
ጀማል ሰይድ
ቦርከና
መደበኛው ጉባኤውን ከአንድ ወር በፊት ያደረገው የፌዴሬሽን ምክር ቤት፤ በደቡብ ክልል አደረጃጀት ጉዳይ ላይ ውሳኔ ለማሳለፍ አስቸኳይ ስብሰባ ሊያካሄድ ነው። በሚቀጥለው ሳምንት ረቡዕ ነሐሴ 11፤ 2014 ለሚደረገው ለዚሁ አስቸኳይ ስብሰባ ጥሪ እንደተደረገላቸው ነገሩኝ ያላቸውን ሁለት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አባላት ጠቅሶ “ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” ዘግቧል።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ተረፈ በዳዳ፤ ምክር ቤቱ አስቸኳይ ስብሰባውን በመጪው ረቡዕ እንደሚያካሂድ ለ“ኢትዮጵያ ኢንሳይደር” አረጋግጠዋል። አቶ ተረፈ ምክር ቤቱ “ከደቡብ ክልል ጋር ተያይዞ የሚወስናቸው ውሳኔዎች ይኖራሉ” ሲሉ ስብሰባው የተጠራበትን ምክንያት ገልጸዋል።
በደቡብ ክልል የሚገኙ አስር ዞኖች እና ስድስት ልዩ ወረዳዎች፤ በሁለት የተለያዩ ክልሎች የመደራጀት ጥያቄያቸውን ባለፈው ሳምንት ሐሙስ ሐምሌ 28፤ 2014 ለፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ጽህፈት ቤት አስገብተዋል። ጥያቄዎቹን የያዙ ሰነዶች ርክክብ ስነ ስርዓት ላይ ንግግር ያደረጉት የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ አገኘሁ ተሻገር፤ “የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጥያቄው ላይ ውይይት አካሄዶ፤ በአጭር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ ወስኖ የሚያሳውቅ ይሆናል” ብለው ነበር።
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena