spot_img
Tuesday, June 25, 2024
Homeዜናየፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈፀምኩም አለ

የፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች ላይ ጥቃት አልፈፀምኩም አለ

ፌደራሉ መንግሥት በትግራይ ኃይሎች

ጀማል ሰይድ
ቦርከና

የኢትዮጵያ ፌደራል መንግሥት ሠራዊት በትግራይ ኃይሎች ላይ በተለያዩ ግንባሮች ላይ ጥቃት ሰንዝሯል በሚል የቀረበበትን ክስ አስተባበለ።

የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት ቢልለኔ ስዩም ትናንት ሐሙስ ነሐሴ 12/2014 ዓ.ም. ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት በትግራይ ኃይሎች ላይ ተኩስ ከፍቷል መባሉ ሐሰት ነው ብለዋል።ቢልለኔ ይህን ያሉት የትግራይ ኃይሎች የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በተለያዩ ግንባሮች ጥቃት ፈጽሞብናል ካሉ በኋላ ነው።

የትግራይ ኃይሎች ረቡዕ ነሐሴ 11/2014 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ የፌደራል መንግሥቱ ጦር በምዕራብ ትግራይ በኩል በከባድ መሳሪያ የታገዘ ጥቃት ፈጽሟል ሲሉ ከከሰሱ በኋላ ነው። የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሰሜን ምዕራብ ትግራይ ደደቢት አካባቢ ባሉ የትግራይ ኃይሎች ላይ በከባድ መሳሪያ ለአንድ ሰዓት የቆየ ድብደባ አድርሷል ሲሉም ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል። በዚህም ለወራት ታውጆ የነበረው የሰብዓዊ እርዳታ የተኩስ አቁም አዋጅ ተጥሷል ብሏል ከትግራይ ወታደራዊ ዕዝ የወጣው መግለጫ።

ይህን መግለጫ ተከትሎ የጠቅላይ ሚንስትሩ ፕሬስ ሴክሬታሪያት በትግራይ ኃይሎች የተሰነዘረው ክስ ከሰላም ንግግር ለመሸሽ እንደ ምክንያት የቀረበ ነው ብለዋል።

የትግራይ ኃይሎች ጥቃት ተፈጽሞብናል ሲሉ መግለጫ ያወጡት በምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ደመቀ መኮንን የሚመራው የሰላም ኮሚቴ በትግራይ የተቋረጡ የመሠረተ ልማት እና መሠረታዊ አገልግሎቶችን ዳግም ለማስጀመር የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ በአጭር ጊዜ ውስጥ መድረስ ይገባል ባሉበት ዕለት ነው።

የተኩስ አቁም ስምምነት ላይ መድረስ ይቻልም ዘንድ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም ንግግሩን እንዲያስጀምር ኮሚቴው ጠይቋል።

የሰላም ውይይቱ የሚካሄድበትን ቦታ እና ጊዜ በፍጥነት ተወስኖ ንግግር እንዲጀመር ከአፍሪካ ኅብረት ጋር በቅርበት እየተሰራ መሆኑንም መገምገሙን ተገልጿል።ተሰነዘረ የተባለውን ጥቃት ተከትሎ የትግራይ ወታደራዊ ዕዝ የአጸፋ ምላሽ እንዳይሰጥ ትዕዛዝ መስጠቱን የጠቆመው መግለጫው “የሰብዓዊ እርዳታ የተኩስ አቁም ጥሰቱ የተፈጸመው በአካባቢው ባለው አዛዥ ጥፋት ወይንስ ሆን ተብሎ ከላይ የተፈጸመ መሆኑን በትዕግስት ሲመለከት ቆይቷል” ብሏል።

የአፍሪካ ኅብረትና መላው ዓለም አቀፉ ዲፕሎማሲያዊ ማኅበረሰብ ሁለት ዓመት ሊጠጋው ወራት የቀሩትን ደም አፋሳሽ ጦርነት በሰላም ለመቋጨት እያደረጉት ያለውን ጥረት ያስታወሰው መግለጫው የትግራይ አመራሮችም ለሰላም ቅድሚያ በመስጠት ምንም አይነት ወታደራዊ ግጭት እንዳይፈጠር ከፍተኛ ጥንቃቄ ሲያደርጉ ቆይተዋል ብሏል።

ከትግራይ ወታደራዊ ዕዝ የወጣው መግለጫ “በትናንትናው ዕለት የተፈጸመው ጥቃትን ጨምሮ የኢትዮጵያ መሪዎች ምዕራብ ትግራይን የትግራይ አካል እንዳይሆን የተቀናጀ ወታደራዊ እና የፖለቲካ ሴራ አጠናክረው ቀጥለዋል” የሚል ክስ አቅርቧል። መግለጫው ለሰላም ድርድር ቦታ እንዳለ ቢጠቅስም “ይህ ጥቃት ምዕራብ ትግራይን ነጻ ለማውጣት እና የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀያቸው ለመመለስ የኃይል አማራጭ እንድንወስድ ያስገድደናል” ሲልም ገልጿል።

በአማራ ክልል ዘንድ የይገባኛል ጥያቄ ያለበትና በአሁኑ ወቅት በአማራ ኃይሎች ቁጥጥር ስር ያለው ምዕራብ ትግራይ ለድርድር የሚቀርብ እንዳልሆነ የትግራይ ኃይሎች በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወሳል። መግለጫው አክሎም ለጦርነቱ እንደገና መጀመር ብቸኛው ተጠያቂ የኢትዮጵያ መንግሥት እንደሆነም ጠቁሟል።

ባለፈው ዓመት ጥቅምት መጨረሻ ላይ ትግራይ ውስጥ ተከስቶ ወደ አማራና አፋር ክልሎች የተዛመተው ደም አፋሳሽ ጦርነት ሺዎችን በመቅጠፍና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን በማፈናቀል መጠነ ሰፊ ሰብዓዊ ቀውስ አድርሷል። በሁለቱም ወገኖች በኩል የሰብዓዊ ተኩስ አቁም አዋጅ ስምምነት ላይ ከተደረሰ በኋላ ጦርነቱ ጋብ ቢልም በትግራይ ያለው የምግብና ነዳጅ ዕጥረት እንዲሁም ስልክ፣ ውሃ፣ መብራት፣ ባንክ የመሳሰሉ መሰረተ ልማቶች ተቋርጠው መቀጠላቸው ሕዝቡን ለፈተና እንዳረጉት የረድዔት ድርጅቶች ይገልጻሉ።

ሁለት ዓመት ሊሞላው የተቃረበውን የርስ በርስ ጦርነት በድርድር ለመቋጨት የአፍሪካ ኅብረት፣ አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና የተለያዩ አገራትና አለም አቀፍ ተቋማት ጥረት እያደረጉ መሆናቸው ይታወቃል። ሁለቱም ወገኖች ለድርድር ዝግጁ መሆናቸውና ተደራዳሪ ኮሚቴም አዋቅረናል ብለዋል።

__

በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here