
ጀማል ሰይድ
ቦርከና
የሶማሌ ክልል መንግስት በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ ሙሁመድ ላይ ” የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው ” በሚል በማህበራዊ ሚዲያዎች የተሰራጨው መረጃ ሀሰተኛ ነው ብሏል፡፡ የክልሉ መንግስት ” በትላንትናው እለት በተለያዩ ሶሻል ሚዲያዎች በሶማሌ ክልል ርእሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፋ ሙሀመድ ላይ የግድያ ሙከራ ተደረገ ተብሎ የተሰራጨው ዜና ከእውነት የራቀ ሀሰተኛ ወሬ መሆኑን ለማሳወቅ እንወዳለን። ” ብሏል።
በትላንትናው ዕለት በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያዎች የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳደርን የሚመለከቱ መረጃዎች ሲሰራጩ ነበር። አንደኛው ይኸው ” የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው ” የሚለው ሲሆን የግድያ ሙከራ ተደረገባቸው የተባለው ለስራ ጉዳይ ” ቢኪ ” የሚባል ቦታ በሄዱበት ወቅት ነው።
ሌላኛው ደግሞ ፤ ርዕሰ መስተዳደር ሙስጠፌ ወደዚሁ ” ቢኪ ” የተባለ ስፍራ በሄዱበት ወቅት ወጣቱን ጨምሮ ፤ ህብረተሰቡ በመቆጣቱ ከፍተኛ ተቃውሞ እንደነበር ፤ ድንጋይም እስከመወርወር የደረሰ ክስተት እንደተፈጠረ የሚገልፅ መረጃ ተሰራጭቷል።
የክልሉ መንግስት ፤ በክልሉ ርዕሰ መስተዳደር ላይ ” የግድያ ሙከራ አልተደረገባቸውም ውሸት ነው ” የሚል መግለጫ ቢሰጥም በተመሳሳይ ሰዓት ስለተሰራጨው የ ” ቢኪ ” ከፍተኛ ተቃውሞ በተመለከተ እንዲሁም ርዕሰ መስተዳደሩ ወደ ተባለው ስፍራ አቅንተው እንደሆነ ፤ ሄደውስ ምን እንደተፈጠረ የገለፀው ነገር የለም ፤ ማስተባበያም አልሰጠም።
ዘግየት ብሎ ከሲቲ ዞን የቲክቫህ ቤተሰብ አባላት በደረሰን መልዕክት ትላንት ፕ/ት ሙስጠፌ ቢኪ ላይ ተቃውሞ ገጥሟቸው እንደነበር፤ የፀጥታ ኃይሎች ሁኔታውን እንደተቆጣጠሩ፣ የግድያ ሙከራ የተባለው ግን ትክክል እንዳልሆነ ገልፀዋል።
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena