spot_img
Monday, June 24, 2024
Homeአበይት ዜናበምዕራብ ኦሮሚያ ለአማራ ተወላጆች ጥበቃ አልተደረገም ሲል ሂውማን ራይትስ ወች መንግስትን ተቸ

በምዕራብ ኦሮሚያ ለአማራ ተወላጆች ጥበቃ አልተደረገም ሲል ሂውማን ራይትስ ወች መንግስትን ተቸ

ጀማል ሰይድ
ቦርከና

በምዕራብ ኦሮሚያ ሰኔ 2022 የታጠቀ ቡድን በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆችን ሲገድል የኢትዮጵያ የጸጥታ ሃይሎች ከጥቃት ለመከላከል ያደረጉት ጥረት ብዙም አልነበረም ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ዛሬ አስታውቋል። 

ከሶስት ወራት ገደማ በኋላ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በህይወት ለተረፉ ነዋሪዎች እንኳ በቂ የመጠለያ፣ የጤና እና የደህንነት ጥበቃ ስጋቶችን መፍታት አልቻለም ሲል ድርጅቱ የኢትዮጵያ መንግስትን ወቅሷል።

እንደ ድርጅቱ ዘገባ ያለፈው ሰኔ 18 ቀን ለስምንት ሰአታት በዘለቀው ግድያ በቶሌ እና በሰኒ ቀበሌዎች በሚገኙ መንደሮች በርካታ ሴቶችና ህፃናትን ጨምሮ ወደ 400 የሚጠጉ የአማራ ተወላጆችን ታጣቂዎች በጥይት ገድለዋል። ድርጅቱ «ማንነታቸው ያልታወቁ»ባላቸው ታጣቂዎች በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶችን እና የንግድ ቤቶችን አቃጥለው አውድመዋል፣ የቤት እንስሳና ሌሎች ንብረቶችንም ዘርፈዋል። የሳተላይት ምስል ትንተና ቢያንስ አምስት መንደሮች መቃጠላቸውን እና ወደ 480 የሚጠጉ ሕንፃዎች መውደማቸውን መረጋገጡን አስፍሯል።ስለ ጥቃቱ  ማስጠንቀቂያ ቢሰጥም በአካባቢው የሰፈሩት የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች ጥቃቱ  ለሰዓታት ሲፈፀም አልመድረሳቸውን ድርጅቱ አስታዉቋል።

ከጎርጎሪያኑ 2019 ጀምሮ የመንግስት ሃይሎች እና ድርጅቱ «የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት»ብሎ የጠራው ታጣቂ ቡድን በምዕራብ ኦሮሚያ ሲዋጉ በኦሮሞ እና በአናሳ ማህበረሰቦች ላይ ከፍተኛ በደል እየደረሰ መሆኑን አመልክቷል። በሰኔ ወር ለተፈጠረው እልቂትም እርስ በእርስ  መወነጃጀላቸውን ገልጾ በገለልተኛ ወገን ምርመራ እንዲደረግ ጠይቋል።

ሂዩማን ራይትስ ዎች በሰኔ እና በነሐሴ ወራት መካከል ከ5 መንደሮች 19 ምስክሮችን እና የተጎጂዎችን ዘመዶች ጨምሮ 25 ሰዎችን በስልክ በማነጋገር ስለ ግድያው መረጃ መሰብሰቡን አመልክቷል።

ድርጅቱ ካነጋገራቸው ሰዎች መካከል በበቆሎ ማሳ ውስጥ ተደብቃ ያመለጠች ሴትን ምስክርነት እንዲህ ሲል ጽፏል።

«የ8 ወር ልጄ ማልቀስ ጀመረ። አንድ ታጣቂ ወደ እኛ አቅጣጫ ከመተኮሱ በፊት ‘እዚያ ተመልከት፣ እዚያ ተመልከት…’ ሲል ሰማሁ። ልጄን በጥይት ተኩሰው ገደሉት። ሬሳውን በለበስኩት ልብስ ጠቀለልኩት። ሌላኛዋ ልጄም በጀርባዋ በጥይት ተመታች። ጥይቱም በአንገቷ  ወጣ… ከዚያም የተጎዳችውን ልጄን ደረቴ ላይ አቅፌ፣ አላህ ህይወቷን እንዲያድናት ጸለይኩ።» ብላለች።

በዚህ ሁኔታ ትልቋ ልጇ በህክምና እርዳታ መትፈፏን  ድርጅቱ በዘገባው አመልክቷል።

በቶሌ እና በሰኒ ቀበሌ በአማራ ተወላጆች ላይ የታጠቁ ሃይሎች የተፈፀመው ጥቃት በምዕራብ ኦሮሚያ  ቄለም ወለጋ ዞን በሃዋ ገላን ወረዳ በተፈፀመው  ሁለት ሳምንት ባልሞላ ጊዜ ውስጥ መሆኑን የመገናኛ ብዙሃን መዘገባቸውን ድርጅቱ አመልክቷል ።

ከቶሌ እና ሴኔ ቀበሌ ከግድያው የተረፉ ሰዎች እንዳሉት በአካባቢው የሚደርሰው ጥቃት ይቀጥላል በሚል ፍራቻ እና በቂ ጥበቃ እና ሰብዓዊ ድጋፍ ባለመኖሩ በርካታ ነዋሪዎች ከኦሮሚያ ለቀው እንዲወጡ እየተገደዱ ነው ብሏል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ፅህፈት ቤት ከቶሌ ቀበሌ ቢያንስ 4,800 ሰዎች ከምዕራብ ኦሮሚያ ደግሞ ከ500,000 በላይ የሚሆኑ ተፈናቅለዋል ብሏል።

ይሁን እንጅ በቂ የገንዘብ ድጋፍ  እና የሰብአዊ ርዳታ ባለመኖሩ እንዲሁም የተደራሽነት ገደብ በመኖሩ ለእርዳታ ቡድኖች ወደ ክልሉ መድረስ ከባድ እንደሆነ ድርጅቱ ዘግቧል። በመሆኑም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ለዕርዳታ አሰጣጥ ምቹ ሁኔታ መፍጠር አለባቸው ሲል ሂውማን ራይትስ ዎች አሳስቧል።

በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኙ ማህበረሰቦች በተደጋጋሚ በሚደርሱ ጥቃቶች በፍርሀት ውስጥ መቆየታቸውን  የገለፀው ዘገባው፤ አሁንም  ቀጣይ  ጥቃት ይደርስብናል በሚል ስጋት እየኖሩ መሆናቸውን አንድ የአካባቢውን ነዋሪ ጠቅሶ ሂውማን ራይትስ ወች ዘግቧል። 

በመሆኑም የኢትዮጵያ ባለስልጣናት ለተጎዱ ማህበረሰቦች አስቸኳይ እና በቂ የሆነ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲሁም ለታማኝ እና ገለልተኛ ምርመራዎች ድጋፍ ለመስጠት በአስቸኳይ መንቀሳቀስ አለባቸው ብሏል ድርጅቱ::

__

በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here