spot_img
Monday, May 29, 2023
Homeአበይት ዜናበትግራይ አንድ ኩንታል ጤፍ ከ17 ሺህ ብር በላይ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ

በትግራይ አንድ ኩንታል ጤፍ ከ17 ሺህ ብር በላይ መሆኑን ነዋሪዎች ተናገሩ

- Advertisement -
 ኩንታል ጤፍ

ጀማል ሰይድ
ቦርከና

ሁለት ዓመት ሊሞላው ጥቂት ወራት የቀረው ጦርነት በተቀሰቀሰባትና መሰረተ ልማቶች በተቋረጡባት ትግራይ ውስጥ አንድ ኩንታል ጤፍ እስከ 17 ሺህ ብር እየተሸጠ እንደሚገኝ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

በክልሉ ውስጥ በእርዳታ አቅርቦት ሥራ ላይ ተሰማርተው የሚገኙ ግለሰቦችም አንድ ኩንታል ጤፍ ከ15 እስከ 17 ሺህ ብር እየተሸጠ እንደሆነ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የአንድ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ሠራተኞች እንዳሉት ክልሉን እያስተዳደሩ ያሉት ባለሥልጣናት በጤፍ የመሸጫ ዋጋ ላይ ተመን ማውጣታቸው የዋጋ ጭማሪውን እንዳባባሰው ተናግረዋል።

የመቀለ ከተማ ነዋሪ የሆነው ዳንኤል በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ በአስከፊ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝ ገልጾ፤ በተለይ የጤፍ ዋጋ ከሕብረተሰቡ አቅም በላይ ሆኗል ብሏል። ለቢቢሲ አስተያየተቸውን የሰጡ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የግረሰ ሰናይ ድርጅቶች ሠራተኞች እንደሚሉት፣ በአሁኑ ወቅት የጤፍ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር በክልሉ የተጣለው የመሸጫ ዋጋ ተመን እጥረት እና የዋጋ መናርን ማስከተሉን ይናገራሉ።

“ጤፍ እጅግ በጣም ተወዷል። ነጋዴዎች በማኅበረሰቡ ላይ ጨክነዋል። የሕብረተሰቡን ሁኔታ ያላገናዘበ ተግባር ነው እየፈጸሙ ያሉት። ከባድ ሁኔታ ነው እያሳለፍን ያለነው። ብዙዎች እንጀራ መመገብ የማይችሉበት ደረጃ ላይ ደርሰናል” በማለት ዳንኤል ያለውን ሁኔታ አስረድቷል።

ሌላኛው በርኽ የተባለ አስተያየት ሰጪ በበኩሉ “ረሃብና ድርቅ አለ። ሕዝቡ ያለውን ተካፍሎ ለመኖር እየሞከረ ነው። ሰዎች ከትግራይ ውጪ ከሚገኙ ቤተሰቦቻቸው እንደምንም ብሎ የሚደርሳቸው ገንዘብ ምንም ነገር ሊገዙበት አልቻሉም። በተለይም የጤፍ ዋጋ የሚቀመስ አይደለም” ብሏል። በርኽ እንደሚለው በአሁኑ ጊዜ ያለው የጤፍ ዋጋብቻ ሳይሆን የስንዴና የስንዴ ዱቄት ዋጋም ከሕብረተሰቡ የመግዛትአቅም ጋር በፍጹም የሚመጣጠን አይደለም።

“አንድ ሰው ሁለት እና ሦስት ሺህ ብር ከቤተሰብ ተልኮለት 25 ኪሎ ጤፍ እንኳን መግዛት የማይችልበት ጊዜ ላይ ነው ያለነው። ሩብ ኩንታል ለመግዛት ከ4 ሺህ ብር በላይ ሊኖርህ ይገባል” ሲል ጨምሮ ገልጿል። በመቀለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት በርኽ እና ዳንኤል እንደሚሉት በክልሉ የጤፍ ዋጋ እጅግ ከፍተኛ በሆነ ሁኔታ እንዲጨምር ምክንያት የሆነው እጥረት በመኖሩ ሳይሆን፣ ነጋዴዎች ተገቢ ያልሆነ ትርፍ ለማግኘት በማሰብ ዋጋውን በማናራቸው ነው። “ነጋዴዎች የያዙትን ጤፍ ደብቀው በመያዝ፤ የለም በማለት እና በደላላዎች በኩል እያወጡ በከፍተኛ ዋጋ በመሸጥ ሕብረተሰቡን እየጎዱ ይገኛሉ። ባለሥልጣናት ይህንን ሁኔታ ለመቆጣጠር እንቅስቃሴ መጀመሩን ቢገልጹም እስከ ዛሬ ግን የመጣ ለውጥ የለም” ብሏል በርኽ።

ዳንኤል በበኩሉ “ነጋዴዎች ‘እኛ በምንወስነው ዋጋ ነው የምንሸጠው’ እያሉ ስለሆነ ነው ችግሩ የተባባሰው” ሲል ያስረዳል። በአሁኑ ጊዜ በኩንታል ከ16 እስከ 17 ሺህ ብር በመክፈል የጤፍ እንጀራ መመገብ ያልቻሉ ሰዎች ከእርዳታ የሚገኘውን ስንዴ እና እንደ አቅማቸው ከሚገዙት ማሽላ እንጀራ ለማዘጋጀት ተገደዋል። ነዋሪዎች እንደሚሉት ከሆነ ነጋዴዎች ይፋዊ ባልሆነ መንገድ አዋሳኝ ከሆኑ የአማራ እና የአፋር አካባቢዎች ነው ጤፍ ወደ ትግራይ ክልል የሚያስገቡት።

በቅርብ ቀናት የተወሰነ ጤፍ መግባቱን ተከትሎ በዋጋ ላይ መሻሻል የታየ ቢሆንም፤ ብዙ ሳይቆይ ወደነበረበት የማይቀመስ ዋጋ መመለሱን ቢቢሲ ከነዋሪዎች ለመገንዘብ ችሏል። ከዚህ በተጨማሪ ከጥቂት ቀናት በፊት የህወሓት ሊቀ መንበር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) ከመቀለ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት ላይ ከተገኙ ተሳታፊዎች መካከል በርካቶች የጤፍ ዋጋ ጉዳይ በማንሳት ቅሬታቸውን አሰምተዋል። ድምጺ ወያነ ባስተላለፈው ዘገባ ከደብረጽዮን (ዶ/ር) ጋር ከተወያዩት ነዋሪዎች መካከል አንዲት እናት ለጤፍ ዋጋ መናር አመራሮችን እና ነጋዴዎችን ተጠያቂ አድርገዋል።

በዚሁ ሕዝባዊ ስብሰባ ላይ ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ እና ማብራሪያ የሰጡት የክልሉ መሪ፤ ተገቢ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ መኖሩን እና ሕጋዊ ያልሆነ የንግድ እንቅስቃሴ መበራከቱን አረጋግጠዋል። “ሕጋዊ ያልሆኑ ነጋዴዎች ጥቂቶች ናቸው። በዝርዝር ይዘናቸዋል። ሕዝቡ ከነገረን ብቻ ሳይሆን ራሳችንም አጣርተናል። እርምጃ ወደ መውሰድም እንገባለን። መረጃ ስናገኝ ወደ ፍርድ እንዲቀርቡ እናደርጋለን” ሲሉ ተደምጠዋል።

ጤፍን ጨምሮ የሌሎች ሸቀጦች መቀለ ከደረሱ በኋላ ወደ ተቀረው የክልሉ ክፍል የሚከፋፈል መሆኑን በመጥቀስ፣ በተቀረው የትግራይ ክፍል የጤፍ ዋጋ መቀለ ከሚሸጠው በላይ መሆኑን ነዋሪዎች ያስረዳሉ። ቢቢሲ ያነጋገራቸው የግረሰ ሰናይ ድርጅት ሠራተኞች ገንዘብ ያለው ጤፍ ልግዛ ቢል እንኳ በቀላሉ ማግኘት ሰለማይቻል በደላላ በኩል ማፈላለግ ግድ ነው። ይህም የአንድ ኩንታል ዋጋን ከ20 ሺህ ብር በላይ ያሻግረዋል ይላሉ።

በሰሜን ኢትዮጵያ የእርስ በእርስ ጦርነት መጀመርን ተከትሎ እንደ ቴሌኮም፣ የኤሌክትሪክ ኃይል እና ባንክን የመሳሰሉ መሠረታዊ አግልግሎቶች ተቋርጠው በሚገኙባት ትግራይ፤ አንድ ኩንታል ጤፍ ከ6 አስከ 8 ሺህ ብር ሲሸጥ ነበር። ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበው ጦርነት በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ያስከተለ ሲሆን፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ በርካታ ሰብዓዊ ድርጅቶች በክልሉ የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች የረሃብ አደጋ ተጋርጦባቸዋል ሲሉ ተደጋጋጋሚ ማሳሰቢያ ሲያወጡ መቆየታቸው ይታወሳል።

የረድኤት ድርጅቶች ባለፉት ወራት እንደ ሰንዴ፣ በቆሎ እና አልሚ ምግቦችን ወደ ትግራይ ሲያደርሱ መቆየታቸው ይታወሳል። ምንም እንኳ ትግራይን እያስተዳደረ ያለው ህወሓት አይስማማ እንጂ ከሳምንታት በፊት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በክልሉ አንዣቦ የነበረው የረሃብ አደጋ ስጋት ተቀልብሷል ብሎ ነበር።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም የኢትዮጵያ ከፍተኛ ኃላፊ ኤድሪያን ቫንዳክናብ ሐምሌ 08/2014 ዓ.ም. ለቢቢሲእንደተናገሩት፤ በትግራይ ክልል ለሚገኙ ከአንድ ሚሊዮን በላይ ሰዎች የሰብዓዊ እርዳታ ማድረስ መቻሉን ገልጸው ነበር። የህወሓት አመራር የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳ ግን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ኃላፊ የረሃብ አደጋ ስጋቱ ተቀልብሷል ማለታቸውን ተችተውታል። ህወሓት ወደ ክልሉ የሚገባው እርዳታ መቆራረጥ እንደሚያጋጥመው እንዲሁም ያለውን እርዳታ ለተረጂዎች ለማድረስ የነዳጅ እጥረት መኖሩን ያመለክታሉ።

__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
12,864FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here