
ጀማል ሰይድ
ቦርከና
የአሸባሪው ህወሓት ታጣቂዎች መቀሌ ከሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን ውስጥ 570 ሺ ሊትር ነዳጅ ዘረፈኝ ሲል የተባበሩት መንግሥታቱ ድርጅት አስታወቀ።
የድርጅቱ ዋና ጸሀፊ አንቶኒዮ ጉተሬስ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክ በሰጡት መግለጫ፤ ታጣቂዎቹ የፈጸሙትን ዝርፊያ በቦታው የነበሩ የመንግስታቱ ድርጅት እርዳታ ሰጪዎች ለማስቆም ቢሞክሩም አልተቻላቸውም ብለዋል፡፡
ድርጅቱ የተዘረፈው ነዳጅ የርዳታ ምግብ፣ የአፈር ማዳበሪያ እና ሌሎች የሰብአዊ እርዳታ ቁሳቁሶችን ለማጓጓዝ የሚውል እንደነበረም ዱጃሪክ ገልጸዋል፡፡
የሽብር ቡድኑ ነዳጁን በመዝረፉ ምክንያት የሰብአዊ ድጋፉ ሥራ እንደሚያስተጓጉለውም ነው የገለጹት።ድርጅቱ የህወሓትን ዝርፊያ አጥብቆ እንደሚያወግዘውም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል። አሜሪካም ህወሓት በመቀሌ የተመድ መጋዘን ላይ የፈፀመው ዝርፊያ እንዳሳሰባት ገልጻለች፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የአፍሪካ ቢሮ ባወጣው መግለጫ፥ ታጣቂ ቡድኑ ትናንት ጠዋት ላይ መቀሌ ወደሚገኘው የድርጅቱ መጋዘን በሀይል በመግባት 12 የነዳጅ ቦቴዎችን በአጠቃላይ 570 ሺህ ሊትር ነዳጅ መዝረፉ ዋሽንግተንን እንዳሳሰባት ጠቁሟል። የነዳጅ ምርቱ የሰብዓዊ እርዳታ ለሚሹ ዜጎች የነብስ አድን ቁሳቁሶች ለማቅረብ አስፈላጊ መሆኑን ነው መግለጫው የጠቆመው።
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ