
ጀማል ሰይድ
ቦርከና
በኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ 46 የሃይማኖት መገናኛ ብዙሃን ተቋማት መካከል 23ቱ ዛሬ የሥራ ፈቃድ እንደሚወስዱ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን አስታወቀ።
የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ሀገራዊ የምክክር መድረክ “የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ለአብሮነት እሴቶች መጠናከር” በሚል መሪ ሃሳብ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ እድሪስ፤ ኢትዮጵያ በወጡ ፖሊሲና አዋጆቿ በብዙ ሀገራት ባልተለመደ መልኩ ዕውቅና መስጠቷን ገልፀው በዚህ መሰረት የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ለተደረገው የምዝገባ ጥሪ ፈጣን ምላሽ ተሰጥተዋል ብለዋል።
በሃገሪቱ ካሉ 46 የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን መካከልም አሥፈላጊውን መረጃ ያሟሉት 23 ያህሉ ዛሬ ከኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ፈቃድ እንደሚቀበሉ ገልፀዋል።
የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ትኩረት የተሰጠው ሃይማኖቶች በሀገር ግንባታ የተጫወቱት ሚና የማይዘነጋ በመሆኑ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ፤ የመንግስት ዋናው ፍላጎት የሃይማኖት መገናኛ ብዙኃን ሕግና ሥርዓት አክብረው በሰላምና አንድነት ዕሴት ግንባታ ላይ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያበረክቱ ነው ሲሉ አብራርተዋል።
የኢትዮጵያ የኃይማኖት ተቋማት ጉባዔ ጠቅላይ ፀሐፊ ሊቀ ትጉሃን ቀሲስ ታጋይ ታደለ በበኩላቸው፤ 93 በመቶ ያህል አማኝ ባለባት ሀገር የሚታየው የሰላም እጦትና የተለያየ ችግር ሃይማኖቶች ተገቢውን አሥተምህሮ ያለመስጠታቸው ምልክት መሆኑን ገልፀዋል።
ሆኖም አሁን በተፈጠሩ ምቹ ሁኔታዎች ሃይማኖቶች በሚዲያዎቻቸው የግብረ ገብነት ትምህር ላይ በትኩረት በመሥራትና ትውልዱን በመቅረፅ ወደመከባበር መመለስ ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ