spot_img
Thursday, July 25, 2024
Homeዜናለጥቂት ሰዎች የሥልጣን ጥማት ተብሎ የትግራይ ወጣቶች መማገዳቸው ልብ የሚሰብር ነው” አቶ...

ለጥቂት ሰዎች የሥልጣን ጥማት ተብሎ የትግራይ ወጣቶች መማገዳቸው ልብ የሚሰብር ነው” አቶ በትሩ ገብረ እግዚአብሔር የዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ዋና ሥራ አስፈጻሚ

 አቶ  በትሩ ገብረ እግዚአብሔር _ የትግራይ ወጣቶች _ Ethiopian News
አቶ በትሩ ገብረ እግዚአብሔር

ጀማል ሰይድ
ቦርከና

በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል በተከሰተው ጦርነት ለጥቂት ሰዎች የሥልጣን ጥማት ተብሎ የትግራይ ወጣቶች በሚያሳዝን ሁኔታ መማገዳቸው ልብ የሚሰብር ነው ሲሉ የዓለምአቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ በትሩ ገብረእግዚአብሄር ተናገሩ።

አቶ በትሩ ከኢ.ፕ.ድ ጋር በነበራቸው ቆይታ እንደገለጹት፤ ጦርነት ለማንም የማይጠቅም አውዳሚ በመሆኑ ከመጀመሩ በፊት መከላከል ተገቢ ነው፡፡ በሀገራችን ነባራዊ ሁኔታም በሰሜን እየደረሰ ባለው ጥፋት መንግስት በሰፊው እጁን ለሰላም የዘረጋ ቢሆንም በጽንፈኞቹ በኩል የተሰጠው ምላሽ ግን አገም-ጠቀም የሆነ እና አንድ እርምጃ ወደፊት ሁለት እርምጃ ወደኋላ የመሄድ አዝማሚያ የያዘ በመሆኑ በጣም አሳሳቢ ነው ብለዋል።

ከሁሉም በላይ ከፍተኛ ጉዳት የደረሰበት የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያውያን ወገኖቹ ጋር በመሆን አሰቃቂ ሰብአዊ ጥፋት የሚያደርሰውን ቡድን ከትከሻው ላይ እንደሚያወርድ ተስፋ እናደርጋለን ሲሉም ተናግረዋል።

አሁንም ቢሆን መንግስት ለሰላም ቁርጠኝነት ያለው በመሆኑ የሕወሓት ኃይሎች የተዘረጋውን የሰላም እጅ በመቀበል ሰላም እንዲፈጠር መስራት ይገባቸዋል ያሉት አቶ በትሩ፤ ለሁሉም መፍትሔው መወያየት እና ሰላም ስለሆነ በአገር አቀፍ ደረጃ ኢትዮጵያን እና ኢትዮጵያዊነትን ለማዳን በሚደረገው እንቅስቃሴ ላይ ሁላችንም አስተዋጽኦ ማድረግ ይገባናል ሲሉ አጸንኦት ሰጥተዋል።

የኢትዮጵያ ችግር የፖለቲካ መሪዎች ወይም አብዛኛው ሰው እንደሚለው የማንነት ችግር ሳይሆን በአብላጫው የድህነት ችግር ነው ሲሉም አክለዋል፡፡ ድህነትን ለመቅረፍ ሰው እራሱን እንዲረዳ እራሱን እንዲችልና ተግቶ እንዲሰራ ከስነልቦናው ጀምሮ ክህሎት እስከማላበስ ድረስ የተለያዩ ጥረቶች ቢደረጉም ችግሩ ሰፊ በመሆኑ እስካሁን ድረስ ከዚህ ችግር አልተላቀቅንም፤ ስለዚህ መሰረታዊ ችግር የሆነውን ድህነት ለመቅረፍ በቂ ትኩረት ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡

አብዛኛውን ጊዜ በአገራችን ላይ የሚቃጡ የውጭ ጥቃቶች የሚደርሱት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ቢሆንም የትግራይ ህዝብ በኢትዮጵያዊነቱ ጠንካራ የሆነ እና ለዘመናት አገሩን ከጥቃት ሲከላከል የኖረ ህዝብ ነው ያሉት አቶ በትሩ፤ ይህ ህዝብ ታፍኖ አደገኛ ተልዕኮ ለሆነው ቡድን መሳሪያ እንዲሆን በመገደዱ እናዝናለን ብለዋል። አቶ በትሩ ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ድርጅት ወደፊት በሚያደርገው ድጋፍ እና ትብብር ተሳትፎም የትግራይ ህዝብ ጭምር በቅድሚያ ትኩረት ተሰጥቶት የሚረዳ መሆኑን አመላክተዋል። እስካሁንም በአማራ እና በአፋር ክልሎች በጦርነቱ የተጎዱትን መደገፍ ቢቻልም በትግራይ ክልል ግን ጽንፈኞቹ ህዝቡን በማፈናቸው ለመደገፍ አለመቻሉን ገልጸዋል።

የትግራይ ህዝብ ሰላም አግኝቶ ስራውን እየሰራ፣ ነጋዴውም ነግዶ፣ ገበሬውም አርሶ የደረሰውን ሰቆቃ መጠገን በሚቻልበት ደረጃ እርዳታ እንዲደረግ ለማስተባበር ብዙ ጥረት የሚደረግ መሆኑንም አመልክተዋል። የማህበረሰባችን ግንዛቤ በሌላው አካባቢ የሚደርሰው ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ እንደሆነው ሁሉ የትግራይ ጉዳይ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጉዳይ መሆኑን ካልተረዳ ችግራችን እየሰፋ የሚመጣ መሆኑን የጠቆሙት አቶ በትሩ፤ ሁሉም ኢትዮጵያዊም ለሀገሩ አንድነት እና ነጻነት ዘብ እንዲቆም ጥሪ አቅርበዋል። ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ድርጅት ባለፉት ጊዜያት በተለያዩ ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና እና ትውልደ ኢትዮጵያውያንን ሲደግፍ መቆየቱን አስታውሰዋል።

ማንኛውም ኢትዮጵያዊ በዓለም ደረጃ በየትም ሀገር ይኑር ሰብአዊ መብቱ ሊከበርለት እንደሚገባ ጠቁመው፤ ይሄንን ለማድረግም በመጀመሪያ ደረጃ አገር የምትፈልግበትን ግዴታ እያሟላ፤ ለመብቱ ዘብ የሚቆም ዜጋ ማፍራት ላይ የማህበረሰቡን ንቃተ-ህሊና ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን አመላክተዋል። የሰብኣዊ መብት ጥሰት እንዳይከሰት አንድ ችግር አቅጣጫ በሚያሳይበት ጊዜ ጥናቶች እና ውይይቶች እንዲደረጉ፤ ያ ደግሞ ለህዝብ እንዲገለጽ ለማድረግ ሙከራ እናደርጋለን። አንድ ጥሰት ከደረሰ በኋላም ተጎጂው ቶሎ ከወደቀበት እንዲነሳ ድጋፍ መስጠት ላይ እናተኩራለን። ይሄንንም በዓለም አቀፍ ደረጃ እየሰራን ነው ብለዋል። በመሆኑም በሳውዲ አረቢያ፣ በሊባኖስ፣ በሊቢያ እና ሌሎችም ሀገሮች ለሚገኙ ኢትዮጵያውያን የሰብአዊ እርዳታ አድርገናል ብለዋል። ዓለም አቀፍ ትብብር ለኢትዮጵያውያን መብት ድርጅት በኢትዮጵያ እስካሁን ቅርንጫፍ ባይኖረውም አሁን ግን መጠነኛ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት በማቋቋም ቀጣይነት ያለው ድጋፍ እና አገልግሎት ለመስጠት መወሰኑንም ጠቁመዋል::

__

በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here