
ልዑልነታቸው ልዑል ኤርሚያስ ሣኅለ ሥላሴ ኃይለ ሥላሴ
፫ መስከረም፪፼፲፭ (September 13, 2022)
ግርማዊት ዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ለእግዚአብሔር የገቡትን ቃል ኪዳን እንዲሁም ለሕዝባቸውና ለመላው የዓለም ሕብረተሰብ የነበራቸውን መሀላ በመፈጸም ፫ ጳጉሜ ፪፼፲፬ ዓ.ም አረፉ። በዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥ ህልፈተ-ሕይወት ብናዝንም፣ በሕይወት ሳሉ ለነበረን ዘላቂ ጓደኝነት፣ ለኢትዮጵያ ሕዝብና ለግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ላሳዩት ወዳጅነት በኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ስም ልንዘክራቸው እንወዳለን።
ንግሥት ኤልሳቤጥ እስከ ሕይወት ፍጻሜአቸው ድረስ ከእግዜር ተመርጠው ቅባዓ-ንግሥ በተቀቡና ለእግዚአብሔር በገቡለት ቃል መሰረት ሕዝባቸውን ያገለገሉ በመሆናቸው እጅግ ከምንወዳቸውና ከምናከብራቸው ዓፄ ኃይለ ሥላሴ ጋር ተመሳሳይ ነበሩ። ሁለቱም በእግዚአብሔር የተቀቡት በልበ ሙሉነት፣ በብልሃት፣ በትዕግስትና በደግነት እግዜርንና የሚወዱትን ሕዝባቸውን በሚገባ ለማገልገል ነበር።
ግርማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥና ዓፄ ኃይለ ሥላሴ እርስ በእርሳቸው እጅግ የሚተማመኑና አንዳቸው ላንደኛቸው ሀገር ሕዝብ ደህንነት እጅግም የሚጨነቁ ነበሩ።
ንግሥት ኤልሳቤጥ ኢትዮጵያን የጎበኙት ዓፄ ኃይለ ሥላሴን ለመጠየቅ፣ የምንወደውን ሕዝባችንን በአይናቸው ለማየትና ውብና ለምለም ሀገራችንን ለመጎብኘት ነበር። በሁለተኛው የጣልያን ወረራ ጊዜ የንግሥት ኤልሳቤጥ ኣባት፣ ዓፄ ጊዮርጊስ ፮ኛው ለዓፄ ኃይለ ሥላሴ መጠጊያ ቦታ እንዲይዙ በመፍቀድ ኢትዮጵያን ጭካኔ ከተሞላው የአምስት ዓመት የጣልያን ይዞታ ነፃ እንድናወጣና ሉዓላዊነታችንን ለሕዝባቸን መልሰን እንድናስረክብ የተሰናዳንበትን ሁኔታ አመቻችተዋል። በአፍሪካና በእስያ የነበረው የቅኝ አገዛዝ ስርአት እያከተመ ሲሄድና ንግሥት ኤልሳቤጥ ከቅኝ ግዛት የአስተዳደር ዘመን በኋላ እንዴት እንግሊዝን ጽኑ መሰረት ባለው ዘውዳዊ ስርአት ላይ ሕዝባቸውን በዘውድ ሕገ-መንግሥታዊ ዴሞክራሲ ማስተዳደር እንደሚቻል በመገንዘባቸው፣ ኢትዮጵያም ውስጥ ስኬታማ የሆነ ጠንካራ ዴሞክራሲ ጽኑ በሆነ የሕገ-መንግሥታዊ ዘውዳዊ ስርአት ላይ መገንባት እንደሚቻል ዓፄ ኃይለ ሥላሴ እንዳዩና እንዳመኑ ምንም ጥርጥር የለውም።
ግርማዊት ንግሥት ለዓፄ ኃይለ ሥላሴ ሁለት ልዩና ታላቅ ስጦታዎች አበርክተውላቸዋል። አንዱ የብሪታኒያ ላዕላይ ማዕረግ (Knight of the Garter) የተሰጣቸው ሲሆን፣ ሌላኛው ደግሞ የታላቅዋ ብሪታንያ ሰራዊት ፊልድ ማርሻል (Field Marshall) ማዕረግ ነው። ግርማዊ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ለንግሥት ኤልሳቤጥ ባል ለልዑል ፍሊጶስ የመጨረሻውን ከፍተኛ የሰለሞናዊ መስቀል ማዕረግ አበርክተውላቸዋል። ከሁለም አንጻር ሲታይ፣ ግርማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥና ግርማዊ ንጉሥ ነገሥት ዓፄ ኃይለ ሥላሴ ለሁለቱ ሕዝቦቻቸው የነበራቸው ጥልቅ ፍቅርና መተሳሰብ እንዲሁም ደግሞ ሁለቱም እስከ ፍጻሜ መንግሥታቸው ድረስ ሕዝባቸውን በታማኝነት ለማገልገል ቃል የገቡ መሆናቸው እንዳስተሳሰራቸው ከልብ በመገንዘብና በማመናቸው ኣንዳቸው ላንዳቸው ተሳስበውና እርስ በርሳቸው ተከባብረው በወዳጅነትና በፍቅር ኖረዋል።
ንግሥት ኤልሳቤጥ ከመስከረም ፼፱፻፷፮ ዓ.ም (1974) መፈንቅለ-መንግሥትና ከ ፳፩ ነሐሴ ፼፱፻፷፯ ዓ.ም የንጉሠ ነገስቱ የግድያ ወንጀል በኋላ ከግርማዊ ጃንሆይና ኢትዮጵያ ጋር የነበራቸውን ጥብቅ ወዳጅነት አስታውሰውና አክብረው በማስቀጠል፣ እንግሊዝ ሀገር ለነበሩና በመፈንቅለ መንግሥቱ ምክንያት ወደ ኢትዮጵያ ለመመለስ ላልቻሉ የንጉሣዊያን ቤተሰቦች ድጋፍ በማድረግ ዘላቂ የቤተሰብ ጓደኛና ባለውለተኛ መሆናቸውን አስመስክረዋል።
እኔ በግሌ የንግሥቲቱ ደግነትና ቸርነት ተካፋይ ስለነበርኩ በቅርበት ንግሥቲቱና የብሪታንያ ሕዝብ ለኢትዮጵያዊያን ሰለሞናዊ የዘር ሀረግ ተወላጅ ዘመዶቻቸው አለኝታና ሰብሳቢም ጭምር እንደነበሩ ለመገንዘብ ችያለሁ።
ግርማዊት ንግሥት የጤና እክል እንኳን ገጥሞአቸው፣ የጤናቸው ሁኔታ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ ሲሄድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከልባቸው አልጠፋም። ባለፈው ዓመት የኢትዮጵያ ዘውድ ምክር ቤት ፲፪ ኅዳር ፪፼፲፬ ዓ.ም ኢትዮጵያዊያን ከብሪታንያና ከተቀሩት ኮመንዌልዝ ሀገሮች በግብረ-አበርነት በኅዳር ፼፱፴፬ ዓ.ም ጣልያንን ያሸነፍንበትን ሰማንያኛው ዓመት የድል በዓል በእንግሊዝ ሀገር አክብረን ነበር። የ፹ኛው አመት ዝክረ-በዓሉ የተሳካ እንዲሆን ንግሥቲቱ ገንቢ አስተያየቶችን በመስጠት በንቃት ተሳትፈዋል። ኢትዮጵያን ነጻ ለማውጣት የሕይወት መስዋዕትነት ለከፈሉ በሺዎች ለሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያን አርበኞችና የብሪታንያና የኮመንዌልዝ ሀይሎች ክብርና እውቅና ኢንዲያገኙ ያስቻልነው የጎንደር ድል በዓል እንዲከበር ባደረግነው የተሳካ ጥረትና ንግሥቲቱም በተጫወቱት ከፍተኛ ሚና ነው።
ስለዚህም፣ እኛም እንደማንረሳቸው ንግሥቲቱ እረስተውን አያውቁም። ንግሥቲቱ ለዓፄ ኃይለ ሥላሴ በነበራቸው አክብሮትና በመላው ዓለም ከሁሉም ሀገሮች የሚበልጥ ያልተቋረጠ ጥንታዊ የንጉሥ ሰለሞንና የንግሥተ-ሳባን ቀጥተኛ ሃረጋችንን በማክበራቸው ምክንያት ኢትዮጵያን ወደ ዓለም-አቀፋዊ የፖሊቲካ መሪነት መድረክ እንድትቀላቀል ጥረት አድርገዋል።
ልጃቸው ግርማዊነታቸው ንጉሥ ቻርልስ ፫ኛው ስለኛና የብሪታንያ ሕዝብ ግንኙነት ጠንቅቀው ያውቃሉ። የነገሥታቶቻችንን አርማ ውንድሰር (Windsor) ከሚገኘው ቤተ-መቅደሳቸው ውስጥ ዖርደር ኦፍ ዘ ጋርተር (Order of the Garter) ተሰቅሎ በርካታ ጊዘያት አይተውታል። ንጉሥ ቻርልስ ግርማዊት ንግስት ከኢትዮጵያ ጋር ስለነበራቸው ዘላቂ ወዳጅነት ጠንቅቀው ያውቃሉ። ስለዚህም፣ እኛም የተወደዱትን እናታቸውን ሲያጡ እንደ ቤተሰብ የሃዘናቸው ተካፋይ ነን። እስካሁን ላበረከቱት፣ ወደፈትም ለሚያበረክቱት ታላቅ አገልግሎት እንዲሁም የዙፋን ወራሽነታቸው እውን እስከሚሆን ድረስ ላሳዩትም ትዕግስትና አክብሮት እግዚአብሔር ጤናና ረጅም እድሜ ሰጥቶ እንዲባርካቸው እንጸልያለን።
ለዩናይትድ ኪንግዶምና ለኮሞንወልዝ ሀገሮች ግርማዊ ንጉሥ ቻርልስ እኛ የኢትዮጵያ ዘውድና ሕዝብ በጎ እንመኝላቸዋለን። ከነርሱ ዘውድ ጋር ለረጅም ዘመናት የተሰማንን የቤተሰባዊነት ፍቅርና ስሜት ከኛም ዘውድ ጋር ምን ጊዜም እንዲሰማቸው እንሻለን። የሕዝቦቻችንን ክብር፣ ማንነትና ዕሴቶችን መሰረት በማድረግ ወደፊት ሊያጋጥመን የሚችለውን ማንኛውንም አይነት ተግዳሮት የምናስተናግድበት መንገድ ለሀገሮቻችን ዕጣ ፈንታና ደህንነት ወሳኝነት እንዳለው በመረዳት በአብሮነት ወደፊት ለመጓዝ እንችላለን።
ከዚህ በላይ የሀላፊነት ጥሪአችንን ልንወጣ የምንችልበት መንገድ ያለ አይመስለንም።
እግዚአብሔር የዳግማዊት ንግሥት ኤልሳቤጥን ነፍሥ ይማርልን። ወደ ፈጣሪዎ ስንሸኝዎት ሀዘናችንን የምንገልጸው በእንባ ነው።
ረጅም እድሜ ለንጉሥ ቻርልስ ፫ኛው ከመልካም ምኞትና ጸሎታችን ጋር አንመኛለን።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ።
__
በዚህ ድረ ገጽ ላይ መጣጥፍ ለማውጣት ከፈለጉ ጽሁፍዎትን በሚከተለው አድራሻ በኢሜይል ይላኩልን info@borkena.com
የቴሌግራም ቻናላችን ፡ t.me/borkena
ትዊተር ፡ @zborkena
ፌስቡክ ፡ Borkena
የቦርከና ቻናልን ስብስክራይብ ለማድረግ እዚህ ይጫኑ