spot_img
Sunday, March 3, 2024
Homeዜናበኢትዮጵያ የተራቡ ዜጎችን ለመርዳት የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር (WFP) ከዩክሬን የሸመተውን ስንዴ የጫነ...

በኢትዮጵያ የተራቡ ዜጎችን ለመርዳት የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር (WFP) ከዩክሬን የሸመተውን ስንዴ የጫነ መርከብ ከኦዴሳ ጉዞ ጀመረ

ስንዴ የጫነ መርከብ

ጀማል ሰይድ  
ቦርከና 

በኢትዮጵያ የተራቡ ዜጎችን ለመርዳት የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር (WFP) ከዩክሬን የሸመተውን ስንዴ የጫነ መርከብ ከኦዴሳ ጉዞ ጀመረ። የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የተከራየው እና የሊባኖስ ሰንደቅ የሚያውለበልበው ብሬቭ ኮማንደር የተባለ መርከብ ጉዞ መጀመሩ የተገለጸው የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጉዳዩን ባጣጣሉበት በትላንትናው ዕለት ነው። 

ከኦዴሳ አጠገብ ከሚገኘው ወደብ የተነሳው መርከብ በቱርክ እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አደራዳሪነት ዩክሬን እና ሩሲያ ሥምምነት ላይ ከደረሱ ወዲህ እህል ለመጫን ወደ ቦታው ያቀና የመጀመሪያ መርከብ ነው። “ይኸ መርከብ በኢትዮጵያ ለተራቡ ሰዎች 23,000 ሜትሪክ ቶን ስንዴ በጅቡቲ ወደብ በኩል ያጓጉዛል” ሲሉ በዩክሬን የዓለም የምግብ መርሐ-ግብር ምክትል ዳይሬክተር ማርያነ ዋርድ ተናግረዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ትላንት እሁድ የድሬዳዋ ነጻ የንግድ ቀጠና ሲመረቅ ባደረጉት ንግግር ግን መንግሥታቸው ከዩክሬን ስንዴ እንዳልሸመተ ገልጸዋል። “ኢትዮጵያ በድርቅ ልትመታ ነው። ድርቅ ኢትዮጵያን ያጠቃታል የሚል ዜና በስፋት ይሰማል። ኢትዮጵያ ስንዴ ገዝታ፤ ስንዴዋ በጀልባ ተጭኗል። የሚል ዜናም ተሰምቷል” ያሉት ዐቢይ “ኢትዮጵያ ስንዴም አልገዛችም፤ ኢትዮጵያ ድርቅም አይመታትም” ሲሉ ተደምጠዋል። 

ዐቢይ በንግግራቸው ሁለቱን ጉዳዮች “ቀድሞ የማጥላላት ዘመቻ አካል” አድርገው አቅርበዋል። ዐቢይ በድሬዳዋ ባደረጉት ንግግር “ስንዴ ኤክስፖርት እናደርጋለን እያሉ ስንዴ ያስገባሉ፤ ስንዴ ኤክስፖርት እናደርጋለን እያሉ በድርቅ ተመቱ ለማለት እንዲያመቻቸው ነው” በማለት በስም ያልጠቀሷቸውን ወገኖች ከሰዋል። 

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዕለቱ በሶማሌ ክልል ፋፈን ዞን ከ8 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ስንዴ ይመረትበታል ያሉትን 127 ሺሕ ሔክታር ኩታ ገጠም የእርሻ ማሳ ጎብኝተው ነበር። ከጉብኝታቸው በኋላ በድሬዳዋ ከተማ ባደረጉት ንግግር ዐቢይ “ስንዴ ከጥቂት ወራት በኋላ ድርቅ ገባ እየተባለም ኤክስፖርት አድርገን ጠላት እናሳፍራለን። ኢትዮጵያውያንን እናስደስታለን” ሲሉ ተናግረዋል። 

ካለፈው ጥቅምት ወር ጀምሮ በአፍሪካ ቀንድ አገራት የተከሰተው ድርቅ 19.4 ሚሊዮን ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ቢሮ አስታውቋል። በድርጅቱ መረጃ መሠረት በኢትዮጵያ፣ ኬንያ እና ሶማሊያ 18.6 ሚሊዮን ሰዎች ብርቱ የምግብ ዋስትና እጦት እና እየጨመረ የሚሔድ የተመጣጠነ ምግብ እጦት ገጥሟቸዋል። ይኸው ድርቅ በኢትዮጵያ ብቻ 7.4 ሚሊዮን ገደማ ሰዎችን ለኃይለኛ የምግብ እጦት ዳርጓል። 

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ “ኢትዮጵያ ድርቅም አይመታትም” ቢሉም በሶማሌ ክልል እና በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን የተከሰተውን በንግግራቸው መልሰው ጠቅሰዋል። “ከዓመት በፊት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ችግር ሲያጋጥም ´የዓለም ሚዲያ በሙሉ ከፍተኛ ድርቅ ስለሚያጋጥም ይኸ ድርቅን ተገን ያደረገ ውጊያ ነው እና አቁሙ` እንባል ነበር” ያሉት ዐቢይ “በወቅቱ እኛ ድርቅ በሰሜን ያገራችን ክፍል የለም፤ አይኖርም ብንልም ሰሚ አልነበረንም” ሲሉ ተደምጠዋል።   ጠቅላይ ምኒስትሩ “በሰሜን ድርቅ ያጋጥማችኋል ብለው በስፋት ሲናገሩ የነበሩ ኃይሎች ሶማሌ እና ቦረና ሲጠቃ እንኳን ተጨማሪ ድጋፍ ማድረግ ቀርቶ ከአምስት ስድስት ዓመት በፊት፤ ከአስር ዓመት በፊት ያደረጉትን ድጋፍ ማድረግ አልቻሉም” ሲሉ ከሰዋል።

__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here