
ጀማል ሰይድ
ቦርከና
አዲስ አበባ፡- አሸባሪው ሕወሓት ለህዝብ የመጣውን እርዳታ ለታጣቂዎቹ እያዋለ በትግራይ ህዝብ ጉሮሮ ላይ ቆሞ የራሱን ስልጣን የሚያደላድል ቡድን መሆኑ ተገለጸ:: ቡድኑ በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እየደረሰበት ያለው ውግዘት አጋዡ የነበረው ሀይል እየሸሸው መሆኑን ያሳያል::
በቀድሞ መንግስት የፓርቲ ኮሚቴ ሥራ አስፈጸሚ አባልና ደራሲ የሆኑት አቶ ገስጥ ተጫኔ በኢትዮጵያ ወቅታዊ ሁኔታ ዙሪያ ለኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት እንዳስታወቁት፤ አሸባሪው የሕወሓት ቡድን ሲመሰረት ጀምሮ ለራሱ እንጂ ለህዝቡ አስቦ አያወቅም፤ ለህዝብ የመጣውን እርዳታ እያከማቸና እየሸጠ ለታጣቂዎቹ ቀለብ እያዋለ ሲዋጋ ነው የቆየው:: በህዝቡ ጉሮሮ ላይ ቆሞ የራሱን ስልጣን የሚያደላድል ነው::
አሸባሪው ሕወሓት ከመነሻው ጀምሮ በዘረፋ የተመሠረተ ቡድን ነው ያሉት አቶ ገስጥ፤ በሥልጣን ላይም እያለ እንዲሁ የኢትዮጵያን ህዝብ ካዝና ሲያራቁት የኖረ፤ ጦርነቱ ከተጀመረ በኋላም የዓለም ምግብ ፕሮግራምንም ሆነ በኢትዮጵያ መንግስት ተፈቅደው የገቡ የእርዳታ ድርጅቶችን መጋዘኖች ሲዘርፍ የቆየ፤ ጦርነቱ ወደ መሀል እየገፋ በመጣ ጊዜም ኮምቦልቻ የሚገኘውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን ከፍቶ የዘረፈ፤ ከዚህም በላይ ለእርዳታ የገቡ ተሽከርካሪዎችን ወስዶ ለጦርነቱ የሚያውል መሆኑን ገልጸዋል::
በደረሰበት ቦታ ሁሉ ህዝብን እየዘረፈ ነው የመጣው፤ ይህን ድርጊቱን በውጭው ማህበረሰብ በተለይም በእርዳታ ሰጪ ድርጅቶችና መሰል ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚያውቁት ቢሆንም አይተው እንዳላየ እያለፉት እንደነበር ጠቅሰዋል:: መጠነኛ ፍንጭ ከመስጠት ውጪ ሲያወግዙት አይስተዋልም ብለዋል:: ይህ ሁሉ ሳይበቃው አሁንም ለእርዳታ ማከፋፈያ ይውል የነበረ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም 570ሺህ ሊትር ነዳጅ በይፋ መዝረፉን ጠቅሰዋል:: መሰል የቡድኑ ተግባራት ለህዝብ የመጣውን እርዳታ ለታጣቂዎቹ እያዋለ በህዝቡ ጉሮሮ ላይ ቆሞ የራሱን ስልጣን ሲያደላድል የቆየ መሆኑን ማሳያ እንደሆነ ተናግረዋል::
በ1977ዓ.ም የድርቅ ወቅት እንኳን ለእርዳታ የመጣውን እህል እርዳታ ሸጦ መሳሪያ ገዝቶ እንደነበር አቶ ገስጥ አስታውሰው፤ የሽብር ቡድኑ በውጊያ አገኘኋቸው፣ ነጻ አወጣኋቸው ባላቸው መሬቶች ሁሉ ያገኛቸውን የመንግስት ንብረት፣ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት፣ ትምህርት ቤትና ህክምና ተቋማትን ጭምር በመዝረፍ ሸጦ ለተወሰኑ መሪዎቹ ሀብት ሲያከማች እንደኖረ ጠቅሰዋል:: የአሁኑ የነዳጅ የዘረፋ ወንጀል የወያኔን ባህሪ ለውጭው ዓለም ግልጽ አድርጎ የሚያሳይ እንደሆነም ጠቁመዋል::
አቶ ገስጥ እንዳሉት፤ አሸባሪው ሕወሓት ከተፈጠረ ጊዜ ጀምሮ የትግራይ ህዝብ አበሳውን ሲያይ የኖረ ነው:: ባለፉት ሁለት ዓመታትም የበለጠ መከራ እያየ ነው:: ይህንን ሁሉ ያደረሰበት የሽብር ቡድኑ ነው:: ምግቡን በራሱ መጋዘን፣ እንዲሁም ማከፋፈያ የሆነውን ነዳጅ ለውጊያ መውሰዱን በውል በመገንዘብ ህዝቡ ቡድኑን ለማስወገድ መነሳት ይኖርበታል::
የኢትዮጵያ መንግስት ለሠላማዊ ድርድር ዝግጁ መሆኑን አቋሙን አሳውቋል ያሉት አቶ ገስጥ፤ ወያኔ ግን ለዚህ ድርድር ፍላጎት የሌለው መሆኑን በተዘዋዋሪ መንገድ ማሳየቱን፤ ቡድኑ በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌላቸውን ነገሮች ሁሉ በቅድመ ሁኔታ ሲያስቀምጣቸው ለድርድሩ ዝግጁ እንዳልሆነ ማሳያ ነው ብለዋል::
ከድርድሩ ይልቅ ለጦርነቱ ዝግጁ መሆኑን በሚያሳይ ሁኔታ አመላክች ተግባራትን ሲያሳይ መቆየቱን በመግለጽ፤ በፊት በነበረው የ17ቱ ዓመት ጦርነት ጊዜ የድርድር ሁኔታዎች በተለያየ ሁኔታ ሳይሳኩ እንደቀሩና ቡድኑ በባህሪው የመደራደር ፍላጎት የሌለው ከመሆኑ የተነሳ ለድርድር የጠራቸውን ሁሉ እያጠፋ የመጣ እንደሆነ አክለው ጠቅሰዋል::
የትግራይ ፖለቲከኞች በተለይም ሠላም ባለባቸው የአገሪቱ ከተሞች የሚኖሩ ትግራዊያን ህዝቡን አግባብተው በቡድኑ ላይ አመጽ ማነሳሳት እንዳለባቸውም መክረዋል::
የሚያወግዙት አካላት በቅን ልቦና እየተናገሩ ከሆነ ወያኔ አጋዡ የነበረው ሀይል እየሸሸው መሆኑን ያሳያል በማለት፤ ቡድኑ ጫና እንዲፈጠርበትም መንግስት መሥራት እንዳለበትና ከሚያግዙት ሀይሎች እንዲገለለ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ እንደሚገባ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ