
ቦርከና
የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ (ህወሓት) ለሶስተኛ ጊዜ የቀሰቀሰው ጦርነት ስድስተኛ ቀኑን ይዟል :: ቡድኑ የቆቦን ከተማ ከተቆጣጠረ በኋላ ጦርነቱ ባብዛኛው በወልዲያ እና በቆቦ መካከል ባሉ ቦታዎች እየተካሄደ እንደሚገኝ የተለያዮ ምንጮች እየጠቀሱ ነው::
የመንግስት ወታደሮች እስካሁን በመከላከል ላይ የተመረሰተ ወጊያ እያደረጉ እንደሆነም ነው የተነገረው:: ምንም እንኳን ህወሓት ከተለያዮ አቅጣጫዎች “የህዝብ ማዕበል” በሚባለው የጦር ስልት ውጊያ የከፈተ ቢሆንም ባሰበው ፍጥነት ወደፊት መግፋት እንዳልቻለ ታውቋል::
ትላንት ከወልዲያ ከተማ ነዋሪዎች መካክል የተኩስ ድምጽ ይሰማ አንደነበረ የተናገሩ ነበሩ:: በዚያው ምክንያት ከተማዋን እየተው ወደ ደሴ ስደት የጀመሩም እንደነበሩ ተሰምቷል::
አፍቃሪ ህወሓት የሆኑ መገናኛ ብዙሃን እና የ “ማህበረሰብ አንቂዎች” ወልዲያ ከተማ በህወሓት ኃይሎች እንደተያዘ ማስወራት ከጀመሩ ሶስት ቀናት ያለፈ ሲሆን እንደ አልጀዚራ ያሉ የውጭ መገናኛ ቡዙሃን ጭምር የሃሰት መረጃውን በስፋት አሰራጭተውታል ::
ሆኖም የወልዲያ ከተማ ባለስልጣናት ዜናው ሃሰተኛ መሆኑን አስረግጠው ህዝቡ የደጀንነት ሚናውን ባግባቡ አየተወጣ ነው ፤ ነዋሪዎችም የእለት ተለት አንቅስቃሴያቸውን እያከናወኑ ነው በሚል መግለጫ ሰተዋል::
ይሄ መረጃ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ የወልደያ ከተማ በኢትዮጵያ ሃይሎች እጂ አንዳለች እና ከወልደያ ከተማም በመስጋት ወተው የነብሩ የተከማዋ ነዋሪዎች መመለስ መጀመራቸውን የቦርከና ዘጋቢ ማረጋገጥ ችሏል::
ስለ ወልደያ ሁኔታ ሃሰተኛ ዜና ከተሰራጨ በኋላ በደሴ ከተማም ሰኞ ማምሻ ላይ እና ማክሰኞ ጠዋት ላይ በነዋሪዎች ላይ የተሰተዋለ የመረበሽ ስሜት እንደነበረ ታውቋል:: ሁኔታው አንዳንድ ነጋዴዎችን እቃ አንዲያሸሹ ያደረገ ሲሆን ከተማዋን በመልቀቅ ወደ አዲስ አበባ እና ባህር ጋር ጉዞ የጀመሩም እንደነበሩም ለማወቅ ተችሏል:: ነዋሪዎች ገንዘብ ከባንክ ለማውጣት ረዣዥም ሰልፎችም ይዘው ታይተዋል::

የወልዲያ ከተማ አመራሮች መግለጫ ከሰጡ በኋላ ሁኔታው ተረጋግቶ አብዛኛው ነዋሪ ወደ እለት ተለት ስራው አንደተመለሰም ዘጋቢያችን ከቦታው አድርሶናል::
ወደ ደሴ ገብተው የነበሩም የወልዲያ ነዋሪዎች መመለስ መጀመራቸው ታውቋል::
የዛሬ አመት ገደማ የህወሓት ቡድን ደሴን አና ወልዲያን ጨምሮ በርካታ የአማራ ክልል አና የአፋር ክልል ከተሞችን ተቆጣጥሮ መጠነ ሰፊ ኢኮኖሚያዊ አና ማህበራዊ ውድመት ማድረሱ ይታወሳል:: በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎችም ህይወታቸውን አጥተዋል፤ በርካቶች ከመኖሪያ ቦታቸው ተፈናቅለው የሰቆቃ ህይወት መርተዋል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ የመንግስት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር የሆኑት ዶክተር ለገሰ ማክሰኞ ለት “የውስጥ ባንዳዎችና ታሪካዊ ጠላቶቻችን ተቀናጅተው የከፈቱብንን ዘርፈ ብዙ ጦርነት ሁሉም ዜጋ በኅብረ ብሔራዊ አንድነት መመከት አለበት” ሲሉ አሳስበዋል::
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድም ወደ አልጀሪያ አድርገውት የነበረውን የስራ ጉብኝት አገባደው ማክሰኞ እለት ወደ ሀገር መመለሳቸውን የመንግስት መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል ::
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ