልሽቶ፤ የዘመናትን የሕዝብ መስተጋብር ክዶ፤ ኢትዮጵያውያንን በጎሣ ከፋፍሎ ለአገር መፍረስ ምቹ ሁኔታን የቀየሰ ሕገ መንግሥት ይቀየር ማለት አግባብነት መኖሩ በመሠረታዊነት የሚነሳ ሲሆን፤ሌሎች ምክንያቶችን እንደሚከተለው በአጭሩ መዳሰስ ይቻላል፡፡ 

2.1 የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት የሕገ መንግሥት ምንነትን መጻረሩ 

ሕገ መንግሥት በተጻፈ እና ባልተጻፈ መልኩ ሊሰደር ይችላል፡፡ የሕገ መንግሥት በጽሑፍ መገኘት ደግሞ የሥልጣኔን ጮራ እና ዘመናዊነትን ያሳያል፡፡ ኢትዮጵያ ለሕገ መንግሥት አዲስ አይደለችም፡፡ካልተጻፉት የመንግሥታት ሕግጋት በተጨማሪ በጥንት ጊዜ ፍትሃ ነገሥት߹ክብረ ነገሥት እና ሥርዓተ መንግሥት ለአያሌ ዓመታት በአገራችን እውን ሆነዋል፡፡ ክብረ ነገሥት እንደማይናድ ሕገ መንግሥት ተደርጎ ከአጼ ይኩኖ አምላክ ከ1270 ዓ.ም ጀምሮ የሰሎሞናዊ ሥርዎ መንግሥት ተነስቶ ለ700 ዓመታት ቀ.ኃ.ሥ ዘመናዊ ሕገ መንግሥት እስከ ተከሉበት 1923 ዓ.ም ድረስ በሥራ ላይ እንደዋለና እንዳገለገለ ታሪክ ያስረዳል፡፡ 

ክብረ ነገሥት ብሔረ ኢትዮጵያን ከሌሎች ብሔሮች ሁሉ የበላይ መሆኑን ያበስራል፡፡ ከፋርሶች። ከአምባይቶችና ከሌሎች ሴማዊ ከሚባሉ ሕዝቦች ሁሉ ከፍ ያደርጋል (የአባ ጠቅል አጼ ኃ.ሥ ዘመነ መንግሥት – በፋንታዬ ወ/ዘሊባኖስ-1999 ገጽ15-16) ፡፡ 

በዘመናዊ ታሪክ ዕይታ የአንድ ሀገር ሕገ መንግሥት ለውስጥ መስተዳድር እና ለውጭ ግንኙነት የፖሊሲ߹ የመርህ߹የሕግ߹ የደንብ እና የመመሪያ መሠረት ነው፡፡ ሕገ መንግሥት የሕጎች ሁሉ የበላይ የሆነ የፖለቲካ߹ የኢኮኖሚ እና የማሕበራዊ መሠረቶችና አቅጣጫዎች የሚቀዱበት ትልቁ ምንጭ ነው፡፡ ሕገ መንግሥት የሕዝብን የማይገረሰስ ሉዓላዊነት፤የግዛት አንድነትን እና ነጻነትን የሚያረጋግጥ፤በአገራዊ ራዕይ የበለጸገ የዲሞክራሲያዊ ሥርዓት መገንባትን፤ ለዕድገት߹ ለብልጽግና ߹ ለዕኩልነት እና ለሕግ የበላይነት የቆመ እና የሥራ ክፍፍልን እና ተጠያቂነትን የሚያሳይ ግዙፍ የተግባር መሣሪያ ነው፡፡ 

ሕገ መንግሥት ከሌላው ሀገር መለያ የሆነ የነጻነት ምልክት ሰንደቅ ዓላማ እና አዋሳኝ አገሮችን በግልጽ  ያስቀምጣል፡፡ ሕገ መንግሥት የሕዝብን ታሪክ ሳያጎድፍ በትክክለኛው ተመሥርቶ የሕዝብን ትስስር አበልጽጎ በሙሉ ነጻነት ለዓለም ተባባሪነት እና ተወዳዳሪነት ብቁ ሆኖ ለመገኘት ብሩህ ተስፋን ሰንቆ ይገኛል፡፡ የሕገ መንግሥት ይዘት ይህን መስሎ መገኘትና መጽደቅ ወሳኙ እና ባለቤቱ የአንድ ሀገር ሕዝብ መሆን ነው፡፡ ሕዝብ የሕገ መንግሥቱ ባለቤት ለመሆኑም በሙሉ ሂደት መረጋገጥ ይኖርበታል፡፡ 

የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሕገ መንግሥት ከላይ የተጠቀሱትን ባህሪያት ሙሉ በሙሉ አሟልቶ አይገኝም፡፡ የአገር ዳር ድንበርን በክልሎች ድንበር ስም ያስቀመጠ፤ ታሪክን መጣስ ብቻ ሳይሆን በይዘቱ አደገኛ፤ በአቀራረቡ እርስ በርስ የተቃረነና የተጣረሰ ድንጋጌዎችን ያሰፈረ፤ ከግልጽነት ይልቅ ብዥታን ያነገሠ ነው፡፡ በዚህ ጉድለቱ የተነሳም በበጎነት ሊጠቀሱ የሚችሉትን ድንጋጌዎች እንዲሸፈኑ አድርጓል፡፡ በጎሣዊ የፖለቲካ ሥርዓቱ ዕኩይ ዓላማ የተነሳ ለጭፍን አሠራር እና ለአገራዊ ራዕይ መጥፋት መሠረት ሆኗል፡፡ በመሆኑም፤እንዲህ ዓይነቱን ሕገ መንግሥት አቅፎ ለመዝለቅ መሞከር አደገኛ ነው፡፡ ምልክቱም ውጤቱም እየታየ ነውና፡፡

2.2 የሕገ መንግሥቱ አወጣጥ ሂደት – ሂደቱ በዋናነት በኢሕአዴግ መሪ ፓርቲ ሕውሐት – ፍላጎት የተመራ ነው፡፡ የሕገ መንግሥቱ ንድፍ ከሕውሐት የየካቲት ወር 1968 ጸረ-አማራ ፖለቲካዊ መግለጫ ዓላማና ፍላጎት ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ የሂደቱ መሠረትና ወጋግራዎች ሕውሐት ሥልጣን ከመያዙ በፊት  በትግል ላይ እያለ ያወጣው ጸረ- አማራ ፖለቲካዊ መግለጫ፤ ዋለልኝ መኮንን በብሔር ጭቆና ትረካ ያወጣው የጥላቻ ቅስቀሳ ጽሑፍ ለመንግሥቱ የፖለቲካ ሥርዓት እንዲሆን መመረጥ፤ የ1983 ዓ.ም የሽግግር መንግሥት ቻርተር እና ብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ለማቋቋም የወጣው አዋጅ ቁጥር 7/1984 የክልሎች ማቋቋሚያ አዋጆች በዋናነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ናቸው፡፡ 

ሀቁ ይህ ሆኖ ሳለ ሕገ መንግሥቱ የሕዝብ ተሳትፎ እንዳለበት ለማስመሰል ሥልጣንን በኃይል የያዘው ኢሕአዴግ/ሕውሐት በራሱ አምሳል ወይም ፍላጎት ያሰባሰባቸወን ግለሰቦችና ዓላማውን የሚጋሩ የፖለቲካ ድርጅቶች/ፓርቲዎች በመፍጠር ሆነ በማሰባሰብ ሕገ መንግሥቱ እንዲጸድቅ ተደርገ፡፡ ሂደቱ ፈጽሞ ዲሞክራሲያዊ አልነበረም፡፡ ሕገ መንግሥቱን በማጽደቁ ሂደት የተሰባሰቡት በስመ ተወካይነት የሕውሐትን አቋም የተቀበሉ ናቸው፡፡ ለሥልጣናቸው ሥጋት የሆኑ ድርጅቶች እንደ ኢሕአፓ߹መኢሶን እና ኢሠፓ ያሉት ተሳትፎ ተነፍገዋል። አንዳንዶቹ ከፈጠሩት ሕገ መንግሥት መንፈስ ውጭ ለምሳሌ አማራው߹አብዛኝ የደቡብ ማሕበረሰቦች እና ሌሎች በርካቶች ተገልለዋል፡፡ በሕውሀት መር ኢሕአዴግ እንኳንስ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች የግንባሩ ሦስቱ አባላትም ዕኩል የተሳትፎ መብት አላገኙም፡፡ የተባሉትን ለማጽደቅ መብት ነበራቸው ካልተባለ በስተቀር እውነተኛ የተሳትፎ መብት አልነበራቸውም፡፡ የተለየ የፖለቲካ አራማጅ ተብለው የተፈረጁ ሚሊዮኖች የዜግነት መብታቸውን ተነፍገው በሂደቱ አልተሳተፉም፡፡ 

በአጭሩ ሕገ መንግሥቱ በሕውሐት የቆየ ፖለቲካዊ አቋም፤ በሽግግር መንግሥት ቻርተር እና በክልሎች አወቃቀር አዋጆች የተመሠረተ እና ሕዝብ ያልመከረበት እና ያልዘከረበት ነበር፡፡ ሕገ መንግሥቱ በሕዝብ ላይ የተጫነ ነው፡፡ 

3 የሕገ መንግሥቱ ዓላማ እና ይዘት 

3.1 የሕገ መንግሥቱ አጠቃላይ ዓላማ ገጽታ/ባህሪይ – ሕገ መንግሥቱ በመግቢያው ላይ አንድ የፖለቲካ እና አንድ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ የመገንባትን አስፈላጊነትን ያመላከተ ሲሆን፤ በዋናነት የሚያጠነጥነው ለዚህ ዓላማ የቆሙት የተለያዩት የኢትዮጵያ ብሔሮች߹ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የራሳቸውን ዕድል በራሳቸው የመወሰን መብትን በመጠቀም በነጻ ፍላጎታቸው በሕግ የበላይነት እና በራሳቸው ፈቃድ ላይ የተመሠረተ እንደሆነ የሚያሳይ ነው፡፡ ይህ የብሔሮች߹ የብሔረሰቦች እና ሕዝቦች አቀራረጽ ለኢትዮጵያ እና በየትኛውም ዓለም ሀገራት የሌለ ነው፡፡ የኢትዮጵያን ታሪክ በመሸርሸር ለይስሙላ ከተጠቀሰው በጎ ዓላማ ጋር የተጣረሰ ነው፡፡ 

3.2 የኢፌዲሪ ሕገ መንግሥት ይዘት – ሕገ መንግሥቱ የከፋፋይ የሰላ ስልቱን አስቀምጧል፡፡ ኢትዮጵያ ዛሬ እንደአገር ራሳቸውን ችለው በነበሩ ብሔሮች߹ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ፈቃደኝነት መመሥረቷንና ከፈለጉ ሁሉም ካላንዳች ገደብ መገንጠል እንደሚችሉ መብት አጎናጽፏል (በመግቢያውና በአንቀጽ 39) ፡፡ በመሆኑም፤ ሕገ መንግሥቱ የሕዝብ አንድነት መንፈስን ያልያዘ ለልዩነት እና ለመለያያት ምቹ ሁኔታን የፈጠረ ነው፡፡ ዛሬ አገራችን ያለችበት ውስብስብ ፈተናና አጣብቂኝ ሁኔታ የሕገ መንግሥቱ ውልድ ማሳያ ነው፡፡

3.3 ታሪካዊ እና ፖለቲካዊ ፋይዳው 

ሕገ መንግሥቱ በኢትዮጵያ ውስጥ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች የየራሳቸው አገር እንደነበራቸው እና በሂደት አንዱ ብሔር ሌሎችን ብሔሮች߹ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች እንደጨቆነ አድርጎ ያስቀመጠ በሀሰት ትርክት ተመሥርቶ ታሪክን አጉድፎ እና ለልዩነት እኩይ መሠረት ጥሎ ጅማሮው “እኛ የኢትዮጵያ ብሔሮች߹ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች” የሚል የአንድነት እና የእውነት ጠር ነው፡፡ 

በዚሁ መግቢያ “መጪው የጋራ ዕድላችን መመሠረት ያለበት ከታሪካችን የወረስነውን የተዛባ ግንኙነት በማረምና የጋራ ጥቅማችንን በማሳደግ ላይ መሆኑን በመቀበል…” ይላል፡፡ ከታሪክ የተወረሰ የተዛባ ግንኙነት የሚለው የተለየ ምርምር አያሻውም፡፡ ሕውሐት አማራን በጨቋኝ ብሔርተኝነት የወነጀለበት የፖለቲካ አቋም መግለጫ ነው፡፡  

4. በተቃርኖ የታጀሉ ድንጋጌዎች እና የፖለቲካ እና የፅንሰ ሀሳብ አገላለጽ ችግር  

4.1 ሕገ መንግሥቱ ያሰፈረውን የአንድ ፖለቲካ እና አንድ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ የመመሥረት ዓላማን ከሚቃረኑት መካከል የሚከተሉት ይገኙበታል፡፡ 

ሀ. በምዕራፍ አንድ አንቀጽ 1/3 የፌዴራል አባሎች የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማና ዓርማ ሊኖራቸው ይችላል፡፡ ዝርዝሩን በየራሳቸው ምክር ቤት ይወስናል በሚል ተደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ ክልሎችን በአባልነት መጠቀሱ እና የየራሳቸው ሰንደቅ ዓላማ እና ዓርማ እንዲኖራቸው ማስቻሉ የአገሪቱ አካል እንዳልሆኑና በፈቃደኝነት የተሰባሰቡ አባሎች በሚፈልጉበት ጊዜ አባልነታቸውን ሊሰርዙ እንደሚችሉ የሚያረጋግጥ ነው፡፡ 

ለ. አንቀጽ 39/1 ማንኛውም የኢትዮጵያ ብሔር߹ ብሔረሰብ߹ ሕዝብ የራሱን ዕድል በራሱ የመወሰን እስከመገንጠል ያለው መብት በማንኛውም መልኩ ያለገደብ የተጠበቀ ነው፡፡ 

ሐ. አንቀጽ 39/2 …. በክልሎች ውስጥ የተካተቱ ብሔሮች߹ ብሔረሰቦች߹ ሕዝቦች በማንኛውም ጊዜ የየራሳቸውን ክልል የማቋቋም መብት አላቸው፡፡ 

ከላይ የተጠቀሱት ድንጋጌዎች በሕገ መንግሥቱ ለይስሙላ ለአንድ የፖለቲካ እና ለአንድ የኢኮኖሚ ማሕበረሰብ ምሥረታ ያመራሉ የሚለውን አገላለጽ የሚቃረኑ ናቸው፡፡ በመሆኑም ያጸደቁትን አከላለል የማፍረስ እና የመገንጠል መብት ሰጥቷል፡፡ የሕገ መንግሥቱን ክልላዊ መዋቅር እና እየቀጠለ ያለውን የክልል መንግሥትነትን በቀጣዩ የመገንጠል መብትን ለማሳካትና አገርን ለመበጣጠስ የፈቀደ ነው፡፡ 

4.2 ፖለቲካዊ የፅንሰ ሀሳብ አጠቃቀም መፋለስ እና ወጥነት አለመኖር 

ሀ. ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 47 ብሔሮች߹ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በማለት በደረጃ ያስቀመጠ ቢሆንም፤ በአንቀጽ 39/5 ላይ ብሔር߹ ብሔረሰብ እና ሕዝብን ካለደረጃ ልዩነት ያስቀመጣቸው በአንድ ፍቺ ነው፡፡ 

ለ. በአንቀጽ 8 ርዕሱ የሕዝብ ሉዓላዊነት ሆኖ በዚሁ አንቀጽ ን.አ. 1 የኢትዮጵያ ብሔሮች߹ ብሔረሰቦች߹ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው ይላል፡፡ ሕዝብ ሦስቱንም ስለመጠቅለሉ የቃሉ ትርጓሜ ወይም ፍቺ ከብሔሮች እና ከብሔረሰቦች ጋር ዕኩል ፍቺ ሰጥቶ በደረጃ ደግሞ ሦስትኛ አድርጎ ያስቀመጠ ነው፡፡ ይፋለሳል፡፡ 

ሐ. በምዕራፍ 1 አንቀጽ 8/1 – የኢትዮጵያ ብሔሮች߹ ብሔረሰቦች߹ ሕዝቦች የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው ይላል፡፡ አንቀጽ 8/2 ሉዓላዊነታቸው የሚገለጸው በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት በመረጣቸው ተወካዮቻቸውና በቀጥታ በሚያደርጉት ዲሞክራሲያዊ ተሳትፎ አማካይነት ይሆናል ይላል፡፡

በምዕራፍ 5 አንቀጽ 50/3 ደግሞ የፌዴራሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌዴራሉ መንግሥት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነው ይላል፡፡ ከላይ ያለውን አንቀጽ ይቃረናል፡፡ ሕዝብ ብቻ ነው የሚለው፡፡ ሕዝብ ደግሞ በዚህ ሕገ መንግሥት መሠረት በፍቺ እንደሌሎች ሆኖ ቢቀርብም በሦስተኛ ደረጃ የተቀመጠ አካል ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት አባላት አሰያየምን በሚያፋልስ መልኩ ያቀረበ ነው፡፡ 

መ. በአንቀጽ 47/4 የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ አባላት እኩል መብትና ሥልጣን አላቸው ይላል፡፡ ግን በአንቀጽ 49/5 የኦሮሚያ ክልል … በአዲስ አበባ ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል ይላል፡፡ ይህ አንቀጽ በሁለት መልኩ እርስ በርስ ተጣርሶ ይገኛል፡፡ 

አንደኛ ክልሎች ዕኩል ናቸው የሚለውን ይጻረራል፡፡ ምክንያቱም የኦሮሚያ ክልል ልዩ ጥቅም ስለሚጠበቅለት ከሌሎች የበለጠ ጥቅም አለው፡፡ ሁለተኛ ልዩ ጥቅሙ በአንቀጽ 40/3 የገጠርም ሆነ የከተማ መሬትና የተፈጥሮ ሀብት ባለቤትነት መብት የመንግሥትና የሕዝብ ብቻ ነው፡፡ መሬት የማይሸጥ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔሮች߹ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የጋራ ንብረት መሆንን እና በአንቀጽ 89/5 መንግሥት መሬትንና የተፈጥሮ ሀብትን በሕዝብ ስም በይዞታው ሥር በማድረግ ለሕዝቡ የጋራ ጥቅምና ዕድገት እንዲውሉ የማድረግ ኃላፊነንት ድንጋጌዎችን ይቃረናል፡፡ 

በመሠረቱ፤ አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ይገኛል የሚለው ድንጋጌ ትክክል ካለመሆኑም በላይ በየትኛውም ክልል ይሁን መሬትና የተፈጥሮ ሀብትን በሕዝብ ስም ባለቤቱ የፌዴራል መንግሥት በመሆኑ በዚህ ክልል ሥር በመሆኑ ብሎ ልዩ ጥቅምን ሊያስገኝ አይገባም፡፡ እንኳንስ ራሱን ለማስተዳደር በቻርተር አዋጅ መብት ለተሰጠው አስተዳደር ይቅርና በክልሉ በራሱ ውስጥ ያለው መሬትና የተፈጥሮ ሀብት የማዕከላዊ መንግሥት መሆኑ መዘንጋት የለበትም፡፡ 

በትክክለኛ ፖለቲካዊ ሥርዓት መንግሥት በማናቸውም ጊዜ ለፖለቲካ߹ኢኮኖሚያዊ እና ማሕበራዊ ጠቀሜታ እና ለአስተዳደር አመቺነት ሲባል የየትኛውም ክልል ካለበት ይበልጥ ሊሰፋ ወይም ሊጠብ እንደሚችል መዘንጋት የለበትም፡፡ በመሠረቱ፤ ሁሉም ክልሎች የመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ አንጡራ ሀብት እንጂ ቋንቋን መሠረት አድርጎ የዚህ የዚያ የሚያሰኝ ፖለቲካዊ ሀሳብ ሆነ ቅመራ ሊኖር አይገባም፡፡ 

ከሌሎች ተመክሮ አንጻር እንኳንስ ክልል አንድ አገር በሌላ አገር ውስጥ የሚገኝ ቢሆንም ልዩ ጥቅምን አያስገኝም፡፡ በደቡብ አፍሪካ አገራዊ ክልል ውስጥ ራሷን የቻለች ነጻ አገር ሌሶቶ ስለተገኘች ደቡብ አፍሪካ በሕገ መንግሥቷ ልዩ ጥቅም ያሰጣታል አይልም፡፡ የትብብር ስምምነት አላቸው እንጂ፡፡ 

ሠ. አንቀጽ 87/1 የሀገሪቱ የመከላከያ ሠራዊት የብሔሮች߹ የብሔረሰቦች እና የሕዝቦችን ሚዛናዊ ተወጽኦ ያካተተ ይሆናል ተብሎ ተደንግጓል፡፡ እንደገና በዚሁ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 5 የመከላከያ ሠራዊቱ ተግባሩን ከፖለቲካ ድርጅቶች ወገናዊነት ነጻ በሆነ አኳኋን ያከናውናል፡፡ ሚዛናዊ ተዋጽኦነቱን ተቀብሎ ከወገናዊነት ነጻ መሆን እንዴት እንደሚቻል ግልጽ ያለመሆን ብቻ ሳይሆን ለተግባራዊነትም አስቸጋሪ ነው፡፡ 

በአንቀጽ 87/4 የመከላከያ ሠራዊቱ በማናቸውም ጊዜ ለሕገ መንግሥቱ ተገዥ ይሆናል ብሎ ደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ ባልከፋ፡፡ ግን ሕገ መንግሥቱ ጎሣዊ መሠረት ያለውና ካለሕዝብ አሜነታ እና እሽታ የተጫነ በመሆኑ ተገዥነቱ በጎሣዊ አወቃቀር የመንግሥት ሥልጣንን ለጨበጠ አካል ታማኝ መሆን ለአገር አንድነትና ሰላም አደጋ ላለመኖር ዋስትና አይሰጥም፡፡ 

መከላከያ ለመስዋዕትነት ዝግጁ ሆኖ የፖለቲካ አመራሩ ለአገር የሚበጅን እንዲሠራ ካላደረገ በአገር ላይ ከፍተኛ ችግር መፈጠሩ አይቀሬ ነው፡፡ ለምሳሌ በሕዝብ ላይ ጭፍጨፋና ውድመት ሲፈጸም መንግሥት በቸልተኝነት ይሁን በሌላ ምክንያት ለመከላከያ መመሪያ ባይሰጥ እና መከላከያም ሕገ መንግሥቱን በማክበር ድርጊቱን ለማስቆም እርምጃ ባይወስድ ሕገ መንግሥቱን የማክበር ከትክክለኝነት ወይም ፍትሃዊነት በምን መመዘኛ መለካት ይቻላል? 

ረ. በአንቀጽ 46 /1 ….መንግሥት በክልሎች የተዋቀረ ነው በማለት ደንግጎ በአንቀጽ 47 የፌዴራል መንግሥት አባላት ክልሎችን በተለያየ ስያሜ ስድሰቱን በክልል ስም߹ 1 በብሔሮች߹ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች  ስም (ደቡብ)߹ 1 በሕዝቦች ስም (ጋምቤላ)߹ 1 በሕዝብ ክልል ስም (ሐረሪ) በጠቅላላ 9 ክልሎችን አስፍሮ ይገኛል(በአሁኑ ጊዜ ከደቡብ የወጡ 2 አዳዲስ ክልሎች ተጨምረዋል )፡፡ሌሎችም እያኮበኮቡ ነው፡፡ 

በአንቀጽ 46/2 ደግሞ —–ክልሎች የሚዋቀሩት በሕዝብ አሰፋፈር߹ቋንቋ߹ ማንነት እና ፈቃድ ላይ በመመሥረት ነው ይላል፡፡ በዚህ ድንጋጌ መሠረት ክልሎች ገና አልተዋቀሩም የሚል አንደምታ የያዘ ነው፡፡ 

የፌዴራል አባልነት እና በፈቃድኝነት መሰባሰብ አገላለጽ ክልሎች ቀድሞውንም ነጻና የተለያዩ እንደነበሩ የሚያሳይ ታሪክን የሚጻረር እና አገራዊ አንድነትን የናደ ነው፡፡ 

4.3 ኢኮኖሚና ንግድ 

ባአንቀጽ 55/1/ለ የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት በክልሎች መካከል የሚኖረውን የንግድ ልውውጥ እንዲሁም የውጭ ንግድ ግንኙነትን በተመለከተ ሕግ እንዲሚያወጣ ደንግጓል፡፡ ይህ ድንጋጌ የብሔሮች߹ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ሉዓላዊነትን አጠናክሮ ያቀረበ የክልሎች ግንኙነት እንደውጭ አገራት ግንኙነት አድርጎ እንዳስቀመጠ የሚያስቆጥር ነው፡፡ 

4.4 ቋንቋ – በአንቀጽ 5/2 አማርኛ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ አድርጎ ደንግጓል፡፡ በአንቀጽ 5/3  ደግሞ ክልሎች የየራሳቸውን ቋንቋ ይወስናሉ ይላል፡፡ የፌዴራሉ የሥራ ቋንቋ ሲባል ሕዝብን በአንድ የመግባቢያ ቋንቋ ማስተሳሰር እና ለአንድነት መጠናከር ብሎም በጋራ መሥራት የሚል ፍቺን እንደያዘ ይገመት ነበር፡፡ የሁለቱ አንቀጾች ተቃርኖ የሥራ ቋንቋ የሚለው የፌዴራል መሥሪያ ቤቶች መጠቀሚያ ማለት መሆኑ ነው፡፡ ስለሆነም ነው የተወሰኑ ክልሎች የራሳቸውን ቋንቋ በሌላው ላይ በመጫን በክልላቸው የሚገኙ አማርኛ እና ሌሎች ቋንቋ ተናጋሪዎች ከፖለቲካ ተሳትፎ – ከመምረጥና መመረጥ፤ የክልል አመራሮችን ስብሰባዎች እና ውሳኔዎች እንዳያውቁ በማድረግ ዜጎች ያሉበት በስም ኢትዮጵያ በተግባር ግን እንደማንኛውም የውጭ ዜጋ ለሀገረ ክልሉ ባይታወር ዜጎች እንዲሆኑ የተደረገው፡፡ 

በአንድ አገር ዜጎች በሚያውቁት ቋንቋ የማይዳኙበት፤የማይማሩበት፤የማይገለገሉበት፤ የክልል መስተዳደርን አዋጆች߹ ሕጎች߹ ደንቦችና መመሪያዎች ማወቅ የማይችሉበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ ክልሎች ለአንድ የተወሰነ ቋንቋ ተናጋሪዎች ሀብት እንድትሆን ተደርጓል፡፡ አማርኛ ብቻ እና ከክልሉ ቋንቋ በስተቀር የየራሳቸውን የአፍ ቋንቋ እና ለዘመናት የጋራ መገልገያ የነበረን የአማርኛ ቋንቋ የሚያውቁ የራሳችሁ ጉዳይ የተባለበት ሁኔታ ነው፡፡ የጎሣ ፖለቲካ ዘመናዊ የ21ኛው ግን ኋላ ቀርና የአምባገነናዊ ሥርዓት መገለጫ ነው የሚባለው ለዚህ ነው፡፡ አንድ አገር በየራሱ የአፍ መፍቻ ቋንቋ የመጠቀም መብት እንዳለ ሆኖ የጋራ ሀብትን በጋራ መግባቢያ ቋንቋ መጠቀም ያለማስቻል ሁኔታ ሲፈጠር ከቅኝ ግዛት ዘመን ማብቂያ ወዲህ የመጀመሪያ ክስተት ነው፡፡ በዚህም ኢትዮጵያ ከሌሎች የአፍሪካ ወንድሞች ጋር ሆና የታገለችበት የጸረ-አፓርታይድ ሥርዓት በኢትዮጵያ መልሶ አቆጠቆጠ የሚያሰኝ ነው፡፡ 

ያልነበረን በቋንቋ አጠቃቀም ጭቆና ነበር ማለትና ሆኖም የተነቀፈና የተወገዘን ጭቆና በተራ ልጫን ማለት ተገቢ አይደለም፡፡ የሁሉም ሀብት የሆነንና የሥልጣኔ መሠረት የሥነ ጽሑፍ ባለቤት ያደረገን ቋንቋ ያውም የራስን መናቅ ሲያሳዝን እንደገና የመጨቆኛ መሣሪያ ማድረግ ኢትዮጵያውያን እና ዓለምን የሚያሳዝን አድራጎት ነው፡፡ እንኳንስ በተሻሻለበት ዘመን ድሮም ለጋራ መግባቢያ ሲባል ትርጁማን ትልቅና የማይታለፍ የሥራ ድርሻ ነበር፡፡ ዓለም ወደአንድ መንደር እንድትንደረደር በሚታሰብበት ወቅት የአንድ ሀገር ሕዝብ እንዳይግባባ በሚችለው ቋንቋ የዜግነት መብቱን እንዳያገኝ ማድረግ አግባብ አይደለም፡፡ የባቢሎን ግንብ መፍረስ በኢትዮጵያ እንዲደገም ማሰብ ደግሞ የርግምትም ርግምት ይሆናል፡፡ 

በመሠረቱ አንድ ክልል የራሱ መገልገያ ቋንቋ ጎን ለጎን ለሁሉም ዜጎች የመግባቢያ ቋንቋ በሆነው በትርጉም ሆነ በየትኛውም መንገድ ማስተናገድ የፌዴራል የሥራ ቋንቋን ምንነት ተግባራዊ ማድረግ እና የአንድነት ሰንሰለትን ማጠናከር ማለት ነው፡፡ሕገ መንግሥቱ በአግባቡ ያልደነገገውና ለተንጋደደ ፍቺና ለዕኩይ ዓላማ ማስፈጸሚያ መሆኑ አንደኛው ማስረጃ ይህ ነው፡፡ 

5. በሕገ መንግሥቱ ያሉ ያረዳድ ችግሮች – የሕገ መንግሥቱ አንዳንድ መሠረታዊ ድንጋጌዎች መንግሥትን ሳይቀር ለብዥታ ያጋለጡ ናቸው፡፡ ለሕገ መንግሥቱ ጥሰትና ለጥንካሬ ድክመትም ምክንያት ሆነዋል፡፡ 

5.1 አንቀጽ 3/1/2 የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ አረንጓዴ ߹ቢጫ ߹ቀይ መሆኑን ገልጾ አርማው ከመሀሉ እንደሚሆንና የአርማው ምንነትም በዚሁ አንቀጽ ውስጥ ተደንግጓል፡፡ ሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓለማ አረንጓዴ߹ ቢጫ߹ ቀይ መሆኑን በማያሻማ መልኩ የደነገገውን ከድንጋጌው ሳይሆን ከሕገ መንግሥቱ ዐኩይ መንፈስ በመያዝ አረንጓዴ߹ ቢጫ߹ ቀይ ሰንደቅ ዓላማ አርማ የለበትም በማለት የሌላ አገር የጠላት ሰንደቅ ዓላማ እንደተያዘ ዓይነት በዜጎች ላይ አላስፈላጊ ድብደባ߹እስር እና እንግልት ሲከፋም ግድያ እሰከመፈጸም ተደርሷል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን መንግሥት – ሁሉም አካላት- ከላይ ታች ሕገ መንግሥቱ የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓላማ በአማርኛም በእንግሊዘኛም የኢትዮጵያ ሰንደቅ ዓለማ አረንጋዴ߹ ቢጫ߹ ቀይ መሆኑን መገንዘብ ያለመቻል ሳይሆን ያለመፈለግ ያሳዝናል፡፡ 

በመሠረቱ፤ ሕገ መንግሥቱ ባይልም እንኳ በአረንጓዴ ߹ቢጫ ߹ቀይ ቀለም ማንም ቢያጌጥ ለብጥብጥ߹ ለእስር እና ለግድያ ማድረስ አልነበረበትም፡፡ በዚህ ምክንያት ራስ ተፈሪዎች ሆኑ ኢትዮጵያውያን በውጭ አገራት ከእኛ ሰንደቅ ዓላማ የተለየ ቀለም ተጠቅማችኋል ተብለው ተመሳሳይ ዕጣ አላጋጠማቸውም፡፡

5.2 በአንቀጽ 59/17 ምክር ቤቱ ጠ/ሚኒሰትርን እና ሌሎች የፌዴራሉ መንግሥት ባለሥላጣናትን ለጥያቄ የመጥራትና የሕግ አስፈጻሚውን አካል አሠራር የመመርመር ሥልጣን አለው፡፡ ግን የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ለጥያቄና መልስ ጠ/ሚኒስትርን ሲያነጋግር በምዕራፍ 5 አንቀጽ 50/3 የተመለከተውን የፌዴራል መንግሥት የበላይ አካል የሆነው ም/ቤት የጠ/ሚኒስትሩ የበታች እና ም/ቤቱ የፌዴራል መንግሥት አካል እንዳልሆነ ሆኖ ይንጸባረቃል፡፡ በተጨማሪም በአንቀጽ 72/2 ጠ/ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ም/ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተጠሪዎች ናቸው ይላል፡፡ ይሁንና፡- 

ሀ. በሕገ መንግሥቱ መሠረት ጠ/ሚኒስትር ም/ቤት ቀርቦ (የሕግ አገላለጽ ሰለሆነ በአንቱነት አልቀረበም)  የመጠየቅ ግዴታ መሆኑ ተዘንግቶ ሁሉም ተናጋሪዎች በአንድ ዓይነት ዘይቤ ቀጥታ ወደጥያቄ ወይም አስተያየት ከመግባት ይልቅ “ጥያቄያችንን ለመመለስ ስለተገኙልን እናመሰግናለን” ይባላል፡፡ የዚህ ዓይነቱ አባባል ለከበሬታ ሲባል ቢሆን ባልከፋ ነበር፡፡ ግን አይደለም፡፡ አባባሉ ጠ/ሚኒስትሩ ም/ቤት ቀርቦ ለአባላቱ ለጥያቄ መልስ መስጠት ግዴታ ሳይሆን ቸርነት መሆኑን የሚያሳይ ስለመሆኑ የሚከተለው አስረጂ ነው፡፡ 

የምክር ቤቱ አባላት በተለመደ መልኩ “መንግሥትዎ ምን አስቧል? መንግሥትዎ ምን አድርጓል?  የሚሉት አባባሎች የም/ቤቱ አባላት ም/ቤታቸውን የፌዴራሉ መንግሥት አካል ያውም ከፍተኛው የመንግሥት አካል መሆኑን የመዘንጋትን ወይም ያለመረዳትን ሁኔታ ያመለክታል፡፡ ያለው አንድ የፈዴራል መንግሥት ነው፡፡ ፌዴራል መንግሥቱ ሦስት አካላት ያሉት መሆኑና ጠ/ሚኒስትሩ የተለየ መንግሥት እንደሚመሩ አድርጎ ማቅረቡ ትክክል አይደለም፡፡ 

በአጠቃላይ የዚህ ዓይነቱ ዓውድ ጠ/ሚኒስትርን የበላይ ም/ቤትን የበታች አድርጎ የመመልከት ሁኔታን ፈጥሯል፡፡ 

5.3 በሕገ መንግሥቱ ምዕራፍ 5/አንቀጽ 50 የኢ.ፌ.ዴ.ሪ በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች የተዋቀረ ነው ይላል፡፡ ክልል መንግሥት ስለመሆኑ አይገልጽም፡፡ ወረድ ብሎ ደግሞ በአንቀጽ 50/6 የክልል መስተዳድር ይላል፡፡ በአንቀጽ 85/2 በዚህ ምዕራፍ ውስጥ “መንግሥት” ማለት እንደሁኔታው የፌዴራል መንግሥት ወይም የክልል መስተዳድሮች ማለት ይሆናል በሚል ድንጋጓል፡፡ በአጠቃላይ ግልጽነት ባለመኖሩ በተግባር የክልሎች አጠራር በተዘበራረቀ መልኩ አንዳንዴ ክልላዊ ወይም ብሔራዊ ክልላዊ ወይም ብሔራዊ መስተዳድር አንዳንዴ ደግሞ መንግሥት እየተባለ መሪዎችም ርዕሰ መስተዳድር ወይም ፕሬዚዴንት በሚል ሲጠሩ ይደመጣል፡፡ በዚህም ዝብርቅር አጠቃቀም በአገሪቱ አንድ ርዕሰ ብሔር߹ አንድ ርዕሰ መስተዳድር /  መንግሥት እና 11 የክልሎች ርዕሰ መስተዳድሮች ወይም ርዕሰ መንግሥታት ወይም 11 ርዕሰ ብሔሮች፤  

ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች አሉ ማለት ነው፡፡ ይህም ከሕገ መንግሥቱ አቀራረጽ ጉድለት እና ከነዛው የተሳሳተ መንፈስ የመነጨ ነው፡፡ 

5.4 በአንቀጽ 49/2/3 የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ራሱን በራሱ የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን እንደሚኖረው ገልጾ ተጠሪነቱ ለፌዴራል መንግሥቱ ይሆናል ይላል፡፡ እዚህ ላይ ሁለት ግልጽ ያልሆኑ ነገሮች አሉ፡፡ ለፌዴራሉ መንግሥት ሲል ለሕግ አውጪው ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ወይስ ለሥራ አስፈጻሚው አካል እንደሆነ ግልጽ አይደለም፡፡የሌሎች ክልሎች ተጠሪነት ለወከላቸው የክልል ሕዝቦች ሲሆን የአ.አ.  

አስተዳደር ተጠሪነቱ ለወከለው ሕዝብ ያለመሆኑም ግልጽ አይደለም፡፡ 

5.5 በአንቀጽ 54/7 ማንኛውም የምክር ቤቱ አባል የመረጠው ሕዝብ አመኔታ ባጣበት ጊዜ በሕግ መሠረት ከም/ቤት አባልነት ይወገዳል ይላል፡፡ ይህን በሚመለከት ሆነ የመንግሥት ሥራ አስፈጻሚን ከጠቅላይ ሚኒስትር ጀምሮ የአፈጻጸም ሕግ እንደሚወጣ አልተመላከተም፡፡ 

6. ለሕገ መንግሥቱ መቀየር አስፈላጊነት ሌሎች ፖለቲካዊ እሳቢዎች 

6.1 የአገር መሪዎች (ፕሬዚዴንት እና ጠቅላይ ሚኒስትር) በሕዝብ ሙሉ ተሳትፎ ውክልናን ያገኙ እንዲሆኑ የሚያስችል ሥርዓት ቢደነገግ ይመረጣል፡፡ በዚህም የፕሬዚዴንት ሚና አሁን ካለው ላቅ ያለ ቢሆን ይመረጣል፡፡ 

6.2 የፌዴራል መንግሥትንና ክልሎችን የሚያስተሳስረው የሕግ አንቀጽ በግልጽ አልተደነገገም፡፡ በአንቀጽ 5/2 አማርኛ የፌዴራሉ መንግሥት የሥራ ቋንቋ ይሆናል ይልና በአንቀጽ 5/3 ደግሞ የፌዴሬሽኑ አባሎች የየራሳቸውን የሥራ ቋንቋ በሕግ ይወስናል በማለት የጋራ ቋንቋን አስቀርቶ ትስስሩ እንዳይኖር አድርጓል፡፡ ይህ አንቀጽ ከላይ ከተገለጸው አንጻር በሚገባ ታስቦበት የጋራ ቋንቋን አጠቃቀም በግልጽ መደንገግ ይኖርበታል፡፡ 

6.3 በአንቀጽ 58/18 ለሕግ አስፈጻሚው አካል በተሰጠ ማንኛውም ሥልጣን ላይ የምክር ቤቱ አባላት በአንድ ሦስተኛ ድምጽ ሲጠይቁ ም/ቤቱ ይወያያል፡፡ ም/ቤቱ በጉዳዩ ላይ የመመካከርና አስፈላጊ መስሎ የታየውን እርምጃ የመውሰድ ሥልጣን አለው ይላል፡፡ እርምጃው እስከምን እንደሚደርስ ግልጽ አይደለም፡፡ የተጠያቂነት አለመኖር ክፍተት እዚህ ላይ ይታያል፡፡

6.4 አንቀጽ 60/1 ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥልጣን ዘመኑ ከማለቁ በፊት አዲስ ምርጫ ለማካሄድ በምክር ቤቱ ፈቃድ ምክር ቤቱ እንዲበተን ለማድረግ ይችላል የሚለው ድንጋጌ ሥልጣኑ ለፐሬዚዴንቱ ቢሆን ይመረጣል፡፡ 

6.5 በፌዴሬሽን ሆነ በሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ተወዳዳሪ ፓርቲዎች በያዙት የድምጽ ብዛት በቀጥታ መቀመጫ ሊያሰጣቸው የሚያስችል ቀመር ሊኖር ይገባል፡፡ ይህም አላስፈላጊ በአንድ ፓርቲ ሙሉ ቁጥጥር ሥር መውደቅን ያስቀራል፡፡በሌላ መልኩ ለተፎካካሪ ፓርቲዎች የሚሰጥ ሹመት በችሮታ ሳይሆን በሕግ ላይ ተመሥርቶ ቢሆን አላሳፈላጊ ፍቺን ያስቀራል፡፡ በመሠረቱ ሥልጣን በዲሞክራሲያዊ ሕግጋት በፉክክር የሚገኝ እንጂ በስጦታ መሆን የለበትም፡፡ በሕግ ያልተመሠረተ የሥልጣን መጋራት በስጦታ በፈቃደኝነት መሆን እሩቅ አያስኬድም፡፡ 

6.6 ምዕራፍ 5 አንቀጽ 50 ላይ የኢ.ፌ.ዴ.ሪ በፌዴራል መንግሥትና በክልሎች የተዋቀረ መሆኑን እና የኢ.ፌ.ዴ.ሪ መንግሥትና ክልሎች የሕግ አውጪነት የሕግ አስፈጻሚነት የዳኝነት ሥልጣን እንዳላቸው እና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካል የፌ. መ. የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት ነው ቢልም ግልጽ የሆነ የጠያቂነት እና የተጠያቂነት ትስስር የለም፡፡ 

5.7 የሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት እንደከፍተኛ የመንግሥት አካልነቱ የክልል መስተዳድርን ተጠያቂነት የሚያደርግ የሕግ ድንጋጌ የለም፡፡ በአንቀጽ 62/9 የፌዴሬሽኑ ምክር ቤት ማንኛውም ክልል ይህን ሕገ መንግሥት በመጣስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደሆነ የፌዴራሉ መንግሥት ጣልቃ እንዲገባ ያዛል የሚለው ድንጋጌ ከዚያ መለስ ባለሥልጣናት በአገር ደረጃ በግል ሆነ በጋራ ተጠያቂ የሚሆኑበት ሁኔታ አልተደነገገም፡፡ 

5.8 በአንቀጽ 72/2 ጠ/ሚኒስትሩና የሚኒስትሮች ም/ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ተጠሪዎች መሆናቸውንና የሚኒስትሮች ምክር ቤት አባላት በመንግሥት ተግባራቸው በጋራ ለሚሰጡት ውሳኔ የጋራ ኃላፊነት እንዳለባቸው ደንግጓል፡፡ በግል ተጠያቂነታቸው ካለመኖሩም በተጨማሪ ለጋራ ተጠያቂነታቸው በምን ሁኔታ እንደሆነ በዚህ ውስጥ አልተመላከተም ወይም በሌላ ሕግ እንደሚወጣም አልተደነገገም፡፡ ይህም ለተጠያቂነት አለመኖር ክፍተት አለው፡፡ 

5.9 የፌ.መንግሥትና ክልሎች አንዱ የሌላውን ሥልጣን የማክበር ግዴታ ቢደነገግም አንደኛው ወይም ሁለቱ ሕጉን ሲጥሱ ምን ማድረግ እንደሚቻል ግልጽ አይደለም፡፡ 

5.10 የፌዴራሉ የዳኝነት ሥልጣን የፍ/ቤቶች ቢሆንም በፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ የሥልጣን አካላት ላይ በተለይም በጋራ እና በተናጠል በፖለቲካዊ ጥፋቶች ላይ ምን የዳኝነት ሚና እንደሚኖረው ግልጽ አይደለም፡፡ 

5.11 አንቀጽ 52/2 /ረ የክልሉን መስተዳድር ሠራተኞች አስተዳደር የሥራ ሁኔታዎች በተመለከተ ሕግ ያወጣል ያስፈጽማል ሆኖም ለአንድ የሥራ መደብ የሚያስፈልጉ የትምህርት የሥልጠናና የልምድ መመዘኛዎች ከአጠቃላይ የሀገሪቱ መመዘኛዎች ጋር የተቀራረቡ መሆናቸውን የማረጋገጥ ኃላፊነት ይኖርበታል ይላል፡፡ ይህ በፌዴራል ደረጃ የሚወጣን የአሠሪና ሠራተኛ ግንኙነት አዋጅን ያላጣቀሰ በመሆኑ በፌዴሬሽኑ እና በክልል ደረጃ የሕግ መፋለስ ሊያስከትል ይችላል፡፡ የማረጋገጥ ኃላፊነቱን ባይወጣ ምን እርምጃ እንደሚወሰድ ግልጽ አይደለም፡፡ 

5.12 የፖለቲካ ፓርቲዎች ውድድር በተለይም በከፍተኛው አመራር የመላው ሕዝብ ተሳትፎ የሌለበት በመሆኑ እንደገና ሊታይ ይገባል፡፡ ለመንግሥትነት የሚደረግ የፓርቲዎች ግዑዛን ውድድር መስሎ ከመታየት ያለፈ አይደለም፡፡ ግለሰቦች ግልጽ ፉክክር የሚያደርጉበት ሥርዓት የሌለው በመሆኑ ይህም በሕገ መንግሥት ተጨማሪ ድንጋጌዎች ሊፈተሽ የሚገባ ነው፡፡ 

በዚህ ጽሑፍ የአገራችን ውስብስብ߹ አስደናጋጭና የከፉ ችግሮች በዝርዝር አልቀረቡም፡፡ ከነጭራሹ አልተነኩም ማለት ይቻላል፡፡ ይሁንና ለሁለም ተግደሮቻችን߹ ፈተናዎችና ችግሮች ብሎም የአገራችንን ህልውና ለመፈታተን የተደረሰበት አንደኛውና ዋንኛው መንስዓ የሕገ መንግሥቱ መሠረት የሆነው የጎሣ ፌዴራሊዝም ሥርዓት ነው፡፡ 

ችግሩ ሕገ መንግሥቱ ተግባራዊ ያለመሆኑ ነው የሚሉ ወገኖች እንዴት ተግባራዊነቱን እንዳልተረዱት ግራ ያጋባል፡፡ የጎሣ ፌዴራሊዝም ከንድፈ ሀሳብ ጀምሮ በተግባር በአገራችን የደረሰውን ዓይነት ግፍና መከራ ውጤት ማምጣት ነው፡፡ እየሆነ እየተገበረ እያለ ተግባራዊ አልሆነም ማለት ጉንጭ አልፋ ክርክር ከመሆን አያልፍም፡፡ የአገር መፍረሱ ጊዜ ተራዘመ መለያየቱ ዘገየ ካልተባለ በስተቀር ጎሣዊ ፌዴራሊዝም የመጨረሻ ውጤቱ ቢዘገይም ተፈጥሯዊ ባህሪይውን ተግባራዊ እያደረገ ነው፡፡ 

በጎ በጎውን እናስብና በስመ ፌዴራሊዝም የዓለም መሳቂያና መሳለቂያ ከመሆንና ወደ አልተፈለገና ወደሚያስፈራን ጉዞ ላለመሄድ መንግሥትና ተፎካካሪ ፓርቲዎች ለአገርና ለሕዝብ ይቁሙ፡፡ ትክክለኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓትን ለመትከል ከላይ የተጠቀሱትን ነጥቦች እና ሌሎች በርካቶችንም ከግንዛቤ ውስጥ በማስገባት በሥራ ላይ ያለውን ሕገ መንግሥት መቀየር ያስፈልጋል፡፡ በዚህም አገርን ማዳን ሕዝብን ከሰቆቃ ኑሮ߹ ከሙሰኝነትና ከድህነት መላቀቅ߹ ትውልድን መታደግ፤ የአገራችንን አንጸባራቁ የአንድነት እና የነጻነት ታሪክ ማደስ ይቻላል፡፡የሚያዋጣን ብቸኛው መንገድ አንድነታችን߹ሰላማችን߹አብሮነታችን߹ሊፋቅ የማይችለውን የደም ትስስራችንን ሳንክድ በኢትዮጵያዊነታችን በፍቅር መያያዝ ነው፡፡ ያለፈውና እየተደረገው ያለው ይብቃን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,864FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here