spot_img
Thursday, July 25, 2024
Homeአበይት ዜናአሸባሪው ህወሓት የጦርነት ትንኮሳ መጀመሩ ተገለፀ

አሸባሪው ህወሓት የጦርነት ትንኮሳ መጀመሩ ተገለፀ

ህወሓት

ጀማል ሰይድ
ቦርከና

አሸባሪው ህወሓት መንግሰትና የኢትዮጵያ ህዝብ የዘረጋውን የሰላም አማራጭ ወደ ኋላ ትቶ ዳግም ወደ ጦርነት ለመግባት ዛሬ ሌሊት በተለያዩ ግንባሮች ትንኮሳ ጀምሯል።አሸባሪው ቡድን ንጋት ላይ ጀምሮ በግዳን ስምዛ እኒ አካባቢውን እንዲሁም በመረዋና ማህጎ አቅጣጫም እስካሁን በንፁሃን ላይ ከባድ መሳሪያ መተኮሱ ተገልጿል። 

ቡድኑ በቆቦ የጀመረው የሀይል ሚዛን ለማዛባት አልሞ እንጅ ዋንኛ የጦርነት ፊቱን ወደ ወልቃይት እንደሚያደርግ ጥርጥር የለም። ስለሆነም መላው የኢትዮጵያ ህዝብ በጉዳዩ ላይ በትኩረት ተሳትፎ አሸባሪው ሀይል የጀመረውን የጦርነት ጉሰማ ሊከላከል እንደሚገባ የማህበራዊ ሚዲያ አንቂዎች መልእክት በማስተላለፍ ላይ ይገኛሉ።

የአሸባሪው ቡድን ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ “በትግራይ ደቡባዊ አቅጣጫ ወታደራዊ ጥቃት ተከፍቶብናል። በዚህም የአፀፋ እርምጃ ጀምረናል” ሲል ህወሓት ወደጦርነት መግባቱን በትዊተር ለአለም አቀፉ ማሕበረሰብ ይፋ አድርጓል። የትግራይ ኃይሎች በደቡባዊ ትግራይ አቅጣጫ በፌደራል መንግሥት እና በአማራ ኃይሎች ጥቃት ተከፍቶብናል አሉ። ራሱን የከትግራይ ሠራዊት ወታድራዊ ኮማንድ”  ብሎ ከሚጠራው ቡድን ተሰጠ በተባለው መግለጫ ዛሬ ረቡዕ፣ ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም. ንጋት 11 ሰዓት ላይ መጠነ ሰፊ ጥቃት ተከፍቶብናል ብሏል። የህወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ  በትዊተር ገፁ  “ከሳምንት ትንኮሳ በኋላ የአማራ ልዩ ኃይል፣ የአማራ ሚሊሻ እና የወሎ ፋኖ እንዲሁም [የመከላከያ] 6ኛ ኮማንድ ጥቃት ከፍተዋል” ብሏል።

በትግራይ ቴሌቪዥን በተነገረው የትግራይ ኃይሎች መግለጫ፤ የአማራ ሚሊሻ እና ፋኖ እና የአገር መከላከያ ሠራዊት ጥምር ኃይል በትግራይ ደቡብ አቅጣጫ መጠነ ሰፊ ጥቃት ጀምረዋል ብሏል። በመግለጫው የፌደራል እና የክልል ኃይሎች የጀመሩት ዘመቻ ዋነኛው ዓላማ “ከምዕራብ ትግራይ እና ምዕራብ ጎንደር ወደ አዲአቦ፣ አስገዲ እና ጸለምቲ እንደሆነ ግልጽ ነው” ብሏል።በመግለጫው ላይ የትግራይ ኃይሎች “ጥቃቱን ለመመከት” እና “ወደ ጸረ ማጥቃት ለመሸጋገር” ሙሉ አቋም ላይ እንገኛለን ብለዋል።

ህወሃት ጥቃቱ ተከፍቶብናል በሚል ጦርነት የጀመረባቸው አካባቢዎች ጮቢ በር፣ ጃኖራ እና ጉባጋላ በሁለቱ ክልሎች አዋሳኝ ድንበር ላይ ይገኛሉ። እነዚህ ሦስት ቦታዎች በትግራይ ክልል ራያ አላማጣ ወረዳ እና በአማራ ክልል ራያ ቆቦ ወረዳ ውስጥ የሚገኙ ናቸው። ጮቢ በር በአማራ ክልል ራያ ቆቦ ወረዳ ውስጥ፣ ከሰሜን የአገሪቱ ክፍል ወደ መሃል አገር በሚወስደው ኤ2 አውራ መንገድ ላይ ይገኛል።

ጃኖራ በተመሳሳይ በራያ ቆቦ ወረዳ ከጮቢ በር በምዕራብ አቅጣጫ ያለ ቀበሌ ነው። ጉባጋላ በተቃራኒው ከጮቢ በር በስተምስራቅ በትግራይ ራያ አላማጣ የሚገኝ ቀበሌ ነው። እነዚህ ሦስት ቀበሌዎች በትግራይ አላማጣ እንዲሁም በአማራ ቆቦ ከተሞች ይዋሰናሉ

ከዚሁ ጋር ተያይዞ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ አውጥቷል።

የትግራይ ህዝብ ችግሮችን ለመፍታት ሰላማዊ አማራጭ ዛሬም፤ ነገም ብቸኛዉ መፍትሄ ነዉ! መንግስት ተገዶ የገባበትን የሰሜኑን ጦርነት በሰላም ለመቋጨት ያስችላሉ ያላቸውን እርምጃዎች ሲወስድ መቆየቱ ይታወቃል። የሽብር ቡድኑ ህወሃት ከወረራቸው የአማራና የአፋር አብዛኞቹ አካባቢዎች ተገፍቶ እንዲወጣ ከተደረገ በኋላ መንግስት፤

• ሙሉ የሰራዊትና ሎጂስቲክስ አቅም እያለው ወደ ትግራይ ክልል ከመግባት መቆጠቡ

•  የተሳለጠና ያልተቋረጠ የሰብአዊ ድጋፍ ወደ ትግራይ ክልል እንዲገባ የተናጠል ተኩስ አቁም ማድረጉና ምቹ ሁኔታን መፍጠሩ

• ለሰላም በር ይከፍታል በሚል እስረኞችን መፍታቱ

• የሰላም አማራጭንም አሟጦ ለመጠቀም እንዲቻል የሰላም አማራጭ አብይ ኮሚቴን በይፋ ወደ ስራ አስገብቶ ግልጽ አቅጣጫንም ማስቀመጡ::

• አስፈላጊ የሆኑ መሰረታዊ ቁሳቁሶች ወደ ትግራይ እንዲጓጓዝ ማድረጉ::

• በአሸባሪዉ ቡድን የወደሙ አገልግሎት መስጫዎችን በመጠገን በሶስተኛ ወገን በኩል ስራ ለማስጀመር እንቅስቃሴ እያደረገ እንደሚገኝ ይታወቃል፡፡

ሆኖም አሸባሪው ቡድን ከውጪ ደጋፊዎቹ ጋር በመሆን ጦርነቱን የመቀጠል ከፍተኛ ፍላጎትን ሲያንጸባርቅ ቆይቷል፡፡ 

ከበባውን እንሰብራለን፣ መተማመኛችን ክንዳችን ነው፣ የትግራይ መሬቶች ተወረዋል፣ እናስለቅቃለን፣ ወዘተ በሚል ፉከራ ታጅበው ባለፉት ስድስት ወራት የተለያዩ ትንኮሳዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል። በምዕራብ በኩል በተደጋጋሚ ሞክረው ሽንፈትን እየተከናነቡ ተመልሰዋል።  በደቡብ ትግራይ በኩልም ተደጋገሚ ሙከራ ቢያደርጉም መንግስት ሙከራቸውን እያከሸፈ ዋናው መፍትሔ የሰላም መንገዱ ነው በሚል ጉዳዩ እንዳይባባስ አድርጓል።

ሆኖም ከመንግስት በኩል የቀረቡለትን በርካታ የሰላም አማራጮች ሁሉ ወደጎን በመተው የሽብር ቡድኑ ህወሃት ታጣቂ ቡድን ሰሞኑን ሲፈጽም የሰነበተዉን ትንኮሳ ገፍቶበት ዛሬ ንጋት ላይ በምስራቅ ግንባር በቢሶበር፣ በዞብል እና በተኩለሽ አቅጣጫዎች ከለሊቱ 11 ሰአት ጀምሮ ጥቃት ፈጽሟል። በወሰደዉ እርምጃም ተኩስ ማቆሙን በይፋ አፍርሷል፡፡ 

የፈጸመው ጥቃትም ሆነ እሱን ተከትሎ ያወጣው መግለጫ አሰቀድሞ ለትንኮሳው ሲዘጋጅ እንደነበር ግልጽ ማሳያ ነው። ጀግናው የመከላከያ ሰራዊታችንና መላው የጸጥታ ሃይላችን ከሽብር ቡድኑ የተሰነዘረውን ጥቃት በተቀናጀ መልኩ በድል እየመከቱት ይገኛሉ።

የዜጎችን ሰላምና ደህንነት ከአሸባሪው ቡድን ለመጠበቅም በወትሮ ዝግጁነት ሁሉም የጸጥታ ሃይላችን በተጠንቀቅ ቆሟል።

ጅራፍ ራሱ ገርፎ ራሱ ይጮሃል እንደሚባለው ቀድሞም በተካኑበት የሃሰት ፕሮፓጋንዳ ስራ ራሳቸዉ ተንኩሰዉ ራሳቸዉ እየጮሁ ይገኛሉ፡፡ ለሰላም እጁን የዘረጋዉን መንግስት በሃሰት በመወንጀል “ድርድሩ አስቀድሞ ከሽፏል” በሚል ለተለያዩ ወገኖች ጦርነቱ እንደማይቀር ሲያደርጉ የነበረዉን ቅስቀሳ በማጠናከር የትግራይን ወጣት ዳግም ሊማግዱት በይፋ አዉጀው ወደ ጦርነት እየተንደረደሩ ነዉ፡፡ 

ሰሞኑን አለም አቀፍ አጫፋሪዎቻቸው ካሸለቡበት ብቅ ብቅ ማለታቸውም የጦርነት ዝግጅቱን በፕሮፓጋንዳ ዘመቻ የማጀብ አካል መሆኑ ግልፅ ሆኗል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የትግራይን ወጣት ለማስጨረስ ሕወሓት የሚያደርገውን የጦርነት ጉሰማ እንዲያቆም ጠንካራ ግፊት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ 

በሃገር ውስጥም ሆነ በመላው አለም የምትገኙ ኢትዮጵያውያን ከዚህ የጥፋት ሃይል የሚሰነዘረውን ጥቃት ለመመከትና ኢትዮጵያን የመበተን ግልጽ አላማ የያዘውን ይህንን የሽብር ቡድን የጥፋት ሙከራ ለማምከን በጋራ እንድንቆም መንግስት ጥሪውን ያቀርባል። 

የሁሉም ኢትዮጵያውያን ጥያቄ መፍትሄ ማግኘት የሚችለው በሰላማዊ መንገድ ብቻ መሆኑን በመገንዘብ ዛሬም ነገም የሰላም አማራጭ የመጀመሪያ መፍትሔ እንደሆነ መንግሥት ፅኑ እምነት አለዉ፡፡ ሆኖም አሸባሪዉ የሕወሓት ቡድን በትንኮሳው ከገፋበት፤ መንግስት ሀገር የማዳን ሕጋዊ፣ ታሪካዊና ሞራላዊ ግዴታ ስላለበት እንዲሁም የሽብር ቡድኑ ወደደም ጠላም ወደ ሰላም አማራጭ እንዲመጣ ለማድረግ አስፈላጊውን እርምጃ ሁሉ ይወስዳል፡፡ ይህንን ለማስፈፀም ደግሞ መንግስትና መላው የፀጥታ ሃይላችን ከነሙሉ ብቃትና ቁመናቸዉ በተጠንቀቅ ላይ ናቸው። ሲል የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት መግለጫ አውጥቷል፡፡

_

በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here