
ጀማል ሰይድ
ቦርከና
ሁለቱ ዞኖችን ለመክፈል ያስፈለገው በሕዝብ ጥያቄ መሆኑም ተመልክቷል። ነዋሪዎቹ የዞኖቹ መከፈል መልካም አስተዳደርንና ልማትን ያመጣል ይላሉ።
በአማራ ክልልም ሁለት ዞኖች የእንከፈል ጥያቄ አቅርበው የክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት ጥያቄውን ተቀብሎ ዞኖቹ እያንዳንዳቸው ለሁለት እንዲከፈሉ መወሰኑን የክልሉ ምክር ቤት ዐስታውቋል። የክልሉ ምክትል አፈ ጉባኤ አቶ አማረ ሰጤ ዛሬ ለዶይቼ ቬለ (DW) አንዳመለከቱት በደቡብ ወሎ ዞን ስር ከነበሩ ወረዳዎች መካከል አብዛኛዎቹ አዲስ በሚደራጀው ዞን ውስጥ ተካትተዋል። ሰሜን ጎጃም በሚል ከነባሩ ምእራብ ጎጃም ተለይተው የተዋቀሩት ደግሞ 7 ወረዳዎችና 3 ከተማ አስተዳደሮች ናቸው ብለዋል።
ዶቼቬሌ ያነጋገራቸው የደቡብ ወሎ ነዋሪው አቶ እሸቱ አሊ ዞኑ እጅግ ሰፊ በመሆኑ ለአስተዳደር አስቸጋሪ ሆኖ በመቆየቱ በመከፈሉ «ደስተኛ ነኝ» ብለዋል።
«ሰሜን ጎጃም» በሚል ከተካተተው ዞን ውስጥ የይልማና ዴንሳ ነዋሪው አቶ ከፍ ያለው እንየው ከዚህ በፊት ወደ ምዕራብ ጎጃም ማዕከል ፍኖተ ሰላም ለመድረስ ከእርቀቱ አኳያ ከፍተኛ እንግልት ይደርስ እንደነበር አስታውሰው ዞኑ ለሁለት መከፈሉ ብዙ ችግሮችን ይፈታል ነው ያሉት፡፡ ፍትህ ፈላጊ አቅመ ደካሞች ከእርቀትና ከወጪ አኳያ ጉዳያቸውን ሳስፈፅሙ የቀሩ ብዙዎች እንደሆኑም አስተያት ሰጪው ጠቁመዋል።
የዞን ይከፈልልን ጥያቄ ይዘው ሲከራከሩ ከነበሩ ኮሚቴዎች መካከል በምዕራብ ጎጃም ዞን የዱር ቤቴ ከተማ አስተዳደር ነዋሪው አቶ ውበት ጥላሁን ለጥያቄያቸው ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ለዶቼ ቬሌ አስረድተዋል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ የዞኖቹን የእንከፈል ጥያቄ አወንታዊ ምላሽ የሰጠ ቢሆንም በቅርቡ ከርዕሰ መስተዳድሩ ጽ/ቤት የወጣ ደብዳቤ እንዳመለከተው በአዲስ የተደራጁ ዞኖች በ2015 ዓ.ም የዝግጅት ምዕራፍ እንዲሆንና በ2016 ዓ.ም ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ እንዲገቡ አሳስቧል።
ነባሩ ምዕራብ ጎጃም 14 ወረዳዎችና 8 ከተማ አስተዳደሮች፣ ደቡብ ወሎ ደግሞ 20 ወረዳዎችና 9 ከተማ አስተዳደሮችን ያቀፉ መሆናቸውን ከየዞኖቹ የመንግስት ጉዳዮች ኮሙዩኒኬሽን መምሪያዎች የተገኘው መረጃ ያሳያል።
_
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ