
ጀማል ሰይድ
ቦርከና
በአሜሪካ የልማት ድርጅት የትራንስፎርም ፕራይመሪ ሄልዝ ኬር የተባለ ግብረ ሰናይ ድርጅት በአማራ ክልል በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው ጤና ተቋማት ከ79 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የሕክምና መሳሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ አደረገ።
የትራንስፎርም ፕራይመሪ ሄልዝ ኬር ኃላፊ እና የፓዝ ፋይንደር ኢንተርናሽናል ዳይሬክተር ዶ/ር መንግስቱ አስናቀ እንዳሉት፣ ድርጅታቸው በጦርነቱ ውድመትና ዝርፊያ ያጋጠማቸውን ጤና ተቋማት መልሶ ለማደራጀት ከ234 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የህክምና ቁሳቁስ ድጋፍ አድርጓል።
አሁን የተደረገው የ79 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር የህክምና መሳሪያዎችና የተለያዩ ቁሳቁስ ድጋፍ የክልሉ ጤና ቢሮን ፍላጎት መሰረት አድርጎ መቅረቡን ጠቁመው፣ይህም የእናቶችን እና ህጻናት ጤናን ለማሻሻል እንደሚያግዝ ተናግረዋል።
የጤና ሚኒስቴር አማካሪ ዶ/ር ማርታ ምንውየለት በበኩላቸው፣ ድርጅቱ በጦርነቱ ውድመትና ዝርፊያ ለደረሰባቸው ጤና ተቋማት ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
ጤና ሚኒስቴር ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት መልሶ ለማደራጀት የተጀመረውን ተግባር አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። የአማራ ክልል ጤና ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መልካሙ አብቴ፣ በጦርነቱ የወደሙና የተዘረፉ ጤና ተቋማት በመንግስትና በአጋር ድርጅቶች ርብርብ መልሶ በማደራጀት ስራ እንዲጀምሩ ተደርጎል። ድርጀቱ ጤና ተቋማት ያለባቸውን ችግር ለይቶ ያደረገው ድጋፍ ተቋማቱን መልሶ በማደራጀት ለሚደረገው ርብርብ ጠቀሜታው የጎላ ነው ያሉት ኃላፊው፣ ሌሎች አጋር ድርጅቶችም እገዛና ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቃቸውን ከጤና ሚኒስቴር የተገኘው መረጃ ያመላክታል።
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena