
ጀማል ሰይድ
ቦርከና
መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተከሰተውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ እልባት ለመስጠት የተቋቋመው የሰላም አማራጭ ዐብይ ኮሚቴ የሰላም ውይይቱን አሰመልክቶ ተቀማጭነታቸው በአዲስ አበባ ላደረጉ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ማብራሪያ ሠጠ።
የዐብይ ኮሚቴው ሠብሳቢ ፤ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭጉዳይ ሚኒስትር አቶ ደመቀ መኮንን በሰጡት ማብራሪያ የፌዴራል መንግስት የተደራዳሪ ቡድን ከማሳወቅ ባለፈ የተለያዩ የሠላም ጥረቶች ማድረጉን ገልጸዋል። መንግስት የአገራዊ ምክክር እንዲደረግ ኮሚሽን ከማዋቀር አንስቶ የተለያዩ የሰላም ጥረቶችን ማከናወኑን ጠቅሰው፣ ለትግራይ የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲደርስ የበኩሉን ሚና እየተወጣ መሆኑን ተናግረዋል።
የፍትሕ ሚኒስትርና የሰላም አማራጭ ዐብይ ኮሚቴ አባል ዶክተር ጌዲዮን ጢሞቴዎስ በበኩላቸው በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ችግር ለመፍታት ስለሚከናወኑ የሰላም ጥረቶች ገለጻ አድርገዋል። የሰላም አማራጭ ዐብይ ኮሚቴ ባወጣው መግለጫ፤ የአፍሪካ ህብረት የሰላም ውይይቱ በአስቸኳይ እንዲጀመርና የሰላም ንግግሩ የሚካሄድበትን ቦታና ጊዜ በፍጠነት ወሰኖ ንግግሩ እንዲጀመር፣ ይህን ማድረግ ይቻል ዘንድ ከአፍሪካ ህብረት ጋር በቅርበት እየተሰራ እንደሆነ መገምገሙን አስታውቋል።
በመድረኩ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የደህንነት አማካሪ ሚኒስትርና የሰላም አማራጭ ዐብይ ኮሚቴ አባል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴንና ሌሎች የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች እንዲሁም የተለያዪ የዓለም አቀፍ የዲፕሎማቲክ ማህበረሰብ አባላት ተገኝተዋል።
_
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena