
ፎዚያ አህመድ
ቦርከና
መንግሥት በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን እያከናወነ ያለውን የሰላም አማራጭ እንደምትደግፍ ሩስያ አስታወቀች።
የሩስያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ምክትል ዳይሬክተር ኢቫን ኒቺዬቭ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙርያ በሰጡት መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት ሰላምን በዘላቂነት ለማስፈን እያከናወነ የሚገኘውን የሰላም አማራጭ ሩስያ በብርቱ ትመለከተዋለች ብለዋል።
በተለይም መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል አስቀድሞ የወሰዳቸውን የተናጠል ተኩስ አቁም፣ የአስቸኳይ ግዜ አዋጅን ማንሳት፣ የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ማቋቋምና የሰብኣዊ ድጋፍ በተሻለ ሁኔታ እንዲዳረስ ያደረገውን ሰፊ እንቅስቃሴ ሩስያ በአበረታችነት ትወስደዋለች ነው ያሉት። በትግራይ ክልል ያለውን ሁኔታ በተመለከተ መንግስት የሚከተለውን የሰላም አማራጭና አካታች የመፍትሔ አቅጣጫ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ለዲፕሎማቲክ ማህበረሰቡ ማሳወቃቸውን ገልጸዋል።
ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን፣ ተጨባጭ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎች ለማድረግና ሰብኣዊ ድጋፉን ለማሳለጥ የሚያስችለውን የሰላም አማራጭ የሩስያ መንግስት እንደሚደግፈው አስታውቀዋል።
“ለአፍሪካዊ ችግር አፍሪካዊ መፍትሔ” በሚል በአፍሪካ ሕብረት በኩል የሚከናወነውን የሰላም አማራጭ የሩስያ መንግስት ይደግፈዋል ሲሉ ነው ያስታወቁት።
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena