spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeዜና«የውስጥ ችግራችን ለውጭ ተጋላጭነታችን ግብዓት እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል» አቶ ሌንጮ ለታ...

«የውስጥ ችግራችን ለውጭ ተጋላጭነታችን ግብዓት እንዳይሆን ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል» አቶ ሌንጮ ለታ – የኦነግ መስራች

አቶ ሌንጮ ለታ
አቶ ሌንጮ ለታ

ጀማል ሰይድ  
ቦርከና 

የውስጥ ችግር በሰፋ ቁጥር ለጠላቶች ሰፊ ዕድል ስለሚፈጥር ተገቢውን ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚያስፈልግ ፖለቲከኛው አቶ ሌንጮ ለታ አመለከቱ።

አቶ ሌንጮ በተለይ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት በሰጡት አስተያየት፣ ሰሞኑን የአልሸባብ በተሳሳተ ስሌት ኢትዮጵያ በውስጥ ችግሯ ምክንያት ራሷን መከላከል እንደማትችል በማሰብ ከዚህ በፊት ባልተለመደ መልኩ ብዙ ታጣቂዎችና ብዙ ጦር መሣሪያ በመያዝ ድንበር ጥሶ መግባቱ እንደ ቀላል የሚታይ ክስተት አይደለም።

ሱዳንም በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል የተደረገውን ጦርነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያን ድንበር ጥሳ ለመግባት ሞክራለች ያሉት አቶ ሌንጮ፤ ከትንኮሳዎች ጀርባ ሌላ ፍላጎት መኖሩ እንዳለ ሆኖ የውስጣችን ችግር አስተዋጽኦ ማድረጉ አያጠያይቅም ብለዋል።

ያም ሆኖ ግን በተለይ በአልሸባብ ላይ የተወሰደው እርምጃ ቡድኑ የሃይማኖት አክራሪነትን ለማስፋትና ሌላውን በመጨፍለቅ ታላቋ ሶማሊያን ለመገንባት የሚደረገውን የቀን ቅዠቱን እንቅስቃሴ እርቃኑን ያስቀረና በተቃራኒው ደግሞ የኢትዮጵያን ጥንካሬ ያስመሰከረ አኩሪ ገድል ነው ያሉት አቶ ሌንጮ፣ ለዘላቂ ድል ግን ብሎም ጠላቶቻችንን ማፈናፈኛ ለማሳጣት ወደ ውስጥ በደንብ መመልከት ተገቢ መሆኑን ጠቁመዋል።

እንደ ዓለም እየተስተዋለ ያለው የሰላም እጦት አሳሳቢ መሆኑ እንዳለ ሆኖ በተለይ በምሥራቅ አፍሪካ በፊት የነበረው በጥርጣሬ የመተያየት ችግር እየሰፋ መጥቷል ያሉት አቶ ሌንጮ፣ በሱዳንም ሆነ በኢትዮጵያ ውስጥ የጸጥታ ችግር እያለ እንደገና በድንበር ሰበብ መጣላት የዚሁ አንዱ ማሳያ መሆኑንና መዘዙ ከባድ እንደሆነም አመላክተዋል።

በታላቁ ህዳሴ ግድብ ምክንያት ግብጽና ሱዳን ሌሎች አገራት ኢትዮጵያን በጥርጣሬ እንዲያዩ አልፎም ኢትዮጵያ እንዳትረጋጋ በውስጥ ጉዳይዋ የሚያሴሩት የሴራ እንቅስቃሴ ቀላል እንዳልሆነ የጠቆሙት ፖለቲከኛው፣ ግድቡ ብዙ ዛቻዎችን በማለፍ ለፍሬ መብቃቱ የሕዝቡ አንድነት ውጤት ነው ብለዋል። በመሆኑም ከሁሉም በላይ የውስጥ አንድነት ማጠናከር ተቀዳሚ ተግባር ማድረግ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል።

ከሁሉም በላይ ግን ሦስተኛ ዙር የውሃ ሙሌት በስኬት በመጠናቀቁ በግድቡ ላይ የሚታቀድ ማንኛውም ሴራ ከኢትዮጵያ ይልቅ የታችኛውን ተፋሰስ አገራት በእጅጉ ስለሚጎዳ ከዚህ በኋላ የግድቡ ደህንነት የጋራ ጉዳይ መሆኑ ትልቅ ድል መሆኑን ገልጸዋል።

እንደ አቶ ሌንጮ ማብራሪያ፣ ኢትዮጵያ በመልካ ምድር አቀማመጧ በቀይ ባህር አካባቢ ስለምትገኝ ጠላቶቿ ከግብጽና ከሱዳን በላይ ነው። የግድቡ ግንባታ ቢጠናቀቅ እንኳ የጠላቶች ሴራ አይቆምም። በእርግጥ ከዚህ በኋላ ለመኖር ሲሉ ለህዳሴ ግድብ ደህንነት የሚጨነቁ የታችኛው ተፋሰስ አገራት ናቸው። ሆኖም አቅጣጫ በመቀየር ሴራዎችን ከማድረግ ወደኋላ አይሉም። የሕዝቡ አንድነት ከተጠናከረ የጠላቶች ሴራ ከንቱ ሆኖ ይቀራል።

የጠላቶችን ትልም ለማምከን ብሎም ኢትዮጵያን የልማትና የዴሞክራሲ ተምሳሌት ለማድረግ ብቸኛው አማራጭ ዴሞክራሲያዊ የሆነ ሕብረ ብሔራዊ ፌዴራሊዝምን ማስፈን መሆኑን ያላቸውን እምነት የተናገሩት አቶ ሌንጮ፣ ለእሳቸው ሌሎች አማራጮች አገሪቱን ወደ ለየለት ቀውስ የሚያመሩ ናቸው። ያም ሆኖ ግን ጉዳዩ በጥቂት ግለሰቦች የሚወሰን ጉዳይ በመሆኑ የትኛው የመንግሥት አወቃቀር እንደሚያዋጣ ለሕዝብ ማቅረብ ያስፈልጋል ብለዋል።

ባለፉት 27 ዓመታት ዴሞክራሲያዊ ያልሆነው ሕብረብሔራዊ ፌዴራሊዝም አገሪቱ ዛሬ ለገባችበት ችግር አንዱና ዋነኛው ምክንያት ነው ያሉት አቶ ሌንጮ፣ ከዚህ አንጻር የበላይነትን ለምደው እኩልነት የማይጥማቸው አካላት መኖራቸው ግልጽ ነው ብለዋል። ሆኖም ብዙኃኑን የኢትዮጵያ ሕዝብ ፍላጎት ማገልገል ከተቻለ ቀሪውን በሂደት መቅረፍ እንደሚቻል አስገንዝበዋል።

__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here