spot_img
Thursday, July 25, 2024
Homeአበይት ዜናየአዲስ አበባ መስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር ከተማዋን ከክልሉ ጋር በሚለዩ የአስተዳደር...

የአዲስ አበባ መስተዳደር እና የኦሮሚያ ክልል መስተዳደር ከተማዋን ከክልሉ ጋር በሚለዩ የአስተዳደር ወሰን ላይ ከስምምነት መድረሳቸው ተገለጸ

Ethiopian News  Amharic _ Addis Ababa  boundary

ጀማል ሰይድ
ቦርከና

የአዲስ አበባ መስተዳደር ኮሙኒኬሽን ቢሮ እናዳለው በአዲስ አበባ ስር የነበሩ አንዳንድ አካባቢዎች ወደ ኦሮሚያ ክልል እንዲካተቱ ሲወሰን፣ ሌሎች ደግሞ ከኦሮሚያ ወደ አዲስ አባባ እንዲካለሉ መደረጋቸውን አስታውቋል።

በዚህ የከተማው አስተዳደር ታሪካዊ ባለው ውሳኔ የኦሮሚያ ክልል በሚያስተዳድርበት እንዲሁም የአዲስ አበባ ከተማም ሲያስተዳሩ በቆዩባቸው ቦታዎች ላይ እንዲቀጥሉ ከስምምነት መደረሱን ገልጿል። ጨምሮም በኦሮሚያ ክልል የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን ውስጥ በመግባት በአዲስ አበባ አስተዳደር ተገንብተዋል የተባሉ ኮንዶሚኒየሞች ወደ ልዩ ዞኑ እንዲካተቱ፣ እንዲሁም አንዳንድ የልዩ ዞኑ አካባቢዎች ወደ አዲስ አበባ እንዲገቡ ተደርጓል ተብሏል።

በዚህም መሠረት ኮዬ ፈጨ፣ ቱሉ ዲምቱ በከፊል እና ጀሞ ቁጥር ሁለት የሚገኙባቸው አካባቢዎች ወደ ኦሮሚያ ክልል የፊንፊኔ ልዩ ዞን ሲካለሉ፣ ኦሮሚያ ክልል የገነባው የቆጣሪ ኮንዶሚኒየም ወይም ለቡ አካባቢ፣ ከፉሪ ሃና እና የኦሮሚያ ኮንዶሚኒየሞችን ጨምሮ እስከ ቀርሳ ወንዝ ያለውን አካባቢ ወደ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እንዲካለሉ ከስምምነት መደረሱ ተገልጿል።

ይህንን ውሳኔን በተመለከተ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲና አዳነች አበቤ ለዘመናት ሲንከባለል የነበረውን እና የሕዝብ ጥያቄ ሆኖ የቆየውን የአስተዳደር ወሰን ጉዳይ “በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት በትጋት እና በቁርጠኝነት፣ ከሕዝባችን ጋር ስንሰራበትና ስንመክርበት ቆይተን ዛሬ በጋራ መድረካችን በስኬት ማጠናቀቅ በመቻላችን ደስታችን ወደር የለውም” ብለዋል።

ይህ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በዙሪያዋ ባለው የኦሮሚያ ክልል የፊንፊኔ ዙሪያ ልዩ ዞን መካከል ያለው ጉዳይ ለሰባት ዓመታት በጋራ የቴክኒክ ኮሚቴ አማካይነት ሲታይ ቆይቷል ተብሏል።

ይህ በሁለቱ መስተዳደሮች መካከል የቆየው የአስተዳደራዊ ወሰን ጉዳይ፤ የአገሪቱ ሕገ መንግሥት እና የአዲስ አበባ ከተማ ቻርተር በሁለቱ አካላት አማካይነት ይፈታል ብሎ ባስቀመጠው መሠረት ከስምምነት ላይ እንደተረሰ ከንቲባዋ መናገራቸው ተዘግቧል። ከንቲባ አዳነች አቤቤ ጨምረውም ይህ ውሳኔ ተግባራዊ በሚሆንባቸው አካባቢዎች የትኛውም አይነት መንግሥታዊ አገልግሎት እንደማይቋረጥ፣ የተለያዩ የአገልግሎት እና የፀጥታ ሥራዎች በሁለቱም አስተዳደሮች እንደሚሰሩ አመልክተዋል።

ይህ በኦሮሚያ እና በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በኩል የአስተዳደር ወሰን የመለየት ከውሳኔ ላይ ሊደረስ መሆኑን ተከትሎ ተግባራዊ እንዲሆን ከሚያበረታቱት ባሻገር፣ ወቅቱ አይደለም በሚል ጥያቄ ያነሱም አካላት አሉ።

ከእነዚህም መካከል የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አንዱ ሲሆን፣ ፓርቲው በቅርቡ ጉዳዩን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ “መሬት ላይ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት የአስተዳደር ወሰን ማካለሉ ጠቃሚ መሆኑ ባይካድም፣ ውሳኔዎቹን ማስተግበር የሚቻለው ዜጎችን አሳትፎ የሂደቱ ባለቤት በማድረግ” ነው ብሎ ነበር። ጨምሮም ይህ ለረጅም ጊዜ በእንጥልጥል የቆየው የአስተዳደር ወሰን ጉዳይን ለመፍታት ሕዝቡና ባሳተፈ ሁኔታ መቋጫ እንዲያገኝ ከማድረግ ባሻገር የሚደረግ ሌላ ሙከራ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን በመግለጽ ሕዝቡ እንዲሳተፍ ጠይቆ ነበር።

በአዲስ አበባ ከተማ እና በዙሪያዋ ባሉ የኦሮሚያ ክልል ዞኖች መካከል ያለው የአስተዳደር ወሰን ጉዳይ ለበርካታ ዘመናት ሲያነጋግር የቆየ ሲሆን፣ በተለይ ከሰባት ዓመታት በፊት ኢህአዴግ ያስተዋወቀው ማስተር ፕላን በአገሪቱ ከባድ ቀውስ ማስከተሉ ይታወሳል። ማስተር ፕላኑ አዲስ አበባን እና የኦሮሚያ አካባቢዎችን በስፋት የሚያስተሳስር ነው የተባለ የነበረ ቢሆንም፣ በኦሮሚያ ውስጥ ከፍተኛ ሕዝባዊ ተቃውሞን ቀስቅሶ ተከትሎት ለመጣው ለውጥ አንድ ምክንያት ሆኖ ነበር።

ሕዝባዊ ተቃውሞውን ተከትሎ የወቅቱ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ለማ መገርሳ፤ ሕዝብ ያልፈቀው ዕቅድ ተፈጻሚ አይሆንም በማለት ምላሽ ከሰጡ በኋላ የማስተር ፕላኑ ዕቅድ ተፈጻሚ ሳይሆን ቀርቷል::

__
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here