spot_img
Sunday, April 14, 2024
Homeዜናየግብፅ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቴዎድሮስ ሁለተኛ የህዳሴው ግድብ ግንባታን በተመለከተ...

የግብፅ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቴዎድሮስ ሁለተኛ የህዳሴው ግድብ ግንባታን በተመለከተ ሶስቱ ሀገራት ከስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጥሪ አቀረቡ

የግብፅ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን

ጀማል ሰይድ
ቦርከና

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በግዙፍነቱ ቀዳሚ የሆነውን የኤሌክትሪክ ሃይል ማመንጫ ጣቢያ ከ10 አመት በፊት በአባይ ወንዝ ላይ መገንባት ከጀመረችበት ጊዜ አንስቶ በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል ያለው ግንኙነት በውጥረት የተሞላ ነው፡፡ ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድቡ ግንባት የታችኛው የተፋሰሱ ሀገራት በሆኑት በግብጽና ሱዳን ላይ ምንም አይነት ጉዳት አያስከትልም፤ ይልቁንም በትነት የሚባክነውን ውሃ በማስቀረትና አመቱን ሙሉ የተስተካከለ የውሃ ፍሰት እንዲያገኙ በማድረግ ለሁለቱ ሀገራት ከፍተኛ ጥቅም አለው የሚል ጽኑ እምነቷን በተደጋጋሚ ስታሰማ ቆይታለች፡፡

በአንጻሩ ግብጽ የውሃ መጠኑን በመቀነስ በሀገሬ ህዝቦች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ያደርሳል በሚል ተደጋጋሚ ቅሬታዎችን በተለያዩ ጊዜያት ታሰማለች፡፡ ሱዳንና ግብጽ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ተመሳሳይ አቋምን በማራመድ የግድቡን ግንባታ ለማስተጓጎል ሲጥሩም ይስተዋላል፡፡ ለአብነት በአረብ ሊግ ፤ በአውሮፓ ህብረት በአሜሪካና በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት የውይይት አጀንዳ እንዲሆን ማድረጋቸውም የሚታወስ ነው፡፡ ይሁን እንጅ ኢትዮጵያ የትኛውም ንግግርም ይሁን ድርድር ከግንባታው አያስተጓጉለኝም በማለት በቅርቡ 3ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ማከናወኗም የሚታወስ ነው፡፡

ግብጽ በተለያዩ አህጉር አቀፍና አለም አቀፍ ተቋማት ያደረገችው ሙከራ ግንባታውን ለማስተጓጎልም ሆነ ወደ አሳሪ ድርድር ለማስገባት ባለመቻሉ አሁን ደግሞ በሃይማኖት ተቋማት አማካኝነት ጉዳዩ ትኩረት እንዲያገኝ የፈለገች ይመስላል፡፡

የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያል ሊቀ ጳጳስ አቡነ ቴዎድሮስ ሁለተኛ ትናንት እሁድ እለት በግብጽ ጉብኝት እያደረጉ የሚገኙትን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የባሌ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ አቡነ ዮሴፍንና ሌሎች አብረዋቸው የተጓዙ ምእመናንን በተቀበሉበት ወቅት እንደተናገሩት፡ ግብጽና ኢትዮጵያ ዘመን ተሸጋሪ ግንኙነት እንዳላቸው አውስተው አሁንም በግድቡ ግንባታ ላይ የተፈጠሩ አለመግባባቶችን በሰላም እንዲፈቱ ግብጽ ሱዳንና ኢትዮጵያ ከስምምነት ላይ እንዲደርሱ ጠይቀዋል፡፡

አክለውም “የናይል ወንዝ ሁልጊዜ እንዲፈስ እንጸልያለን፤ በኢትዮጵያም የተስተካከለ ዝናብ እንዲኖር ፈጣሪን እንለምናለን፡፡ በግብጽ ናይል ወንዝን እንደ አባታችን፤ ውሃው የሚመጣበትን ምድር ደግሞ እንደ እናታችን ነው የምንመለከተው፡፡’’ በማለት ተናግረዋል፡፡

አህራም ኦንላይን እንደዘገበው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያንና የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ዘመናትን የተሻገረ የጠበቀ ግንኙነት አላቸው፡፡ የግብጽ ኮፕቲክ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አ.ኤ.አ በ2015 በኢትዮጵያ ጉብኝት ማድረጋቸውን ያስታወሰው ዘገባው ከአቡነ ቴዎድሮስ ጉብኝት ቀደም ብሎ ደግሞ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ አቡነ ማቲያስ በግብጽ ጉብኝት አድርገው እንደነበርም ዘገባው አስታውሷል፡፡

አቡነ ማቲያስ በግብጽ ጉብኝት ባደረጉበት ወቅት ከግብጹ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ጋር ተገናኝተው መክረዋል፡፡ በወቅቱ ፕሬዚዳንቱ ለአቡኑ ግብጽ የኢትዮጵያን የመልማት ፍላጎት ትደግፋለች፡፡ አባይ ለኢትዮጵያ የመልማት ጥያቄ ነው ፤ ለግብጻውያን ደግሞ የህይወት ጉዳይ ነው፡፡ ማለታቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡

_

በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here