
ጀማል ሰይድ
ቦርከና
ከኦሮሚያ ክልል ተፈናቅለው በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የተለያዩ አካባቢዎችና በደብረ ብርሃን ከተማ የሚገኙ በሺዎች የሚቆጠሩ ተፈናቃዮች ለከፋ ጉዳትና እንግልት እየተጋለጡ መሆናቸው በተለያዬ ጊዜ ሲገለፅ ቆይቷል። ተፈናቃዮቹ መንግስት በአግባቡ ርዳታ እያደረገልን አይደለም ሲሉም በተደጋጋሚ ቅሬታቸውን አቅርበዋል።
በተለያዩ መጠለያዎች የሚገኙት እነዚህ ተፈናቃዮች አሁን ካለባቸው ዘርፈ ብዙ ችግር ባሻገር፣ በአንድ ክፍል ውስጥ በተጨፋፈቀ መንገድ ለመኖር መገደዳቸው ለተለያዩ የጤና ችግሮች እንዲጋለጡ አድርጓቸዋል። ከሰሞኑም በደብረብርሃን ከተማ ወይንሸት ካምፕ ከሚገኙ ተፈናቃዮች 117 የሚሆኑት በምግብ መመረዝ መታመማቸው ተገልጿል።፡፡
የደብረ ብርሃን ከተማ ጤና መምሪያ ሃላፊ አቶ በቀለ ገብሬ በሰጡት መግለጫ እንደገለጹት ነሀሴ 15 ቀን 2014ዓ.ም በወይንሸት መጠለያ ካምፕ ውስጥ ከሚገኙ ተፈናቃዮች ውስጥ ለ3 መቶ ተፈናቃዮች የማዕድ ማጋራት ፕሮግራም መካሄዱን ገልጸው ከተመገቡት ውስጥ 117ቱ መታመማቸውን አስረድተዋል፡፡ ሓላፊው ችግሩ እንደተከሰተም የከተማው አመራሮች፣የጸጥታ መዋቅር አካላትና የጤና ባለሙያዎች ባደረጉት ርብርብ የታመሙትን ወገኖች በፍጥነት ደብረ ብርሃን ሪፈራል ሆስፒታል፣04 ጤና ጣቢያ፣አየር ጤና፣ እና ጠባሴ ጤና ጣቢያዎች በመውሰድ እንዲታከሙ ማድረግ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
በተደገው ጥረትና ርብርብ ታመው ከነበሩት ውስጥ 1 መቶ 16ቱ ወደ መጠለያ ጣቢያቸው መመለሳቸውን አረጋግጠው አንድ ሰው ግን አሁንም ህክምናውን እየተከታተለ እንደሚገኝ አመላክተዋል፡፡
ከምግቡ ጋር ተያይዞ ለተፈጠረው ችግር መንስዔው ምን እንደሆነ ለማወቅ ለደብረብርሃን ሪፈራል ሆስታል ናሙናው ተሰጥቶ በምርመራ ላይ እንደሚገኝ ያስረዱት አቶ በቀለ ውጤቱ እንደደረሳቸው ለህዝብ ይፋ እንደሚደረግ አሳውቀዋል፡፡ የችግሩን መንስዔ ውጤት እንደደረሰ ትክክለኛውን መራጃ በድጋሚ ይፋ እስከሚደረግ ድረስ ህብረተሰቡ በትዕግስት እንዲጠባበቅ ሲሉ የመምሲያ ሃላፊው ለደብረ ብርሃን ከተማ ኮሚኒኬሽን ተናግረዋል።
ተፈናቃዮቹ አሁን ያሉበት መጠነ ሰፊ ችግር እንዳለ ሆኖ የቀጣይ እጣፈንታቸው በውል አለመታወቁ ጉዳዩን አሳሳቢ ያደርገዋል።
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena