spot_img
Wednesday, October 4, 2023
Homeነፃ አስተያየትወያኔ በዐማራ እና በአፋር ሕዝብ ላይ እንዲያካሂድ የተደረገውን አዲስ ዙር የጭፍጨፋ ሴራ በሚመለከት...

ወያኔ በዐማራ እና በአፋር ሕዝብ ላይ እንዲያካሂድ የተደረገውን አዲስ ዙር የጭፍጨፋ ሴራ በሚመለከት የተሰጠ መግለጫ

advertisement

ወያኔ በዐማራ እና በአፋር ሕዝብ ላይ እንዲያካሂድ የተደረገውን አዲስ ዙር የጭፍጨፋ ሴራ በሚመለከት  የተሰጠ መግለጫ፤August 30, 2022 ዋሽንግተን ዲ.ሲ. – Washington D.C. 

ነሐሴ 23 ቀን 2014፥ ዋሽንግተን ዲ.ሲ.  

ሰሞኑን በወያኔ ተንኳሽነት እና በጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥት ሴራ በተሞላው ቸልተኝነት በዐማራ እና በአፋር ሕዝብ ላይ የተከፈተውን አዲስ ዙር ጥቃት፣ አጥብቀን እያወገዝን፤ ሰላም-ወዳዱ የኢትዮጵያ ሕዝብ እና መላው የዓለም ኅብረተሰብ ለሁኔታው ተገቢ ትኩረት ሰጥተው ለተደጋጋሚ ጥቃት ሰለባ የሆነውን ወገን እንዲታደጉ እንጠይቃለን። 

በአለፉት ሁለት ዓመታት እንደታየው፣ የጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አህመድ መንግሥት ዋና ዓላማ የወያኔን በጭካኔ  የተሞላ ወረራ በጦር ሜዳ ድል አድርጎ የአገርን ሉዐላዊነት ማስከበር እና የሕዝብን ቀጣይ ሰቆቃ ማስቆም ሳይሆን፣  ይህ አዲስ ዙር ጥቃትም የዐማራውን ክፍል አዳክሞ፣ በኦሮሞ ፖለቲከኞች የሚቀነቀነውን እና በገሃድ እየተፈጸመ  ያለውን የኦሮሞ የበላይነት ሕልም እውን ማድረግ መሆኑ በተግባር የተረጋገጠ ሃቅ ነው።  

ለሃያ-ሰባት ዓመታት የኢትዮጵያን ሕዝብ፣ በተለይም የዐማራውን ወገን፣ በጭቆና ሲያሰቃይ ቆይቶ፣ በሕዝብ መራር ትግል ከሥልጣን የተወገደው፣ በሕዝብ ተወካዮች ምክር-ቤትም ሽብርተኛ ተብሎ በይፋ የተፈረጀው እና በአንድ ወቅት ዱቄት ሆኗል የተባለው ሕወሓት፣ በዐቢይ አህመድ መንግሥት እንዲያንሰራራ ተደርጎ፣ በዐማራ እና  በአፋር ክልሎች ላይ ትውልድ የማይረሳው ጭፍጨፋ፣ ዝርፊያ እና ዘግናኝ ወንጀሎችን ፈጽሟል።  

ወያኔ ከማዕከላዊ የመንግሥት ሥልጣን ከተወገደ ጀምሮ ለአጠቃላይ ጦርነት ያደርግ ለነበረው ዝግጅት የሚገባውን ትኩረት ባለመስጠት ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ/ም በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ጦር ላይ የተደረገው  አስቃቂ የአገር ክህደት ወንጀል እስከሚፈጸም የታየው ቸልተኝነት፣ በተወሰደው ሕዝብ የደገፈው የአጸፋ እርምጃ 

በብዙ መስዋዕትነት የተገኘውን ድል ብላሽ ያስቀረው እና ምንም ዓይነት ወታደራዊም ሆነ ፖለቲካዊ አሳማኝ ምክንያት በሌለው ሁኔታ በድንገት ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ/ም ትግራይን ለወያኔ በመተወ ጦሩን ጠቅልሎ ከትግራይ ማስወጣት እና ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ቁልፍ ቦታዎች በመተው ይህ ዱብዳ ይሆናል ብሎ ያልጠበቀው፣ ቅድመ-ዝግጅት እንኳ እንዲያደርግ ዕድል ያላገኘው እና አንዳችም ማስጠንቀቂያ ያልተሰጠው የአፋር እና የዐማራ ሕዝብ ለአሰቃቂ ወረራ እንዲጋለጥ መደረጉ፣ ወረራውን ለመቋቋም በታየው የመንግሥት አሳፋሪ መዝረክረክ የተደፋፈረው ወራሪ ኃይል ወደ አዲስ አበባ መገስገሱ ያሰጋው ብልጽግና ያቀረበውን የድረሱልኝ ጥሪ ሕዝብ ተቀብሎ በተደረገው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ በታኅሣሥ 2014 ዓ.ም. ለማፈግፈግ የተገደደውን ትሕነግ ከገባበት እንዳይወጣ፣ ቢያንስ ዳግም ስጋት እንዳይሆን ማድረግ ሲገባ፣ እንደ ድል-አድራጊ ከነከባድ መሣሪያው እንዲመለስ፣ አልፎም በወረራ ከያዛቸው ቦታዎች ጠቅልሎ እንዲወጣ አለመደረጉ፣ ሳያንስ ጦርነትን የድርጅታዊ ኅልውና ማስቀጠያ አድርጎ የሚያይ እና ካለ-ጦርነት መኖር የሚችል የማይመስለው ይህ የሽብር ቡድን የሚያደርገውን ሁሉን-አቀፍ ዝግጅት ችላ በማለት የዐቢይ አህመድ የብልጽግና መንግሥት ሕዝብን ለዚህ አዲስ ዙር ወረራ፣ አገርንም ለቀጣይ ሰቆቃ ዳርጓል። 

በሕዝብ እና በአገር ላይ ለደረሰ ይህ ሁሉ ችግር የብልጽግና መንግሥት ኃላፊነት የመውሰድም ሆነ አንዳችም የተጠያቂነት መንፈስ የማይታይበት መሆኑ ታይቷል። አገራችንን እና ሕዝባችንን ለከባድ አደጋ የዳረጉ እነዚህ ችግሮች የደረሱት ግን አንዳንዶች እንደሚሉት ከመንግሥት አቅም ማጣት፣ አለፍ ሲልም በአዘቦታዊ ቸልተኝነት ወይም በተራ ግድፈት የተፈጸመ ድክመት ሣይሆን መሰሪ ሴራ የተጠናወተው እኩይ ተግባር ከመሆን ለይቶ ማየት ጤናማም፣ አሳማኝም አይሆንም። 

ያለፉት አራት ዓመታት በአጠቃላይ፣ በተለይ ግን ያለፉት ሁለት ዓመታት በሕዝብ እና በአገር ላይ ከደረሱት ከባድ ችግሮች አኳያ ለዐቢይ አህመድ እና ለሚመራው አስተዳደር ከሥልጣን መገለል በቂ ምክንያት መሆን  ሲገባ፤ አልፎ-ተርፎ የኦነግን የፖለቲካ መርኃ-ግብር በተራቀቀ ሁኔታ በሥራ ለመተርጎም የሚያግዝ ጠቃሚ  መሣሪያ ሆኖ ተገኝቷል።

ከዚያም አልፎ፣ የዐቢይ አህመድ መንግሥት፣ ለዐማራና ለኢትዮጵያ ነፃነት ደጀን የሆኑትን የፋኖ አርበኞች፣  የሚዲያ አባላትን፣ የሰብዓዊ መብት ታጋዮችን እና የተረኛነት ዓላማን ለማራመድ እንቅፋት ይሆናሉ ብሎ  የገመታቸውን ግለ-ሰቦች እና ቡድኖች፣ በእስራት እና በማዋከብ ሲያሰቃይ ቆይቷል::  

የዐማራ ተወላጆች በኦሮሞ ክልል እና በሰሜን ሸዋ በግፍ እንዲገደሉ እና ከፍጅት የተረፉትም በዱር በገደል ተሰደው በአሳዛኝ ችግር እና በሕይወት የመኖር ዋስትና እንዲነፈጉ ተደርጓል። የዐማራ ክፍል ነዋሪዎች እየተመረጡ  ወደ አዲስ አበባ ከተማ እንዳይገቡ በየጊዜው እየታገዱ ይገኛሉ። የአዲስ አባባ ከተማም ዕድል በነዋሪዎች ድምጽ  ሳይሆን፣ በኦሮሞነታቸው ተመርጠው በተሾሙ የከተማው አስተዳዳሪዎች እና በኦሮሞ ክልል መሪዎች ፍላጎት ብቻ  እየተወሰነ ይገኛል።  

ስለዚህ፣ ዛሬ በወያኔ የተለኮሰው ተከታታይ ጦርነት፣ የዐማራውን ኅልዉና ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ  ለማጨለም፣ የጥፋት መንትዮች በሆኑት በሕወሓት እና ኦሮሙማ መሪዎች የታቀደ መሆኑን የዐማራው እና ሌላው  ሰላም-ወዳድ የኢትዮጵያ ክፍል ተረድቶ፣ ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን የትግል መስመሮች በጥልቀት እንዲያጤን በጥብቅ እናሳስባለን፤ 

1. የአገርን አንድነት እና ሉዐላዊነት ማስከበር የፌደራል መከላከያ ኃይል ኃላፊነት እና ተልዕኮ ስለሆነ፣ ኃይሉ የዘር  እና የፖለቲካ ወገናዊነት ሳያሳይ የተጣለበትን አገራዊ እና ሕዝባዊ ግዴታውን በብቃት መወጣት በሚያስችለው መልክ በግንባር ቀደምነት እንዲዋጋ ግፊት ማድረግ እና የሚቻለዉን ድጋፍ ሁሉ መስጠት፤ 

በዚህ ረገድ ለአገር መከላከያ ሠራዊታችን የምናሳስበው ትሕነግ በሰሜን-ዕዝ ጦር ላይ የፈጸመውን አረመኔኣዊ የአገር ክህደት ወንጀል ተከትሎ በከፍተኛ መስዋዕትነት ያስመዘገበው እጅግ የሚያኮራ ድል የተጠበቀውን ግብ ሳያስጨብጥ ትሕነግ ማንሰራራት ብቻ ሳይሆን ለአገር ዳግም ስጋት እንዲሆን እና ሕዝብ ሠላሙን አጥቶ እጅግ ለከፋ አደጋ እንዲጋለጥ መደረጉ ሁላችንንም የሚያሳስብ መሆኑ ግልጽ ቢሆንም፣ አይከፍሉ መስዋዕትነት ለምትከፍሉት የሠራዊታችን አባላት ግን የበለጠ እንደሚሰማችሁ እና እንደምትረዱት እናምናለን። የማንኛውም ግዳጅ ውጤት ግን የሚከፈለውን መስዋዕትነት ሊመጥን ይገባል። 

ትሕነግ አሁን የለኮሰውን ጦርነት ለመቀልበስ በምታደርጉት ትግል፣ የአገር እና የሕዝብ ዕጣ-ፈንታ ብቻ ሳይሆን ከዚህ መሠሪ የክህደት ቡድን ጋር ሲፋለሙ በጀግንነት ክቡር ሕይወታቸውን የሰዉትን፣ ለምርኮ ተዳርገው በባዶ እግራቸው አሰልፎ ለሕዝብ ትዕይንት በማቅረብ ያዋረዳቸውን እና አሁንም በሰቆቃ ውስጥ የሚገኙትን አባሎች እያሰባችሁ እንደሚሆን አያጠራጥርም። በመሆኑም፣ አሁን በትሕነግ የጥፋት ኃይል ዳግም እየተፈጸመ ያለውን ወረራ በአስተማማኝ ለመቀልበስ የሚከፈለው መስዋዕትነት ግቡ እንዳለፉት ጊዜዎች ባልታስበ መልኩ በአጭር ተቀጭቶ የሕዝብን ቅስም በሚሰብር ሁኔታ ለወራሪው ቡድን ሌላ ዕድል የሚሰጥ፣ ሠራዊቱንም አገርንም ለአዋራጅ ሽንፈት የዳረጉ የበላይ መሪዎችን በወታደራዊ ሥርዓት እና ደንብ መሠረት ተጠያቂ በማድረግ ፈንታ በሹመት እና ሽልማት የሚያንበሽብሽ ሊሆን አይገባም። ከጎናችሁ ተሠልፈው አኩሪ ግዳጃቸውን የተወጡ፣ አገርን የታደጉ የፋኖ፣ የሚሊሽያ እና የልዩ-ኃይል ወገኖቻችሁን ግዳጅ ሲያልቅ ለፖለቲከኞች ጊዚያዊ ጥቅም ሲባል ተሳዳጅ እንዳይሆኑ ያስፈልጋል። 

2. የፋኖ እና ሌላው የዐማራ ተዋጊ ክፍል ተቀዳሚ ሚና የክልሉን ሕዝብ ከአደጋ መታደግ ቢሆንም፣ እንደየሁኔታው ከአገር መከላከያ ጎን በመሠለፍ በተናበበ እና በተደጋገፈ መልክ ግዳጃቸውን ሊወጡ ይችላሉ። የክልሉ ልዩ ኃይልም፣ ሚሊሽያም ሆነ ፋኖ ግዳጆቻቸውን ሲወጡ ካለፉት አሉታዊ ልምዶች ትምሕርት የተወሰደበት እና የዐማራው ሕዝብ ከተደቀኑበት ተደራራቢ ችግሮች አኳያ እየታየ የኃይል ቁጠባን ባገናዘበ መልክ ሊሆን ይገባል።

 በመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ሀብት፣ ከአገሪቱ መከላከያ ኃይል ተወዳዳሪ ሆኖ የተዋቀረው የኦሮሞ ልዩ  ኃይል፣ ከወያኔ ጋር ለሚደረገዉ ፍልሚያ የሚጠበቅበትን አስተዋጽዖ እንዲያደርግ በሥልጣን ላይ በሚገኙት  የኦሮሞ መሪዎች ላይ የማያባራ ግፊት ማድረግ፤ 

4. በውጭ የሚገኙ ለፍትኅ እና ለእኩልነት የቆሙ ኢትዮጵያውያን፣ በኢትዮጵያዊነት መንፈስ የሕወሓት እና  ኦሮሙማ መሪዎችን ድብቅ ሴራ ባገናዘበ መልክ ቀጣይነት ያለው እንቅስቃሴ ማድረግ፤ በመንግሥትም ይሁን በፀረ-አንድነት የሽብር ቡድኖች በአገር እና በሕዝብ ላይ የሚደርሱ ችግሮችን ለመላው ዓለም ሕዝብ ማስረዳት፤ 

5. የኦነግ መሪዎች ከሕወሓት አጋሮቻቸው ጋር በምስጢር በሚያደርጉት ድርድር፣ የዐማራ ሕዝብ ርስት የሆኑት  የራያ፣ የወልቃይት ጠለምት እና የመሳሰሉት ቦታዎች እንደገና በሕወሓት እጅ እንዳይገቡ የሚያስፈልገውን  ክትትል እና ዝግጅት ማድረግ፤ 

6. በመጨረሻም፤ ቀደም ሲል የሕወሓት፣ ዛሬ ደግሞ የዐቢይ አህመድ ፀረ-ዐማራ አጀንዳ አስፈጻሚና የወንጀል  ተባባሪ የሆኑት የዐማራ ክልል መሪዎች፣ ትውልድ የማይረሳው የክህደት ድርጊት እየፈፀሙ ወገናችንን ለባሰ  ሰቆቃ፣ እልቂት እና አደጋ በቀጣይነት እንዳይዳርጉ ከፍተኛ ተጽዕኖ ማድረግ። 

ድል ለተበደለ ሕዝብ! 

Signatories:  

1. Adwa Great African Victory Association (AGAVA) 
2. All Shewa Ethiopian People Multipurpose International Association  
3. The Amhara Association in Queensland, Australia 
4. Amhara Dimtse Serechit 
5. Amhara Well-being and Development Association 
6. Communities of Ethiopians in Finland 
7. Concerned Amharas in the Diaspora 
8. Ethio-Canadian Human Rights Association 
9. The Ethiopian Broadcast Group 
10.Ethiopian Civic Development Council (ECDC) 
11.Freedom and Justice for Telemt Amhara 
12.Global Alliance for Justice – The Ethiopian Cause 
13.Global Amhara Coalition 
14.Gonder Hibret for Ethiopian Unity 
15.Major Lemma Woldetsadik Memorial Foundation 
16.Network of Ethiopian Scholars (NES) 
17.Radio Yenesew Ethiopia 
18.Selassie Stand Up, Inc. 
19. Vision Ethiopia 
20. Worldwide Ethiopian Civic Associations Network (WE-CAN)

__

በነጻ አስተያየት መድረክ የሚቀርቡ ሃሳቦች የጸሃፊውን እንጂ የግድ የቦርከናን ድረገጽ ሃሳብ ላያንጸባርቁ ይችላሉ፡፡ በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena 

- Advertisement -Early Bird Holiday Deals! Before you know it, the holidays will be right around the corner! Take advantage of our early bird deals today and save up to $40 on our fees with code SPOT40!
Stay Connected
28,789FansLike
13,733FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here