spot_img
Wednesday, June 12, 2024
Homeአበይት ዜናየህወሃት የሰላም ድርድር ጥያቄና አንድምታው

የህወሃት የሰላም ድርድር ጥያቄና አንድምታው

ደብረጺዎን ገብረሚካኤል
መንግስት በአሸባሪነት የፈረጀው የህወሓት ሊቀመንበር ደብረጺዎን ገብረሚካኤል በመጀመሪያው ዙር ጦርነት ሸሽተውበታል ከተባለው የተንቤን በርሃ ተመልሰው በመቀሌ ለደጋፊዎቻቸው ደስታቸውን ሲገልጹ (ፎቶው ከቲዮው ዮርክ ታይምስ የተገኘ ነው)

ጀማል ሰይድ
ቦርከና

ህወሀት በአፍሪካ ህብረት ስር ለሚደረገዉ ድርድር ዝግጁ መሆኑንና ሌተናል ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ እና አቶ ጌታቸዉ ረዳን ተደራዳሪ አድርጎ መሰየሙን አስታወቀ ፡፡

ሁለት አመት ሊሞላዉ የተቃረበዉ የህወሀትና የኢትዮጵያ መንግስት ጦርነት ለአምስት ወራት በተኩስ አቁም ስምምነት ከተቋረጠ በኋላ በነሀሴ ወር አጋማሽ እንደገና ማገርሸቱ ይታወቃል፡፡ ጦርነቱ በርካታ ዜጎችን ከቀያቸዉ በማፈናቀል  ለስቃይና ለእንግልት ዳርጓል፡፡ ቁጥራቸዉ ቀላል የማይባል ዜጎችን ህይወትም ቀጥፏል፡፡ጦርነቱ የሀገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ አሉታዊ ተፅእኖ በመፍጠርም ለኑሮ ዉድነት መባበስ ዋነኛዉ ምክንያት መሆኑን የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡ ጦርነቱን በዘላቂነት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የፌደራሉ መንግሰት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ለሚደረገዉ ድርድር ዝግጁ መሆኑን በመግለፅ በምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴርና የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አቶ ደመቀ መኮነን የሚመራ ሰባት አባላት ያሉትን ቡድን ይፋ ማድረጉ ይታወቃል፡፡በፌደራሉ መንግስት በሽብርተኝነት የተፈረጀዉ ህወሀት በበኩሉ በተደጋጋሚ በሰጣቸዉ መግለጫዎች በአፍሪ ህብረት ስር የሚደረገዉ ድርድር የሚፈለገዉን ዘላቂ ሰላም አያመጣም፤ ድርድሩ ላይ ሌሎች አካላቶችም ሊሳተፉ ይገባል፡፡ የተደራዳሪዎችን ስምም ማሳወቁ ተራ ፖለቲካዊ ትርፍ ከማግኘት ውጭ ስብሰባዉም የሚፈጥረዉ ነገር የለም ሲል መሰንበቱ የሚታወስ ነዉ፡፡

ለሶስተኛ ጊዜ በተቀሰቀሰዉ ጦርነት ሁለቱም ሀይሎች ለጦርነቱ መቀስቀስ አንዱ ሌላዉን ሲወቅሱ መቆየታቸዉም ይታወቃል፡፡

ህወሀት ትናንት ምሽት በኢትዮጵያ አዲስ አመት ዕለት የዉጭ ጉዳይ ሁኔታዎቹን በሚያሳዉቅበት ፅ/ቤት በኩል ባወጣዉ መግለጫ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚካሄደዉ የሰላም ድርድር ሂደት ዉስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን እና የሰላም ተደራዳሪ መሰየሙን አስታዉቋል፡፡እንደ ድርጅቱ ገለፃ በአዲሱ አመት በአጠቃላይ በኢትዮጵያ በተለይ ደግሞ በትግራይ ተኩስ የማይሰማበት፣ መሰረታዊ አገልግሎቶች እና የሰብአዊ እርዳታ እቀባ የሚያበቃበት እንዲሆን ፍላጎታቸዉ መሆኑን ያትታል፡፡ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ለሚደረገዉ ድርድር አመቺ ሁኔታን ለመፍጠርም አስቸኳይ  እና በጋራ ስምምነት ግጭቶችን ለማስቆም  እንደሚስማማና ይህንንም ተከትሎ በሚካሄድ ድርድር ተሳታፊ ለመሆን ዝግጁ መሆናቸዉን አስታዉቀዋል፡፡

ከሀያ ሁለት ወራት በላይ የዘለቀዉን ጦርነት ለማስቆም የተለያዩ ወገኖች ጥረት ሲያደርጉ ቢቆዩም ሊሳካላቸዉ አልቻለም፡፡ በተለይ ባለፈዉ አንድ አመት የአፍካ ህብረት የምስራቅ አፍሪካ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሶጎን ኦባሳንጆ ከአዲስ አበባ ወደ መቀሌ በመመላለስ ያደረጉት ጥረት ተጠቃሽ ነዉ፡፡ ህወሃት በኦባሳንጆ በኩል የአፍሪካ ህብረት እያደረገ ያለውን የሰላም ጥረት በተደጋጋሚ የሚያጣጥል መግለጫ ሲሰጥ ሰንብቷል፡፡አሁን በህብረቱ ለሚደረግ የሰላም ድርድር ፈቃደኛ መሆኑንና ተአማኒነት ያለዉ ድርድር እንደሚያካሂድ አቶ ጌታቸዉ ረዳንና ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይን መወከሉን በይፋ አስታዉቋል፡፡

አቶ ጌታችዉ ረዳ የህዋሃት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልና የትግራይ ወታደራዊ ማዕከል ቃል አቀባይ በመሆን እያገለገለ ይገኛል፡፡ አቶ ጌታቸዉ ረዳ ከዚህ በፊት ህወሃት የፌደራል መንግስቱን ስልጣን በተቆጣጠረበት ወቅት በዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ዉስጥ በከፍተኛ የስልጣን ደረጃ ማገልገሉ የሚታወስ ሲሆን የመንግስት ኮሚኒኬሽን ፅ/ቤት ሚኒስቴር እንደነበርም ይታወቃል፡፡

ሌ/ጀነራል ፃድቃን ገ/ትንሳይ የህወሃት ነባር ታጋይ ከሚላቸው ውስጥ ሲሆን በትግል ወቅትና ከትግል በኋላ በጦር አመራርነት አገልግሏል፡፡ጄነራሉ ከ1993 የኢፌድሪ መከላከያ ሚ/ር ጠቅላይ አታማጆር ሹም የነበረ ሲሆን በ1993 በህወሃት አመራሮች መከከል ተፈጥሮ በነበረዉ የሥልጣን ሽኩቻ ምክንያት መባረሩ ይታወቃል፡፡ ህወሃት የሰሜን ዕዝን ካጠቃ በኋላ ወደተንቤን በርሃ በመሸሸግ እንደገና አቋሙን ሲያደራጅ የትግራይ ሰራዊት  ከፍተኛ አዛዥ በመሆን እያገለገለ መሆኑ በተለያየ ጊዜ ተገልጧል፡፡

የህወሃትን የሰላም ጥሪ አስመልክቶ የተለያዩ አስተያየቶች እየተደመጡ  ነዉ፡፡ህወሃት ከአፈጣጠሩ  ጀምሮ በድርድር የማያምን ፤ የኔ ሀሳብ ብቻ ያሸንፍ የሚል ግትር አቋም ያለዉ ድርጂት  በመሆኑ ምን አልባት አሁን ላይ በግንባር ጦርነት ያሰበዉ ሳይሳከለት ሲቀር ድርድሩን  እራሱን ለማደራጀት  እንደጊዜ መግዣ ሊጠቀምበት አስቦ ነዉ፡፡ ድርጂቱ  በመቀበል  መርህ አያምንም፡፡ ጊዜ ሲያገኝ ሰበብ ፈጥሮ የለመደዉን ወረራ መቀጠሉ አይቀርም የሚል ሲሆን በሌላ ወገን ደግሞ ኢትዮጵያ ሰላምና መረጋጋት ያስፈልጋታል፡፡ ጦርነትን የሚሸከም ኢኮኖሚ የላትም በመሆኑም የኢትዮጵያ ሉአላዊ አንድነት ስጋት ላይ የማይጥል ከሆነ በሚል ሰላም መፍጠርን በበጎ የተመለከቱ አሉ፡፡

ህወሃት ማታ ለሰላም ዝግጁ መሆኑን ቢገልፅም ዛሬ ከማለዳ ጀምሮ ሱዳን የሚገኘዉ የሳምሪ ቡድን በመተማ ቲሃ በኩል ጥቃት መክፈቱን የተለያዩ መረጃዎች እያመለከቱ ነዉ፡፡ ይህ ትንኮሳም ድርጅቱ ካለጦርነት መኖር እንደማይችል ማሳያ ነዉ ተብሏል፡፡ የሰላም ጥሪዉን አስመልክቶ እስካሁን ድረስ ከፌደራል መንግስት በኩል የተሰጠ አሰተያየት የለም፡፡ የኢፌድሪ ሰላም ሚኒስቴር ዴኤታ አቶ ታዬ ደንደኣ ግን በቲዉተር ገፃችዉ ባሰፈሩት መልዕክት ህወሃት በአፍሪካ ህብረት በኩል ለሚደረገዉ የሰላም ድርድር ዝግጁ መሆኑን ማስታወቁ ትልቅ ለውጥ ነው፡፡ ነገር ግን አንድ ሊታለፍ የማይገባው አለም አቀፋዊ መርህ አለ፡፡ ይሄውም በአንድ ሀገር ውስጥ አንድ የሀገር መካላከያ ሰራዊት ተቋም ብቻ ነው መኖር ያለበት፡፡ በመሆኑም የትግራይ መከላከያ ሰራዊት በሚል ህወሃት ያደራጀው ሀይል ትጥቁን ያለምንም ቅድመ ሁኔታ መፍታት አለበት፡፡ ይህ ከሆነ ሰላም ለሁላችንም አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡

__

በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com  

የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena 
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ

ማስታወቂያ
Stay Connected
28,789FansLike
13,920FollowersFollow
8,540SubscribersSubscribe
Stacy Adams
Must Read
Related News

LEAVE A REPLY

Please enter your comment!
Please enter your name here