
ፎዚያ አህመድ
ቦርከና
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ እቅዱን ይፋ ካደረገ ከሰአታት በኋላ ህዋሃት ጦርነት መክፈቱ ተሰምቷል፡፡
በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ባሳለፍነው ሰኔ ወር የመግባቢያ ሰነድ የተፈራረሙት የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰቦችና የኢትዮጵየ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤቶች አባላትና ተወካዮች በትናንትናው እለት የመጀመሪያ ውይይት አድርገዋል፡፡
በኢትዮጵዊያን መካከል ያለውን ስር የሰደደ ልዩነት በምክክር ለመፍታት የታቀደው ሀገራዊ የምክክር ሂደት እና በሂደቱ ሁለቱ አካላት ሊጫወቱት በሚችሉት ሚና ላይ ትኩረት በማድረግ ተወያይተዋል፡፡ የኢትዮጵያ ሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ዳይሬክተር አቶ ሄኖክ ከዚህ በፊት የሲቪል ማህበረሰቦች ድርጅት እና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተቀራርበው አይሰሩም ነበር ብለዋል፡፡ሁለቱ አካላት በጋር ለመስራት የተስማሙባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት በማድረግ ፍሬያማ የሆነ ስራ ለመስራት የውይይት መድረክ መዘጋጀቱ ተገልጿል፡፡በኢትዮጵያ የግጭት መነሻ የሆኑ ልዩነቶችን በመፍታት ሰላም እንዲሰፍን ይሰራል የተባለውን የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽንን ለማገዝ በሚችሉበት ሚና ላይ ከባለድርሸ አካላት ጋር መመካከራቸውን አቶ ሄኖክ ተናግረዋል፡፡
የሲቪል ማህበራት በተናጠልና ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር ደግሞ በጋራ በመሆን በሃገር የምክክር ሂደቱ የሚኖራቸውን ተሳትፎ በተመለከተ ከሃገራዊ ምክክሩ ኮሚሽነሮች ጋር ተደጋጋሚ ውይይት ማድረጋቸውን የገለፁት አቶ ሄኖክ የጋራ ማእቀፍ ለማዘጋጀት ስምምነት ላይ መደረሱን ገልጸዋል፡፡የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤትም ከሲቪል ማህበራትና ከሃገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ ጋር ተቀራርቦ እየሰራ መሆኑን ምክር ቤቱ ሰብሳቢ ዶ/ር ራሄል ባፌ ተናግረወላ፡፡ምክር ቤቱ በኮሚሽኑ አባላት ገለልተኝነት ላይ ጥያቄ እንዳለው አንስተው ይሄ ግን የሚረጋገጠው ወደ ስራ ገብተው በሚተገብሯቸው ጉዳዮች ነው ብለዋል፡፡ ሁላችንም የምንሰራው ለሀገራችን ነውና የሚፈጠሩ ግድፈቶችን እያሻሻልን በጋራ መስራት እንደሚቻል ገልጸዋል፡፡
ከሃገራዊ ምክክር ኮሚሽን አባላት መካከል አንዱ የሆኑት ዶ/ር ዮናስ አባዬ ኮሚሽኑ ስራውን በገለልተኝነት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ የፖለቲካ ፓርቲዎች እና የሲቪል ማህበራት ኮሚሽኑ ዋና ባለድርሻ አካላት መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ የሃገራዊ ምክክር ዋና አላማው ሰላምን በሰላማዊ መንገድ ማስፈንን ባህል ማድረግ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ሁሉንም አካባቢዎችና የህብረሰብ ክፍሎች ለማካተት በሚደረገው ጥረት ግጭት ያለባቸውን አካባቢዎችም ተደራሽ ለማድረግ እየሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡ በስራቸው ሂደት ከሃገር ውስጥም ሆነ ከውጭ ሃገር መንግስታት ማንም ጣልቃ እየገባ አለመሆኑን ተናግረዋል፡፡
ሃገራዊ ምክክሩ ለኢትዮጵያ አዲስ የፖለቲካ መሰረት እንደሚጥል ያላቸውን እምነት የገለፁት ዶ/ር ዮናስ የኮሚሽኑ አባላት ወደ ትግራይ የመጓዝ እቅድ እንዳለቸው ገልቀዋል፡፡ የሃገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ ስራ እንዲሳካ ሁሉም ኢትዮጵያዊ እንዲተባበርም ጠይቋል፡፡ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎቹን አጠናቆ የዝግጅት ምእራፍ ላይ የሚገኘው ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽኑ በዚህኛው ምዕራፍ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመወያየት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል፡፡
_
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ